Skip to main content
x
ክቡር ሚንስተር

ክቡር ሚንስተር

[የክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ አማካሪያቸው ገባ]

 • ፈለግከኝ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • በአስቸኳይ ማድረግ አለብን፡፡
 • ምንድነው የምናደርገው?
 • የሠራተኞች ስብሰባ፡፡
 • እየቀለድክ ነው?
 • ኧረ የምሬን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ እኔ በስብሰባ የማባክነው ጊዜ የለኝም፡፡
 • ይኼ እኮ የሚባክን ጊዜ አይደለም፡፡
 • ከስብሰባ ምን ይገኛል?
 • ክቡር ሚኒስትር ሠራተኛው እኮ ብዙ ብሶት አለው፡፡
 • የምን ብሶት?
 • ሠራተኞች እኮ አጠቃላይ ስብሰባ ይደረግ እያሉ ከጠየቁ ቆዩ፡፡
 • አርፈው ሥራቸውን ለምን አይሠሩም?
 • ክቡር ሚኒስትር በርካታ ብሶቶች ውስጣቸው ስላለ መወያየት ይፈልጋሉ፡፡
 • የምን ብሶት ነው?
 • የመልካም አስተዳደር ብሶት፡፡
 • እና ምን እያልክ ነው?
 • ስብሰባ ማድረግ ግዴታችን ነው፡፡
 • እንግዲያው ከስብሰባው በፊት መወያየት ያለብን ጉዳዮች አሉ፡፡
 • ምን ዓይነት ጉዳዮች?
 • የቅድመ ስብሰባ ውይይት ነዋ፡፡
 • እኮ ምንድን ናቸው?
 • በመጀመሪያ ስብሰባው ላይ ማን ነው የሚገኘው የሚለው ላይ መወያየት አለብን፡፡
 • ሁሉም ሠራተኛ ነዋ የሚገኘው፡፡
 • ይህን እኮ ነው የምልህ፡፡
 • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ከአነስተኛና ጥቃቅን ሠራተኞች ጋር ተሰብስቤ እንድነጋገር ትፈልጋለህ?
 • ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ከዋና ዋና ኃላፊዎች ጋር ነው መሰብሰብ የምፈልገው፡፡
 • ግን ክቡር ሚኒስትር በርካታ ብሶት ያለው እኮ ታችኛው ሠራተኛ ውስጥ ነው፡፡
 • ነገርኩህ እኮ እኔ ከእነሱ ጋር መሰብሰብ አልችልም፡፡
 • እሺ ሌላስ?
 • ሌላው ቃለ ጉባዔውን ማን ነው የሚይዘው ላይ መስማማት አለብን፡፡
 • ያው ከመሀከላችን አንዱ ይይዘዋል፡፡
 • አልስማማም ስልህ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ገለልተኛ የሆነ ወገን ነው ቃለ ጉባዔውን መያዝ ያለበት፡፡
 • ምን?
 • አየህ፣ ቃለ ጉባዔው ላይ ያልተናገርነው ነገር ሊገባ ስለሚችል ገለልተኛ ወገን ነው መያዝ ያለበት፡፡
 • ገለልተኛ ወገን ማን ነው ታዲያ?
 • ከውጭ መቅጠር ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ቃለ ጉባዔ የሚይዝ አካል ይቀጠር፡፡
 • እንዴት ነው የሚቀጠረው?
 • በጨረታ ነዋ፡፡
 • እ…
 • አየህ፣ አሠራራችን ግልጽ መሆን አለበት፡፡
 • ምን ዓይነት ጨረታ ነው የሚወጣው?
 • ከዚያ በፊት የሚቀድም ነገር አለ፡፡
 • ምን?
 • የጨረታ ዶክመንቱን የሚያዘጋጅ ኮሚቴ፡፡
 • በቃ መቼም አይካሄድም በሉኛ?
 • ምኑ?
 • ስብሰባው፡፡
 • ነገርኩህ እኮ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፡፡
 • ስለዚህ እኔ ከእርስዎ ጋር ላድርጋ፡፡
 • ምን?
 • ስብሰባ፡፡
 • የምን ስብሰባ?
 • የተናጠል!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ደወሉላቸው]

 • መቼም አንብበኸዋል?
 • ምኑን?
 • ጋዜጣ አላነበብክም?
 • እኔ ለወሬ ጊዜ የለኝም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እነሱ ከወሬ ውጪ ምን ያውቃሉ?
 • ኧረ ከሚኒስትር ይኼ አይጠበቅም፡፡
 • ነገርኩሽ እኮ እኔ የማነበው ልማታዊ የሆኑ ጋዜጦችን ነው፡፡
 • ስማ ለማንኛውም ጉድ ሆነናል፡፡
 • የምን ጉድ ነው?
 • ቆሟል እያሉ ነው፡፡
 • ምን ብላክ ማርኬት ነው?
 • ኧረ አይደለም፡፡
 • ታዲያ እኛ ያወጣነው ጨረታ ነው?
 • የለም፡፡ የለም፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የቆመው?
 • ኤክስፖርት፡፡
 • የምን ኤክስፖርት?
 • የቦሎቄ፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ይኸው ፓኪስታን የኢትዮጵያ ቦሎቄ አገሬ እንዳይገባ ብላለች፡፡
 • እኔ ጠፋሁ፡፡
 • ምርቱ ሊበላሽብኝ ነው፡፡
 • ይኼ የፀረ ልማቶች ወሬ ነው፡፡
 • እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡
 • አየሽ ፓኪስታንም ፀረ ልማቶች አሉ ማለት ነው፡፡
 • ይኼን ዲስኩርህን እዛው፡፡
 • ተይው እኔ ችግሩ ገብቶኛል፡፡
 • ምንድን ነው?
 • ፓኪስታን ውስጥም መሽገዋል ማለት ነው፡፡
 • እነማን?
 • ኪራይ ሰብሳቢዎች!

[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እየተደረገ ነው?
 • ምን ተደረገ?
 • አገር ሲጎዳ እንዴት ዝም ይባላል?
 • ማን ነው አገር የጎዳው?
 • የውጪ ንግዳችን አሽቆልቁሏል እየተባለ አይደል እንዴ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢዎችን መታገል አለብን፡፡
 • ስለምንድን ነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • ፓኪስታን ይኸው ቦሎቄያችን እንዳይገባ ከለከለች አይደል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር በግልጽ የቦሎቄ ንግድ ውስጥ እንዳሉ መናገር ጀመሩ ማለት ነው?
 • እኔ እኮ መንግሥትን ለማገዝ ነው ሴክተሩ ውስጥ የገባሁት፡፡
 • በምንድን ነው የሚያግዙት?
 • የውጭ ንግዳችንን ለማጎልበት ነዋ፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም አሁን በአስቸኳይ ወደ ፓኪስታን መላክ አለበት፡፡
 • ምንድነው የሚላከው?
 • የልዑካን ቡድን!

[የክቡር ሚኒስትሩ የወንድም ልጅ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • ኧረ ከባድ ችግር ውስጥ ነኝ፡፡
 • ሰባት ሻንጣ ሞባይል ገብቶልሃል አይደል እንዴ?
 • እሱማ ገብቷል ጋሼ፡፡
 • ባለፈው ከግማሽ በላይ የሆኑትን ሸጫለሁ ብለኸኛል አይደል እንዴ?
 • አዎን ጋሼ፡፡
 • ታዲያ የምን ከባድ ችግር ነው?
 • ታክሱ ጋሼ፡፡
 • ሞባይሎቹ ያለታክስ እንዲገቡ እኮ ነው ያስደረኩልህ?
 • እሱ ነው ችግር የፈጠረው፡፡
 • የምን ችግር ነው?
 • ይኸው ጣቢያ ነው ያለሁት፡፡
 • ለምን?
 • ለምርመራ ተፈልጌ፡፡
 • አንድ ስልክ ልደውል፡፡
 • እሺ ጋሼ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ መርማሪው ጋ ደወሉ]

 • ሄሎ! ማን ልበል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝቡ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲራራቅ ነው እንዴ ሐሳባችሁ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝቡ ዘመናዊ እንዲሆን ብሎ የወንድሜ ልጅ ሰባት ሻንጣ ሞባይል አስገባ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው እናንተ ለምርመራ ትፈለጋለህ ብላችሁ አስራችሁታል፡፡
 • ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሞባይል ማስገባቱ ምኑ ነው ጥፋቱ?
 • ታክስ አልከፈለም፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን ይክፈል?
 • ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • በሌሊት በረሃ ለበረሃ ተጓጉዞ አይደል እንዴ ያስገባው?
 • ስለዚህ ለእኔ ታክስ ይክፈለኛ?
 • ምን?
 • አንድ ሻንጣ ሞባይል!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ደወለላቸው]

 • ሰሙ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • ትራምፕ ያለውን ነዋ፡፡
 • ምን አለ?
 • ጦራችን ሶማሊያ ይገባል እያለ ነው፡፡
 • ታዲያ እኔ ምን አገባኝ?
 • ያገባዎታል እንጂ፡፡
 • እንዴት?
 • ይኼ እኮ የሚገርም የቢዝነስ ኦፖርቹኒቲ ነው፡፡
 • የምን የቢዝነስ ኦፖርቹኒቲ?
 • የአሜሪካ ጦር ሶማሊያ ከገባ እኛ ማቅረብ እንችላለን፡፡
 • ምን?
 • ምግብ ነዋ፡፡
 • ለማን?
 • ለአሜሪካ ጦር፡፡
 • አንተ እውነትም ጂኒየስ ነህ፡፡
 • ደላላ የሆንኩት እኮ ለዛ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን እናድርግ?
 • በአስቸኳይ ላይሰንስ ማውጣት አለብን፡፡
 • የምን ላይሰንስ?
 • የኤክስፖርት፡፡
 • ምን ኤክስፖርት ለማድረግ?
 • በርገር!