Skip to main content
x

እስከ መቼ ወደ ውጭ ምርት እንመለከታለን?


በዳዊት ወልደ ኢየሱስ

ኢትዮጵያ በርካታ ታሪክ ያላት የራሷ የሆነ…እየተባለ የሚነገርላትና ቢነገርላትም  ታላላቅ ምስክር የሚሆኑ የታሪክ አሻራ ያላት አገር ናት፡፡ በእርግጥም ዘመናትን ወደ ኋላ ስንጠቀልል አገራችን ጥቂት ከነበሩ ታላላቅ አገሮች መካከል ስሟ ተጠቃሽ ነበረ፡፡ ያ ስም እየደበዘዘ ሄዶም በረሃብና በጦርነት ስሟ መነሳት ጀመረ፡፡ አሁን ይኼንን ስም ለማደስ ወደ ትንሳዔ እየመጣች ያለችበት ጊዜ ነው፡፡

ታሪክ በታሪክነቱ ዋጋ ያለው ቢሆንም፣ እንዲህ ነበርን እያልን ማውራቱ ግን ትርጉም የለውም፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የነበሩትን በመሆን በሁሉም ዘርፍ ታሪክን በመድገም ነው ዳግም ወደ ቀደመ ክብራችንና ታሪካችን የምንመለሰው፡፡ ለዚህ ደግሞ እኛው በእኛው በመደጋገፍ፣ በመስማማት፣ ለአንድ ዓላማ ለአገር ዕድገት በአንድ ላይ በመሥራት፣ እንዲሁም የአገርን ምርት በመጠቀም አብሮ ማደግ የሚቻል ይሆናል፡፡

ምናልባት በርካታ የፖለቲካ ልዩነቶች ይኖሩናል፣ ነገር ግን አገር አንድ ናት፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶችን ልንከተል እንችላለን፣ የምንኖረው ግን በአንድ አገር ውስጥ ነው፡፡ የቋንቋና የባህል ልዩነት መኖርም ለአንድ አገር ዕድገት የሚያመጣው ተፅዕኖ መኖር የለበትም፡፡ እኛ ኢትዮያውያን ነንና! ስለዚህ ልዩነታችን ውበታችን ነው ብለን አገራችንን የሸፈነውን የድህነትና የኋላቀርነት ጨለማ መግፈፍ ይጠበቅብናል፡፡

ይኼንን እንደ መነሻ አልኩ እንጂ ዋናው ሐሳቤ “በአገር ምርት እንኩራ!” በሚለው ሐሳብ ላይ የበኩሌን ሐሳብ ልሰነዝር ነው፡፡ “ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልም” አይደል የሚባለው? የሚወረወረው ግን አገር የሚገነባ የሐሳብ ድንጋይ፣ መለያየትን አስወግዶ አንድ የሚያደርግና የሚያስተሳስርን የፍቅር ገመድ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

አገራችን በፈጣን የዕድገት ጎዳና እየተጓዘች ያለች መሆኗ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለዚህም የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ሚዲያዎች፣ የምጣኔ ሀብት ምሁራንና ድርጅቶች፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችና የአገር መሪዎች ምስክር ናቸው፡፡ ከምስክሮች ባለፈም “ለቀባሪ አረዱት” እንዳይሆንብን እንጂ፣ እኛ ዜጎች ለውጦች እንዳሉ ምስክሮች ነን፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን የዕድገቱን ፍሬ እየቀመስን ነው? ስንቶቻችንስ የአገር ምርት ኩራት መሆኑን አምነን ተቀብለናል? በአገራችን በሚመረቱ ምርቶችስ ስንቶቻችን ተማምነን እንገዛለን? ይኼ ጥያቄ ሁሉንም የሚመለከት ነው፡፡ 

ለአብነት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አንዱ የሆነውን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ንዑስ ዘርፍ ላንሳ፡፡ ይኼ ንዑስ ዘርፍ ገቢ ምርትን ከመተካት አንፃር ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበ ያለ ነው፡፡ ከብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በአገራችን ከ400 በላይ የሚሆኑ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 85 በመቶ የሚሆኑትም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ1.6 ሚሊዮን ቶን በላይ የተለያዩ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ምርቶችን ማምረት የሚችል የኢንዱስትሪዎች አቅም እየተፈጠረ መሆኑ መረጃው ያሳያል፡፡

ይኼም “በ2017 በአፍሪካ ቀዳሚ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ቀላል የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኢንዱስትሪ በመገንባት፣ ለከባድ ኢንዱስትሪ ልማት መሠረት መጣል” የሚለውን የአገራችን ራዕይ ለማሳካት በር ከፋች ነው፡፡

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ታዲያ ገቢ ምርትን ለመተካት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን፣ እንደማሳያም የተለያዩ ጥሬ ብረቶችን በማቅጠን ለግንባታና ለፋብሪኬሽን የሚያግዙ ጠፍጣፋ ቆርቆሮዎችንና ብረቶችን በማምረት፣ ለጣሪያ ክዳን የሚሆኑ ግብዓችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የማምረት አቅም ተፈጥሯል፡፡

በተለይም እየተካሄደ ላለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት የሚሆኑ የቶቦላሬ ምርቶችን በአገር ውስጥ አቅም መሸፈን በሚቻልበት ደረጃ መደረሱ ይበል የሚያሰኝ  ተግባር ነው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች በአገራችን ለሚገነቡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ግብዓት የሚሆኑ በአገር ውስጥ የተመረቱ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ምርቶችን ጥቅም ላይ መዋላቸው ደግሞ፣ የንዑስ ዘርፉን የዕድገት ጎዳና በጉልህ የሚያሳይና የውጭ አገር ብረት ለምኔ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ምን አለ? ለምንስ የውጪው ነገር ያምረናል?

ለስኳር ኢንዱስትሪዎች ግንባታ የሚውሉ ኮምፖነቶችን ከ70 እስከ 80 በመቶ በራስ አቅም ማምረት መቻሉ፣ በዓመት እስከ 1,000 የሚደርሱ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን የመገጣጠም አቅም መፈጠሩ፣ እስከ 5,000 የሚገመቱ የእርሻ መሣሪያዎችን ወይም ትራክተሮችንና 4,000 የሚደርሱ ተሳቢዎችን በአገር ውስጥ የማምረት አቅም መፈጠሩ፣ በዚህ ዘርፍ የአገራችን ጉዞ ምን እንደሚመስል ማሳያ ነው፡፡ 

የኤሌክትሮኒክስና የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን በተመለከተም በአሁኑ ጊዜ ገቢ ምርቶችን መተካት ተችሏል፡፡ የቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ማብሰያዎችን፣ ማሞቂያዎችንና ሌሎች ኢኩዩፕመንቶችን በከፍተኛ አቅም ለማምረት የሚያስችሉ ፋብሪካዎች መገንባታቸው ገቢ ምርቶችን ለመተካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ታምኗል፡፡ የኬብል ምርቶችም ወደ አውሮፓና አፍሪካ አገሮች ኤክስፖርት እየተደረጉ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከ11 በላይ የሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች የተቋቋሙ ሲሆን፣ በምርቶቹም የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪን የማስገኘት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው፡፡ በኢንስቲትዩቱ ያለው መረጃ የሚያሳየው በዘንድሮው በጀት ዓመት በአንድ የሞባይል ኩባንያ ብቻ ከ43.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ፣ ዘርፉ ምን ያህል ትኩረት የሚሻ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡

በተጨማሪም ከ16 የማያንሱ የቴሌቪዥን መገጣጠሚያ ፋብሪካ መኖራቸው፣ የኮምፒዩተርና ተያያዥ የቢሮ ዕቃዎችን ለማምረት አቅም እየተፈጠረ መምጣቱም አበረታች ተግባር ነው፡፡

በአውቶሞቲቭና በሌሎች ተሸከርካሪዎች ላይ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው በቁጥር 45,900 የማምረት አቅም መፈጠሩና 31 ቢሊዮን ብር መድረሱ፣ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪ ደግሞ በቁጥር 30,000 የማምረት አቅም ላይ ሲደረስ 3.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ የንዑስ ዘርፉን ፈጣን ዕድገት የሚያመላክት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከገቢዎችና ጉምሩክ በተገኘ መረጃ በ2009 ዓ.ም. ብቻ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገቡት ተሸከርካሪዎች 43,723 ሲሆኑ፣ ለዚህም 30.2 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡ እስኪ ወገኖች ምርቱ በአገር ውስጥ እየተመረተ ይኼን ያህል መኪኖች መግዛት ለምን አስፈለገ? ለእነዚህ መኪኖች የተደረገው ወጪ አሁን በመከናወን ላይ ላሉ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ቢውል አገሪቱ መድረስ ለምትፈልገው የዕድገት ደረጃ ድርሻቸው የጎላ ይሆን ነበር፡፡  እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነበር!

የሚገርመው ደግሞ በመንግሥት ተቋማት፣ በግል ድርጅቶችና በግለሰቦች ዘንድ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ ለግንባታዎቻችን የምንጠቀማቸው ግብዓቶች፣ ለግብርና የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች አሁንም ድረስ ከውጭ የሚገቡ መሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም የአገር ምርትን መጠቀም የአንድ አካል የአመለካከት ችግር ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ዜጋ የሚነካ መሆኑን በዚህ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

እነ ቻይና፣ ህንድ፣ ወዘተ የራሳቸውን ምርት በየትኛውም አገር ሲሄዱ እንደሚጠቀሙ2 በዚህም አገራቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ይነገራል፡፡ ወደ እኛ ዜጎች ስንመጣ ደግሞ ከተማረው እስከ ተራው ዜጋ፣ ከባለሥልጣኑ እስከ ተራው ሠራተኛ፣ ከባለፀጋው እስከ ደሃው ያለው ዜጋ በአገሩ ምርት በመኩራት ረገድ ከፍተኛ የሆነ የአመለካከት ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ ነገር ግን ተናጋሪውም ሆነ ሰሚው ወደ እውነቱ መቅረብ አልቻሉም፡፡ እስኪ ይብቃ! ያደጉ አገሮችን ቤቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን ናፍቀን እስከ መቼ? እኛ እኮ ኢትዮጵያውን ነን! ኩሩ ሕዝብ፣ አልደፈር ባይ፣ በቅኝ ለተገዙት የነፃነት ምልክት፡፡ ይኼ ወኔ የት ሄደ?

ስለዚህ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ምርቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ ምርቶች ላይም ከፍተኛ እምነት ኖሮን፣ የአገራችንን ምርቶች በመጠቀም እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ አገራችንን ለማሠለፍ በጋራ እንነሳ፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉንም ርብርብ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም ከማውራት ወደ ተግባር እንግባ፡፡ የአገራችን ምርቶች የምንኮራባቸው እንጂ የምናፍርባቸው መሆን የለባቸውምና!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡