Skip to main content
x

ኮንዶሚኒየም እስከመቼ ለአመራር እየታደለ ይዘለቃል?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተማውን ገጽታ በመለወጥና በርካታ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ሲያከናውን የቆየው ተግባር ያስመሰግነዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር የልማት እንቅስቃሴውን የሚያከናውነው ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ ሳያገኝ ከራሱ የውስጥ ገቢ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ አስተዳደሩ ለልማት የሚያውለውን የመንግሥት በጀት መሥሪያ ቤቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው የከተማው የበላይ አመራር የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡

ከዚህ አንፃር የአሁኑ የከተማው አስተዳደር የተሻለ ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ቅንጡና ውድ ዋጋ የሚወጣባቸው ተሽከርካሪ ግዢ እንዲቆም፣ ለሥራ የሚያስፈልጉ የአገር ውስጥ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲዘጉ፣ መሥሪያ ቤቶች ለግምግማ በሚል ሰበብ ከከተማ እየወጡ በውድ ሆቴሎች የሚያካሂዷቸው ስብሰባዎችም እንዲቀሩ የወሰደው  ዕርምጃ ጥሩ ቢሆንም፣ አሁንም የግለሰብ ሕንፃዎችን የሚከራዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለቢሮ ኪራይ የሚያወጡት ወጪ እየተባባሰ መሄዱን ግን ሊያስብበት ይገባል፡፡

ይህ የከተማ አስተዳዳሩ የወጪ ቅነሳ ጉዳይ ቀጥሎ ለሚነሳው ርዕስ መንደርደሪያ ስለሆነ ነው፡፡ የመንግሥት በጀት አብዛኛው ለልማት ከመዋል ይልቅ በየዓመቱ ውድ የቢሮ ዕቃ ለሚያቀያይሩ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ብክነት መዋል የለበትም የሚል አቋም አለኝ፡፡

በከተማችን እየተከናወነ ከሚገኘው የልማት ሥራ አንዱ የቤቶች ግንባታ ሲሆን፣ ብዙዎችም በተስፋ የሚጠብቁት ነው፡፡ ግንባታውን እያከናወኑ ካሉት ሁለት የመንግሥት ተቋማት አንዱ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በአዋጅ ቁጥር 15/96 ከተቋቋመ ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት ቤት ይደርሰናል በማለት ተመዝግበው ሲጠባበቁ ከነበሩት ውስጥ በግምት ከ25 በመቶ የማይበልጡት በዕጣ ቤት ቢደርሳቸውም፣ በ2005 ዓ.ም. እንደ አዲስ የተመዘገቡትን ጨምሮ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ቤት ፈላጊዎች ለዓመታት በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የከተማው አስተዳደር ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግነው ሲሆን፣ የተገነቡትን ቤቶች እንዴት እንደሚያስተላልፍ በአዋጅ ቁጥር 19/97 እና በአዋጅ ቁጥር 7/2001 ድንጋጌ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፍትሕ ቢሮ በቅርቡ ያሳተመው የከተማው ደንቦች ጥራዝ፣ ለአመራር በኪራይ ስለሚሰጥ የኮንዶሚኒየም ቤት የሚደነግገው ደንብ ቁጥር 38/2001 እንዲወጣ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራራ፣ ለከተማው አስተዳደር ሥራ አስፈላጊና ብቁ የሆኑ ሠራተኞች፣ ለክልል መሥሪያ ቤቶች፣ ለፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወይም ከአስተዳደሩ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በቋሚነት በሹመት ወደ ከተማው አስተዳዳር ሊመደቡ የሚችሉበት ሁኔታ በመኖሩ፣ በከተማው አስተዳዳር የተሾሙት ባለሥልጣናት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይችሉ ዘንድ ቢያንስ የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን መቅረፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ይላል፡፡ በከተማው አስተዳደር ነዋሪ ሆነው በተለያዩ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ አደጋዎች ሳቢያ ከመኖሪያ ቤታቸው የሚፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በልዩ ሁኔታ ከዕጣ ውጪ የመኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣ በመንግሥት ቤት ነዋሪ ሆነው በልዩ ሁኔታ በልማት ምክንያት መኖሪያ ቤታቸውን የሚያጡ ሰዎች ከከተማው አስተዳዳር መኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው ሕጉ አስፍሯል፡፡

 ሆኖም ይህንን የሕግ አግባብ በመጠቀም ቤት የወሰዱ የከተማው ኃላፊዎች፣ በአመራርነታቸው ወቅት የወሰዱትን የኮንዶሚኒየም ቤት ከአመራርነታቸው ሲነሱ ግን ማንም አላስመለሳቸውም፡፡

በአሁኑ ወቅት ኃላፊነታቸውን የለቀቁ በርካታ የቀድሞ ኃላፊዎች፣ ቤት እያላቸውም በቤት ላይ ተጨማሪ ቤት ቢሰጣቸውንም ሳያስረክቡ በመሄዳቸው ዕጣ ይወጣልኛል ብሎ በተሰፋ እየተጠባበቀ ከሚገኘው ነዋሪ ዕድል እየተቀነሰ አዲስ ለሚሾሙ ኃላፊዎች ቤት ማደሉ ቀጥሏል፡፡ የከተማው አስተዳደር ባወጣው በዚህ ደንብ መሠረት ተሿሚው ከሹመቱ ሲነሳ የኪራይ ውሉ ተቋርጦ፣ ቤቱን የከተማው አስተዳደር ይረከባል ይላል፡፡

ይሁን እንጂ የተሰጣቸውን የኮንዶሚኒየም ቤት ሳያስረክቡ፣ የግላቸውን ቤት እያከራዩ እንዲኖሩ የተፈቀደላቸው የቀድሞ ኃላፊዎች፣ የተበረከተላቸውን ስጦታ ይዘው እንዲቀጥሉ መደረጉ የከተማ አስተዳዳሩ ራሱ ያወጣውን ደንብ ካለመተግሩም ባሻገር ለሕጉ ተገዢ እንዳልሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ ይህ ድርጊት በዚሁ ከቀጠለ ከሚገነባው የኮንዶሚኒየም ቤት ይደርሰኛል በማለት በተስፋ የሚጠብቀው ዜጋ ተስፋ እንዲቆርጥ የሚገፋፋ ድርጊት ነው፡፡

አስተዳደሩ ከባለዕድለኞች እየቀነሰ ቤት ላለውም ቤት ለሌለውም በኃላፊነት ለተቀመጠ ሁሉ ሲያድል የነበረው የኮንዶሚኒየም ቤት በጣም በዝቅተኛ ዋጋ የመሆኑስ ነገር እስከመቼ ይቀጥላል? የከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው ለሚሾማቸው ኃላፊዎች ቤት ማደል የግድ ካስፈለገው፣ በአስተዳደሩ ባለቤትነት ሥር የሚውሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ገዝቶ በኃላፊነት በሚቆዩበት ጊዜ እንዲጠቀሙበት፣ ከኃላፊነት ሲነሱ ደግሞ ለተተኪ አስረክበው እንዲወጡ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በኃላፊነት የተሾመ ከኃላፊነቱ ሲነሳ ቤቱን ማስረከብ የለበትም ከሚል ከግል ፍላጎት የተነሳ በልማድ ሲኬድበት የቆየውን አካሄድ፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ኃላፊዎችም ነግ በእኔ ከሚል መነሻ ላይቀበሉት ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ አግባብ ምርጥ ሊባል የሚችል ተሞክሮ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት የውክልና ዘመናቸውን ሲጨርሱ፣ የተሰጣቸውን የመንግሥት ቤት ለሌላው አዲስ የምክር ቤት አባል እንዲያስረክቡ ይደረጋል፡፡

የከተማው አስተዳዳር ለተሿሚዎች የሚያከራያቸው ቤቶች በጣም በዝቅተኛ ዋጋ ማከራየቱ ጭምር አግባብነት የለውም፡፡ ለቤት ኪራይ ተብሎ ከደመወዛቸው ጋር ከሚከፈላቸው የቤት አበል በታች በጣም በወረደ ዋጋ ባለሦስት መኝታ ቤት በ400 ብር ብቻ ማከራየቱ ለምን ያሰኛል፡፡ ቤት በኪራይ ለተሰጠው አመራር ከቤቱ ዋጋ ከሦስት ዕጥፍ በላይ በደመወዙ ላይ እየተጨመረለት ባለበት አካሄድ የቤት አበል መከፈል አይጠበቅበትም፡፡ የለበትም፡፡

የመንግሥት በጀት አላግባብ መባከን ስለሌበት፣ ለዚህም አስተዳደሩ መፍትሔ እንዲፈልግለትና ልክ እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱን ሕንፃ አሠርቶ አመራሮቹን በአንድ የተወሰነ አካባቢ ቢያከራያቸው፣ የከተማው አስተዳደር ካለበት መረጃ በአግባቡ የመያዝ ችግር ሊያላቅቀውና በዕጣ ከሚቀርቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የተመዝጋቢዎች ዕድል እያጣበበና እየቆነጠረ ለአመራር ከማደል ሊያወጣው ስለሚችል እንዲህ ያለውን አሠራር ሊከተል ይገባል እንላለን፡፡

(ሚካኤል ምሥግና አፅብሃ፣ ከሳር ቤት)