Skip to main content
x
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የውጭ ዲፕሎማት ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተወያዩ ነው]

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የውጭ ዲፕሎማት ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተወያዩ ነው]

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የውጭ ዲፕሎማት ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተወያዩ ነው]

 • ዛሬ ምን እግር ጣለህ እባክህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ችግር ነው ያመጣኝ፡፡
 • የምን ችግር?
 • አገሩን እኮ ዘጋጋችሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ብትፈልግ በቦሌ፣ ብትፈልግ በሞያሌ አገሩ ክፍት አይደል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ምን እያሉ ነው?
 • አገሪቱ አልተዘጋጋችም እያልኩህ ነው፡፡
 • አገሪቱ ከዓለም ጋር ተቆራርጣ እኮ ፍዳችንን አየን፡፡
 • እንዴት ነው የምትቆራረጠው?
 • ኢንተርኔት ዘግታችሁ እኮ ሥራ ፈታን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሱን ነው እንዴ የምትለው?
 • ይኼ እኮ ለእኛ ከባድ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የሚከብደው እባክህ?
 • አንድ ሳምንት ሙሉ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ምን ማለት ነው?
 • 250 ሚሊዮን ብር የወጣበት ፈተና ይቅለጥ እንዴ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር አይቀልዱ?
 • እኔ ቀልድ አላውቅም፡፡
 • ቀልድ ባያውቁማ የአፍሪካ መዲና የሆነች አገር ስትዘጋጋ ዝም አይሉም ነበር፡፡
 • የአፍሪካ መዲና መሆኗንማ ዓለም ያውቀዋል፡፡
 • የአፍሪካ መግቢያ በር ትሆናለች ስንል ጓሮ ልታደርጓት እኮ ነው፡፡
 • እስኪ አንተ በግልህ ምን ተጎዳህ?
 • በዚህ ዲጂታል ዘመን ሥራችን ቆመ እኮ ነው የምለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼን ያህል?
 • እኛ እኮ መረጃዎቻችንን በኢሜይልና በትዊተር ነው የምንለዋወጠው፡፡
 • ምን?
 • ከአገራችን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች የምንገናኘው በፖስታ ቤት እንዳልሆነም ያውቃሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላስ እባክህ ክቡር ዲፕሎማት?
 • የአገራችን ኢንቨስተሮችም በጣም ግራ ተጋብተዋል፡፡
 • የእነሱም ሥራ በኢንተርኔት ነው በለኛ የእኛ ኮሚክ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ ከሔክታርና ከካሬ ሜትር ወጥተን ቋንቋችን ሳይቀር ተለውጧል እኮ?
 • ምን ማለት ይሆን ይኼ ደግሞ?
 • ሜጋ ባይትና ጊጋ ባይት ይባላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኋላቀሮች ናችሁ እያልከን ነው?
 • አልወጣኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ነው፣ መተላለፊያው ደግሞ ኢንተርኔት ነው ማለቴ ነው፡፡
 • እኔ እሱ አልጠፋኝም፡፡
 • ታዲያ ለምን ይሞግቱኛል ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ሳምንት ተቋረጠ ብለህ አቧራ ለምን ታስነሳለህ?
 • አንድ ደቂቃስ ቢሆን እንዴት ይቋረጣል ክቡር ሚኒስትር?
 • ብሔራዊ ፈተናዎቻችንን ከሌቦች እንዴት እንጠብቅ ታዲያ?
 • በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን መፍጠር ነዋ፡፡
 • እንዴት ነው የሚፈጠረው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
 • በጥቅሉ ንገረኛ?
 • ጥቅሉማ ጠንካራ ሲስተም መገንባት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ዓይነት ሲስተም እባክህ?
 • ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሲስተም!

[ክቡር ሚኒስትሩ ዲፕሎማቱን ካሰናበቱ በኋላ ለጉዳይ ከመጣ እንግዳ ጋር እየተነጋገሩ ነው]

 • አንተን ደግሞ ምን ይሆን ያመጣህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሥራ መሥራት አቃተኝ፡፡
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • ድርጅቴ ከ300 በላይ ዜጎችን ቀጥሮ ያሠራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጣም ጥሩ ነው፡፡
 • አሁን ግን መሮኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • ኢንተርኔት ተቋርጦ ሥራችን ሙሉ በሙሉ ቀጥ አለ፡፡
 • አሁን ተከፍቶ የለ እንዴ?
 • ሌላ ጊዜስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ችግሩን የጋራ ማድረግ ነዋ፡፡
 • ኢንተርኔት ድንገት ሳናውቅ እየተቋረጠ እንዴት ችግሩ የጋራ ይሁን ይባላል?
 • የዜግነት ግዴታ ነዋ፡፡
 • እሱ አልጠፋኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የጠፋህ ታዲያ?
 • መጀመሪያ ችግሩ ምን እንደሆነ ስንጠይቅ ጂቡቲ ላይ ኬብል ተቆርጦ ነው ተባለ?
 • እሺ?
 • ከዚያ ደግሞ ብሔራዊ ፈተና እንዳይሰረቅ ነው ተባለ፡፡
 • እሺ?
 • ማን አዘዘ? ማን ቆረጠው? ሲባል እኮ በቅጡ የሚመልስ የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለሁሉም ጥያቄ መልስ እንዴት ይኖራል?
 • ኢንተርኔት ከመቋረጡ በፊት ተዘጋጁ ማለት ማንን ገደለ?
 • አንተ ደግሞ ታበዛዋለህ፡፡
 • ጭራሽ እኔን ይወቅሱኛል ክቡር ሚኒስትር?
 • አይዞህ ታገስ፡፡
 • በየቀኑ እኮ ብዙ ሺሕ ብሮች እየከሰርኩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለአገርህ የምትከፍለው መስዋዕትነት ነው፡፡
 • በደመነፍስ ሲሆን እኮ ለአገር ትልቅ ኪሳራ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሱ አልጠፋኝም እባክህ፡፡
 • ታዲያ ለምን ያስጮሁኛል ክቡር ሚኒስትር?
 • የአንድን ሳምንት ችግርን የዓመት አስመሰልከዋ፡፡
 • ለእኔ እኮ እያንዳንዷ ደቂቃ ገንዘብ ናት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ መመፃደቅ አይመስልህም?
 • ክቡር ሚኒስትር ይልቅ ቢታሰብበት ይሻላል፡፡
 • ምኑ ነው የሚታሰብበት?
 • በአግባቡ መሥራት ሲያቅተን መዝጋት ልማድ እየሆነብን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሺ?
 • ሲስተሙ መሥራት እያቃተው ሥራ ማደናቀፍ ባህሉ ሆኗል፡፡
 • እሺ የእኛ ፈላስፋ?
 • እኔ ይህንን ብያለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለምን ሲስተም ነው የምታወራው?
 • ስለሚሠራና ስለማይሠራ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የእኛ ሲስተም ምን ሆነ ታዲያ?
 • ተቆራረጠ ክቡር ሚኒስትር!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠርተውት እየተነጋገሩ ነው]

 • ኢንተርኔት አንድ ሳምንት ተዘጋ ተብሎ የምን ጫጫታ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ያሳዝናል፡፡
 • ምንድነው የሚያሳዝነው?
 • የውጭ ኢንቨስተሮች እየተበሳጩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆንን አሉ?
 • ፈጽሞ መሥራት አልቻሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማምረትና ኢንተርኔትን ምን አገናኛቸው?
 • በዚህ ዘመን እንዲህ አይባልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • ሁሉም ነገር የተገናኘው ከኢንተርኔት ጋር ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እስቲ በምሳሌ አስረዳኝ?
 • ለምሳሌ ቻይናዎች እዚህ አገር የአራት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አላቸው፡፡
 • እሺ?
 • ከ111 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ቀጥረዋል፡፡
 • ጥሩ፡፡
 • ቻይና ካሉ ወይም ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በየቀኑ ብዙ ጊዜ ይገናኛሉ፡፡
 • ስልክ አለ አይደል?
 • የዳታ ልውውጥ ቢሉ፣ የዶክመንቶች ቅብብል ቢሉ በኢንተርኔት እኮ ነው የሚቀላጠፈው፡፡
 • ሌላስ?
 • ቱርኮች፣ ህንዶች፣ ጣሊያኖች፣ አሜሪካኖች … እዚህ ብዙ ሥራ አላቸው፡፡
 • አየህ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለን?
 • የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚመጣው እኮ ምቹ ሁኔታ ሲኖር ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ምን ጎደለ ታዲያ?
 • የቢሮክራሲው አልበቃ ብሎ አንድ ሳምንት ኢንተርኔት ሲቋረጥ ያሳስባል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንድ ሳምንት እኮ ትንሽ ነው ምን ነካህ?
 • ለኢንቨስተር ደቂቃ ማለት እኮ ወርቅ ነው፡፡
 • አታጋን እባክህ፡፡
 • በዚያ ላይ ደግሞ …
 • ደግሞ ምን?
 • ብዙ ዜጎቻችን እንጀራቸው የተያያዘው ከኢንተርኔት ጋር ነው፡፡
 • ለምሳሌ?
 • ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎች፣ ባንኮች፣ ላኪዎች፣ አስመጪዎች፣ … ብዙ ማለት ይቻላል፡፡
 • እነሱ ደግሞ ምን ሆኑ?
 • እነሱም ሥራ ፈተው ከረሙ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ በምን አወቅክ?
 • ከብዙ ሰዎች ጋር ተወያይቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አቶ አማካሪ ምን ይደረግ ታዲያ?
 • አሁን ኢንተርኔቱ እየተለቀቀ ቢሆንም…
 • ቢሆንም ምን?
 • አንድ ነገር ያስፈልገናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ፈተና ይሰረቃል ብሎ ድርግም ከማድረግ…
 • ምን ይደረግ?
 • ውስጥን መፈተሽና ሥርዓት ማስያዝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የፈተና ሌባ እያለ እንዴት ዝም ይባላል?
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ተረት አስታወሱኝ፡፡
 • ምን ይሆን እሱ?
 • አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ምሽት ላይ ቤት ሲደርሱ ብቸኛ ልጃቸው አኩርፎ ጠበቃቸው]

 • አንተ ደግሞ ምን ሆነሃል?
 • ዳዲ ጉድ ሆንኩኝ፡፡
 • የምን ጉድ?
 • የሚቀጥለው ዓመት የምገባበት ዩኒቨርሲቲ ነዋ…
 • ዩኒቨርሲቲው ምን ሆነ?
 • ዩኒቨርሲቲው ዘጋኝ፡፡
 • ልሳኑ ይዘጋና ለምንድነው የሚዘጋህ፡፡
 • ዳዲ ዴድላይኑ አልፎ ነዋ፡፡
 • የምን ዴድላይን ነው የምትለው?
 • ዳዲ ዶክመንቶቼን የምልክበት ነዋ፡፡
 • በጊዜ አትልክም ነበር አንተ ሰነፍ፡፡
 • ጉድ ያደረገኝ መንግሥት ነው፡፡
 • ምን አልክ አንተ?
 • መንግሥት ጉድ አደረገኝ አልኩህ ዳዲ፡፡
 • አንተንና መንግሥት ምን አገናኛችሁ?
 • አሁንማ ተቆራረጥን፡፡
 • በምን ምክንያት?
 • ዕድሌን አበላሸው፡፡
 • መንግሥት ያንተን ዕድል እንዴት ያበላሻል እባክህ?
 • ዘግቶት ነዋ ያበላሸው ዳዲ፡፡
 • ምኑን ነው የዘጋው?
 • ኢንተርኔቱን!