Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ የኮክቴል ግብዣ ላይ አንድ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት እያነጋራቸው ነው

ክቡር ሚኒስትሩ የኮክቴል ግብዣ ላይ አንድ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት እያነጋራቸው ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ የኮክቴል ግብዣ ላይ አንድ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት እያነጋራቸው ነው]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንደምን አለህ ሚስተር ዲፕሎማት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አዲሱ ሹመት ተስማማዎት?
 • አገሬን ለማገልገል ሁሌም ዝግጁ ስለሆንኩ ችግር የለም፡፡
 • አገር ሲሉ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡
 • ምን ይሆን?
 • ለመሆኑ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዴት ነው?
 • እንደምታየው ነዋ፡፡
 • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዚሁ መቀጠሉ ነው?
 • በእሱ እኮ ነው ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረው፡፡
 • በአዋጁ ብቻ መቀጠል አለባችሁ እንዴ?
 • እንግዲህ ሁኔታው ይወስነዋል፡፡
 • ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር አኳያስ?
 • መጀመሪያ እሳት ይጠፋል፣ ከዚያ ለቀሪው ይታሰባል፡፡
 • በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር. . .
 • አቤት?
 • የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን እንዴት አገኙት?
 • አንተን ልጠይቅህ እንጂ?
 • እኔማ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ቢቀርብ ተመራጭ ነበር እላለሁ፡፡
 • ኮሚሽኑም እኮ በነፃነት ነው የሠራው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከመንግሥት በጀት እየተመደበለት እንዴት ነፃ ይሆናል?
 • የእናተን አናውቅም እንዴ?
 • ምኑን?
 • ሪፖርት የሚያቀርቡ እነ ምናምን ዎች ማን ነው ጃስ የሚላቸው?
 • ቢያንስ እኛ ሲስተም ዘርግተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሲስተማቲክ ብትለው ይሻላል እባክህ፡፡
 • ምን ለማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የዘረጋችሁት ሲስተም መሰሪና ሴረኛ መሆኑን ስለማውቅ ነዋ፡፡
 • ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለብን እኮ?
 • አትቀልድ እባክህ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እናንተ እኮ የምትናገሩትና የምትሠሩት የተለያየ ነው፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ዴሞክራሲ ትላላችሁ፣ ከለየላቸው አምባገነኖች ጋር ዋንጫ ታነሳላችሁ፡፡
 • እንዴ?
 • እኛን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በዴሞክራሲ ዕጦት እየከሰሳችሁ የለየላቸውን ታሞካሻላችሁ፡፡
 • ለምሳሌ?
 • ስም አልጠራም ታውቃለህ ክቡር ዲፕሎማት፡፡
 • ኢትዮጵያ እኮ በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች የምዕራባውያን ስትራቴጂካዊ አጋር ናት፡፡
 • ይኼማ ግልጽ ነው፡፡
 • በሰላም ማስከበርም ትልቅ ተሳትፎ አላት፡፡
 • ዓለም ያውቀዋል፡፡
 • በአገር ውስጥ ግን ተቃዋሚዎችን አትታገሱም፡፡
 • ልዩነታችን እኮ እዚህ ላይ ነው፡፡
 • ችግሩን ማሻሻል ለምን ያቅታል ክቡር ሚኒስትር?
 • የዕይታ ችግር አለባችሁ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ማየትና መስማት የምትወዱት ኔጌቲቭ ነገሮችን ነው፡፡
 • ኧረ ፖዘቲቭ ነገሮችን እናያለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ለምን ትነዘንዘኛለህ?
 • የሚያሳዝኑ ነገሮች ስለሚበዙ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዕይታህን አስተካክል፡፡
 • በምን ላስተካክል?
 • አሪፍ መነጽር ያስፈልግሃል ክቡር ዲፕሎማት፡፡
 • ምን ዓይነት መነጽር?
 • ካስፈለገህ ሜድ ኢን ቻይና!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮአቸው ውስጥ ከአማካሪያቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

 • የዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ያሳስባል፡፡
 • ምኑ ነው የሚያሳስበው?
 • ይኼው አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ተፋጠዋል፡፡
 • ምን እንሁን ነው የሚሉት?
 • አሜሪካ ሶሪያን በክሩዝ ሚሳይል ከደበደበች በኋላ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁለቱን ምን አፋጠጣቸው ታዲያ?
 • ክሩዝ ሚሳይሎቹን የተኮሱት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲያመሩ በመደረጉ ነው፡፡
 • ማን ነው ይኼንን የሚያደርገው?
 • ፕሬዚዳንቱ ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ትራምፕ?
 • አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እነዚህ ሰዎች በእሳት እንደሚጫወቱ አይገባቸውም?
 • ይኼ የተለመደ የመንግሥታት ችግር ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አይሰሙም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው የማይሰሙት?
 • ሲመከሩ ነዋ፡፡
 • ምንድነው የሚመከሩት?
 • አሁን እኔ የእርስዎ አማካሪ ነኝ፡፡
 • እሺ እባክህ?
 • ብዙ ነገሮችን ሳማክርዎት መቼ ይሰሙኛል?
 • ለምሳሌ?
 • ሲወስኑ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ይመሥረቱ ስል አይሰሙኝም፡፡
 • ሌላስ?
 • ፍሌክሰብል ይሁኑ ስል አይሰሙኝም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ግትርነት ያበዛሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ግትር ለምን እንደምሆን ታውቃለህ?
 • አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምክሮችህ ልፍስፍስ ስለሆኑ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • መለሳለስ ትወዳለህ፡፡
 • የሚጠቅም ከሆነ መለሳለስ እኮ ጥሩ ነው፡፡
 • እኔ ደግሞ ኮስተር ያለ ውሳኔ ያስደስተኛል፡፡
 • ሕዝብ እኮ ኮስተር ሲባልበት አይወድም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምግቡ በርበሬ መጠጡ አረቄ በሆነበት አገር ውስጥ?
 • ኧረ የማይገናኝ ነገር አይናገሩ ክቡር ሚኒስትር?
 • ችግርህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ትፈራለህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሕዝብ እኮ እንዲህ ዓይነቱን ዘራፍ አይወድም፡፡
 • አንተ አልክ፡፡
 • እስቲ ወጣ ብለው ሕዝብን ያዳምጡ?
 • አንተ ችግር አለብህ ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የእኔ ኃላፊነት እኮ እየዞሩ ወሬ መቃረም አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሠርቶ ማሠራት ነው ይግባህ፡፡
 • ግልጽ አልሆነልኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ሥራህን መቀየር አለብህ፡፡
 • ምን ለመሆን?
 • በደብዳቤ ይገለጽልሃል፡፡
 • የት ሊመድቡኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • መዝገብ ቤት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለቅሶ ለመድረስ ሄደው ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር ወሬ ይዘዋል]

 • ከፓርቲዎች ድርድር ዘላችሁ ወጣችሁ አይደል?
 • እናንተም የምትፈልጉት ይህንን ነው፡፡
 • እኛ ደግሞ ምን አደረግን?
 • ኢሕአዴግ መደራደር ያለበት እኮ ከታዋቂ ተቃዋሚ ጋር ነው፡፡
 • ማን ነው ደግሞ ደረጃ የሚያወጣው?
 • እኛ ባለን ተደማጭነት፣ በደጋፊ ብዛትና በሪከርዳችን የተሻልን ነን፡፡
 • ‹የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ› እንዳትባሉ ብቻ፡፡
 • እናንተ ደግሞ ከአነስተኛና ጥቃቅን ጋር መቀጠል ትችላላችሁ የተከበሩ ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እኮ የማይገባኝ . . .
 • ምንድነው የተከበሩ?
 • እናንተ ዕድሜ ልካችሁን እንዳጭበረበራችሁ ልትኖሩ ነው?
 • በማጭበርበርማ አንታማም፡፡
 • ማን ይታማላችሁ ታዲያ?
 • መቼም የምርጫ ኮሮጆ ስንገለብጥ አንታወቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እናንተ?
 • አዎ እኛ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እናንተ እኮ. . .
 • እኛ ምን?
 • ምን ይተርፋችኋል?
 • እስቲ ይናገሩ?
 • በዳያስፖራ የመዋጮ ገንዘብ ትባሉ የለ?
 • ይህቺ የጅምላ ፍረጃ ትባላለች የተከበሩ፡፡
 • አንዴ ግንባር፣ ውህደት፣ ጥምረት. . . እያላችሁ የምትባሉት በምንድነው ታዲያ?
 • ይህቺ ይህቺማ የማን ሥራ እንደሆነች ይታወቃል፡፡
 • እንዴት እባክህ?
 • እያሰረጋችሁ እያስገባችሁብን ስትጫወቱብን እንደነበር እናውቃለን እኮ?
 • አኼኼ. . .
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በመዋጮ  ገንዘብ ተባልታችሁ ስታበቁ ሰበብ አታጡም፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን?
 • እኛ እናንተን አናምንም፡፡
 • ስለዚህ?
 • ውይይትም ይባል ድርድር በጅምላ ሳይሆን በተናጠል ይሁንና እንገናኝ፡፡
 • ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ነው?
 • ለሕዝብ ስትሉ ብታደርጉት ይመረጣል፡፡
 • በቁምህ ትቃዣለህ መሰል?
 • እንዴት የተከበሩ?
 • ሕዝብማ ፋይዳ እንደሌላችሁ ያውቃል፡፡
 • ይህ አካሄድ ያዋጣል የተከበሩ?
 • እናንተማ እንወያይ ስንላችሁ የተሸነፍን መስሏችሁ ነበር፡፡
 • ሕዝብ ሰንጎ ሲይዛችሁ አይደለም አንዴ እንወያይ፣ አንዴ እንደራደር ስትሉ የነበረው?
 • ተሳስተሃል፡፡
 • እኔ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ነኝ ታዲያ?
 • ምንድነው ስህተቴ?
 • ፖለቲካው አልገባህም፡፡
 • እንዴት ሆኖ ክቡርነትዎ?
 • የፓርቲ ፖለቲካ ጌም አልገባህም፡፡
 • ጌም?
 • አዎን ጌም፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ካንዲ ክራሽ ልበልህ?

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው የዕለቱን ፕሮግራማቸውን እንድትነግራቸው ጠርተዋት እየተነጋገሩ ነው]

 • እስኪ የዕለቱን ውሎዬን ንገሪኝ፡፡
 • ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ከአማካሪዎት ጋር ቀጠሮ ተይዟል፡፡
 • ሰርዢው፡፡
 • አምስት ሰዓት ሲሆን ከጀርመን የመጣ ዳያስፖራ ቀጠሮ ይዟል፡፡
 • ምንድነው የሚፈልገው?
 • በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ወቅታዊ ጉዳይ ከፈለገ ቴሌቪዥን ተመልከት በይው፡፡
 • ለምን አያናግሩትም ክቡር ሚኒስትር?
 • ወቅታዊ ጉዳይ የሚነገረው በሚዲያ እንጂ በእኔ አይደለም፡፡
 • ስድስት ሰዓት ሲሆን ጉዳይ አለኝ ያሉ ኢንቨስተር ይመጣሉ፡፡
 • ምድነው የሚፈልጉት?
 • ቅሬታ ለማቅረብ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው ቅሬታቸው?
 • የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልኩም ነው የሚሉት፡፡
 • እኔ ምን ላድርግላቸው ታዲያ?
 • የት ይሂዱ ክብር ሚኒስትር?
 • ወደ ላይ ሄደው ቅሬታቸውን ያቅርቡ፡፡
 • የተባለውን አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን  ተባለ?
 • ቅሬታዎች በየደረጃው መፈታት አለባቸው፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው ያሉት፡፡
 • መቼ ነው ያሉት?
 • ሰሞኑን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላስ ምን አሉ?
 • እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ ቅሬታ ሰሚ አይደለሁም ብለዋል፡፡
 • ወይ ጉድ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አይ ወዲህ ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁንስ የመረረኝ ነገር. . .
 • ምን መረረዎት?
 • እኔም ቅሬታ መስማት ሰልችቶኛል፡፡
 • ምን ይደረግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቅሬታ የሚያስተናግድ ሚኒስቴር መቋቋም አለበት፡፡
 • በቃ ካቢኔ ስብሰባ ላይ ያንሱት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቀልጂ አንቺ፡፡
 • ቀልድ ብችል ኖሮ. . .
 • ለነገሩ እንኳንም አልቻልሽ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • አጉል እቀልዳለሁ ስትይ ካገኘሽው ጋር ስትላተሚ ነበር የምትውይው፡፡
 • መቀለድ ካልቻልኩ ምን ብሆን ይሻለኛል ክቡር ሚኒስትር?
 • ወሬ አመላላሽ!
 • እኔ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ነኝ ታዲያ!