Skip to main content
x

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይልቅ አስቸኳይ መፍትሔ ይፈለግ!

ከቅርብ ቀናት በፊት በአገሪቱ ለአሥር ወራት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ከዕረፍት ተመልሶ አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በአብዛኛው የአገሪቷ ቦታዎች በአንፃራዊነት ሰላም በመስፈኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ወስኗል፡፡ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ዋነኛ ምክንያት ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የነበሩት ብጥብጦች መሆናቸው ይታወሳል፡፡ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የነበሩት ተከታታይ ብጥብጦች በዋናነት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት ነበሩ፡፡

በወቅቱ በሁለቱ ክልሎች የተቀሰቀሱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እየበረቱ መጥተው በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል፡፡ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞም ምክንያት በባለሀብቶችና በአገር ሀብት ላይ የደረሰው ጉዳት፣ የአገሪቷ ኢኮኖሚም ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ አልፏል፡፡

መንግሥትም ለሕዝባዊ ተቃውሞው መነሻ ዋነኛ ምክንያት ነው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌያለሁ ሲል ተሰምቷል፡፡ አገሪቷ በአስቸኳይ አዋጅ ጊዜ በነበረችባቸው አሥር ወራት ውስጥ ከፍተኛ ተሃድሶ ውስጥ ነበርኩ ያለው መንግሥት፣ በቅርቡ በመንግሥትና በአገር ላይ በቢሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ ጉዳት አድርሰዋል ያላቸው ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ጀምሯል፡፡

መንግሥት በቅርቡ በከፈተው የሙስና ዘመቻም ከ55 በላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲታሰሩ፣ የ210 ግለሰቦች ንብረት በፍርድ ቤት መታገዱንም ሰምተናል፡፡ እንግዲህ በጥልቅ ታድሻለሁ ያለው መንግሥት በአገሪቱ በአንፃራዊነት ሰላም በመስፈኑ የአስቸኳይ ጊዜውን አንስቶታል፡፡

ሆኖም ግን የአስቸኳይ ጊዜ በተነሳ ማግስት በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች የሚሰሙት ወሬዎች ደስ የሚሉ አይደለም፡፡ በተለይ የአስቸኳይ ጊዜው ከመታወጁ በፊት ሕዝባዊ ተቃውሞ ይካሄድባቸው በነበሩት አካባቢዎች ዳግሞ ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌ የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር ፈትቻለሁ ማለቱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ አገሪቷም ዳግም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በኢኮኖሚው ለይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ መቋቋም ትችላለች ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት በግልጽ ተቃውሞ ከሚያሰሙት ዜጎች ጋር በመወያየት መፍትሔ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው አገሪቷ ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ከመግባቷ በፊት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ለውይይት ይቀመጡ፡፡ ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በፊት አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልግ፡፡

 (ኃይሉ በለጠ፣ ከአዲስ አበባ)

*****

‹ለፅድቅ እየተጋች ያለች አገር ኢትዮጵያ›

ከወር በፊት ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ደግነትን ለኢትዮጵያ ያላበሰና ከዜጎቿ በላይ ለሌሎች ዜጎች የምትጨነቅ አገር እንደሆነች የሚገለጽ ዜና አስነበበን፡፡ ይገርማል፡፡ ‹ሀብታሟ› አገሬ በግዛቷ ውስጥ ለተጠለሉ ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የጎረቤት አገር ስደተኞች የሥራ ዕድል ልትፈጥርላቸው መሆኑ አጃኢብ ያሰኛል፡፡ ይህቺ የፖለቲካ ቀልድ ምን ያህል አትራፊ እንደሆነች ይጠፋችኋል ብዬ አልገምትም፡፡ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የጎረቤት አገር ስደተኞችን በገፍ ተቀብላ ማስተናገዷ፣ አልፎ ተርፎ ‹አዛኝቷ› ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) በኩል አድናቆትንና ከበሬታን እንዳሰጣት ተደጋግሞ ተነግሮን ነበር፡፡

በዚያ ሙገሳና ሽንገላ ሞራሏ ከፍ ያለው ውዷ አገሬ ዛሬ ደግሞ ለስደተኛ ዜጎች በሙሉ የሥራ ዕድል ልታመቻችላቸው፣ መታወቂያና መንጃ ፈቃድ ወዘተ. ከኢትዮጵያዊው በበለጠ መልኩ ለማገልገል እየሠራች መሆኑ በእውነት ለፅድቅ እየተጋች ያለች አገር ናት እንድል አስገድዶኛል፡፡ ኧረ እንዲያው የፖለቲካ ጨዋታውም ቀርቶ የኢኮኖሚ ሥሌቱም ሳይነሳ ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባል የናጠጠች አገራችን በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲዎች የምታስመርቃቸውን ልጆቿን እንደ ቡናና ቆዳ ኤክስፖርት ልታደርጋቻው ነው? ወይስ በሚሊዮን የሚቆጠረው ሥራ አጥ ኢትዮጵያውያንን የሚታደግ ዳቦ ከሰማይ ይወርድላታል? ኧረ እየተስተዋለ!!

የትግራዩ ፕሬዚዳንትም ተናገሩት የተባለውም የሚያስደንቅ ነው፡፡ ‹‹በመቐለ የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኤርትራውያን እንጂ ለትግራውያን ሥራ አጦች አይደለም፤›› አሉን በገደምዳሜ፡፡ ኧረ ሌላ ጉድ ሳንሰማ መስከረም በጠባ፡፡ እንዲያው በምን ሥሌት ይሆን የትግራዩ ሥራ አጥ ወገኔ ሥራ ሳያገኝ፣ የኤርትራው ስደተኛ ሥራ የሚሰጠው? ይህቺም የፖለቲካ ሽሙጥ መሆኗ ነው? በመጨረሻም ስደተኞችን በተለይም የኤርትራን ከተቻለም ጠቅላላውን የኤርትራን ሕዝብ ከኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ነጥሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈርና ‹ወዲ አፎምን› ብቻቸውን አስመራ ቤተ መንግሥት ለማስቀረት አገሬ የያዘችው ውጥንም እንዳለ በውስጠ ወይራ ተነገረን፡፡ ለሕፃናቶች እንኳን የማይመጥን ቀልድ ይመስላል፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ በ‹ነካ እጇ› የደቡብ ሱዳን ዜጎችንስ ከሳልቫ ኪር አገዛዝ ለመነጠል እየተጋች ይሆን? የሱማሌን ሕዝብስ? ድንቅ የዓመቱ የፖለቲካ ቀልድ ይላችኋል ይኼ ነው፡፡ የአገራችን የውስጥ ፖለቲካ አልጠራ እያለ ሲያስቸግር ደግሞ የውጭውን ፖለቲካ በስደተኞች አዛኝነትና ተንከባካቢነት ስም ድፍርስርሱ የወጣ ፖለቲካ ማውራት እንዴት ደስ ይላል? በየዓመቱ ከ100 ሺሕ በላይ ተመራቂ ወጣቶች የሥራ ያለህ የሚሉባት አገር፣ በሚሊዮን የሚቀጠር ሥራ አጥ በሞሉባት ኢትዮጵያ፣ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ረሃብተኛ ዜጎቿን ዳቦ ለማብላት መከራ የምታይ አገር፣ ኢትዮጵያውያን በቋንቋና በብሔር ተከልለው የግንብ አጥር በሠሩባት በዚህ ዘመን፣ ‹‹ከክልሌ ውጣልኝ የአንተ ክልል እዚያ ነው›› እየተባለ ንብረት ሳይቀር እየተቀማ በሚሰደድባት ኢትዮጵያ፣ ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የጎረቤት አገር ስደተኞች ዜጎቿ የሥራ ዕድል ልትፈጥር ነው ሲባል እንዲያው በደፈናው የጊዜው ምርጥ የፖለቲካ ፌዝ ልበለው ይሆን? የውጭ አገር ስደተኞችን ከማስተማር አልፋ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣ የዜግነት ሰነድና የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በመክፈት ስደተኞችን በሙሉ ሥራ ልታስይዛቸው የምትሞክር ደጓ አገር ኢትዮጵያ! ድንቄም አሉ አያታችን! መቼም በዚህ ዜና እነ አሜሪካና አውሮፓ ሳይቀኑ ይቀራሉ ብላችሁ ነው?

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከአዲስ አበባ)