Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው አርፍደው ከሰዓት በኋላ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት

ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው አርፍደው ከሰዓት በኋላ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው አርፍደው ከሰዓት በኋላ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት አደርክ?
 • እንዴት አደርክ?
 • ምነው?
 • ሰዓቱን ዓይተውታል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ከሰዓት በኋላ ነው ብለህ ነው?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለማንኛውም የጠዋቱ ስብሰባ እንዴት ነበር?
 • ስብሰባው በጥሩ ሁኔታ ሄዷል፡፡
 • ሪፖርቱ የት አለ?
 • እየተዘጋጀ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንደጨረስከው አምጣልኝ፡፡
 • ምን ገጥሞዎት ነው ግን ያረፈዱት ክቡር ሚኒስትር?
 • ትናንት ማታ ግብዣ ነበረብኝ፡፡
 • የልጅዎ ምረቃ ነበር እንዴ?
 • የፈረንጆቹ ምረቃ እኮ እንደ እኛ በክረምት አይደለም፡፡
 • ታዲያ ሎተሪ ወጣልዎት?
 • አንተ እኔ ከመቼ ጀምሮ ነው ሎተሪ የምቆርጠው?
 • ለነገሩ በኮሚሽን የሚያገኙት ራሱ ሎተሪ በሉት፡፡
 • ምን አልክ አንተ?
 • ሰምተዋል፡፡
 • ኧረ ጆሮህን ይድነፈው፡፡
 • ለነገሩ የሁልጊዜ ፀሎትዎ ይኼ ነው አይደል?
 • ማለት?
 • የሚሠሩትን ነገር ሰው እንዳይሰማውና እንዳያየው ነዋ፡፡
 • እስቲ መቀባጠርህን አቁም፡፡
 • ለመሆኑ ምን ገጥሞዎት ነው?
 • የምረዳቸው ልጆች ሊጉን ሊቀላቀሉ ነው፡፡
 • የፓርቲው የወጣቶች ሊግን ነው የሚቀላቀሉት?
 • ምን ይቀባጥራል ይኼ?
 • ምነው?
 • ፕሪሚየር ሊጉን ነው እንጂ የምልህ?
 • ስለ እግር ኳስ ነው እንዴ የሚያወሩት?
 • እህሳ?
 • ለማንኛውም እንኳን ደስ አለዎት፡፡
 • ይኼ ግን በእንኳን ደስ አለዎት ብቻ የሚታለፍ አይደለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሚወራውን ወሬ ግን ሰምተዋል?
 • የምን ወሬ?
 • አንዳንድ ቡድኖች ሊጉን አይመጥኑም እየተባለ ነው፡፡
 • ሳይመጥኑ እንዴት ሊጉን መቀላቀል ቻሉ?
 • ያው በገንዘብ ኃይል ነዋ፡፡
 • የገንዘብ ኃይል ስትል?
 • ፈረንጆቹ ማች ፊክሲንግ የሚሉት ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • በቃ ቡድኖች ከፍተኛ ገንዘብ ይከፈላቸውና ከአቅም በታች እንዲጫወቱ ይደረጋል፡፡
 • ምን የሚሉት ነገር ነው?
 • ይኼ እኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና እንዲያውም በርካታ የጣሊያን ቡድኖች የተዋረዱበት ቅሌት ነው፡፡
 • ስለጣሊያን ታዲያ እኛ ምን አገባን? ጣሊያን እንዲያውም ፋሽስት ነው፡፡
 • ኧረ እንደዚህ አይባልም ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ እንዲያውም የእነሱ ወሬ እንደሆነ እናውቃለን፡፡
 • እኔ እኮ የሰማሁትን ነው እየነገርኩዎት ያለሁት፡፡
 • የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው ስልህ?
 • እና እዚህ አገር ማች ፊክሲንግ የለም እያሉኝ ነው?
 • እና የእርስዎ ቡድን በገንዘብ ኃይል ነው ሊጉን የተቀላቀለው እያልከኝ ነው?
 • እንደሰማሁትማ እርስዎም ገንዘብ አዋጥተዋል አሉ፡፡
 • እኔማ ያዋጣሁት 100 ሺሕ ብር ለትጥቅ የሚውል ነው፡፡
 • ትጥቅ ሲሉኝ ቡድኑ የጦር መሣሪያ አለው እንዴ?
 • ምን ይላል ይኼ? ማሊያ፣ ጫማ ምናምን ማለቴ ነው፡፡
 • በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር ሌላም ወሬ ሰምቻለሁ፡፡
 • የምን ወሬ?
 • አሁን አሁን ኳሱ ከመዝናኛነት ባለፈ የብሔር ፖለቲካ እየነገሠበት መጥቷል እየተባለ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ማለቴ እግር ኳሳችን የፖለቲካ መድረክ እየሆነ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • ለነገሩ ሕዝቡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ስለጠበበበት የእግር ኳስ ሜዳውን የፖለቲካ መድረክ ቢያደርገው አይገርምም፡፡
 • ለማንኛውም ቡድናችን ግስጋሴውን ገና ይቀጥላል፡፡
 • ወዴት?
 • ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ፡፡
 • የትኛውን?
 • የአውሮፓውን!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ተካፍለው ከተሰብሳቢዎቹ ጋር በሻይ ሰዓት እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘት በጣም ያስደስታል፡፡
 • ስብሰባውን የተሳተፍኩት እኮ ፓርቲያችን የደረሰበትን ደረጃ ለእናንተ ለማካፈል ነው፡፡
 • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው ፓርቲያችን እኮ ለአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት የሚዲያ ፎረም ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመርጧል፡፡
 • ሰማን እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ ደግሞ የሚያሳየው የምንከተለው ሲስተም ትክክል መሆኑን ያመለክታል፡፡
 • የምን ሲስተም ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የልማታዊ መንግሥት ነዋ፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • አያችሁ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከልማታዊ መንግሥት ጋር አዋህደን ትልቅ ግንብ ነው የምንገነባው፡፡
 • የምን ግንብ ነው?
 • የባቢሎን ግንብ የሚያስንቅ ነዋ፡፡
 • እኮ ምን የሚያደርግ?
 • ኒዮሊበራሊዝምን የሚመክት ነዋ፡፡
 • የኢሕአዴግ የሚዲያ ስትራቴጂ ግን እኮ ፕሮአክቲቭ አይደለም ይባላል?
 • ፕሮአክቲቭ ስትል?
 • ያው ከሚዲያው ጋር በየጊዜው እየተገናኘ መረጃ አይሰጥማ፡፡
 • አየህ የተሳሳትከው እዚህ ላይ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ የምንከተለው ስትራቴጂ ሌላ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት ነው?
 • እንዲያውም ለስትራቴጂያችን ጥሩ የእንግሊዝኛ ሐረግ አለን፡፡
 • ምን የምትል?
 • ‹‹Silence is the best answer›› የምትል፡፡
 • እ. . .
 • ስትራቴጂያችን ፀጥ ማስባል ነው፡፡
 • ማለት?
 • ሚዲያውንም ሆነ ማንኛውንም አካል ፀጥ ማስባል ነው፡፡
 • በምንድነው ፀጥ የምታስብሉት?
 • ከቻልክ እንደ ፀረ ሽብር ሕጉ ዓይነት አውጥተህ ፀጥ ታሰኛለህ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ካልቻልክ ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝም ታሰኛለህ፡፡
 • ወይ ጉድ፡፡
 • ስለዚህ ጋዜጠኞችን እያስፈራራህና እያሸማቀክ ከአገር እንዲሰደዱ በማድረግ አፍ ማዘጋት ነው፡፡
 • ወይ ግሩም፡፡
 • ከዚያ አገሪቷን በቁጥጥር ሥር ታውላለህ፡፡
 • ይገርማል፡፡
 • ከዚያ የሚወራው ሁሉ ስለልማትና ልማት ብቻ ይሆናል፡፡
 • እና ይኼን ልምድ ነው ለሌሎቹ የምንታካፍሉት?
 • በሚገባ፡፡
 • ለመሆኑ ይኼን ልምድ ከሰሜን ኮሪያ ነው የቀሰማችሁት?
 • የራሳችን ነው እንጂ፡፡ እንዲያውም ከእኛ ሌሎች ኮፒ እያደረጉትም ነው፡፡
 • እነማን?
 • እነ አሜሪካ፡፡
 • ምን?
 • ይኸው ትራምፕ ሚዲያን አላገኝም እያለ አይደለም እንዴ?
 • በጣም ይገርማል፡፡
 • እኛ የሥልጣኔ ምንጭ መሆናችንን አትርሳ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ይኼን እያወሩ ሳለ አንድ ባለሥልጣን ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ሲገቡ ከበዋቸው የነበሩት ተሰብሳቢዎች ትተዋቸው ሄዱ]

 • እንዴ እናንተ?
 • ምነው?
 • ወዴት ነው የምትሄዱት?
 • ሰማንዎት እኮ?
 • አልጨረስኩም እኮ?
 • ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡
 • ማለት?
 • እርስዎ. . .
 • እ. . .
 • አልፎብዎታል!

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸውን በርግዶ ገባ]

 • አንተ ሥርዓት የለህም?
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡
 • የምን ችግር ነው የምታወራው?
 • አገሪቷ ችግር ውስጥ ናት፡፡
 • አንተ ሁሌ ከችግር ውጪ አታወራም እንዴ?
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ ግን ዓይንህ አያይም?
 • ኧረ ያያል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አገሪቷ እኮ እያደገች መሆኗን አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ መስክረዋል፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ይኸው ባቡር በየሠፈሩ ልናስገባ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ኢንዱስትሪ ፓርክ በየሠፈሩ እንደ አበባ እየበቀለ ነው፡፡
 • ስለጃፓን ነው እንዴ የሚያወሩኝ?
 • ስለአገራችን ነው እንጂ፡፡
 • ኧረ ተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑን ነው የምተወው? ከዚህ በላይ አገሪቷን ወርቅ እንድንቀባት ነው እንዴ የምትፈልጉት?
 • ኧረ እኔ እንደ እሱ አልወጣኝም፡፡
 • ወይስ ኢንዱስትሪ ፓርክ በየቤቱ ይገንባ?
 • ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ለማንኛውም እኔ እንደ እሱ አይደለም ያልኩት፡፡ ለምን አያዳምጡም?
 • አንተ ከእሮሮ ውጪ ስለማታወራ አላዳምጥም፡፡
 • ለነገሩ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ እኮ ይኼ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • አለማዳመጥ፡፡
 • ማንን?
 • ሕዝቡን ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ሕዝቡ ያለበት በሽታ ሌላ፣ እናንተ የምትሰጡት መድኃኒት ሌላ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ለካንሰር በሽታ የሳንባ መድኃኒት አይሰጥም፡፡
 • እሺ የእኔ ሐኪም? ለመሆኑ የባህል ሐኪም ነህ ወይስ. . .
 • ቀልዱን ይተውት ክቡር ሚኒስትር?
 • መቼ ነው ሕዝቡ ካንሰር፣ ሳንባ ምናምን የያዘው?
 • ክቡር ሚኒስትሩ አገሪቷ ታማለች፣ በአስቸኳይ መድኃኒት ያሻታል፡፡
 • ምንድን ነው ያመማት?
 • ሕመሟንማ በተደጋጋሚ ሕዝብ ቢናገርም ማዳመጥ አልቻላችሁም፡፡
 • ምንድነው የምትዘባርቀው?
 • ይኸው አገሪቷ ውስጥ ተቃውሞ እንደ አዲስ ተቀስቅሷል፡፡
 • የምን ተቃውሞ ነው?
 • በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡
 • መፍትሔ ሰጥተነው አልነበር እንዴ?
 • ይኼን እኮ ነው የምልዎት፡፡
 • ማለት?
 • ሕዝቡ የሚፈልገው ሌላ እናንተ የምትሰጡት ሌላ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ይኸው በግብር ምክንያት በኦሮሚያ በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞ ተጀምሯል፡፡
 • ግብር አልከፍልም እያሉ ነው?
 • የቀን ገቢ ግምቱ ተቆለለ እያሉ ነው፡፡
 • አየህ አንተ የነጋዴን ባህሪ አታውቀውም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ቀጣፊዎች ናቸው፡፡
 • ሁሉም እንደዚያ እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ?
 • እኔ ባህሪያቸውን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡
 • እንዴ እርስዎም እንደዚያ ነዎት ማለት ነው?
 • ምን
 • አጭበርባሪ!