Skip to main content
x
ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 43 የአቫንዛ ሜትር ታክሲዎች ሥራ ጀምሩ

ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 43 የአቫንዛ ሜትር ታክሲዎች ሥራ ጀምሩ

የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪስት ታክሲዎች በዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ለመተካት እንዲያስችል መንግሥት ከታክስ ነፃ እንዲገቡ በመፍቀዱ ምክንያት 43 ዘመናዊ አቫንዛ ሜትር ታክሲዎች ወደ ሥራ ገቡ፡፡

በ2008 ዓ.ም. ከተመዘገቡት 26 የታክሲ ማኅበራት ውስጥ አንዱ የሆነው የኮንፎርት ሜትር ታክሲ ማኅበር አንዱ ሲሆን፣ 14,882,321 ብር ወጪ አቫንዛ ሞዴል ቶዮታ ታክሲዎቹን ሐምሌ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ተረክቦ ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡

ታክሲዎቹን ለመረከብ ስድስት ወራት የፈጀበት ማኅበሩ፣ ቀደም ብሎ ላዳ ላርገስ ከተባለ የተሽከርካሪ አስመጪ ጋር በ300 ሺሕ ብር ለመግዛት ቢስማማም፣ ከግዢ በኋላ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ባለመስማማት ስምምነቱ በማፍረስ ከሞኤንኮ ጋር መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡

70 በመቶ በብርሃን ባንክ አማካይነት ብድር የተመቻቸላቸው ሲሆን፣ 30 በመቶውን (110 ሺሕ ብር) የማኅበሩ አባላት በማውጣትና በ13.75 በመቶ የብድር ወለድ ታሳቢ ክፍያ ታክሲዎቹን ተረክበዋል፡፡

በአምስት ዓመት የብድር መክፈያ ጊዜ ውስጥ ዕዳቸውን ማጠናቀቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ሁለት ዓይነት የአከፋፈል ዘዴ እንደተቀመጠላቸውም ተጠቅሷል፡፡ የሦስት ወራት የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ ሙሉ ክፍያውን መክፈል ለሚፈልጉ፣ አለያም በየወሩ ከ4000 ብር ጀምሮ መክፈል እንዲችሉ ወይም በወር ከ8,500 ብር በላይ ክፍያ በመፈጸም ዕዳቸውን ማቃለል የሚችሉበትን አሠራር ባንኩ ማመቻቸቱን የኮንፈርት ሜትር ታክሲ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ባልቻ አብራርተዋል፡፡

ከዓመት በፊት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበት ዋጋ 463 ሺሕ ብር የነበረ ቢሆንም፣ መኪናዎቹ እስኪገቡ ባለው ጊዜ ውስጥ የዶላር የምንዛሪ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በአንዱ መኪና ብቻ የ22 ሺሕ ብር ጭማሪ በማሳየቱ፣ ዋጋውን ወደ 485 ሺሕ ብር እንደደረሰ አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡

ሰባት ሰው ማሳፈር የሚችሉት አቫንዛ ታክሲዎች፣ ጂፒኤስና የጉዞ ርቀት መለኪያ ሜትር፣ አውቶማቲክ ማርሽ፣ ቪቪቲ-አይ ሞተር የተገጠመላቸው እንደሆኑ የሞኤንኮ ጨረታና ሽያጭ ክፍል ኃላፊ ቀረጥ ሙሉጌታ ሰይፈ አብራርተዋል፡፡

አዲሶቹ ታክሲዎች 1,500 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያላቸው፣ የመቆጣጠሪያ ካሜራ የኪሎ ሜትር መለኪያና መቁጠሪያ፣ የአቅጣጫ ማመልከቻ (ጂፒኤስ) የተገጠመላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ታክሲ የተባለው ድርጅት ባሰናዳው ዘመናዊ የስልክ ጥሪዎች ማስፈንጠሪያ (አፕልኬሽን) አማካይነት የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡ ደንበኞች ኮምፎርት ታክሲ አገልግሎትን ለማግኘት በ8707 በመደወል የ24 ሰዓትና የሰባት ቀናት አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ የኢታ ኢትዮጵያ ታክሲ መሥራች አቶ ተመስገን ገብረ ሕይወት አብራርተዋል፡፡

ከመነሻ ጀምሮ በኪሎ ሜትር 13 ብር ተደርጎ የመሳፈሪያ ዋጋው በመንግሥት በተቀመጠው ተመን መሠረት፣ ማኅበሩ ተጠቃሚውን ለማገልገል ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይሁንና ክርክር ያስነሳውን ይኼንን የታሪፍ መጠን በሒደት ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የማያዋጣ ከሆነ ለመፍታት እንደሚሞከር አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ የወጣው ታሪፍ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ማኅበራቱ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ አንፃር እንደሆነና ማኅበሩን ለማሳደግ የተማረ ኃይል ቀጥረው ለማሠራት ወጪ ስለሚጠይቃቸውና በአገሪቱ ያለው የመንገድ ልማት የተቀመጠው ታሪፍ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የኮንፈርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አክለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ማኅበሩ የተለያዩ የቁጠባ መንገዶችን በመከታተልና ወደፊት ከመንግሥት መሬት በመጠየቅ የነዳጅ ማደያና የቱሪስት ተሽከርካሪዎች ላይ በሰፊው መሰማራት እንደሚፈልጉ ጠቀሰዋል፡፡

ኮንፈርት ሜትር ታክሲ ማኅበርን ጨምሮ አራት ማኅበሮች ከሞኤንኮ የአቫንዛ  ተሽከርካሪዎችን የተረከቡ ሲሆን፣ በክልልም በሐዋሳ ከተማ ማኅበር ተቋቁሞ  በዘርፉ ለመሰማራት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

ትዩ ዘመናዊ ታክሲ ማኅበር 35 ታክሲዎችን፣ ቦሌ ኤርፖርትና ሆቴል ታክሲ ማኅበር 79፣ ግሬይ ታክሲ 35፣ እንዲሁም ኮምፎርት ሳሎን ታክሲ ማኅበር 43 ዘመናዊ ታክሲዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 192 ታክሲዎችን አቫንዛ ዘመናዊ ታክሲዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ኢታ ግንቦት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትና የዘመናዊ ስልክ ታክሲ መጥሪያ አፕልኬሸን የ24/7 ቀናት የታክሲ ጥሪ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅት ነው፡፡ ኢታ ታክሲ መጥሪያ ሶፍትዌር በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያኖች የተሠራ ሶፍትዌር ነው፡፡