Skip to main content
x
ክቡር ሚንስተር

ክቡር ሚንስተር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሥራ ወጥተው ቤታቸው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ዛሬ መቼም ያልጠበቅኩትን ነገር ነው የሰማሁት፡፡
 • ምንድነው ያልጠበቅሽው ነገር?
 • አስቸኳይ በተጠራው ፓርላማ የወሰናችሁትን ነዋ?
 • ያለመክሰስ መብት መነሳቱን ነው?
 • በነገራችን ላይ ሰው የበርካታ ሰዎች ያለመከሰስ መብት ይነሳል ብሎ ጠብቆ ነበር፡፡
 • ማለት? አልገባኝም?
 • እንዴ ስኳር የላሱት በርካቶች ናቸው ነው የሚባለው?
 • ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
 • እንዲያውም ሰሞኑን ስኳሩ ከፍ ያላለ ባለሥልጣን የለም አሉ፡፡
 • ወሬውንማ ማን ብሎሽ?
 • የምሬን ነው ሕዝቡ እየጠየቀ ነው፡፡
 • ምን ብሎ?
 • እውነት ስኳር የላሱት እነዚህ ብቻ ናቸው ወይ? ብሎ ነዋ፡፡
 • እንግዲህ እሱን ጥያቄ ስኳሩን የላሱትን ሰዎች ጠይቂያቸው፡፡
 • እየጠየቅኩህ እኮ ነው አንተን?
 • አሃ ልሰሃል እያልሽ ነው?
 • እሱን ልቦናህ ያውቀዋል፡፡
 • ለማንኛውም ያልተጠየቅሽውን አታውሪ፡፡
 • በነገራችን ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ታነሱታላችሁ ብዬም አልጠበቅኩም፡፡
 • እንዴት አልጠበቅሽም?
 • ከታወጀ ዓመት ሳይሞላው ይነሳል ብዬ አልገመትኩም፡፡
 • በመጀመርያ እንዲያውም ለስድስት ወራት ተብሎ ነበር የታወጀው፡፡
 • ማለቴ አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ አዋጁን የሚያስነሳ ስላልመሰለኝ ነው፡፡
 • አገሪቷ ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው?
 • ያው ከቀን ገቢ ግምት ጋር ሰው እየተንጫጫ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ተቃውሞዎች አሉ፡፡ ባለሥልጣናትም እንደ ቆሎ እየተዘገኑ እስር ቤት እየገቡ ነው፡፡
 • እሺ ሌላስ?
 • ይኼ ሁሉ ችግር እያለ አስቸኳይ አዋጁ ይነሳ ማለታችሁ ገርሞኝ ነው፡፡
 • አዋጁን እኮ ያስነሳነው ዋናዎቹን አስቸጋሪዎች ስላስገባናቸው ነው፡፡
 • ለዚያ ነው ያነሳችሁት?
 • ከዚያ ባለፈም አገሪቷ አንፃራዊ ሰላም ላይ ናት፡፡
 • አንፃራዊ ሰላም ማለት?
 • ይኸው ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ይገባሉ፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡም ጫና እያሳደረብን ነው፡፡
 • ምን ብሎ?
 • ቱሪስቶች በአዋጁ ምክንያት እንደ በፊቱ እየገቡ አይደለማ?
 • ለነገሩ መነሳቱ እኔን በጣም አስደስቶኛል፡፡
 • ለምን?
 • ባለፈው ያሰብናትን ነገር እናሳካለና፡፡
 • ምንድን ነበረች እሷ?
 • የቱር ኩባንያ መክፈቱን ነዋ፡፡
 • እ. . .
 • እኔ እኮ ጫፍ ላይ ደርሼ ነው ያቆምኩት፡፡
 • ለምንድነው ያቆምሽው?
 • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ ቱሪዝም እንደሚቀዘቅዝ ገብቶኝ ነዋ፡፡
 • አርቆ አሳቢ ነሽ እኮ ነው፡፡
 • ስማ ከዚህ ዘርፍ እኮ የሚገኘው በዶላር ነው፡፡
 • እሱማ ልክ ነሽ፡፡
 • ስለዚህ የውጭ ምንዛሪም ችግር አይሆንብንም፡፡
 • ምን ላድርግሽ አንቺን?
 • ኢንቨስተር ነዋ፡፡
 • አንቺ እኮ ከሰው ሁሉ  ተለይተሽ. . .
 • የተባረኩ ነኝ?
 • ሙሰኛ ነሽ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ያለመንጃ ፈቃድ ጠጥቶ ሲያሽከረክር ትራፊክ ፖሊስ ይይዘዋል]

 • እንዴ? ለመሆኑ አንተ ዕድሜህ ስንት ነው?
 • ምን አገባህ?
 • ምን አገባህ? ትራፊክ ፖሊስ እኮ ነኝ፡፡ ምን አገባህ ማለት አትችልም፡፡
 • ፖሊስ ብትሆንስ ታዲያ?
 • እስኪ መንጃ ፈቃድህን አምጣ፡፡
 • አላመጣም፡፡
 • ይቺን ይወዳል፡፡ የምን ድንፋታ ነው?
 • ሰውዬ ዞር በልልኝ ልሂድበት፡፡
 • እንዴ ጠጥተሃል ደግሞ?
 • በአንተ ገንዘብ አልጠጣሁ፣ ምን አገባህ ታዲያ?
 • መናገር እስኪያቅትህ እኮ ነው እየተኮላተፍክ ያለኸው?
 • እሱ አንተን አይመለከትህም፡፡
 • ደግሞ የድፍረትህ ድፍረት በዚህ በጠራራ ፀሐይ ነው እንዴ የምትጠጣው?
 • ከፈለግኩ ከእንቅልፌ ስነሳ ከቁርሴ ጋር አብሬ መጠጣት እችላለሁ፡፡
 • ለመሆኑ በጠራራው እንዲህ የሆንከው የቀን  ገቢ ግምት ከፍተኛ ገንዘብ መጥቶብህ ነው?
 • ምን አልከኝ?
 • ለነገሩ አንተ ዕድሜህም ለንግድ ገና አልደረሰም፡፡
 • ሰውዬ ዞር በልልኝ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን ከመኪና ወርደህ ትነፋለህ፡፡
 • እኔ ኦረዲ ነፍቼ ነው የመጣሁት፡፡
 • ምን?
 • ዊድ ነዋ፡፡
 • እንዴ አደንዛዥ ዕፅ ትጠቀማለህ ማለት ነው?
 • ምን ይገርምሃል ታዲያ? እንኳን እኔ አትሌቶቻችንም ይወስዱ የለ እንዴ?
 • በል በል አንተም መኪናውም ትታሰራላችሁ፡፡
 • ኪኪኪ. . .
 • ምን ያስቅሃል?
 • እኔ እስር ቤት?
 • አዎን፡፡
 • በል አንተ ራስህ እንዳትገባ፡፡
 • ማለት?
 • አላወቅከኝም መሰለኝ?
 • ማን ነህ አንተ?
 • የእንትና ልጅ ነኝ፡፡
 • የማን?
 • የክቡር ሚኒስትሩ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ወዲያው ስልክ ይደውልላቸዋል]

 • ሄሎ ዳዲ፡፡
 • እሺ  ጎረምሳው፡፡
 • ይኸው ትራፊክ ይዞ እያሰቃየኝ ነው፡፡
 • ማንን? አንተን?
 • አዎ ዳዲ፡፡
 • እንዴት ቢዳፈረኝ ነው?
 • ስነግረው እኮ አልሰማ ብሎኝ ነው፡፡
 • ማንነቴን ነግረኸው ነው የሚያሰቃይህ?
 • ብነግረው ሊሰማኝ አልቻለም ስልህ?
 • በጣም  ተናንቀናል ማለት ነው?
 • አይገርምህም ዳዲ?
 • እስኪ ስልኩን አቀብለው፡፡

[ትራፊክ ፖሊሱ ማንንም እንደማያናግር ነገረው]

 • ስልኩን አልቀበልም አለኝ ዳዲ፡፡
 • በጣም ተደፋፍረናል ማለት ነው፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ ዳዲ?
 • ይኸውልህ መኪናውን ዳር አቁመውና ቁልፉን ለራሱ ስጠው፡፡
 • ከዚያስ?
 • እኔ ከእሱ እረከበዋለሁ፡፡
 • ቁልፉን ነው?
 • ቁልፉን ብቻ ሳይሆን . . .
 • እ. . .
 • ሥልጣኑንም!

[ክቡር ሚኒስትር ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቢሮ እየሄዱ ነው]

 • ሰሞኑን እየተፈጠረ ያለውን ነገር እየተከታተሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • በጣም ብዙ ነገር አለ፡፡
 • ምን ሰምተህ ነው?
 • ኔማር የሚሉት ተጫዋች በ198 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸጠ ሲባል ሰምቼ ገርሞኝ ነዋ?
 • ምኑ ነው የገረመህ?
 • በዛው ሳምንት የሶማሊያ በጀት 170 ሚሊዮን ፓውንድ መሆኑ በሶሻል ሚዲያ ሲናፈስ ነበር፡፡
 • ምን ይጠበስ ታዲያ?
 • ማለቴ የአንድ ተጫዋች ግዥ ከአንድ አገር በጀት መብለጡ አስገርሞኝ ነው?
 • ለምንድነው የማታውቀውን ነገር የምትዘባርቀው?
 • ለነገሩ ሌላም ያስደነቀኝ ነገር ነበር፡፡
 • ምን?
 • ይኸው በሙስና ተጠርጥረው የገቡት ግለሰቦች ያደረሱት ጉዳት ከአንዳንድ ክልሎች በጀት ይበልጣል አሉ፡፡
 • አንተ የመቼው ፖለቲካ ተንታኝ ነህ?
 • እንዲያው የታዘብኩትን ላውራ ብዬ ነው፡፡
 • ነገርኩህ የአንተ ሥራ እኔን ከቦታ ቦታ ማመላስ ነው፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር እኔም እኮ ዜጋ ነኝ፡፡ ስለዚህ አገሪቷ ውስጥ የሚካሄደው ጉዳይ ይመለከተኛል፡፡
 • እሱን የለመድክበት ቢራ ቤት ማውራት ትችላለህ፡፡
 • ለነገሩ አሁን ከቢራ ቤት ውጪ ስለኢትዮጵያዊነት ማውራት እንደ ስህተት እየተቆጠረ ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ይኸው በሩጫ መድረኩ ላይ ራሱ ይኼን ጉዳይ እያየነው አይደል እንዴ?
 • ምን እያልክ ነው?
 • እንደ አገር ለኢትዮጵያ በቡድን ከመሥራት ይልቅ ግለኝነት እየተንፀባረቀ ነው እኮ?
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ለነገሩ ይኼ ጣጣ የእንትን ጣጣ እንደሆነ እናውቃለን፡፡
 • የምን ጣጣ ነው?
 • የፌዴራሊዝም፡፡
 • እስኪ የፖለቲካ ትንተናህን አቆየው፡፡
 • እሺ አንድ ነገር ግን ልነግርዎት እፈልጋለሁ፡፡
 • ምን?
 • ሰሞኑን የሚጥለው ኃይለኛ ዝናብ የሥራ መደቤን ከመኪና ሾፌርነት ወደ መርከበኛነት እንዳያስቀይረኝ እየሠጋሁ ነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • መንገዶቹ ወደ ሰው ሠራሽ ሐይቅነት እየተለወጡ ነው፡፡
 • ምን?
 • ለማንኛውም መንግሥት የመንገድ ፕሮጀክቶቹን በሌላ ፕሮጀክቶች መቀየራቸውን ያጋለጠ ይመስለኛል፡፡
 • በምን መቀየሩን?
 • በግድብ!

[ሰሞኑን በሙስና ተጠርጥረው በታሰሩ ባለሥልጣናት ምክንያት የፈራ የመንገድ ኮንትራክተር ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደወለ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እዚህ አገር አለህ እንዴ?
 • ከአገሬ የት እሄዳለሁ ብለው ነው?
 • ሰሞኑን ሰዎች ስልኩ አይሠራም ብለው ጠይቀውኝ ስለነበር ነው፡፡
 • እሱማ ብዙ እየወተራብኝ ነው፡፡
 • ምንድነው የተወራብህ?
 • ሰሞኑን እስር ቤት መግባትህ አይቀርም እያሉኝ ነው፡፡
 • ለዚያ ነው ስልክህን ያጠፋኸው?
 • ያው ቤተሰብም ስለተደናገጠ ከግርግሩ ልራቅ ብዬ ነው፡፡
 • ታዲያ እኔ ጋ እንዴት ደወልክ?
 • የሚወራው ወሬ ሊያስተኛኝ ስላልቻለ ነው፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ? አንተ ስኳሯን ልሰህ ነበር እንዴ?
 • እሱማ ሐኪም ስኳር አትውሰድ ብሎኝ ነበር፡፡
 • ለምን ወሰድክ ታዲያ?
 • ያው ተገድጄ ነዋ፡፡
 • ተገድጄ ስትል?
 • ያው ለአንዳንድ ኃላፊ ስጦታ ነገር ሰጥቼ አውቃለሁ፡፡
 • ተወዳድረህ እንድትሠራ እንጂ ጊፍት ሰጥተህ እንድታሸንፍ ማን ፈቀደልህ?
 • ያው ተወዳድረን ካለፍን በኋላ ገንዘብ ለማስለቀቅ ስጦታ መልቀቅ ስላለብን ነው፡፡
 • ምን ልርዳህ ታዲያ?
 • እንዲያማልዱኝ ፈልጌ ነዋ፡፡
 • ምንድነው የማማልድህ?
 • እስር ቤት እንዳልጣል ነዋ፡፡
 • እንዳማልድህ ከፈለክ ለእኔ መመማለጃ አስገባልኝ፡፡
 • ምንድነው መማለጃው?
 • ቪ8!