Skip to main content
x
[ክቡር ሚኒስትሩ ጠዋት ወደ ሥራ ከመሄዳቸው በፊት ከሴት ልጃቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

[ክቡር ሚኒስትሩ ጠዋት ወደ ሥራ ከመሄዳቸው በፊት ከሴት ልጃቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

 • በጠዋት አጥብቀሽ እፈልግሃለሁ ያልሽኝ ለምን ይሆን?
 • ዳዲ ለቁምነገር ነው፡፡
 • ቁምነገር?
 • አዎ ውድ አባቴ፡፡
 • እስኪ ንገሪኝ?
 • ዩኒቨርሲቲ ጨርሼ ሥራ ከያዥኩ ሁለት ዓመት አለፈኝ፡፡
 • ልክ ነሽ ልጄ፡፡
 • አሁን ደግሞ የሕይወቴን አዲስ ምዕራፍ ልጀምር ነው፡፡
 • እሱ ደግሞ ምን ይሆን?
 • ዳዲ ማግባት እፈልጋለሁ፡፡
 • እንዴ?
 • ምነው ዳዲ?
 • አንቺ  እኮ ለትዳር ገና ነሽ ልጄ?
 • አሁን ሃያውን ለማጋመስ እየተቃረብኩ ነው አባቴ፡፡
 • ቢሆንም ገና ነሽ፡፡
 • እሱማ የታወቀ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • ልጅ ለወላጁ መቼም ቢሆን ትንሽ እንደሆነ፡፡
 • ተሳሳትኩ ታዲያ?
 • ከ18 ዓመት በኋላ እንደሱ አይባልም ዳዲ፡፡
 • ለመሆኑ ማንን ነው የምታገቢው?
 • ቦይፍሬንዴን ነዋ፡፡
 • ይኼ ጨብራራውን?
 • ቁምነገሩ እሱ ሳይሆን ማንነቱ ነው ዳዲ፡፡
 • የምን ማንነት ነው የምትይው?
 • ሰው የመሆን ማንነት ዳዲ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ከልቡ ሰው ነው ማለቴ ነው አባቴ፡፡
 • ለመሆኑ ምን አለው?
 • ማለት?
 • አንቺን የሚያስተዳድርበት ምን አለው?
 • እሱም እንደኔ ይሠራል፡፡
 • ተቀጣሪ ነው እንዳትይኝ ብቻ?
 • ምናለበት ዳዲ?
 • ለመሆኑ ቤት አለው?
 • የለውም፡፡
 • ባንክ ውስጥ ገንዘብ አለው?
 • ለድንገተኛ መጠባበቂያ ያህል ትንሽ አለው፡፡
 • የራሱ መኪና አለው?
 • ወደፊት እንገዛለን አባቴ፡፡
 • ስንት ሚሊየነሮች እየተፈጠሩ ባለበት አገር ቺስታ ታገቢያለሽ?
 • አብረን ሠርተን ስለምናገኝ አያሳስበኝም አባቴ፡፡
 • የዘመኑ ብልጦች ሀብታም ያሳድዳሉ አንቺ ግን ደሃ ላይ ተለጥፈሻል፡፡
 • እኔ እኮ ትዳር ልያዝ አልኩኝ እንጂ ሌላ አላልኩህም ዳዲ፡፡
 • ትዳር እኮ የሚያምረው ከብር ጋር ነው፡፡
 • የእኔ ነፍስ የራባት ፍቅር ነው አባቴ፡፡
 • ቤት ከሌለው የት ልትኖሩ ነው ታዲያ?
 • ኮንዶሚኒየም እስኪደርሰን እንከራያለና፡፡
 • ባይደርሳችሁስ?
 • ኮንዶሚኒየሙ ቶሎ ቶሎ እንዲገነባ አድርጉዋ እናንተ፡፡
 • እየገነባን አይደለም እንዴ?
 • አቃተን እያላችሁ አይደል አባቴ?
 • ምን ኑው የሚያቅተን?
 • በሚፈለገው መጠን ቤት ገንብቶ ለሕዝቡ መስጠት ነዋ፡፡
 • ልማታዊ መንግሥታችን በፍጹም አያቅተውም፡፡
 • ገንዘብ መመደብ ካቅሜ በላይ ሆነ እያለ እኮ ነው አባቴ፡፡
 • ይኼ የፀረ ሰላም…
 • ኧረ አባቴ?
 • ምነው?
 • የእናንተው ሰዎች ስላሉት ዝም ብትል ይሻልሃል፡፡
 • ልጄ ከባልሽ ጋር የት ልትወድቂ ነው ታዲያ?
 • ሕዝቡ እንደሚሆነው እሆናለሁ፡፡
 • ወይ ፍርጃ?

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ጎረቤታቸው መጡ]

 • ጎረቤቴ እንደምን ነዎት?
 • ደህና ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጠዋት ከየት ተገኙ?
 • ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እስኪ ይንገሩኝ፡፡
 • የልጄ ነገር አሳስቦኝ ነው፡፡
 • ባለፈው ዓመት የዳሯት አንዲት ልጅዎ ምን ሆነች?
 • ለመውለድ ተቃርባለች ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼማ በጣም ደስ ይላል፡፡
 • ድሮ ልጅ ሲወለድ ደስ ይል ነበር…
 • እንዴ አሁንስ?
 • አሁንማ ያሳቅቃል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • እሷና ባልዋ የገቢያቸውን ግማሽ ለቤት ኪራይ ነው የሚከፍሉት፡፡
 • እሺ እባክዎን?
 • በዚህ ላይ ለተመዘገቡት ኮንዶሚኒየም ይቆጥባሉ፡፡
 • እሺ?
 • አሁን ደግሞ ልጅ ሲወለድ ወጪያቸው ይጨምራል፡፡
 • እህ…
 • ኮንዶሚኒየም ቤት ይደርሰናል ብለው ነበር ችግሩን እየታገሱ የቆዩት፡፡
 • ልማታዊ አስተሳሰብ አላቸው ማለት ነው፡፡
 • አሁንማ መንግሥት ገንዘብ ማውጣት አልችልም መባሉ ሲሰማ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡
 • ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ አይዞዎት፡፡
 • ቀደም ሲሉ ብዙ አማራጮች ሲቀርቡ መንግሥት አልሰማ አለ፡፡
 • ለምሳሌ?
 • ለአገር ውስጥና ለውጭ ኮንትራክተሮች በጨረታ ሰጥቶ ቢያስገነባ ይኼ ሁሉ ትርምስ አይፈጠርም ነበር፡፡
 • እንዴት?
 • መንግሥት በጀት መዳቢ፣ ተቆጣጣሪ፣ የግንባታ ማቴሪያል አቅራቢ፣ ወዘተ መሆን አልነበረበትም፡፡
 • ምን ቢሆን ጥሩ ነው?
 • ጠንካራ ፖሊሲ ቢወጣ እኮ የተሻለ ገቢ ያለው ቢፈልግ በሪል ስቴት፣ ካልፈለገ በማኅበር እንዲደራጅ ማድረግ፡፡
 • ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውስ?
 • ኩባንያዎችን ከባንኮች ጋር አቆራኝቶ በሞርጌጅ አሠራር እንዲገነቡ ማድረግ፡፡
 • ስለዚህ?
 • ከ12 ዓመት በኋላ ድንገት ብቅ ብሎ ገንዘብ ማቅረብ አቃተኝ ማለት ያስደነግጣል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ልማታዊ መንግሥታችን ለችግሩ መፍትሔ አያጣም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መደማመጥ ቢኖር እኮ መተራመስ አይኖርም ነበር፡፡
 • መንግሥት አያዳምጥም እያሉ ነው ጎረቤቴ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የተሳሳቱ ይመስለኛል፡፡
 • እኔ ልሳሳት እችላለሁ፡፡ ይኼ ሁሉ ቤት ፈላጊ ሕዝብ ግን የሚሳሳት አይመስለኝም፡፡
 • አሁን ምን ይደረግ ታዲያ?
 • መፍትሔው አንድ ብቻ ነው፡፡
 • ምን ይሆን እሱ?
 • በጥናት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ለመቅረፅ…
 • ምን?
 • ብቃትና ሥነ ምግባር ያላቸውን መሾም፡፡
 • ምን ማለት ይሆን ይኼ ደግሞ?
 • ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› ይባላል፡፡
 • ወይ ጉድ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደደረሱ አማካሪያቸው ተከትሏቸው ገባ]

 • ምንድነው በጠዋት የሚያሯሩጥህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ትናንት አንድ ዘመዴን ልጠይቅ ሄጄ ነበር፡፡
 • የት ነው የሄድከው፡፡
 • ቱሉዲምቱ ኮንዶሚኒየም ሳይት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጣም ትልቅ ሳይት ነው አሉ፡፡
 • በጣም ትልቅ ነው ግን…
 • ግን ምን?
 • በጣም የሚያማምሩ ቤቶች ያሉትን ያህል…
 • እና?
 • ክቡር ሚኒስትር አንዳንዶች ያየሁዋቸው ያሳቅቃሉ፡፡
 • እንዴት?
 • በባለሙያ ያልተገነቡ የሚመስሉ የተጣመሙና የተወለጋገዱ ብሎኮች ይታያሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼን ያህል?
 • ክቡር ሚኒስትር ውስጣቸው ሲገቡ ደግሞ የበለጠ ይደነግጣሉ፡፡
 • እንዴት እባክህ?
 • ጣሪያ፣ ግድግዳና ወለላቸውን ቢያዩ ቤት መሆናቸውን ይጠራጠራሉ፡፡
 • ምን?
 • የፍሳሽ ማስተላለፊያና የኤሌክትሪክ ኬብሎችን አቀባበር ቢያዩ ራስዎን ይዘው ይጮሃሉ፡፡
 • ተቆጣጣሪ የለም ማለት ነው?
 • እሱ አይደል እንዴ የሚያስደነግጠው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሌላ የምትለው አለህ?
 • የጥራት ጉድለት አልበቃ ብሎ መንግሥት ወደፊት ገንዘብ እንደማያቀርብ መሰማቱ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡
 • ይኼን ያህል?
 • ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ እንዲህ ሲባል ያስደነግጣል እኮ?
 • ምናልባት ሌላ የታሰበ ነገር ቢኖርስ?
 • ክቡር ሚኒስትር አማራጭ ሳያቀርብ አቃተኝ ማለት እኮ ብስጭት ይፈጥራል፡፡
 • አንተም እንደ ማንም ሰው ዝም ብለህ ታወራለህ እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር እንዴት ላውራ ታዲያ?
 • እንደ አስፈጻሚ ነው ማውራት ያለብህ፡፡
 • ምን ብዬ ክቡር ሚኒስትር?
 • ልማታዊ መንግሥታችን መፍትሔ አለው እያልክ ነዋ፡፡
 • ይኼ አባባል እኮ መሰላቸት እየፈጠረ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን መሰላቸት?
 • ያወራሉ እንጂ በተግባር አያሳዩም እየተባለ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡

[ክቡር ሚኒስትር በስልክ ከባለቤታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ልጃችን የነገረችሽ ነገር አለ?
 • ምንድነው የምትነግረኝ?
 • ዛሬ ጠዋት የሆነ ነገር ነግራኝ ነበር፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • አልሰማሁም እንዳትይ ብቻ?
 • አንተው ንገረኛ፡፡
 • ላገባ ነው አለችኝ፡፡
 • ምን?
 • ባል ልታገባ ነው፡፡
 • የእኔ ልጅ?
 • ኧረ እባክሽ የሁለታችንም ናት፡፡
 • ማንን ነው የምታገባው?
 • ቦይፍሬንዷን ነዋ፡፡
 • የትኛውን?
 • ስንት ታውቂያለሽ?
 • የዘመኑ ልጆች ዛሬ ካንዱ፣ ነገ ደግሞ…
 • ምን?
 • መቀያየር ይወዳሉ ለማለት ነው፡፡
 • የእኔ ልጅ ግን ጨዋ ናት፡፡
 • እሺ ትሁንልህ፡፡
 • እና ተዘጋጂ፡፡
 • ለምኑ?
 • ለሠርጉ ነዋ፡፡
 • ማንን ነው የምታገባው?
 • ያንን ጨብራራ ፀጉር ያለውን ነው፡፡
 • እሱ ደግሞ ምን አለው?
 • እሷን ጠይቂያት፡፡
 • እኔ ከእሷ ጋር አልዳረቅም ንገረኝ፡፡
 • እንደሷ ደመወዝተኛ ነው፡፡
 • ኧረረረ…
 • ምነው?
 • አይሞከርም፡፡
 • እንዴት?
 • ስንት ሀብታም በሞላበት አገር…
 • ለማን ልትድሪያት አሰብሽ
 • እሱን ለእኔ ተወው፡፡
 • አንቺ የምትችያት አይመስለኝም፡፡
 • ዓይኔ እያየ ከማንም ሞላጫ ደሃ ጋር አትጋባም፡፡
 • እንግዲያው ከቻልሽ ይቅናሽ፡፡
 • ለመሆኑ ቤት አለው?
 • የለውም፡፡
 • መኪና አለው?
 • የለውም፡፡
 • ገንዘብስ?
 • የለውም፡፡
 • ባለ ባዶ ኪስ ባል አይሆናትም፡፡
 • ምን ይሆናል ታዲያ?
 • ጥገኛ በለው፡፡
 • ኧረ ሰው እንዳይሰማሽ?
 • ይኼ ኮንዶሚኒየም የሌለው እንዴት ልጄን ያገባል?
 • እሷ ግን ሁሉንም አብረን እናሟላለን ብላለች፡፡
 • ኧረ አታበሳጨኝ እባክህ?
 • ምን ሆነሻል?
 • እኔ እኮ አንቀባርሬ ያሳደግኳት…
 • እህ?
 • የኮንዶሚኒየም ወረፋ እንድትጠብቅ አይደለም ገባህ?
 • እሷ ግን ሕዝብ እንደሆነው እንሆናለን ብላለች ገባሽ?
 • ይኼንን እዚያ ሄደሽ አውሪ በላት፡፡
 • የት ነው የምታወራው?
 • ድድ ማስጫ፡፡
 • የት ነው እሱ?
 • ሥራ ፈቶች ሠፈር፡፡
 • አንቺ ያምሻል እንዴ?
 • እኔ ጤነኛ ነኝ፡፡
 • ጤነኛ ከሆንሸ ውሳኔዋን ማክበር አለብሽ፡፡
 • ጤነኛ የወፈፌ ውሳኔ የማክበር ግዴታ የለበትም፡፡
 • አንቺ ወይም እሷ ጤነኛ መሆናችሁ እያጠራጠረኝ ነው፡፡
 • ተወው አንተ ራስህ ችግር አለብህ፡፡
 • እኔ ደግሞ ምን አደረግኩ?
 • ወላዋይ ነህ፡፡
 • እኔ ወላዋይ ነኝ?
 • ባለፈው ምን ብለው ነበር የገመገሙህ?
 • እኔን?
 • እኔን ነው ታዲያ?
 • ምን ተብዬ ተገመገምኩ?
 • አቋምህ ይዋዥቃል አልተባልክም?
 • እና?
 • አሁን የእኔ ተራ ነው፡፡
 • ምን ለመሆን?
 • ልጄ ከነጣ ደሃ ጋር አትጋባም፡፡
 • እንቢ ብትልስ?
 • እገዛላታለሁ፡፡
 • ምንድነው የምትገዢው?
 • ሀብታም፡፡
 • ከየት?
 • ዕድሜ ለፎርብስ!
 • ሆሆሆ….