Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው ውስጥ እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ተመራማሪ ከሆነ የቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኙ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው ውስጥ እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ምን ሆነዋል?
 • ምን ሆንኩ?
 • ፊትዎ በጣም ጠቋቁሯል፡፡
 • ምን የማያጠቁር ነገር አለ ብለህ ነው?
 • ቤት ሰላም አይደለም እንዴ?
 • አሁን አሁን ሁሉ ነገር እያስጠላኝ መጥቷል፡፡
 • ሁሉ ነገር ሲሉ? ዘመኑ የከፍታ ነው እየተባለ?
 • ወይ ከፍታ?
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር? አየሩ ራሱ ከክረምት ወደ በጋ በሚቀየርበት በዚህ ወቅት ምንድን ነው እንደዚህ መሆን?
 • ወይ አዲስ ዘመን?
 • ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ ለእኔ ሁሉም ነገር ነው የጨለመብኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ዝም ብሎ ክፉ ነገር ማሰብ ጥሩ አይደለም፡፡
 • ወድጄ አይደለም ጥሩ ነገር ለማሰብ ሞክሬ ነበር፡፡
 • ምን አስበው ነበር?
 • ያው የከፍታ ዘመን ነው ብዬ በአዲስ መንፈስ ዘመኑን ለመጀመር ወስኜ ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ገጠመዎት?
 • ሁሉ ነገር ከፍ የሚያደርግ አይደለማ፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው በዚህ ዓመት ከፍ ካለው ቪ8 ወደ አነስተኛ መኪና ተዘዋወርን፡፡
 • እሱስ ልክ ነው፡፡
 • እኔ የደመወዝ ከፍታ ስጠብቅ ጭራሽ ወደ ቅነሳ መጣብን፡፡
 • ምን ያደርጉታል?
 • በቃ ስነግርህ ሁሉ ነገር ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡
 • እንዲህማ በቀላሉ እጅ መስጠት አያስፈልግም፡፡
 • ከምወደው ሕዝብ ጋር እንኳን መገናኘት አልቻልኩም፡፡
 • ምነው ስልክዎ ተቆረጠ እንዴ?
 • ይኸው ዊኬንድ ላይ ስንት የስልክ ጥሪ ነው የተቀበልኩት፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ያስለመድከን ነገር ቀረ ብሎ ስንት ሰው ነው የደወለልኝ፡፡
 • ኮሚሽን የሚሰጧቸው ሰዎች ናቸው?
 • ምን ይላል ይኼ? አጀንዳና ካላንደር መቼ አሳተምን?
 • የማተሚያ ቤቱ ሰዎች ደወሉልዎት እንዴ?
 • ለማንኛውም የከፍታው ነገር አስከፍቶኛል፡፡
 • ኧረ ይኼን ያህል አያማሩ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ የአሁኑ የእኔ ኑሮ እኮ ኑሮ አይደለም፡፡
 • ምን እያሉ ነው?
 • ስማ ዛፍ ላይ እንደሚተኛ ሰው እኮ እንቅልፍ የለኝም፡፡
 • ለመሆኑ ምን ሆነው ነው?
 • ስንት ጓደኞቼ እንደታሰሩ ተመልከት፡፡
 • እሱማ ማን ቀረ?
 • እኔ የቢሮዬ በር ሲንኳኳ ጠረጴዛ ሥር መግባት ራሱ ሰልችቶኛል፡፡
 • ለምንድነው ጠረጴዛ ሥር የሚገቡት ክቡር ሚኒስትር?
 • ፖሊስ እየመጣ እየመሰለኝ፡፡
 • ታዲያ እዚያ ተሸሽገው ያመልጣሉ ብለው ነው?
 • እንዲያው የድንጋጤዬ ብዛት ነው እንጂ፣ ጉድጓድ ውስጥ ብገባም እንደማላመልጥ አውቀዋለሁ፡፡
 • ታዲያ ይኼን ያህል ሽብር ምንድነው?
 • ስማ ቀን ቀን እንደዚህ አሳልፌ ማታ እንኳን ገብቼ መተኛት አልችልም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዲሁ ስባንን ነው የሚነጋው፡፡
 • ምን ተሻለዎት ታዲያ?
 • ሚስቴማ ፀበል ሞክር ብላኝ ነበር፡፡
 • እሱ ጥሩ ሐሳብ አይመስለኝም፡፡
 • ለምን?
 • ሰይጣኑ ቢለፈልፍ ምን ሊል እንደሚችል አስበውታል?
 • ምን ይላል?
 • አንዴ ሙስና ነኝ ሲል…
 • እ…
 • አንዴ ኪራይ ሰብሳቢ ነኝ ሲል መዋረድዎት ነው፡፡
 • እሱም አለ ለካ?
 • አንዴ ብረት ነኝ ሌላ ጊዜ ስኳር ነኝ እያለ ስንት ጉድ ነው የሚያወጣው፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለ? ጭራሽ ሥጋቴን ከፍ አደረግከው፡፡
 • ያው የከፍታ ዘመን ነዋ፡፡
 • ነገርኩህ በዋናነት በዚህ የከፍታ ዘመን ከፍ እያሉ ያስቸገሩኝ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡
 • ምንና ምን ናቸው?
 • ግፊትና ስኳሬ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ተመራማሪ ከሆነ የቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኙ]

 • ምነው ጠፉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሥልጠና ላይ ነበርኩ፡፡
 • የምን ሥልጠና?
 • በአገሪቷ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት?
 • ይቻላል፡፡
 • በዓለም ላይ እንደ ኢሕአዴግ ሥልጠና የሚወድ ድርጅት አለ?
 • እየቀለድክ ነው?
 • እውነቴን ነው እንጂ ከዓመት ዓመት ሥልጠና ላይ ናችሁ እኮ?
 • ሕዝቡን ለማገልገል ሥልጠና ወሳኝ ነው፡፡
 • በእርግጥ ሕዝቡን ለማገልገል ነው ሥልጠና የምትቀመጡት?
 • ታዲያ ለምንድነው?
 • ለአበል ነዋ፡፡
 • ምን ይላል ይኼ?
 • ለመሆኑ ስለምንድን ነው የምትሠለጥኑት?
 • ስለአገሪቷ ልማትና ዕድገት ነዋ፡፡
 • ሁሌ አብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት እንዴት ሥልጠና ይሆናል?
 • አንተ የተማርክ ሰው አይደለህ እንዴ?
 • ይጠራጠራሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሥልጠና ምን ያደርጋል እንዴት ትለኛለህ?
 • ሁሌ እንዴት ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት ትሠለጥናላችሁ?
 • እውቀትህን በሥልጠና ነው የምታዳብረው፡፡
 • ለነገሩ የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ አይደል ነገሩ?
 • ሞኝ ናችሁ እያልከን ነው?
 • ብልጥማ ብትሆኑ በአሁኑ ወቅት ከሥልጠና የሚቀድመው ሌላ ነገር ነው፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ሕዝብን ማዳመጥ፡፡
 • ሕዝብን ለማዳመጥም እኮ ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡
 • እሱንማ ብታደርጉ አንድ ነገር ነበር፡፡
 • ምኑን?
 • ሕዝብ ማዳመጡን፡፡
 • ማዳመጣችን አይቀርም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ካመለጣችሁ በኋላ ጣጣው የከፋ ይሆናል፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ከዓመት ዓመት ግምገማ፣ ሥልጠናና ስብሰባ ናችሁ፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ሕዝቡን መቼ ነው የምታገለግሉት?
 • ሕዝቡን ለማገልገል አይደል እንዴ የምንገማገመውና የምንሠለጥነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በዚህ አካሄዳችሁ አገሪቷን ወደ መጥፎ ቦታ እንዳትወስዷት?
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ይኸው በየቦታው የሚሰማው ብጥብጥና ተቃውሞ የብዙዎች ሥጋት እየሆነ ነው፡፡
 • አየህ የጥፋት ኃይሎችን መስማት የለብህም፡፡
 • ለነገሩ አሁን አንድ ነገር እየገባኝ ነው፡፡
 • ምንድነው የገባህ?
 • የምትሠለጥኑት ለምን እንደሆነ ተረድቼዋለሁ፡፡
 • ለምንድን ነው የምንሠለጥነው?
 • ላለመሻሻል!

 

[ለክቡር ሚኒስትሩ የእህታቸው ልጅ ከኒውዮርክ ደወለላቸው]

 • ጋሼ በተደጋጋሚ ስልክ ስደውልልህ አታነሳም፡፡
 • ስብሰባ ላይ ሆኜ ነው፣ ምን ገጥሞህ ነው?
 • ቀጠሮ እንደነበረን ረሳኸው እንዴ?
 • የምን ቀጠሮ?
 • ባለፈው ደውለህ ስትፎክርብኝ አልነበረ እንዴ?
 • ምን ብዬ?
 • ለUN ስብሰባ ኒውዮርክ እመጣለሁ ብለከኝ ነበር እኮ?
 • አልሆነም ባክህ፣ በዚህኛው ጉዞ ቀጡኝ ባክህ፡፡
 • አንተም ትቀጣለህ እንዴ ጋሼ?
 • ምን ማድረግ ይቻላል ብለህ ነው?
 • እኔ እኮ ባለፈው ሚስቴ የሞባይል ቤት ከፈተች ስትለኝ በጣም ደስ ብሎኝ ተዘጋጅቼ ነበር የምጠብቅህ?
 • የምን ዝግጅት ነው?
 • ያው እታባ አስተምራ ለዚህ ስላበቃችኝ ውለታዋን በትንሹም እንኳን እመልሳለሁ ብዬ አስቤ ነበራ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • አንተ ባለሥልጣን ስለሆንክ ያው ሻንጣህ አይፈተሽም አይደል?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ለሞባይል ቤቷ አንድ ሙሉ ሻንጣ ሞባይል ገዝቼ አስቀምጬ ነበር፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ እንግዲህ?
 • እኔማ ለልጆቹ ከአራት ሻንጣ በላይ ነበር ልብስ የገዛሁት፡፡
 • አዲስ መመርያ ወጥቶ እኮ እየተጨናነቅን ነው፡፡ ሁሉም ነገር እባክህ አስጠልቶኛል፡፡
 • ምነው ጋሼ?
 • እውነቱን ብነግርህ ብመጣም…
 • እ…
 • አልመለስም ነበር!

 

[ሌላ የክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራ ወዳጅ ደወለላቸው]

 • ምንድነው የምሰማው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሰማህ ደግሞ?
 • ባለፈው የውጭ አገር ኑሮ ሰልችቶኛል አላልኩዎትም ነበር፡፡
 • ነግረኸኝ ነበር፡፡
 • ወደ አገር ቤትም መመለስ እንደምፈልግ አጫውቼዎት አልነበር፡፡
 • እኔም እኮ እዚህ የተሻለ ነገር እንዳለ ነግሬሃለሁ፡፡
 • ታዲያ አሁን ምን እያደረጋችሁ ነው?
 • ይኸው እንደ አንተ ዓይነት ዳያስፖራዎች እዚህ እንዲሰበሰቡ ልማቱን እያሳለጥነው ነው፡፡
 • ቀልዱን ቢተውት አይሻልም ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • አሁን የምሰማው ነገር እኮ አገር ቤት እንድንመጣ የሚያደርግ ሳይሆን የሚያሸሽና የሚያስፈራ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስፈራው?
 • ይኸው በየቦታው አይደል እንዴ ግጭትና ዕልቂት ያለው? ከዚያም በላይ አገሪቷ መረጋጋት ካቃታት ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ነገር አደጋ ላይ ነው፡፡
 • ኢትዮጵያዊነት ምን ሆነ?
 • ይኸው በብሔር በመከፋፈል ኢትዮጵያዊነት አደጋ ውስጥ እየገባ ነው፡፡
 • እ…
 • በፊት እኮ እዚህ በብሔርና በጎሳ ኢትዮጵያዊ ተከፋፍሎ ቤተ ክርስቲያንና ምግብ ቤት ሲጠቀም ነበር፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • አሁን ግን ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያም እንደዚያው መሆኑ አይቀርም፡፡
 • እባክህ ይኼ የጠላት ወሬ ነው፡፡
 • ይኸው በየፌስቡኩ የመንግሥት ባለሥልጣናት አይደል እንዴ መግለጫ እየሰጡ ያሉት?
 • እሱማ አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በኋላ ግን ተጠያቂ መሆናችሁ አይቀርም፡፡
 • የምን?
 • የታሪክ!

 

 • [ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው አስጠሩት]
 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • መሥሪያ ቤታችን ላይ አንዳንድ ሥጋቶች አሉ፡፡
 • የምን ሥጋቶች?
 • መንግሥት መሥሪያ ቤታችን ላይ እያንዣበበ ነው፡፡
 • ለምን?
 • ያው ይደረጉ የነበሩ ምዝበራዎችን ሊያጣራ ነዋ፡፡
 • ያጣራ ታዲያ ማን ይፈራል?
 • ስማ የማላውቅ ይመስልሃል?
 • ምኑን?
 • እኔ የበላኋቸውን ኮሚሽኖች ስታቀባብል እንደበረ ነዋ?
 • እ…
 • ስማ አሁን መደንገጥ ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ ስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ አለብን፡፡
 • የምን ስትራቴጂ?
 • ሳንጠቃ ማጥቃት፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • በአስቸኳይ በመሥሪያ ቤታችን ስለሚሠሩ ፕሮጀክቶች የሚገልጽ ሪፖርት ይዘጋጅ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አየህ የሚዘጋጀው ሪፖርት መሥሪያ ቤታችን ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆን ማሳየት አለብን፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከዚያም ባለፈ ፕሮጀክቶቹ ፎቶና ቪዲዮ ይነሱ፡፡
 • አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች እኮ ግማሽ እንኳን አልደረሱም፡፡
 • ሪፖርቱ ከተዘጋጀ ማን መጥቶ ቼክ ያደርጋል?
 • ክቡር ሚኒስትር በአዲሱ መመርያ መሠረት ግን ሪፖርቱ ቢዘጋጅም ኅትመት ስለተከለከልን ማሳተም አንችልም፡፡ በዚያ ላይ እንደ ድሮው እንኳን በአጀንዳ መካከል የፕሮጀክቶችን ፎቶ እንኳን እንዳናስቀምጥ እሱም ተከልክሏል፡፡
 • አንተ ለስሙ ወጣት ነህ፡፡
 • ምነው ክቡር ማኒስትር?
 • ብቻ ሪፖርቱን አዘጋጅተህ ስጠኝ እኔ እለቀዋለሁ፡፡
 • በምን?
 • በፌስቡክ!