Skip to main content
x
ከምግብነት በላይ

ከምግብነት በላይ

ከአዳማ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ዴራ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ምግብ ለማዘጋጀት ማጀታቸው ገብተው ደፋ ቀና ማለት ጀምረዋል፡፡ በትንሽ ማሰሮ የተጣደው ውኃ እንደፈላ መጠኑን በእጃቸው ለክተው ጨው ጨመሩበት፡፡ ከዚያም በሰፌድ ላይ የነበረውን ዱቄት ይነሰንሱበት ጀመሩ፡፡ ጉልቻውን አልፎ የሚወጣውን ነበልባል ከምንም ባለመቁጠር ማሰሮውን በእግራቸው በመያዝ ዱቄቱን በደንብ አድርገው ከውኃው ማቀላቀልና ማገንፋት ጀመሩ፡፡ ውኃ ጠብ እያደረጉ ለ30 ደቂቃ ያህልም እሳት ላይ ካበሰሉት በኋላ ገንፎውን ወደ ማቅረቢያው ገለበጡት፡፡

ማቅረቢያው ከእንጨት የተሠራ እንደ ማሰሮው ጎድጎድ ያለ ዋንጫ የሚመስል (ቆሬ) ነው፡፡ ገንፎውን እንዳይዝ ውስጡን በቅቤና በበርበሬ ለቅልቀውታል፡፡ ገንፎውን ወደ ቆሬው ከገለበጡ በኋላ ውስጡ እንዳለ ያገለባብጡት ያዙ፡፡ ከዚያም የኳስ ቅርፅ የያዘውን ገንፎ መሀሉን ከፍተው ቅቤና በርበሬ አደረጉበት፡፡ ማዕድ ቀርቦ እስኪበላ ቅቤው እንዳይቀዘቅዝ በሚል ቅቤና በርበሬ የገባበትን ሥፍራ መልሰው ጠፍጠፍ ባደረጉት ገንፎ ከደኑት፡፡ ዳር ዳሩ ላይም ከቀንድ የተሠሩ ቄንጠኛ ማንኪያዎች ሰካኩበት፡፡ ከርቀት ሲመለከቱት ምግብ ሳይሆን የጠረጴዛ ጌጥ ይመስላል፡፡

አቀራረቡ እንኳንስ ገንፎ በልቶ ያደገን ሰው ሌላውንም ቢሆን የሚያጓጓ ነው፡፡ ትኩስና በቅቤ የራሰ ሲሆን፣ ተሻምተው የሚበሉት ዓይነት ነው፡፡ ከጎናቸው ሆኖ አንዴ ማማሰያውን ተቀብሎ በማገንፋት፣ አንዴ ደግሞ ቅቤ በመጨመር ሲረዳቸውና አብሯቸው ሲሠራ የነበረው ሼፍ ዮሐንስ ገብረ የሱስ ገንፎውን ለመቅመስ ማዕድ እስኪቀርብ አልጠበቀም፡፡ ከማድ ቤት ሳይወጡ ነበር አንድ ማንኪያ የጎረሰው፡፡ አጎራረሱ ምራቅ ያስውጣል፡፡ አይጋሩት ነገር ተጋብዘው የተገኙበት ድግስ ሳይሆን በቴሌቭዥን በሚመለከቱት የሼፍ ዮሐንስ የምግብ አዘገጃጀት ፕሮግራም ላይ የቀረበ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ከአዳማ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ዴራ የተባለች ቦታ ተቀርፆ ከዓመት በፊት በዩቲዩብ ድረ ገጽ ላይ የተለጠፈ ነው፡፡

ገንፎ ከኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ጥሩ ገንፎ ለማዘጋጀት የተለየ ሙያ ይጠይቃል፡፡ ዱቄቱ ከውኃ ጋር መቼ መቀላቀል፣ እሳት ላይ ምን ያህል ጊዜ መቆየትና እንዴት መማሰል እንዳለበት  ካላወቁ ገንፎ መሥራት ከባድ ነው፡፡ የአንዲት ሴት ሙያም የሚፈተንበት ነው፡፡ ዶሮ በልቶ ችክን ያለ ወጥ የመሥራት ያህል ከባድ ባይሆንም ልምድ ይጠይቃል፡፡ ገንፎ አሠራሩ ብቻ ሳይሆን አቀራረቡም ልዩ ጥበብ አለው፡፡

‹‹ለመብላት አይደለም የተፈጠርነው፡፡ የምንበላው ለመኖር ነው፡፡ ለዚህም በምግብ ልንዝናና ልንደሰትበት ይገባል፤›› ይላል ሼፍ ዮሐንስ፡፡ እንደዚህ በጥንቃቄ ተሠርተው የሚቀርቡ ምግቦች ደግሞ ሁሉም የሚስማማባቸውና እርካታ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በልቶ መጥገብ ብቻ ሳይሆን የአምሮት ስሜት የሚፈጥሩና የሚናፈቁ ናቸው፡፡ ረሃብን ከማስታገስ ባለፈ የሚያስደስቱ፣ የሚያዝናኑም ይሆናሉ፡፡

በጥንቃቄ የተዘጋጀ ምግብ በጥሩ ሁኔታ ሲቀርብ አምስቱንም የስሜት ህዋሳት የሚሰማ ልዩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በልተው ወዲያው የሚረሱት አይደለም፡፡ ትዝታ ሆኖ በአዕምሮ ውስጥ የሚቀረፅ፣ በሌላ ጊዜ አምሮት የሚፈጠር፣ አሊያም የጥሩ ምግብ መመዘኛ አድርገው የሚወስዱት እንደሆነ ሼፍ ዮሐንስ ይናገራል፡፡ በባለሙያ የተሠራ ምግብ ከመብልነት ባለፈ ብዙ ነገር ነው፡፡ አሠራሩ፣ አቀራረቡና አመጋገቡ ሳይቀር ጥበብ ነው፡፡ ከዚህ ሲያልፍም በምግብ የተለያዩ ቅርፆችን በማውጣት አዲስ ነገር ለማሳየት የሚሞክሩም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ በዳቦና ኬክ አሠራር ላይ እየተለመደ የመጣውን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአገር ባህል ጥልፍ የደመቀ ቬሎ ለብሳለች፡፡ ፀጉሯም በጥሩ ሁኔታ ተፈሽኗል፡፡ ከደረቷ ተነስቶ ቁልቁል የሚወርደው ጥልፍ መሀል መሀሉ ላይ መስቀል ጣል ጣል ብሎበታል፡፡ ለፎቶ ግራፍ የተዘጋጀች ሙሽራ ትመስላለች፡፡ አንዲህ አምሮባትና ንግሥት መስላ ሲያዩዋት ሰው እንጂ ከአፍታ በኋላ ቆራርሰው የሚቀራመቷት ኬክ አትመስልም፡፡ መሰል ሥራዎች በተለያዩ ካፊቴሪያና ኬክ ቤቶች ማየት እየተለመደ የመጣና ምግብን ከመብልነት በዘለለ በጥበብ መልክ ማቅረብ እንደሚቻል ምስክር የሆኑ ናቸው፡፡

በዚህ ሙያ ለዓመታት የቆየው አወቀ አለሙ፣ ደንበኞቹ ያመጡለትን ማንኛውንም ዓይነት ዲዛይን አስመስሎ ይሠራላቸዋል፡፡ ለሕፃናትና ለአዋቂዎች የሚሠራው ኬክ እንደየ ምርጫቸው የተለያየ ነው፡፡ ሕፃናት ለልደታቸው በአውሮፕላን ቅርፅ የተሠራ፣ በሚወዱት አሻንጉሊት ምስል አሊያም በሚወዱት የፊልም ፓፔት መልክ እንዲሠራላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ትልቅ የሆሊውድ አርቲስቶች የተወኑበትና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ሚኒየንስ በተባለው አኒሜሽን ፊልም ያሉት ፓፔቶችን አስመስሎ የ12 ዓመት ልደቱን ለሚያከብር ታዳጊ የጋገረው ኬክ በዚህ ረገድ ይጠቀሳል፡፡ ለልደታቸው ባርቢን የመሰለች ኬክ መቁረስ የሚፈልጉም በተደጋጋሚ ጊዜ ባርቢን አስመስሎ እንዲሠራላቸው ያደርጋሉ፡፡

የ80 ዓመት የልደት በዓላቸውን ለሚያከብሩ አዛውንት የሠራው ኬክም ልዩ ጥበብ ከሚታይባቸው መካከል ነው፡፡ ጠየም ያሉ አዛውንት የማንበቢያ መነፅራቸውን ዓይናቸው ላይ አድርገው፣ ከዘራቸውን ከተቀመጡበት ሶፋው ጎን አስቀምጠው፣ የሚያነቡትን መጽሐፍ ጣጥለው በተቀመጡበት እንቅልፍ ጥሏቸው ይታይሉ፡፡ ለሚያያቸው አሻንጉሊት እንጂ ፈፅሞ ኬክ አይመስሉም፡፡

ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሚሰራቸው ኬኮች የተለየ ነገር ለማሳየት የሞከረው በወንድሙ ልጅ የልደት ፕሮግራም ላይ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ የሠራው አራት ማዕዘን ኬክ መሀሉ ላይ የመዋኛ ገንዳ ነበር፡፡ የመጀመርያው ቢሆንም ከሰዎች ያገኘው ምላሽ እንዲገፋበት ያበረታታው ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በኬክ የተለያዩ ቅርፆች መሥራትን ሥራው አደረገው፡፡ ‹‹ስዕል አሞካክራለሁ፤›› የሚለው አወቀ፣ ሙያውን ይበልጥ ያዳበረው ከዩቲዩብ ላይ የተለያዩ ቪዲዮዎችን በመመልከት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህም ሙያውንም አንድ ዕርምጃ ለማስኬድ እንዳስቻለው ይናገራል፡፡

ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል እንደሚባለው፣ የሚስብና የሚያጓጓ ነገር ሠርቶ ማቅረብ ያስደስተዋል፡፡ ይሁንና የተለያዩ ግብዓቶችን ለማግኘት ይቸገራል፡፡ ‹‹የተለያዩ ጥልቅ የሆኑ ዲዛይኖችን ፕሪንት የምናደርግበት ፕሪንተሮች የሉንም፡፡ ከከረሜላ የሚሠሩ ፈርጦችንም አገር ውስጥ ማግኘት አንችልም፤›› የሚለው አወቀ፣ የተወሰኑትን ግብዓቶች በሰው በሰው ለማስመጣት ጥረት ቢያደርግም በቂ አለመሆኑን ይናገራል፡፡

ያለውን ነገር ተጠቅሞ የሚሠራቸው ሥራዎች ግን ደንበኞቹን የሚያስደስቱ ናቸው፡፡ ኬኮቹ ጥበብ የሚታይባቸው፣ የተለየ ልፋት የሚጠይቁ ናቸውና ከሌሎቹ መደበኛ ኬኮች በተለየ ዋጋቸው ይጨምራል፡፡ አንድ ኪሎ ግራም ኬክ እንደየቦታው ቢለያይም መደበኛ ዋጋው ከ210 እስከ 300 ብር ድረስ ሲሆን፣ አወቀ የሚሠራቸው ኬኮች ግን በኪሎ ግራም 550 ብር ይሸጣሉ፡፡ በብዛት ለሠርግና ለልደት ዝግጅቶች የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ አብዛኛው ገበያው የልደት እንደሆነ ይናገራል፡፡

የኬክ ሥራው ላይ ሙሉ ትኩረቱን ያድርግ እንጂ የቡፌ ምግብ ዝግጅት ላይም ያስውብ (ዲኮር) ያደርግ ነበር፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በተለይ በትልልቅ ሆቴሎች የሚዘጋጁ የቡፌ ምግቦች ለየት ያለ ዲኮር ይደረግባቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ አቀራረባቸው የማይወዱትን ምግብ ሳይቀር እንዲደፍሩ የሚያጓጉ ይሆናሉ፡፡ በየቀኑ ከማዕድ የማይጠፉ የተሰለቹ ምግቦች ሳይቀሩ ቡፌ ላይ አዲስና አጓጊ ሆነው ይታያሉ፡፡

ቡፌ ላይ የሚታዩ አትክልቶች አቆራረጥና አከታተፋቸው ለየት ያለና የሚስብ ይሆናል፡፡ ዳቦ የሚቀርብባቸው ቅርጫቶች ሳይቀሩ በሚገርም ሁኔታ በሳጠራ መልክ የተሠሩና ሚናቸውን ሲጨርሱ የሚበሉ ዳቦ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ጣዕማቸው እንደመልካቸው የማይሆንባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም፣ በመልክ በመልኩ የሚደረደሩ የምግብ ዓይነቶች ኅብረ ቀለማቸው ከአቀራረባቸው ጋር  ልዩ ጥበብ የሚታይባቸው ይሆናሉ፡፡

ምግብ ማዘጋጀት አሰልቺ ሥራ የሚሆንባቸው አሉ፡፡ እንደዚህም ደግሞ ማብሰል የማይችሉ ወይም አንችልም ብለው የሚጨነቁ ብዙ አሉ፡፡ ምግብ የማብሰል ፍራቻ ያለባቸው (ሚጄሮካፎቢያ) ጥቂት አይደሉም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ምግብ ማዘጋጀት የሚያስደስታቸው አሉ፡፡ እንዲያውም ምግብ ማብሰል ፈጠራን ስለሚያካትት ለጭንቀትና ለተለያዩ የሥነ ልቦና ችግሮች እንደ ሕክምና ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ምግብ ሲያዘጋጁ ምንም ነገር ሳይረብሻቸው በፅሞና መሥራት የሚፈልጉም አሉ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎችም ምግብ ማዘጋጀትን ከሜዲቴሽን ጋር ያገናኙታል፡፡

የ38 ዓመቱ ሼፍ ኤልያስ ሲሳይ ምግብን በተመስጦ ከሚሠሩ መካከል ነው፡፡ ‹‹ምግብን የሚሠራው ልብ ነው፡፡ ሳበስል በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከልብ ከተሠራም ይጣፍጣል፤›› በማለት ምግብ ማዘጋጀት መረጋጋትና ተመስጦን የሚጠይቅ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የምግብ ጥበብ ከማዘጋጀት እንደሚጀምርም ይስማማል፡፡ በልዩ ተመስጦ ከልብ የተሠራን ምግብ አሳምሮ ማቅረብም ሌላው ጥበብ ነው፡፡ ‹‹ምግብ ላይ አልሠራንም ገና ብዙ ይቀረናል፤›› የሚለው ኤልያስ፣ ብዙ የተሻሉ ነገሮችን ማሳየት እንደሚቻል ያምናል፡፡ አሁን ያለበት የዕድገት ሒደትም ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲተያይ የተሻለ መሆኑን ያክላል፡፡

በትኩስ መጠጦች ሳይቀር ጥበብ ይታያል፡፡ የካፊቴሪያ ድባብ ከሆነው የማንኪያና ሹካ ካካታ፣ የስኒና ብርጭቆ ፍጭት፣ የወንበር ኳኳታ፣ የኬኮችና የትኩስ መጠጦች ሽታ፣ የሰዎች ጫጫታ ባሻገር በየማኪያቶና በየካፑችኖ ስኒዎች ውስጥ የሚታየው ጥበብ ሌላው የካፊቴሪያ መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ አስተናጋጁ በትንሿ ስኒ የሚያቀርብልዎን ማኪያቶ ፉት ከማለቶ በፊት አረፋው ላይ በቡናማ ቀለም የተሳለ የልብ ቅርፅ፣ ፓንዳ ወይም ሌላ ዓይነት ቅርፅ ያያሉ፡፡ ሁለት ጊዜ ያህል ፉት ሲሉ የሚጠፋ ቢሆንም የሚፈጥረው ስሜት ግን ይቆያል፡፡

በምግብ የተለያዩ ጥበቦችን መሥራት በብዛት በውጭ ምግቦች ላይ የተለመደ ቢሆንም በባህላዊ ምግቦችም ይታያል፡፡ ለቁርጥ የሚቀርብ ጥሬ ሥጋ ሳይቀር አጓጊ ሆኖ ሲቀርብ ይታያል፡፡ ለስለስ ያለ ቀይ ሥጋ በሥልት ተቆርጦ፣ አዋዜ ከጎኑ ተደርጎ፣ በኮባ ቅጠል ላይ ቀርቦ ሲታይ ልምዱ የሌላቸውንም ቢሆን እንዲሞክሩት ያደፋፍራል፡፡ እንጀራንም በተለያዩ ከለሮች ጋግሮ ማዘጋጀት ተለምዷል፡፡ 

ከአናቱ ቃሪያ ጣልጣል ተደርጎበት እስከነ እሳቱ በሸክላ የሚቀርበው የገል ጥብስ፣ ቅቤ ጨፍ ብሎበት በጣባ የሚቀርበው ክትፎ፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችና ከለሮች ታሽቶ በስሱ ተጋግሮ የሚቀርበው ቆጮ አምሮት የሚቀሰቅሱና በልዩ ልዩ አቀራረብ የሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ ቀምሰው ከሚያጣጥሙት በላይ አቀራረባቸው ይስባል፡፡ በምግብ አቀራረቡ የተመሰጡም ከመቅመሳቸው አስቀድመው ስልካቸውን አውጥተው ፎቶ ያነሳሉ፡፡ ከዚያም በፌስቡክ አሊያም በሌሎች ማኅበራዊ ድረ ገጾች ፎቶውን በመልቀቅ ሌላውን ምራቅ ያስውጣሉ፡፡ ይህም ምግብ ከምግብነት ባለፈ ብዙ ነገር መሆኑን ያሳያል፡፡