Skip to main content
x

ኢትዮጵያ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም በሕግ ይፈቀድ እንዴ?

ክፍል አንድ

በዳንኤል አረጋዊ ኃይሉ

ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት የጥቂት አገሮችና ሕዝቦች ችግር የነበረው አደንዛዥ ዕፅ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ችግር በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናና ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1971 የፀደቀው የሳይኮትሮፒክ ዕፆች ቃል ኪዳን፣ የናርኮቲክ መድኃኒቶችና የሳይኮትሮፒክ ዕፆች ሕገወጥ ዝውውርን ለመቆጣጠር እ.ኤ.አ. በ1988 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል ኪዳንና እ.ኤ.አ. በ1999 እንደ አዲስ ተደራጅቶ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመድኃኒት ቁጥጥርና ወንጀል መከላከል ጽሕፈት ቤት (UNODCCP) መቋቋም፣ ለአደንዛዥ ዕፅ የተሰጠውን ዓለም አቀፍ ትኩረት ማሳየት ይችላሉ፡፡

የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ምንድነው?

 

"UNODCCP" እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በሰጠው የቃላት ፍቺ መሠረት አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት (Drug Abuse) ማለት፣ ዓለም አቀፋዊ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሳይኮአክቲቭ ውጤት ያላቸውን ዕፆች ከሕክምና ወይም ሳይንሳዊ ዓላማ ውጪ መጠቀም ነው፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው የአልኮልና የመድኃኒቶች የቃላት መፍቻ መጽሐፍ (Lexicon) መሠረት፣ ሳይኮአክቲቭ ውጤት ያላቸው ዕፆች የሚባሉት ወደ ሰውነት ሲገቡ የአዕምሮን የአስተሳሰብ ወይም የስሜት ሒደት የሚለውጡ መድኃኒቶች ናቸው፡፡ በዚሁ ሰነድ የተሰጠው ሌላ ፍቺ እንደሚያመለክተው ሳይኮትሮፒክ ወይም ሳይኮአክቲቭ ዕፆች የሚባሉት ኬሚካላዊ ይዘታቸው በዋነኝነት በተጠቃሚው ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ መድኃኒቶች ናቸው፡፡

የአደንዛዥ ዕፅ ዓይነቶችና የጎንዮሽ ጉዳት

 

ባለሙያዎች የአደንዛዥ ዕፅ ዓይነቶችን በሦስት መደቦች ከፍለው ያስቀምጧቸዋል፡፡ እነሱም ዲፕሬሳንት (Depressant)፣ አነቃቂ (Stimulant) እና ሃሉሲኖጀንስ (Hallucinogen) ናቸው፡፡  ዲፕሬሳንት ዕፆች የነርቭ ሥርዓታችን ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩና የተጠቃሚውን አዕምሮ በሰው ሠራሽ መንገድ ከጭንቀትና ከውጥረት ዕረፍት የሚሰጡ ወይም ዘና የሚያደርጉ ዕፆች ናቸው፡፡ ዕፆቹ በተጠቃሚዎች ዘንድ የሚመረጡበት ዋነኛ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ በአንድ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ላይ በዚህ ሰሞን የቀረቡት የሥነ አዕምሮ ባለሙያው ዶ/ር ምሕረት ደበበ፣ ከአደንዛዥ ዕፆች የሚገኘውን ይህንን የደስታ ስሜት ‹‹ያልተለፋበት ደስታ›› ብለው ገልጸውታል፡፡ ሄሮይን በዚህ ምድብ ውስጥ ይመደባል፡፡ አነቃቂ ዕፆች የነርቭን እንቅስቃሴ የሚቀሰቅሱ፣ የሚያበለፅጉና የሚጨምሩ ናቸው፡፡ ኮኬይንና ክራክ በዚህ ምድብ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ሃሉሲኖጀን (Hallucinogen) ዕፆች አዕምሮን በከፍተኛ ደረጃ በመቀየር የላቀ ደስታን፣ ከፍተኛ ጭንቀትን፣ የስሜት መታወክን ወይም የስሜት ህዋሳት መረጃ ማዛባትን የሚፈጥሩ ዕፆች ናቸው፡፡ ካናቢስ ወይም ማሪዋና ወይም ሀሺሽና ኤክስታሲይ በዚህ ምድብ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ካናቢስ ወይም ማሪዋና ወይም ሀሺሽ ጥቅም ላይ እንደሚውሉበት ቦታና እንደ አዘገጃጀታቸው አንዳንዴ በአማራጭ ስምምነት፣ አንዳንዴ አንዱ ለሌላው በጥቅል ስምምነት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላሉ፡፡

ዲፕሬሳንት (Depressants) ዕፆች ሱስ የማስያዝ አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ፣ ዕፆቹን መጠቀም ጀምሮ ማቆም በተጠቃሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ አነቃቂ ዕፆች ሰውነትን የመመረዝ፣ የልብ ምትንና የደም ግፊትን በከፍተኛ ደረጃ የመጨመርና ፀብ ፀብ የሚያሰኝ ባህርይ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የተጠቃሚውን የማመዛዘን አቅም ስለሚያዛቡት ለአደጋ ወይም ለአደጋኛ ባህርይ ያጋልጡታል፡፡ ለምሳሌ ይህን ዕፅ ተጠቅሞ የጦዘ ሰው እንቅልፍ ላይ ያለ ወንድሙ እንዲሞቀው ብሎ በለበሰው ብርድ ልብስ ላይ እሳት ሊለኩስበት ይችላል፡፡ አልያም መሬት ላይ ጠብ ያለች ውኃ መዋኛ ገንዳ መስላው እዋኛለሁ ብሎ ዘሎ ሊፈጠፈጥባት ይችላል፡፡ አልያም ‹‹መላዕክት አምጣቸው ስላሉኝ ወደ ሰማይ ይዣቸው እሄዳለሁ›› በማለት ጨቅላ ልጆቹን አቅፎ በኮንዶሚኒየም መስኮት ሊዘል ይችላል፡፡ ሃሉሲኖጀን (Hallucinogens) ዕፆች ተጠቃሚው የሌለ ነገርን እንዳለ እንዲያስብ፣ ሌሎች ሰዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠራጠር ወይም የድብርት ስሜት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ይችላሉ፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያም ሆነ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተከናወኑ ጥናቶችና በጉዳዩ ላይ የተጻፉ መጽሐፍት እንደሚጠቁሙት፣ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ጠንቆች ባሻገር በፍጥነትም ሆነ በሒደት ከፍተኛ የጤና ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ ማሪዋና አልፎ አልፎ መጠቀም እንኳን የተጠቃሚውን የአስተሳስብ ዕድገት ማወክና የአጭር ጊዜ ሁነቶችን የማስታወስ ብቃቱን ማዳከም ይችላል፡፡ አደንዛዥ ዕፅ በተጠቃሚው ጤና ላይ ከሚያመጣው ጉዳት ባሻገር ወንጀልን በማስፋፋት፣ ቤተሰብን በመበተን፣ ለሕክምና በሚወጣ ወጪ፣ አምራች ዜጋን ከሥራ ውጪ በማድረግ፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርንና ጥቅምን ለመቆጣጠር እንደ ፖሊስ ያሉት የፍትሕ አካላት የሚያወጡትን ወጪ በማናር፣ ወዘተ በአንድ አገር ማኅበራዊ ሕይወት፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይፈጥራል፡፡

አደንዛዥ ዕፅ በአሜሪካና በላቲን አሜሪካ አገሮች ላይ የጋረጠው ፈተና 

አንድ አመሻሽ ላይ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ለረጅም ዓመት ከኖረ ወዳጄ ጋር ከአንድ ባቡር ጣቢያ ወጥተን ወደ ዋናው መንገድ እናመራለን፡፡ ዕድሜዋ በግምት በ50ዎቹ መጀመሪያ የሚሆን አንዲት ሴት የአውቶብስ ማለፊያ መንገዱ መሀል ቆማለች፡፡ የሰውነቷን ሚዛን መጠበቅ አቅቷት ጫማውን ለማሰር እንዳጎነበሰ ሰው ከወገቧ ተጎንብሳ ወደ አንድ እግሯ አዘንብላለች፡፡ መሬት የነካውን ቦርሳዋን አንስታ ለማንገት ትታገላለች፡፡ ቀና ብላ ለመቆም ደጋግማ ብትሞክርም አቅም እያጣች መልሳ ወደ መሬት ተዘቅዝቃ ታጎነብሳለች፡፡ ጭንቅላቷ ብቻውን ይንዠዋዠዋል፡፡ በሁኔታዋ ስለተገረምኩ እንደ መቆም ብዬ አስተውላት ጀመር፡፡ ወዳጄ ግን አልፎኝ ሄዷል፡፡ አጠገቤ በነበረው አውቶብስ መጠበቂያ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችና መንገደኞች በሴትየዋ እየሳቁ ይዘባበቱባታል፡፡ አብዛኛው አላፊ አግዳሚም ሆነ አውቶብስ ጠባቂው ግን የሴትየዋን ሁኔታ ከምንም አልቆጠረው፡፡ ፈንጠር ብሎ ቆሞ የሚጠብቀኝ ወዳጄ በሴትዮዋ ሁኔታ በመገረሜ ፈገግ እያለ ‹‹እንሂድ ባክህ ዳኒ ‘She is Just High’›› (በአደንዛዥ ዕጥ ጦዛ ነውiii) አለኝ፡፡ በዚህ መሀል አንድ የአውቶብስ ሹፌር ሴትዮዋን ደግፎ ወደ አንዱ የአውቶብስ መጠበቂያ ውስጥ አስገባት፡፡ ወንበሩ ላይ ተዘረረች፡፡

በሌላ ቀን ጠዋት ከአንድ ሌላ ባቡር ጣቢያ እንደወጣሁ አውቶብስ መናኸሪያው ውስጥ የፖሊስ ተሽከርካሪዎችና አንድ አምቡላንስ የአደጋ ጊዜ መብራቶቻቸውን ብልጭ ብልጭ እያደረጉ ተበታትነው ቆመዋል፡፡ የተወሰኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና ፖሊሶች አንድ ቦታ ሰብሰብ ብለው ራሳቸውን የሳቱ አንድ አዛውንትን በስትሬቸር ላይ አስተኝተው የሕክምና ዕርዳታ ይሰጧቸዋል፡፡ ሌሎች ፖሊሶች ወዲህ ወዲያ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሕክምና ዕርዳታ እየተሰጣቸው የነበሩትን አዛውንት ዓይቶ የመጣ አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ ወጣት ከአጠገቤ ሰብሰብ ብለው የቆሙትን ሰዎች እየተቀላቀለ፣ ‘How come he got high at this time of the day?!’ አለ ንዴቱን በሚገልጽ አነጋገር፡፡ ወጣቱን ያናደደው የአዛውንቱ በአደንዛዥ ዕፅ መጦዝ ሳይሆን በጠዋቱ መጦዛቸው ነው፡፡

ደግሞ በሌላ ቀን በግምት ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ዕድሜው በግምት ከ16 ዓመት የማይበልጠው በአደንዛዥ ዕፅ የጦዘ ታዳጊ ግርግዳ ጥግ ይዞ ቆሞ አየሁ፡፡ ዓይኖቹ ላለመጨፈን ይታገላሉ፡፡ ለሃጩ እንደ ጨቅላ ሕፃን ልብሱ ላይ ይዝረከረካል፡፡ ዓይነ ምድሩን ልብሱ ላይ ለቆታል . . .፡፡ በጣም ፈዛዛና ስሜት አልባ ሆኖ ፈገግ ይላል፡፡ በዙሪያው ስላለው ቅንጣት ነገር እንኳን ግንዛቤ የለውም፡፡ አጠገቡ ከነበሩት ሰዎች አብዛኛዎቹ ሽታውን በመጠየፍ በስድብና በጩኸት ይሸሹት ነበር፡፡ በአዘኔታ ያዩት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዲት እናት ጠጋ ብለው አፉን በናፕኪን ካበሱለት በኋላ፣ ከኪሱ እያወጣ ይጥላቸው የነበሩትን ተንቀሳቃሽ ስልኩንና ጥቂት ዶላሮች ከመሬት አንስተው ዙሪያውን ላለው ሰው እያሳዩ ወደ ጃኬቱ ኪስ ውስጥ ከተቱለት፡፡

በተለያዩ ቦታዎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአደንዛዥ ዕፅ ጦዘው ራሳቸውን ለሳቱ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን . . . የሕክምና ዕርዳታ ሲሰጧቸው ደጋግሜ ተመልክቻለሁ፡፡ በተለይ በተወሰኑ ሠፈሮችና አካባቢዎች ሳልፍ አልያም አውቶብስ ስጠብቅ ደጋግሞ አፍንጫዬን እያበገነ ያስቸገረኝ ሽታ ማሪዋና በመባል የሚታወቀው የአደንዛዥ ዕፅ ሽታ መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡ ክራክ ተብሎ የሚጠራውን አደንዛዥ ዕፅ ለመፍጨት የሚጠቅሙ በኪስ የሚያዙ ዕቃዎችንና አደንዛዥ ዕፅ ለማጨስ የሚያገለግሉ መጠቅለያ ወረቀቶችን እንደ ስኳርና ውኃ ለሽያጭ የሚያቀርቡ ግሮሰሪዎች (Convenient Stores) ጥቂት አይደሉም፡፡

እኔን ጨምሮ አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያውያን መንገድ ዳር ላስቲክና ማዳበሪያ ተከናንበው የተኙ ቤት አልባ ወገኖቻችንን አልያም ዕርቃናቸውን በየጎዳናው የሚጓዙ በአዕምሮ ሕመም የተያዙ ወገኖቻችንን ማየት የማይደንቀንን ያህል፣ የዋሽንግተን ዲሲና የሜሪላንድ ከተማ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች በአደንዛዥ ዕፅ የጦዘ ሰው ማየት ቢያሳዝናቸው እንጂ እንደማያስደንቃቸው በነበረችኝ አጭር ቆይታ ተገንዝቤያለሁ፡፡ በሌሎች የአሜሪካ ክፍሎችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ለማወቅ አልተቸገርኩም፡፡ ያ በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ያየሁት ሕፃን ልጅ ግን የችግሩን አስከፊነት ከምንም ጊዜ በላይ እንዳየውና አሁን ባለንበት ሁኔታ ከቀጠልን፣ የአገራችን መፃዒ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ረድቶኛል፡፡ ይቺን ጽሑፍ መጻፍ የጀመርኩትም የዚያን ዕለት ማታ ነበር፡፡

በአሜሪካ የሚገኝ የኒዩሮሳይንስ ማኅበር ‹‹ብሬይን ፋክትስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው የጥናት ጽሑፍ እንደሚጠቁመው፣ ከአገረ አሜሪካ ዋነኛ አሳሳቢ የጤና ችግሮች መካከል የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት አንዱ ነው፡፡ ስድስት በመቶ የሚሆኑት ማለትም ወደ 15 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጓችዋ በቋሚነት አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የአልኮል መጠጥና ትንባሆ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች የተነሳ፣ አገሪቷ በየዓመቱ 276 ሚሊዮን ዶላር ለሚደርስ ወጪ ዳርጓታል፡፡ የአሜሪካውያን ሜዲካል ኮሌጆች ማኅበር እ.ኤ.አ በ2004 ባሳተመው ጽሑፍ እ.ኤ.አ በ2004 ብቻ 22.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ አሜሪካውያን የአልኮል መጠጥና የአደንዛዥ ዕፅ ሱስን ለማስወገድ ሕክምና ማግኘት ያስፈላጋቸው ቢሆንም፣ ከእነዚህ ውስጥ ሕክምናውን የወሰዱት 3.8 ሚሊዮን ብቻ ነበሩ፡፡

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች አደንዛዥ ዕፅን ‹‹ለመዝናኛነት›› (For Recreational Use) በቤት ውስጥ መጠቀምን የሚፈቅድና እጅግ አነስተኛ መጠን ያለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዞ መገኘትን የማይከለክሉ ሕግጋትን እያወጡ ነው፡፡ ለእነዚህ የሕግ መሻሻሎች በምክንያትነት የሚቀመጡ መንስዔዎች የተለያዩ ቢሆኑም፣ ዋነኞቹ ግን በየግዛቶቹ ያለውን የአደንዛዥ ዕፅ ሥርጭትና የተጠቃሚውን ብዛት መቆጣጠር አለመቻሉ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ ጉዳትን በማወቅ ዕፁ በምንም ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳይውል መጠቀምን የሚቃወሙና የተጠቃሚው ቁጥር እንዳይስፋፋ የሚታገሉ ግለሰቦችና ተቋማት አሉ፡፡ ሆኖም ጥቂት የማይባለው የማኅበረሰባቸው ክፍልና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምን እንደ ግብረ ሰዶም ሁሉ የግለሰቦች መብት፣ ምርጫና ዝንባሌ አድርገው በመቁጠር ዕፅ መጠቀም ሕጋዊ እንዲሆን ከፍተኛ ድጋፋቸውን ሲሰጡ፣ ቅስቀሳ ሲያደርጉና ሲያቀነቅኑ በስፋት ይስተዋላሉ፡፡

በዓለማችን ከሚሠራጨው የአደንዛዥ ዕፅ ምርት ሰፊውን ድርሻ የያዙት ኮሎምቢያና ሜክሲኮ ውስጥ የሚገኙ የአደንዛዥ ዕፅ አብቃይ፣ አከፋፋይና ተጠቃሚ ቡድኖች (Drug Cartels) የአገራቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን በሥልጣን ላይ ካሉ መንግሥቶቻቸው የላቀ ተፅዕኖ ማሳደር ችለዋል፡፡ እነዚህ አገሮች የአደንዛዥ ዕፅ ምርትን፣ ሥርጭትንና ተጠቃሚነትን ለመቆጣጠር ለዘመናት ቢለፉም በቀላሉ የማይወጡት ቀጥ ያለ ዳገት ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞቻቸውና የመንግሥት አመራሮቻቸው ሳይቀሩ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምና ማሠራጨትን ሕጋዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከአደንዛዥ ዕፅ ሥርጭትና ተጠቃሚነት አንፃር ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ከእነ አሜሪካ ተሞክሮ ምን እንማራለን? ድርጊቱን ለመከላከል እየተጓዝንበት ያለነው መንገድስ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

በቀጣይ ክፍል ጽሑፌ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ ሽያጭና ተጠቃሚነት በአገራችን ምን ያህል እንደተስፋፋ በተለያየ የአገራችን ክፍሎች የተከናወኑ ጥናቶች፣ በተለያዩ ፍርድ ቤቱ የቀረቡ ጉዳዮችን፣ በመገናኛ ብዙኃን የወጡ ዘገባዎችንና የአደንዛዥ ዕፅ ጥቅም ላይ የሚውልባቸውን ቦታዎችና ሁኔታዎች በመጠቃቀስ አደንዛዥ ዕፅ በአገራችን የደቀነው ፈተናና ዝምታችንን ለመስበር ይረዳሉ ብዬ ያሰብኳቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች በማቅረብ ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ፡፡  

ትዝብቴን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ ብቻ የምንዋጋ፣ ከግል ክብርና ጥቅማችን በላይ ለአገራችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች ያድርገን፡፡ ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ፡፡ ሰላም፡፡                                                                 

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን (LL.B, LL.M, MSW) አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡