Skip to main content
x
ኢጋድን የተገዳደረው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት

ኢጋድን የተገዳደረው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት

በአፍሪካ 54ኛ አገር ሆና ከሱዳን ካርቱም እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2011 ነፃነቷን ያገኘችው ደቡብ ሱዳን፣ ነፃነቷን በቅጡ ማጣጣም የተሳናት ብዙም ሳትቆይ ነበር፡፡ በፕሬዚዳንቱ ሳልቫ ኪርና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረ አለመግባባትና የሪክ ማቻር ከሥልጣን መሰናበት፣ በአገሪቱ ከሚገኙ አሥር ግዛቶች በዘጠኙ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአገሪቱ በጦርነት የሚፋለሙ ሰባት ቡድኖች ሲኖሩ፣ ወገንተኝነታቸውም በብሔር ተከፋፍለው አንዱ ወን ለሳልቫ ኪር ሌላው ለሪክ ማቻር ነው፡፡ በዚህም ደቡብ ሱዳናውያኑ ለመፈናቀል፣ ለስደት ለረሃብ ብሎም ለሞት ተዳርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2013 ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት እስከ 13 ሚሊዮን የሚደርሱትን ሕዝቦች ለውጥረት ዳርጓል፡፡ 300 ሺሕ ያህል ሲሞቱ፣ ሁለት ሚሊዮን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በተለይ ወደ ኬንያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ተሰደዋል፡፡ ኢትዮጵያም ግማሽ ያህሉን አስተናግዳለች፡፡

በጎሳ ተከፋፍለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለገቡት ደቡብ ሱዳናዊያን መንስዔው ፕሬዚዳንት ኪርና የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ማቻር አለመግባባት፣ እንደ ደቡብ ሱዳናዊ ሳይሆን እንደ ጎሳ ማሰብ ብሎም የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ ይኼም የእርስ በርስ ጦርነቱን አጉልቶት ደቡብ ሱዳናውያን ከጦርነት መውጫ አጥተዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የበኩሉን ጥረት ቢያደርግም ተግባራዊነቱ ላይ ክፍተት አለ፡፡

በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ከአምስት ወራት በኋላ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ለማደራደር ኢጋድ በአዲስ አበባ የጠራው ስብሰባ ተሳክቶለት ተፋላሚዎቹ ከሰላም ስምምነት ቢደርሱም፣ ስምምነቱ ለቀናት ሳይዘልቅ ፈርሷል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው ውይይት ሪክ ማቻር ከሳልቫ ኪር ጋር በመሆን በጋራ ችግሩን እንዲፈቱ ጁባ የመግባት ዕድል ገጥሟቸው የነበረ ቢሆንም፣ ይኼኛውም ስምምነት ከሽፎ ሪክ ማቻር መልሰው ኮብልለዋል፡፡ ይኼም የኢጋድን ጥረት ያንኳሰሰ፣ የሰላሙን ተስፋ ያጨለመ ነበር፡፡

በደቡብ ሱዳን ያለውን የርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመፍታት ግንባር ቀደሙን ሚና እየተጫወተ ያለው ኢጋድ ያልተሳካለት፣ የኢጋድ አባል አገሮች በአቋማቸው መከፋፈላቸው ነው መባሉም በአንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም እርሻ ድርጅት ዳይሬክተር ሚስተር ጆሴ ግራዚያኖ፣ በደቡብ ሱዳን የሚፋለሙ ቡድኖች በኢጋድ አባል አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት እየተጠቀሙ ነው ማለታቸውን ኦል አፍሪካ ዘግቧል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ፣ ከኢጋድ አባል አገሮች የተወሰኑት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ደጋፊ መሆናቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ለዶክተር ሪክ ማቻር ወግነው ወደ አማፅያኑ ማድላታቸው የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆንና በአገሪቱ ሰላም እንዳይሰፍን አድርጓል፡፡

የኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸውና በደቡብ ሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ሊያበቃ በሚችልበት ላይ መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረው፣ ክፍፍሉ ጦርነት ባንኮታኮታት ደቡብ ሱዳን ውስጥ የተከሰተው ረሃብ አስከፊ ደረጃ እንዲደርስ አንድ ምክንያት ሆኗል፣ ዕርዳታ ሰጪዎችም ምንም ውጤት ባለማያታቸው ተሰላችተዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ባለው የእርስ በርስ ግጭት ቀጣናውም ውጥረት ውስጥ ገብቷል፡፡ የቀጣናው አገሮችም ስደተኞችን ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡

የሰላም ድርድሩ በቅጡ ያልፈታውን የደቡብ ሱዳን ቀውስ ለመታደግ በወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተጠራው የኢጋድ ልዩ ስብሰባ ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ስብሰባውን አስመልክተው እንዳሉት፣ የኢጋድ ስብሰባ ያረጋገጠው በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የኢጋድ አባል አገሮች አንድ ቋንቋ መናገራቸውን ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የተፈረመውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነትና ትግበራ በተመለከተ፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የሰላም ስምምነቱን ለመጀመር የወሰዳቸውን በጎ ጅምሮች ተሰብሳቢዎቹ ዋጋ ሰጥተውታል፡፡

በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ የእርቅ ሥራ መጀመር፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም፣ ሰብዓዊ ዕርዳታን በተመለከተ ኬንያና ሱዳን የዕርዳታ ማስገቢያ መስመር መስጠታቸውም የኢጋድን የአደራዳሪነት ሚና ውጤት የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሰላማዊ ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ተቋማዊ ግንባታ ላይ እየሠራ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የፀጥታ መዋቅሮቹ ላይ እንደገና እየሠራ መሆኑ አዎንታዊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጎ ዕርምጃዎች ቢኖሩም የኢጋድ አባል አገሮች ደቡብ ሱዳን ውስጥ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አልተቻለም በሚለው ላይ ይስማማሉ፡፡ በደቡብ ሱዳን ግጭቶች መኖራቸው፣ የተኩስ ድምፅ መሰማቱ፣ ተጨማሪ የታጠቁ ኃይሎች እየመጡ መሆኑም እንደሚያሳስበው ኢጋድ አሳውቋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የመፍትሔ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በኢጋድ ስብሰባ ተወስኗል፡፡ ለዚህም በሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መካከል ከሁለት ዓመት በፊት የተፈረመውን የሰላም ስምምነት የሚያጠናክርና መልሶ የሚያይ መድረክ እንዲመሠረት ተወስኗል፡፡ ይህም የደቡብ ሱዳንን የሰላም ስምምነት የያዘው የኢጋድ አካል የሰላም ስምምነቱን የትግበራ ጊዜ እንደገና እንዲያየው ያስችላል፡፡

የኢጋድ አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርጉና የአዲስ አበባውን የሰላም ስምምነት ትግበራ የጊዜ ሰሌዳን በድጋሚ እንዲያዩም ተስማምተዋል፡፡ የአዲስ አበባውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ለመከታተል የተቋቋመው ኮሚሽንና የኢጋድ ሴክሬታሪያትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መባሉን አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባው ስምምነት በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት ብቸኛው መንገድ ነው ብለውም መስማማታቸውንና ይኼንን ሐሳብ ኢጋድ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደገፉት መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

በኢጋድ በኩል በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ አንዳንድ ሚዲያዎች ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን አቅም የለውም ብለው ሲዘግቡ ይስተዋላል፡፡

አቶ መለስ እንደሚሉት፣ ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ይኼንን ውቅድ አድርጎታል፡፡ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በሪክ ማቻር መካከል በአዲስ አበባ የተደረሰው የሰላም ስምምነት መኖሩንም ያረጋገጠ ነበር፡፡ ትግበራው ላይ የተወሰነ መጓተት ቢኖርም፣ በደቡብ ሱዳን አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ተጨማሪ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢጋድ አባል አገሮች ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ በደቡብ ሱዳን ሰላም በማስፈን ሒደት ለመምከር ሰኞ በአዲስ አበባ ስብሰባ የተቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንጋይ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ፣ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓሊ ሐሰን ካይሬ፣ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ዓሊ ዮሱፍና የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ አሚና መሐመድ ናቸው፡፡