Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የባንክ ኃላፊ ጋ ደወሉ

ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የባንክ ኃላፊ ጋ ደወሉ

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ በቃ እኔ ካልደወልኩ አትደውልም?
 • ምን ክቡር ሚኒስትር ያው ጊዜው ሒሳብ የምንዘጋበት ወቅት እኮ ነው?
 • እሱማ የጠፋኸው ለምን እንደሆነ ይገባኛል?
 • በጣም ቢዚ ነበርን፡፡
 • ያው ካገኘኸው ቦነስ ጋብዘኝ እንዳልልህ ነው አይደል?
 • ኧረ ሰሞኑን እንዲያውም አመም አድርጎኝ ነበር፡፡
 • ውይ ምነው?
 • ለሕክምና ወደ ውጭ ሄጄ ነበር፡፡
 • ያው ዳጐስ ያለ አበል ይዘህ ነዋ የሄድከው?
 • ኪኪኪ…
 • እንደ እርስዎ መስሎዎት ነው አይደል?
 • ማለት? አበል አልተሰጠኝም ለማለት ነው?
 • ኧረ እኔ ራሴ ባጠራቀምኳት ገንዘብ ነው የምታከመው፡፡
 • እሱን እንኳን ተወው፡፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የውጭ ምንዛሪው በእጅህ አይደል እንዴ ያለው?
 • ቢኖርስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው የቻልከውን ያህል ዘገን አድርገህ ነው የምትሄደው ብዬ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ባንኩ እኮ የግሌ ሳይሆን የሕዝብ ነው፡፡
 • ታዲያ መቼም ውጭ አገር በኢትዮጵያ ብር አትገበያይ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን በራሴ ገንዘብ ነው የምታከመው፡፡
 • እኔ እኮ ጉንፋን ሲያመኝ ለአበሏ ስል ዘልዬ ባንኮክ ነው የምሄደው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ ጋ ግን እንደዚያ የለም፡፡
 • ለማንኛውም ዛሬ ለቁም ነገር ፈልጌህ ነው፡፡
 • ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
 • አዲሱ የበጀት ዓመት ጀመራችሁ አይደል እንዴ?
 • ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አዲሱን ዓመትም እየተቃረበ ነው፡፡
 • እሱማ ትንሽ ይቀረዋል፡፡
 • አይ ያው ዝግጅቱን ከዚሁ ነው የምትጀምሩት ብዬ ነው፡፡
 • የምን ዝግጅት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ የካላንደርና የአጀንዳ ኅትመቱን ነዋ፡፡
 • እሱንማ ጨረታ አውጥተናል፡፡
 • ጨረታ ምን ያደርጋል?
 • እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛው ነና ጉዳዩን መጨረስ ያለብን፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ባለፈው ነግሬህ ነበር እኮ?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • አዲስ ያቋቋምኩት ማተሚያ ቤት አለ ብዬ ነዋ፡፡
 • ተወዳደሩ እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ እኮ በውድድር አላምንም፡፡
 • ታዲያ በምንድነው የሚያምኑት?
 • ልማታዊ አስተሳሰብ አለው ወይ በሚለው ነዋ፡፡
 • ይቅርታ ያድርጉልኝና ክቡር ሚኒስትር፣ እኛ ደግሞ በውድድር ነው የምናምነው፡፡
 • አንተ አይገባህም እንዴ?
 • ጨረታውን ካልተወዳደሩ ምንም ልረዳዎት አልችልም፡፡
 • እኔ እኮ ሁላችንም የምንጠቀምበትን መንገድ አስቤ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አጣብቂኝ ውስጥ እየከተቱኝ ነው፡፡
 • የምን አጣብቂኝ ነው?
 • ያው ባንኩ እኮ በቦርድ ነው የሚመራው፡፡
 • ለሥራው አዲስ ነህ እንዴ? ከሌሎቹስ ጋር እንደዚህ አይደል እንዴ የምሠራው?
 • እኔ የሌሎቹን አላውቅም፡፡
 • አንተ ሐሳብ የሆነብህ ነገር ምንድነው?
 • ሥራዬን እንዳያሳጡኝ ነዋ፡፡
 • ስለእሱ አታስብ፡፡
 • የልጆች አባት እንደሆንኩ ያውቃሉ?
 • ከተባረርክም እኔ አስቀጥርሃለሁ፡፡
 • የት?
 • የእኛው ባንክ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የመንግሥት የልማት ድርጀት ኃላፊ ጋ ይደውላሉ]

 • ሰላም ወዳጄ፡፡
 • እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ዛሬ እንዴት ደወሉልኝ እባክዎ?
 • ለብርቱ ጉዳይ ፈልጌህ ነው፡፡
 • ምነው ያቺን ሪፖርት ፈልገው ነው?
 • የምን ሪፖርት ነው?
 • ባለፈው ቦርድ ስብሰባ ላይ የቀረበውን ነዋ፡፡
 • ስማ እኔና አንተ ከቦርድ ባለፈ ወዳጅነታችንን ማጠንከር አለብን፡፡
 • ካሉማ ደስ ይለኛል፡፡
 • አንተን ሳይህ ንቁ ነገር ስለሆንክ አንድ ፕሮጀክት አስቤልህ ነበር፡፡
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያው ከፊታችን አዲስ ዓመት አለ፡፡
 • ግን ገና ነው እኮ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቢሆንም አንድ ነገር አስቤ ነበር፡፡
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው ድርጅታችሁ ካላንደርና አጀንዳ ማሳተሙ አይቀርም ብዬ ነው፡፡
 • እሱማ በመላው አገሪቷና በውጭ ባሉን ኤምባሲዎቻችን ነው የምናሰራጨው፡፡
 • አየህ እዚህ ላይ ነው ጥሩ ሥራ የምንሠራው፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሥራውን ለእኔ ትሰጠኛለህ?
 • የምን ሥራ ክቡር ሚኒስትር?
 • የካላንደሩንና የአጀንዳውን ሥራ ነዋ፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር አካሄዱን እያወቁት?
 • አካሄዱ ምን ችግር አለው?
 • ማለቴ ስንትና ስንት የግዢ ሒደት አለዋ፡፡
 • ምን በፊት ከነበረው ኃላፊ ጋር እንደዚህ አይደል እንዴ የምንሠራው?
 • ቢሆንም ግን ትንሽ ያሠጋል፡፡
 • እኔው አይደለሁ እንዴ የቦርድ ሰብሳቢ?
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ከሥራዬ እንዳልፈናቀል ብዬ ነዋ፡፡
 • ብትፈናቀልስ?
 • የልጆች አባት መሆኔን ረሱት እንዴ?
 • ከዚህ የምታገኘው ኮሚሽን እኮ አንቀባሮ ነው የሚያኖርህ፡፡
 • ስለዚህ ክቡር ሚኒስትር?
 • ያዋጣሃል፡፡
 • ምኑ?
 • ሙስናው!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዛሬ ከየት ተገኘህ እባክህ?
 • እኔ እኮ ዘመድ ጠያቂ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሱ እንኳን ጉዳይ ሲኖርህ ነው የምትደውለው፡፡
 • በእውነት ዛሬ ሰላም ልልዎት ነው የደወልኩት፡፡
 • ቁም ነገረኛ ወጥቶሃል ማለት ነው?
 • በዚህ እንኳን አልታማም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው ታዲያ?
 • ያውቁት የለ የእኛን ሥራ፣ አንዱ ሲደክም ሌላው ይነሳል፡፡
 • ጥሩ ነው ይልቁንስ እንኳን ደወልክ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እናንተ ካላንደርና አጀንዳ ታሳትማላችሁ አይደል?
 • ኧረ ለእኛ ሥራ እኮ እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ብዙም አይጠቅምም፡፡
 • አየህ ቢዝነስህ የሚደክመው እኮ ለዚህ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ፕሮሞሽን ላይ እየሠራህ አይደለም?
 • ያው የእኛ ሥራ እኮ ኤክስፖርት ማድረግና እዚህ አገር የምናስገባቸውን ዕቃዎች መጋዘን ተከራይቶ መሸጥ ነው፡፡
 • ቢሆንም አየህ የምትሠራውን ሥራ ለመንግሥትም ሆነ ለሌሎች አካላት ማስተዋወቅ አለብህ፡፡
 • ታዲያ ምን እየመከሩኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ካላንደርና አጀንዳ ማሳተም ግዴታ ነው፡፡
 • ችግሩ ደግሞ የማውቀው ማተሚያ ቤትም የለም፡፡
 • ስለእሱ አታስብ፡፡
 • እንዴት?
 • እኔ ያስመጣሁዋቸው የማተሚያ ማሽኖች አሉ፡፡
 • እንደዚያ ከሆነማ ለእኔ ሥራ አቀለሉልኝ፡፡
 • ስለዚህ ሥራውን ትሰጠኛለህ?
 • አዎ ግን ከእርስዎም የምፈልገው ነገር አለ፡፡
 • ምን?
 • 10 ሺሕ ሔክታር መሬት!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ደወሉላቸው]

 • እሺ የእኛ አዋቂዎች፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ታውቃላችሁ?
 • ያው አገሪቷን በልማት ጎዳና እያስጓዝናት ነው፡፡
 • እኔ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?
 • ጠይቂኝ፡፡
 • ከልጅ ልጅ ቢለዩ፣ ዓመትም አይቆዩም ሲባል አልሰማህም?
 • ሰምቻለሁ፡፡
 • እኛ ታዲያ የእንጀራ ልጆች ነን?
 • ማን ናችሁ እናንተ?
 • እኛ ‹‹ሀ››ዎች፡፡
 • ‹‹ሀ››ዎች ስትይ?
 • እኛ ደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች፡፡
 • ራስሽን ከጉሊትና ከጀበና ቡና ሻጭ እኩል ማየት ጀመርሽ?
 • አየህ ግብር እኮ ለሁሉም ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡
 • እሱማ ፍትሐዊ ነው፡፡
 • ታዲያ ለምንድነው አንድ አገር ውስጥ ሁለት ዓይነት አሠራር የሚኖረው?
 • አንቺ ሴትዮ ጤነኛ ነሽ?
 • በጣም ጤነኛ ነኝ፡፡
 • ምን እያልሽ ነው ታዲያ?
 • በጣም ብዙ ሰዎችን እያስከፋችሁ ነው፡፡
 • ማለት?
 • የከተማው ሚሊየነር፣ ቢሊየነር እንዲሁም የከተማው ከፍተኛ ኢንቨስተር ተከፍቷል፡፡
 • እንዴት ነው እናንተ ከጉሊት ቸርቻሪ ጋር አንድ የምትሆኑት?
 • ምን አለበት?
 • ሴትዮ ምን ይደረግ እያልሽ ነው?
 • እኛ እንደ ጉሊት ቸርቻሪዎቹ ያመነውን እንክፈል፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • ሲባል አልሰማሽም እንዴ?
 • ምን?
 • ነጋዴን ያመነ…
 • እ…
 • ጉም የዘገነ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ኢንቨስተር ስልክ ደወሉ]

 • ሄሎ ወዳጄ እንዴት ነህ?
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ዛሬ ከየት ተገኙ?
 • ያው አንተ ስለማትደውል፣ እኔ ልደውል ብዬ ነው፡፡
 • ሥራ ስለሚበዛብኝ እኮ ነው፡፡
 • እስቲ ስለአንዳንድ ነገር እንወያይ ብዬ ነው፡፡
 • ስለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው እናንተ ትልልቅ ባለሀብቶች ስለሆናችሁ ካልረዳችሁን የት እንደርሳለን ብለህ ነው?
 • የቻልነውን እያደረግን ነው እንግዲህ?
 • አሁን ካሳዑዲ የሚመጡ ወገኖቻችንን እዚህ ለማቋቋም አስበናል፡፡
 • ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ግን የእናንተንም ዕርዳታ እንፈልጋለን፡፡
 • እና ከሕዝብ ገንዘብ ሊሰበስቡ ነው?
 • መጀመሪያማ ከባለሀብቱ ነው እንጂ፡፡
 • እኛ ምን በወጣን?
 • ምን እያልክ ነው?
 • በቃ ሁሉም በዚህ መዋጮ በምትሉት ነገር ደስተኛ አይደለም፡፡
 • ለምን?
 • የሚወራውን አይሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ተወራ ደግሞ?
 • ባለፈው ለቆሼ ተብሎ በገንዘብና በዓይነት ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ነው የተሰበሰበው፡፡
 • ጥሩ ነዋ ታዲያ?
 • ግን ተጎጂዎቹ በሚገባ እየተረዱ አለመሆኑን ሚዲያዎች እያናፈሱት ነው፡፡
 • ወሬኞች በላቸው፣ አርፈው ሥራቸውን አይሠሩም?
 • ይኼ አይደል እንዴ ሥራቸው?
 • ማቃጠር?
 • ማቃጠር ሳይሆን በተለያዩ አካላት የሚሠሩ ስህተቶችን ማጋለጥ፡፡
 • እነሱ እባክህ ያልበላቸውን ነው የሚያኩት፡፡
 • እሱ ብቻ አይደለም፡፡
 • ሌላ ምን አለ?
 • ይኸው በዚህ 40/60 እንኳን ስንቱ ሙሉ ክፍያ ከፍሎ ቤት ሲጠባበቅ ጥቂቶች ብቻ ነው ቤት ያገኙት፡፡
 • መንግሥት እንግዲህ የቻለውን እያደረገ ነው፣ ከዚህ በላይ ምን ይደረግ?
 • እኔማ ክቡር ሚኒስትር ለሳዑዲ ተመላሾች ብለው አፍዎን እንዳያበላሹ ብዬ ነው፡፡
 • ማለት?
 • የሚወራውማ መንግሥት በተለያዩ የመዋጮ ጉዳዮች ጨዋታ ጀምሯል እየተባለ ነው፡፡
 • የምን ጨዋታ?
 • እሟ ቀሊጦ!