Skip to main content
x
ከ40 በመቶ ያላነሰ የጥሬ ቆዳ አቅርቦት የሚገኝበት የፋሲካ በዓል ቀደምት የከብት ምንጮቹን እያጣ ነው

ከ40 በመቶ ያላነሰ የጥሬ ቆዳ አቅርቦት የሚገኝበት የፋሲካ በዓል ቀደምት የከብት ምንጮቹን እያጣ ነው

  • ድርቅና የመኖ እጥረት የምዕራብ ኦሮሚያ ሠንጋዎችን ከመሀል አገር እንዳሸሹ ይነገራል

በኢትዮጵያ ከሚከበሩ በዓላት መካከል በአንፃራዊነት ከፍተኛ የከብት ዕርድ የሚፈጸምበትና የአገሪቱን 40 በመቶ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት እንደሚሸፈን የሚነገርለት የፋሰካ በዓል፣ ከዚህ ቀደም በዋና የከብት ምንጭነት የሚታወቁና ለዓመታት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ የምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች በሰሜን ሸዋ በተለይም ከጎንደር በመጠኑ ከጅሩ የሚመጡ የዕርድ ከብቶች ገበያውን የማረጋጋት ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ 

በየዓመቱ በአገሪቱ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ የበግ፣ የፍየልና የበሬ ዕርድ እንደሚፈጸም ሲገመት፣ ከዚህ ውስጥ የ40 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዝ የሚታመነው የፋሲካ በዓል እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ፋሲካ በዓል ወቅትም ተመሳሳይ መጠን ያለው ከብት ለዕርድ እንደቀረበ ይታሰባል፡፡ ከዚህ የዕርድ መጠን ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት ከብቶች የሚቀርቡት ከምዕራብ ሸዋ፣ በተለይም ከቦረና፣ ከጅማና ከሰላሌ እንዲሁም በደቡብ በኩል ከክብረ መንግሥት ይመጡ የነበሩ ሠንጋዎች አሁን ላይ ቁጥራቸው እየተመናመኑ መምጣታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ገበያዎች ከሚቀርቡ ሠንጋዎች አብዛኛውን ድርሻ በመያዝ በተለይ በፆመ ሁዳዴ የሁለት ወር ቆይታ ወቅት ገበያውን የሚቆጣጠሩት የቦረና ከብቶች ከዕይታ መጥፋታቸውን የገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቄራ አካባቢ የከብት ግብይት ማዕከል አስተባባሪው አቶ ተክኤ ግደይ ናቸው፡፡ አቶ ተክኤ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ በተለምዶ በፆሙ ወቅት ሳይቀር ከፍተኛ የገበያ ድርሻ በመያዝ ይቀርቡ የነበሩት የቦረና አካባቢ ሠንጋዎች ዘንድሮ አልገቡም፡፡ በመሆኑም ከፍተኛውን የገበያ የበላይነት በመያዝ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የአዲስ አበባን አቅርቦት አረጋግተው የቆዩት ከጎንደር ሲገቡ የቆዩ ከብቶች ሆነዋል፡፡ አሁንም ድረስ በዚሁ መሠረት የቀጠለው የገበያው ሁኔታ የፋሲካ በዓልንም እንደዚሁ በጎንደር አቅርቦት ለመሸፈን እንደተቻለ አቶ ተክኤ አብራርዋል፡፡

የቦረና አካባቢ ከብቶች ከገበያ ከቀሩባቸው ምክንያቶች መካከል እንደ አቶ ተክኤ ማብራሪያ በብዛት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ሲሆን፣ ለከብቶቹ የሚውል መኖ እንደልብ ማግኘት ባለመቻሉም ጭምር ለገበያ ሲቀርቡ ማየት አልተቻለም፡፡ የከብቶቹ አቅርቦት አነስተኛ መሆን በዋጋቸውም ላይ ጭማሪ በማስከተሉ፣ ነጋዴዎች ወደ መሀል አገር ማጓጓዙን እንዳላዋጣቸው ይነገራል፡፡ ይህም ሆኖ ሌሎች ከሚቀርቡ ምክንያቶች መካከል በአብዛኛው የኮንትሮባንድ ገበያው ልቅ እየሆነ መምጣቱ አንድ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በቅርቡ እንደ አዲስ የተቋቋመው የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ሚኒስቴር በሥሩ የሚመራው የኢትዮጵያ የቀንድ ከብት ግብይት መረጃ ሥርዓት ድረ ገጽ እንደሚያትተው ከሐረር በተለይም ከባቢሌ የሚመጡ ሠንጋዎች፣ በጎችና ፍየሎችን ወቅታዊ የገበያ ዋጋና አቅርቦት ይተነትናል፡፡ መረጃም ይሰጣል፡፡ ይሁንና በበዓላት ወቅት ወደ መሀል አገር ስለሚገባው የከብት ብዛትና የዋጋ ሥሪት ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት አንደኛው የዚህ ምክንያት የመረጃ ሥርዓቱን የሚመሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ደጋግሞ መቀያየር፣ በሥራው ሒደት ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ የገበያውን እንቅስቃሴና የሚታዩበት ለውጦች ለማሳየት አላስቻለም፡፡ በመሆኑም በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአፋርና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የገበያ ማዕከላት ስለሚካሄዱት ግብይቶች ወቅታዊ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡  

ይሁንና ከዚህ ቀደም በበዓላት ወቅት ተመራጭ የነበሩትን የሐረር ሠንጋዎች የተኩት ከጎንደር የሚመጡት ሲሆኑ፣ ከወለጋ፣ ከጅማና ከመሳሰሉት የምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች ይገቡ የነበሩ ሠንጋዎች እየተመናመኑ መጥተዋል ተብሏል፡፡ በመሆኑም ከሰሜን ሸዋ አካባቢ በተለይም ከጅሩ የገቡ ሠንዎች ቢኖሩም የጎንደር ሠንጋዎችን ያህል ከፍተኛ ቁጥር እንዳልያዙ ታውቋል፡፡ በዋጋ ደረጃም ቢሆን የጎንደር ሠንጋዎች ከሐረር ይልቅ በዋጋ ቅናሽ እንዳሳዩ ተጠቅሷል፡፡ ለአብነትም በሳምንቱ የገበያ ቀናት ማለትም ረቡዕና ሐሙስ በዋለው የቄራ ገበያ የጎንደር ሠንጋዎች ከ12 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ 25 ሺሕ ብር ድረስ ዋጋ ሲያወጡ ተስተውለዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተመራጮቹ ቅልብ የሐረር ሠንጋዎች ከ25 እስከ 27 ሺሕ ብር ዋጋ ይሰጣቸው እንደነበር ከአቶ ተክኤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የጎንደር ሠንጋዎች ከ700 በላይ ኪሎ ሜትር ተጓጉዘው ወደ መሀል አገር ሲመጡ በዋጋ ደረጃ እንደምን ሊቀንሱ ቻሉ? ለሚለው ጥያቄ፣ የፆሙን ወራት ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ ገበያውን የያዙት የጎንደር ሠንጋዎች በመሆናቸው በዋጋ ደረጃም ይህ ነው የሚባል ጫና እንዳልታየባቸው ያብራሩት አቶ ተክኤ፣ ከዚህ ቀደም በኮንትሮባንድ በቀላሉ በመተማ በኩል ይወጡ የነበሩ ከብቶች በአሁኑ ወቅት ግን በዚህ መንገድ ሊወጡ ባለመቻላቸው፣ ትልቁ የገበያ መዳረሻቸው መሀል አገር እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት የከብቶቹ አቅርቦት በተለየ መንገድ ሊበራከትና ገበያውን ሊቆጣጠር እንደቻለ ግምት መኖሩን አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የከብት መገበያያ ጣቢያ ከሆኑት የሸጎሌ፣ የቀራሮ እንዲሁም የቄራ ገበያዎች መካከል በብዛት ጉልህ ድርሻ የያዘው የቄራ ገበያ ከ2,000 ያላነሱ ሠንጋዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው የገለጹት አቶ ተክኤ፣ በፋሲካ በዓል እስከ 1,500 የሚገመት ሠንጋ በቄራ በረት ውስጥ መስተናገዱን ይገምታሉ፡፡

አብዛኛው በላተኛ በቅርጫ ለማረድ እንደሚገኝ ሲገመት፣ አብላጫውን ድርሻ የሚይዙት ግን ልኳንዳ ቤቶች ሆነዋል፡፡ ከሰሞኑ የሠርግ ወቅት ስለሚሆንም ከፍተኛ ዋጋ የሚጠየቅባቸው በልዩ ሁኔታ ተቀልበው የደለቡ የጅሩ ሠንጋዎች እንደሚገቡም ይጠበቃል፡፡ ከሠርግ ባሻገር የተወሰኑ ልኳንዳ ቤቶች በትዕዛዝ የሚያመጧቸው ቅልብ ሠንጋዎችም እስከ 40 ሺሕ ብር ሲጠየቅባቸው እንደነበር ባለፈው ዓመት ከነበረው የገበያ አጋጣሚያቸው አስተባባሪው ይናገራሉ፡፡

የበዓል ሥጋ አቅርቦት በዚህ መልኩ ሲገለጽ፣ በጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅርቦት መስክም የፋሲካ በዓል ከፍተኛ ድርሻ በመያዝ የአገሪቱን የቆዳና ሌጦ ፋብሪካዎች በመመገብ ድርሻው የጎላ ሆኖ ይገኛል፡፡ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል ከአገሪቱ የከብት ዕርድ ውስጥ እስከ አራት ሚሊዮን የሚገመት ወይም 40 በመቶውን የሚሸፍን ጥሬ ቆዳና ሌጦ ለገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም ስድስት ሚሊዮን ያህል ዕርድ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ ከዚህ ውስጥ እስከ 400 መቶ ሺሕ የሚገመት ጥሬ ቆዳና ሌጦ ሊሰበሰብ እንደሚችል በመጥቀስ አቶ ብርሃኑ የገበያውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡