Skip to main content
x
ከባድ ጊዜ ያሳለፉ የቱሪዝም ዘርፉ ተዋናዮች ተስፋ የሚያደርጉት አዲስ ዓመት

ከባድ ጊዜ ያሳለፉ የቱሪዝም ዘርፉ ተዋናዮች ተስፋ የሚያደርጉት አዲስ ዓመት

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የታየው ፖለቲካዊ ትኩሳት፣ የኢኮኖሚውን ዘርፎች ሲነካካ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ ከውጭ የሚገባው የኢንቨስትመንት ፍሰት በአፍሪካ ቀዳሚ መሆን የቻለው በዚሁ ጊዜ ውስጥም ቢሆንም፣ አገር ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ግን የፖለቲካው ትኩሳት ሰለባ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ ንብረቶቻቸውና የመሠረተ ልማት አውታሮቻቸው ጉዳት ስለደረሰባቸው ለመንግሥት የካሳ ክፍያ ጥያቄ ማቅረባቸውም ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ መንግሥትም በገባው ዋስትና መሠረት ይህንኑ ለማድረግ ሲያጠናና የደረሰውን ጉዳት መጠን ሲመረምር መቆየቱም ይታወቃል፡፡ 

በዚሁ በፖለቲካ ሰበብ ጫና ውስጥ ገብቶ የሰነበተው ሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ነው፡፡ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ተከትሎ አውጆት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ባለመረጋጋቱ ከደረሰው የበለጠ በአዋጁ ሰበብ ጉዳት እንዳጋጠማቸው በርካቶች ሲገልጹ እንደቆዩ ይታወሳል፡፡ መንግሥት አዋጅ ማውጣቱ ብቻም ሳይሆን አሁንም ድረስ ያዝ ለቀቅ የሚለው የአገሮች የጉዞ ክልከላና ማስጠንቀቂያ በቱሪዝም ዘርፉ ተዋንያን ላይ ያሳረፈው ጫና ቀላል አልነበረም፡፡

በዚህ መስክ በተለይ ሆቴሎችና አስጎብኝዎች ድርጅቶች ከባድ ጊዜ እንዳሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡ በዚያም ላይ መንግሥት ኢንተርኔት እንዲዘጋ ማድረጉም፣ ከቱሪዝም ዘርፉ ባሻገር በሌሎችም ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ የተወደው ዕርምጃ በተለይ በሆቴልና መስተንግዶ ዘርፍ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት የገቡ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን የተፈታተነም ነበር፡፡ በርካታ ጎብኝዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በተጨማሪ በኢንተርኔት መዘጋት ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ ለማድረግ ያቀዱትን ጉዞ እንዲሰርዙ እንዳስገደደ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በሆቴል ረገድ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች የመኝታ ኪራያቸው ከ20 በመቶ ላይ ከመቀነሱም በላይ፣ ለደረሰባቸው የ380 ሚሊዮን ብር ኪሳራ የመንግሥትን ድጋፍ ለመጠየቅ የተገደዱበት ጊዜ ሆኖ አልፏል፡፡ ከውጭ አስጎብኝና የጉዞ ድርጅቶ ጋር በትብብር የሚሠሩ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም በተደጋጋሚ የተያዙ የጉዞና የጉብኝት ፕሮግራሞች እየተሰረዙባቸው ሲቸገሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በግል አቪዬሽን አገልግሎት መስክ የተመሰማሩ ድርጅቶችም በ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ጉዳት በማስተናገድ የኪሳራ ዓመት ለማሳለፍ መገደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉ በዚህ አኳኋን በርካታ ሥጋቶች ውስጥ ቢያልፍም፣ አሁንም ድረስ የሚጠበቀውን ያህል የውጭ ምንዛሪና የቱሪስቶች ፍሰት እያስተናገደ እንደሚገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ምንም እንኳ የቱሪስቶች መቅረት ሥጋት እንሚሆንበት በ2009 ዓ.ም. መጀመርያ ሰሞን ዳር ዳር እያለ ሲገለጽ ቢደመጥም፣ ከጎብኝዎች ቁጥርም ሆነ ሲያገኝ ከነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ አኳያ የተሰጋውን ያህል ችግር ውስጥ እንዳልነበር አስታውቋል፡፡ ከ900 ሺሕ በላይ ቱሪስቶች አገሪቱን መጎብኘታቸውንና ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ይህም ቢባል ግን በአገሪቱ ለታየው ችግር መንግሥት የሠራው የግንኙነትና የመረጃ አቅርቦት ተግባር በውጭ ጎብኝዎችና አስጎብኝ ድርጅቶች ሲተች ታይቷል፡፡ ስለ ፀጥታው ችግርና አደጋው በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች ስላለመከሰቱ፣ የተከሰተባቸው አካባቢዎችም ቢሆኑ ለጎብኝዎች በምን አግባብ ሥጋት እንደሚሆኑ፣ መንገዶች በየት አቅጣጫ እንደተዘጉ፣ በየት በኩል ማለፍ እንደሚቻል፣ የትኞቹ አካባቢዎች ከፀጥታ አደጋ ነፃ ናቸው፣ የትኞቹን የቱሪስት መዳረሻዎች ያለ ሥጋት መጎብኘት ይቻላል የሚሉ መረጃዎችን ማግኘት እንዳልቻሉ ሲገልጹ የነበሩ ጎብኝዎች፣ በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ግጭትና የፀጥታ ሥጋት ይበልጥ እንዲጋነንና ጎብኝዎችም ከሚገባው በላይ ጥንቃቄ በማድረግ ከመምጣት እንዲታቀቡ ማስገደዱን በተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡

በ2009 ዓ.ም. 3.5 ቢሊዮን ዶላር ያስገኘው የቱሪዝም ኢንዱስትሪው፣ ከ900 ሺሕ በላይ ጎብኝዎችም ተስተናግደውበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና በተከሰተው የፀጥታ ችግር፣ በተለይም በመጀመርያዎቹ ሁለት ሩብ ዓመታት (በመጀመርያው ስድስት ወራት) ሲጠበቅ ከነበረው ፍሰት ይልቅ እስከ 16 በመቶ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከታየውም ይልቅ በ2009 ዓ.ም. የ2.5 በመቶ ብቻ የገቢ ቅናሽ መመዝገቡን ሚኒስቴሩ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡

አዲሱ ዓመት ከመባቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በነሐሴ ወር የተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከእንግሊዝና ከአሜሪካ ለሚመጡ ጎብኝዎች በብዙ የሚጠበቅ ዕፎይታ ነበር፡፡ የእንግሊዙ ‹‹ዘ ጋርዲያን›› ጋዜጣ በድረ ገጹ ባስነበበው ዘገባም፣ በርካታ እንግሊዛውያን ጎብኝዎች በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸው የወጣውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሳይሆን፣ በአብዛኛው ተስፋ የሚያደርጉት በኢትዮጵያ መንግሥት የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት እንደሆነ አስፍሯል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ለበርካታ የኢኮኖሚው አውታሮች ትልቅ ዕፎይታ እንደነበር ግልጽ ቢሆንም፣ በተለይ ለቱሪዝም ዘርፍ ግን እጅጉን ሚና እንዳለው አያጠያይቅም፡፡ የአገሪቱ ዋናው የቱሪስቶች ፍሰት የሚመዘገብበት ወቅት፣ ከመስከረም እስከ ጥር ወይም የካቲት አጋማሽ ባለው ወቅት ውስጥ በመሆኑም ጭምር፣ የተነሳው አዋጅና የሚታየው አንፃራዊ የፀጥታ መሻሻል ለዘርፉ መነቃቃት ተስፋ እንደሚደረግ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡