Skip to main content
x
የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር የቴዲ አፍሮ ዘፈን እየሰማ ክቡር ሚኒስትሩ መኪና ውስጥ ገቡ

የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር የቴዲ አፍሮ ዘፈን እየሰማ ክቡር ሚኒስትሩ መኪና ውስጥ ገቡ

[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር የቴዲ አፍሮ ዘፈን እየሰማ ክቡር ሚኒስትሩ መኪና ውስጥ ገቡ]

 • አንተ ፀረ ሰላም ሆነሃል መሰለኝ?
 • ምን አጠፈሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • ዝም ብዬ ሳስብ ፀረ ልማትም ትመስለኛለህ፡፡
 • በጠዋቱ ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ በጠዋቱ ምን ሆንክ ልበል እንጂ?
 • ኧረ እኔ ምንም አልሆንኩም፡፡
 • ምን እየሰማህ ነው?
 • ‹ኢትዮጵያ› የሚለውን የቴዲ አፍሮ ሲዲ ነዋ፡፡
 • እሱን ዘፈን መኪናዬ ውስጥ ማን ክፈት አለህ?
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር መኪናው የእርስዎ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡
 • ምን አልክ አንተ?
 • ማለቴ መኪናው መሥሪያ ቤቱ የመደበለዎት የመንግሥት ንብረት መስሎኝ?
 • አንተን ማን ንብረት ተቆጣጣሪ አደረገህ?
 • ኧረ ምን ቆርጦኝ?
 • ታዲያ ምን ያስቀባጥርሃል?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን ኢሕአዴግን ሳስበው አንዳንድ ጊዜ ግርም ይለኛል፡፡
 • ምኑ ነው የሚገርምህ?
 • ያው በቃ ራሱ እግር ላይ መተኮስ ያበዛል፡፡
 • እሺ የእኔ ፈላስፋ?
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፣ አንዳንዴ የኢሕአዴግ ጠላት ራሱ ኢሕአዴግ ይመስለኛል፡፡
 • ዛሬማ የፖለቲካ ተንታኝም ለመሆን ይዳዳሃል?
 • የፖለቲካ ተንታኝ ለመሆን ፈልጌ ሳይሆን ዊኬንድ ላይ የተፈጸመው ነገር አስገርሞኝ ነው፡፡
 • ዊኬንድ ላይ ምን ተፈጸመ?
 • የቴዲ አፍሮ የአልበም ምረቃ መሰረዘ አስገርሞኝ ነዋ፡፡
 • ምኑ ነው የሚገርመው?
 • እንዴ መንግሥት እንደዚህ ወርዶ ከዘፋኙ ጋር እስጥ አገባ ሲገባ አይገርምም?
 • ለመሆኑ አንተ ስምህ ከእሱ ጋር ሞክሼ ስለሆነ ነው እንደዚህ የምትከራከርለት?
 • አንዳንዴ የመንግሥት አካሄድ ግራ ስለሚያጋባ ነው፡፡
 • ምኑ ነው ግራ የሚያጋባው?
 • አንዳንዶቹ ቴዲን የፍቅር ሰባኪ ነው ይሉታል፡፡
 • አንተም የፍቅር ሰባኪ ነው ብለህ ታምናለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር በልጁ ፍቅር ያልተነደፈ ማን አለ?
 • እኔ፡፡
 • እንግዲህ ሊሆን ይችላል፣ ግን መንግሥት የፍቅር ቀን አከብራለሁ እያለ እንዲህ ዓይነት ከፍቅር የጎደለ ድርጊት ሲያደርግ ትንሽ ግር ይላል፡፡
 • በነገራችን ላይ እኛም ሕዝቡን እንዴት በፍቅር ልንነድፈው እንችላለን?
 • ኪኪኪ. . .
 • ምን ታገጣለህ?
 • መስተፋቅር አሠሩዋ፡፡
 • ቀልደህ ሞተሃል፡፡
 • የምሬን ነው እሱን ብትሞክሩት ይሻላችኋል፡፡
 • ወሬኛ ቢጤ ነህ፡፡
 • ለማንኛውም አንድ የናጠጠች ሀብታም አክስት አለችኝ፡፡
 • እና ምን ይጠበስልህ?
 • ጠዋት ደውላ እርስዎን እንዳማክርዎት ነግራኝ ነበር፡፡
 • ምንድነው የምታማክረኝ?
 • በሚቀጥለው ሳምንት ድል ያለ ድግስ ትደግሳለች፡፡
 • ታዲያ እኔን የድግስ አማካሪ ነው ያላት ማነው?
 • ያው እርስዎ ብዙ ድግስ ስለሚደግሱ ቢያማክሯት ምን ችግር አለው?
 • አንተ ግን እንዴት ነው የናቅከኝ?
 • ለማንኛውም ስለድግሱ እንዲያማክሯት ሳይሆን የልጇ ምርቃት እንዳይበላሽባት ስለፈራች እርስዎ እንዲያሰጧት ነው፡፡
 • ምንድነው የማሰጣት?
 • የምርቃት ፈቃድ!

[አንድ ደላላ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • ምን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ግድብ፣ መንገድ፣ ባቡር. . . ኧረ ስንቱ?
 • አሁን ጋዜጣ አንብቤ ነው የምደውልልዎት፡፡
 • እነሱ ከወሬ ውጪ ምን ያውቃሉ ብለህ ነው? ደግሞ ምን አሉ?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን እርስዎ ምን አጠፉ?
 • ምን አጠፋ ብለው ጻፉ ደግሞ?
 • ማለቴ የሚኒስትር ሚስት በቪ8 ብትሄድ ምን አለበት?
 • ሲያንሳት ነው፡፡
 • የሚኒስትር ልጆች ፓጃሮ ቢነዱ ምኑ ነው ችግሩ?
 • እንዳንተ የሚያስብ እኮ ነው ያጣነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በእውነት በእጅጉ ነው ያዘንኩት፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ ይኸው መመርያ ወጣብን፡፡
 • በጣም ደግሞ ያስገረመኝ ከተማው ውስጥ በቪ8 ምናምን መንቀሳቀስ አትችሉም የተባለው ነው?
 • እንግዲህ ሁሌ ከከተማ እየወጣን እንድንገናኝ ሊያስገድዱን ነው?
 • ለማንኛውም አንድ ሐሳብ ይዤ ነው የደወልኩት፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • መመርያው ላይ ከዚህ በኋላ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአገር ውስጥ መኪና ብቻ እንዲገዙ መባሉን አንብቤያለሁ፡፡
 • ልክ ነው ወዳጄ፡፡
 • ታዲያ ለምን አናቋቁምም?
 • ምን?
 • መኪና መገጣጠሚያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በደላላው በኩል የመኪና መገጣሚያ ለማቋቋም ፍላጎት ያለውን ባለሀብት በአንድ ትልቅ ሆቴል አገኙት]

 • ክቡር ሚኒስትር ስለተገናኘን በጣም ተደስቻለሁ፡፡
 • እኔም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካውን ለማቋቋም አንዳንድ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡
 • ምን ዓይነት ነገሮች?
 • ለምሳሌ ሰፊ የሆነ መሬት ያስፈልገናል፡፡
 • ስለእሱ ምንም አታስብ፡፡
 • ከዚያ ባለፈ ፋብሪካውን የምናቋቁምበት ብድር ከባንኮች ማግኘት አለብን፡፡
 • እሱንም በአጭር ጊዜ ማግኘት እንችላለን፡፡
 • ከዚያ ውጪ ያለውን ነገር ለእኔ ተውት፡፡
 • በአጭር ጊዜ ፋብሪካውን ዕውን ማድረግ እንችላለን ማለት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ በኩል ያሉትን ነገሮች ካመቻቹ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንገባለን፡፡
 • ሌላ ምን ያስፈልጋል?
 • ፋብሪካው እንደ ተቋቋመ የመንግሥት መኪኖች ከእኛ ብቻ እንዲገዙ ማድረግ ነው፡፡
 • ቢያንስ የእኔ መሥሪያ ቤት መኪኖች ሙሉ ለሙሉ ከዚያ ፋብሪካ እንዲገዙ አደርጋለሁ፡፡
 • እንደዛ ከሆነ በአጭር ጊዜ እንከብራለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በከፍታ ዘመኑ ከፍ ማለት ነው እንግዲህ፡፡
 • ከፍ ለማለት ምን ይፈልጋሉ?
 • ፎቅ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ለምሳ ሄደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ነገ የተሳልኩትን ዣንጥላ ማስገባት አለብኝ፡፡
 • የምን ስለት ነው?
 • እሱ የከፈተውን ጉሮሮ እሱ ይሞላዋል ብዬ ተደፍቼ ነበር የፀለይኩት፡፡
 • የምን ፀሎት ነው የምታወሪው?
 • እንዴ መንግሥት መኪናዬን ሲቀማኝ ወጪ ቆጥቡ ምናምን ብሎ ሁሉን ነገር ሲያስቀረው የምገባበት ጠፍቶኝ ነበር፡፡
 • አሁን ምን ተገኘ ታዲያ?
 • ይኸው የከፍታ ዘመን ታወጀ አይደል እንዴ?
 • ለከፍታ ዘመን እኮ ከመንግሥት ካዝና ምንም አይነካም፡፡
 • ከግሉስ ቢሆን ዋናው የእኛ አካውንት ከፍ ማለቱ ነው፡፡
 • ምን አስበሽ ነው?
 • ስማ የፍቅር ቀን ተብሎ ሲከበር ብዙ ገንዘብ ማግኘት እንችላለን፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • መቼም ፍቅር ሁሌም ቢሆን ከአበባ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነሽ፡፡
 • ስለዚህ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች በፍቅር ቀን አበባ የሚገዙት ከእኔ ይሆናል፡፡
 • አይ አንቺ ምን ላድርግሽ?
 • ከፍቅር ጋር አያይዘን ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እናሸበርቃቸዋለን፡፡
 • ለዲኮር ቤትሽ ሥራ ተገኘለት ማለት ነው?
 • ለቫለንተይንስ ዴይ የሠራነውን ገንዘብ ረሳኸው እንዴ?
 • እሱ ቀን የኒዮሊበራሎች ስለሆነ አልወደውም፣ ለዛም ነው መንግሥት በራሱ የፍቅር ቀን ብሎ የሰየመው፡፡
 • የሰላም ቀን ሲከበር ደግሞ ነጭ ባንዲራ እንቸበችባለን፡፡
 • በነገራችን ላይ ይህ ሥራ ፈጣሪ ጭንቅላትንሽን በጣም ነው የማደንቀው፡፡
 • ምን እሱ ብቻ?
 • ሌላ ምን አለአለ?
 • ሰው ለሰላም ቀን ነጭ መልበስ ስላበት ሁሉም ሠራተኛ የአገር ልብስ እንዲገዛኝ ታስደርገዋለህ፡፡
 • ይኼ ደግሞ የአገር ባህል ልብስ ቤትሽን ገበያ ያደራዋል፡፡
 • እሱን ነው የምልህ፡፡
 • በእውነት ኮራሁብሽ፡፡
 • አሁን ገበያችን ሁሌ እንዲደራ አንድ ነገር ማድረግ አለብህ፡፡
 • ምን?
 • እነዚህ የፍቅርና የሰላም ቀናት በዓመት አንዴ ብቻ መከበር የለባቸውም፡፡
 • ታዲያ ስንቴ ይከበሩ?
 • ሁልቀን!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • የከፍታ ዘመን እንዴት ማምጣት እንችላለን?
 • ሙስናን በማጥፋት፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ድህነትን በመቀነስ፣ ዴሞክራሲን በማስፈን፣ ልማትን በማፋጠን፣ እንዲሁም በሌሎች፡፡
 • አንተ ፀረ ልማት ነህ መሰለኝ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • መንግሥት የከፍታ ዘመናችንን የምናውጀው የተለያዩ ቀናትን በማክበር ነው ብሏል፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ አሁን የምልህን ብቻ አድርግ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • የፍቅር ቀንን በደመቀ ሁኔታ እናከብረዋለን፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • አበባና ሻማ ይገዛል፡፡
 • እሺ?
 • ከዚያም መሥሪያ ቤታችን በቀይ አበባና በሻማ ያሸበርቃል፡፡
 • እ. . .
 • ሠራተኛው ምሳውን ሲበላ ራቱን የበላ እስኪመስለው ድረስ መሥሪያ ቤቱ በሻማና በአበባ ይዋብ፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ሠራተኛው እርስ በርሱ በጥልቅ ፍቅር እንዲወድቅ ማድረግ አለብን፡፡
 • እ. . .
 • እንዲያውም ወይን ራሱ ከፍቅር ጋር ስለሚሄድ እንገዛለን፡፡
 • ከየት?
 • እነዚህ ያልኩህን ሁላ የሚያቀርብልን ድርጅት አግኝቻለሁ፡፡
 • ያለጨረታ ነው የምንገዛው?
 • ያዘዝኩህን ብቻ ፈጽም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ካወጣቸው ቀናት በተጨማሪ የሚከበር ቀን አለ እንዴ?
 • የምን ቀን?
 • የሙስና ቀን!