Skip to main content
x

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በታምሩ ጽጌና በዳዊት እንደሻው

ከሕዝብ ለልማት የተሰበሰበ ግብርን ጨምሮ በተለያዩ ሀብቶች ላይ እምነት በማጉደልና በሥልጣን በመባለግ የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ደላሎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ የመንግሥት ከሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ማንነት ግን አልተገለጸም፡፡

መንግሥት በሙስና ጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ከሌሎችም ተቋማት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ለሕዝብ በገባው ቃል መሠረት ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ጥናቶችን ሲያደርግ መክረሙን፣ በተለይም በአዲስ አበባና በፌዴራል ኦዲት መሥሪያ ቤቶች ሪፖርቶች መሠረት የማጣራት ሥራ ካከናወነ በኋላ፣ እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ 34 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና ቁጥራቸው ሊጨምር እንደሚችል የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ነጋዴዎች፣ ደላሎችና ሌሎች ግለሰቦችም የተካተቱበት መሆኑን የገለጹት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው የተጠርጣሪዎቹን ስም ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ በቁጥር እንደተገለጸው 26 የመንግሥት የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ሲሆኑ፣ ሰባቱ ነጋዴዎች፣ አንዱ ደግሞ ደላላ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የደላሎቹ ቁጥር እንደሚጨምር ተሰምቷል፡፡

ይህ ዘመቻ የተደረገው ቀደም ብሎ የፌዴራል ዋና ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ እንደ አዲስ ተደራጅተው ጥናት እንዲደረግ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ነው ብለዋል፡፡ በጥናት የተለዩትንና ከሙስና ጋር ንክኪ እንዳላቸው መንግሥት መረጃ ካገኘባቸው በርካቶች የተወሰኑትን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ኃላፊው አክለዋል፡፡

ከሙስና ጋር የተያያዙ ወንጀሎች በጣም ውስብስብና መረጃው የሚገኝበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መንግሥት ጊዜ እንደወሰደበት ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ጥናት ሲያደርግ እንደቆየና አሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ብቻ ሳይሆን ከዚህም በላይ እንደሚኖሩ ገልጸው፣ በሒደት መንግሥት እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው በአፅንኦት የተናገሩት ይህ ዕርምጃ የተወሰደው ያለ መረጃ አለመሆኑን ሕዝቡ እንዲገነዘብ ነው፡፡ ‹‹ሕዝባችን ይህ ዕርምጃ ያለ መረጃ አለመወሰዱን ማወቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ሕዝቡም ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡