Skip to main content
x
ኢትዮጵያዊነት በፍትሐዊነት ይድመቅ!

ኢትዮጵያዊነት በፍትሐዊነት ይድመቅ!

አገር የምታድገው፣ የምትዘምነው፣ በዴሞክራሲያዊ ጎዳና መጓዝ የምትችለውና ለዜጎቿ እኩል መሆኗ በተግባር የሚረጋገጠው በፍትሐዊነት ስትደምቅ ነው፡፡ ለአንዱ እናት ለሌላው እንጀራ እናት የምትሆነው ደግሞ ኢፍትሐዊነት ሲነግሥባት ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚነቱ ሲረጋገጥ፣ መብቱ ሲከበርለትና ግዴታውን ሲወጣ እርካታ ይፈጠራል፡፡ ጠያቂ የመሆን መብት እንዳለው ሁሉ ተጠያቂነቱም በእኩልነት ሲረጋገጥ ማኅበራዊ ፍትሕ ይሰፍናል፡፡ አድልኦና መድልኦ የሌለበት ሥርዓት እንዲፈጠር ሁሉም የዜግነት ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ መንግሥት ለሕዝብ ባለበት ኃላፊነት መሠረት በእያንዳንዱ የሚወስደው ዕርምጃ ፍትሐዊነትን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ሕዝብም መንግሥት ፍትሐዊ የሆኑ አሠራሮችን እንዲያሰፍን መወትወት አለበት፡፡ ይህ በገቢር ይታይ ዘንድ ደግሞ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ለፍትሐዊነት ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚደምቀው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን ትልቅ ምሥል የሚጋፉ ድርጊቶች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ድርጊቶች ማስቆም የሚቻለው ፍትሐዊነት በማስፈን ነው፡፡ ይህች ኅብረ ብሔራዊት አገር በርካታ ማንነቶች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ አመለካከቶችና ፍላጎቶች ያሉዋቸው ዜጎች የሚኖሩባት ናት፡፡ ለዘመናት ተጋብተውና ተዋልደው በሰላም ከመኖር በላይ፣ ለአገራቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ምክንያት ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በጋራ ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡ አገርን የምታህል ትልቅ መለያ በማስቀደም መስዕዋትነት የከፈሉ በርካታ ዜጎች በትውልድ ቅብብል ውስጥ አልፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በየጊዜው በተነሱ ገዥዎች ቁም ስቅሉን ማየቱን መካድ አይቻልም፡፡ በደስታውም ሆነ በመከራው አንድ ላይ ሆኖ አገሩን ሲጠብቅ የኖረ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች መኖሩም አይዘነጋም፡፡ ከኮሎኒያሊስቶች ጋር ተፋልሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንፀባራቂ ታሪክ የሠራ ሕዝብ እርስ በርሱ ተከባብሮ በመኖርም ወደር የለውም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የዘመናት ጥያቄው ማኅበራዊ ፍትሕ ነው፡፡ አድልኦና መድልኦ የሌበት ፍትሕ፡፡

ማኅበራዊ ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ ደግሞ ለሕግ የበላይነት የሚገዛ ሥርዓት መገንባት የግድ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚመጣው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ሲያቅተው ግን የተዓማኒነት ጥያቄ ይነሳባታል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በተጀመረው የፀረ ሙስና ዘመቻ የተለያዩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ ጉዳት በማድረስ ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሲያዙም ሆነ፣ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ዕግድ ሲጣልባቸው የሚዳኙት በሕግ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ሕግ ደግሞ ሁሉንም ዜጋ እኩል ይመለከታል ተብሎ ስለሚታሰብ ተጠያቂነት በራሱ ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ አንዱ አጥፍተሃል ተብሎ የተጠረጠረበትን ወንጀል ሌላው ፈጽሞት ዝም ከተባለ አሠራሩ ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ ማን ምን ሲፈጽም ነው በሕግ ተጠያቂ የሚሆነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፣ መንግሥት በግልጽነት የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡ ዜጎች በሚወሰደው ዕርምጃ ፍትሐዊነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ከሆነና ምላሽ ካላገኙ ተዓማኒነት ከንቱ ይሆናል፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑና ተጠያቂነታቸውም በዚያው ልክ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ ለፍትሐዊነት ሲባል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን አኩሪውንና ጨዋነት የተሞላበትን ኢትዮጵያዊ ባህል በማስቀደም ለፍትሕ መስፈን አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ፍትሐዊነት የሚሰፍነው ከሸፍጥና ከበቀል የፀዳ ማኅበረሰብ ሲኖር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማኅበረሰብ ከአሉባልታና ከተራ ሐሜት በመላቀቅ እውነታ ላይ ይመሠረታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ‹ማን? መቼ? የት? ለምን? እንዴት?› የሚባሉ ወርቃማ ጥያቄዎችን በመጠቀም በሥነ አመክኖአዊ ዘዴ የተጣራ መረጃ ያፈላልጋል፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ ደግሞ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ያደርሰዋል፡፡ ይህ ተሟልቶ ሲገኝ ከአስተያየት ጀምሮ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሁሉ ፍትሐዊ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በዚህ መንገድ ይደምቃል፡፡ መብቱን ማስከበር የሚችል ዜጋ በግብታዊነት ከመነሳሳት ይልቅ በመርህ ላይ ተመሥርቶ መንግሥትንም ሆነ ሹማምንቱን ማፋጠጥ ይችላል፡፡ ሕግ ማስከበር የተነሳውን አካል ጭምር ያነቃዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የተለመደው አዙሪት ውስጥ ሲገባ ግን ለውድመትና ለዕልቂት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ ለአገርም ለሕዝብም አይበጁም፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሲባል የሚከፋቸው፣ የሕዝብን አንድነት ከማየት ይልቅ መከፋፈል የሚፈልጉ፣ ኅብረ ብሔራዊነትን ሳይሆን ጠባብነትን የሚያቀነቅኑ፣ ዜጎችን በማንነታቸው የሚያቋሽሹና ባህላቸውን የሚፀየፉ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት የሚሞክሩ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ እሴት ለመናድ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ ለጠላት ዒላማ የሆነች አገር እንድትፈጠር በተለያዩ መንገዶች በመቀስቀስ ሕዝቡን ለመከፋፈል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እነዚህን ለመከተል መሞከር ንፋስን መከተል በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር አለባቸው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ይመለከተናል የሚሉ አገር ወዳድ ዜጎችና የመንግሥት አካላት በንቃት መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶች የበላይነቱን እንዳያገኙ አገር በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር እንድትተዳደር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ መንግሥት በእያንዳንዱ ሥራው ውስጥ ፍትሐዊነት ሲጠፋ፣ የሕዝቡንና የአገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ኃይሎች ከየአቅጣጫው ይነሳሉ፡፡ ፍትሐዊነት የጎደላቸው ዕርምጃዎች ማንነትንና ሌሎች መሰል መገለጫዎችን እየታከኩ አገርን ለጥቃት፣ ሕዝብን ለትርምስ ይዳርጋሉ፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት እንዲሰማቸው ይገፋፋሉ፡፡ አንዱ ወገን እየተጠቀመ ሌላው እየተገፋ ከመሰለው ደግሞ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ሁሌም እንደምንለው የሕግ የበላይነት የዚህች ታሪካዊት አገር መመኪያ መሆን አለበት፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ በተግባር የሚረጋገጠው፣ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩበትና ያሻቸውን የሚመርጡበት ዓውድ ሲመቻች ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣኑ የመጨረሻ ባለቤት መሆኑ ማረጋገጫው ሕግ ሲከበር ብቻ ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል የሚኖረው ሕዝብ ቀጣሪ መንግሥት ተቀጣሪ መሆኑ በገቢር ሲታይ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነኝ ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር የሚችለው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩትን መብቶች ያለምንም መሸራረፍ ሲያስከብር ነው፡፡ ያኔ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ይጨምራል፡፡ የጥላቻና የበቀል ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ምድር ተኖ ይጠፋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በዘርና በመሳሰሉት ለመከፋፈል የሚያሰፈስፉ ኃይሎችን ያመክናል፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑና ተጠያቂነታቸውም በዚያው መጠን ሲሆን አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ የዜጎቿ ሁለገብ ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይጨምራል፡፡ የዕድገቷ ፍሬ ለሁሉም ፍትሐዊ ሆኖ ይዳረሳል፡፡ የሚናፈቀው ዴሞክራሲ ዕውን ይሆናል፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ ኢትዮጵያዊነት በፍትሐዊነት ይድመቅ እንላለን!