Skip to main content
x

ውኃ የበላው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት

በተመስገን ቢራቱ

ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መሠረታዊ እሳቤዎች መካካል አንዱ፣ በአገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ዋስትና መስጠት ነበር፡፡ በዚህ መነሻም ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል፡፡ በዴሞክራሲው መስክ የመጣ ለውጥ መኖሩ ባይካድም፣ ግን በርካታ እንቅፋቶችና የአስተሳሳብ ዝንፈቶች እንዳሉም ግልጽ ሆኖ የሚታይበት ወቅት ላይም እንገኛለን፡፡

ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የአንድ ገዥ ፓርቲ እየተጠናከረ መሄድና በተደጋጋሚ በምርጫ መመረጥ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላም በአገሪቱ ጭላንጭል ተስፋ የሚጣልበት ተገዳዳሪ ፓርቲ በመጥፋቱ ነው፡፡ በሌላ በኩል አሁንም ድረስ ‹ፖለቲካና ኮረንቲ› በሩቁ ብሎ ነገር ዓለሙን ሁሉ በታሪክ አጋጣሚ ኃላፊነት ላይ ለወጡ ሰዎች የተወ ዜጋ ቁጥሩ ከፍ እያለ በመሄዱ ነው፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን መሆን መሠረት ናቸው የሚባሉት የዴሞክራሲ ተቋማትም፣ በነፃና በገለልተኝነት ብቻ ሳይሆን በአቅም ጭምር ክፉኛ በመታማታቸውም ነው፡፡ አሁንም ድረስ የፖለቲካ ልዩነት በጠላትነት የሚያፈራርጅ ‹ቆሻሻ› የሥራ መስክ እየመሰለ  በመሄዱም  ነው፡፡

በመሠረቱ ኢሕአዴግ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ አተኩሮ 25 ዓመታት አይደለም፣ ሌላ ይኼንኑ ያህል ጊዜ በሥልጣን ላይ ቢቀጥል ሒደቱ ከመደበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ጋር አይጋጭም፡፡ በሌሎች አገሮችም  አንድ ፓርቲ በአውራነት በተደጋጋሚ እየተመረጠ የፓርላማውን አብዛኛው ወይም በሙሉ መቀመጫ ይዞ መንግሥትን የሚመራበትን አሠራር የሚያሳዩ በርካታ ተጠቃሽ ምሳሌዎች አሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ኤኤንሲ) እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተደጋጋሚ እየተመረጠ አገሪቱን የሚመራ አውራ ፓርቲ ነው፡፡ ይኼም በጥቁር ደጋፊዎቹ ድምፅ ያገኘው ነው፡፡ ሰሜናዊ አየርላንድ እ.ኤ.አ. ከ1921 እስከ 1972 ድረስ (ለ51 ዓመታት) የተመራችው በአልስተር ዩኒየኒስት ፓርቲ አውራነት ነው፡፡ ይኼም ፓርቲው የፕሮቴስታንት ተከታይ የሆነውን የአብዛኛውን ሕዝብ ድምፅ በማግኘቱ ነው፡፡ በጃፓንና በሌሎች አገሮችም ተጠቃሽ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን በብሔራዊ ደረጃ አንድ አውራ ፓርቲ የሚመራ ቢሆንም፣ በንዑስ አገራዊ ክፍሎች ወይም ክልሎች ወይም የምርጫ አካባቢዎች ሌላ ፓርቲ በተደጋጋሚ እያሸነፈ የክልሉ አውራ ፓርቲ የሚሆንበት አሠራር አለ፡፡ ለምሳሌ ኤኤንሲ በብሔራዊ ደረጃ አውራ ፓርቲ በሆነበት አገር፣ የተቃዋሚው ዴሞክራቲክ አላየንስ ፓርቲ በምዕራባዊው ኬፕ (ዌስተርን ኬፕ) ግዛት (ክልል) በተደጋጋሚ በምርጫ እያሸነፈ አውራ ፓርቲ የሆነበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ ማለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በብሔራዊ ደረጃ አቅማቸው ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በአንድ የተለየ አካባቢ ሰፊ ደጋፊ የሚያገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡ ጠንክረው በሠሩበት አካባቢ አውራ ፓርቲ ሆነው የሚቀጥሉበት ሥርዓት አለ ማለት ነው፡፡

ከሰሞኑ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አዳማ ላይ የሲቪክ ማኅበራት መሪዎችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ አሰናድቶ ነበር፡፡ ይኼ ነሐሴ 13 እና 14 2009 ዓ.ም. የተካሄደ ስብሰባ አሁንም ጥንካሬን አጎልብቶ፣ ድክመትን ቀርፎ ሁሉን አቀፍ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን አጠናክሮ ለመቀጠል ያለመ ሳይሆን፣ ለወደፊትም የገዥውን ፓርቲ  አሸናፊነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የቋመጠ አካሄድ የሚመስል ነው፡፡ አሁንም የምርጫ ቦርድ ሰዎች የሚነሱት በአገሪቱ 66 የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉት በምኅዳሩ መስፋት ምክንያት ነው የሚለው እንቆቅልሽ ላይ ነው፡፡ አሁንም አገራችን በመራጮች ቁጥር ከዓለም ሁለተኛ ነች (እዚህ ላይ በገጠር የምርጫ ካርድ ያልያዘ ዜጋ የሚደርስበት ጫና እንኳን ለአንድ ጊዜ ለሁልጊዜም ካርዱን ይዞ ቁጭ ልበል የሚለው ሕዝብ በሚሊዮን የሚቆጠር ነው) በሚለው ‹ዶሮን ሲያታልሏት...› ጨዋታ ላይ ነው፡፡ አሁንም ሕገ መንግሥቱን፣ የተሻሻለውን የምርጫ ሕግ 532./1999፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ 573/2000 እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር ሕግ 662/2002 እየጠቀሰ ምን ይወጣላቸዋል የሚል ‹የወረቀት ነብሮችን› ማስፈራሪያ ማድረግ ላይ ነው፡፡

እውነት ለመናገር ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በዚህ አገር የመድበለ ፓርቲና ጠንካራ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጎለብት ቢያስብ በሰል ያለ ምክክር መጀመር የነበረበት፣ ከገለልተኛ ምሁራንና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መሆን ነበረበት፡፡ በአሁኑ ውይይት ግን በቅርቡ በአምባሳደርነት የተሾሙት የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር መርጋ በቃናን ጨምሮ በርካታ የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ኮታ ለመሙላት የተሳተፉበት ሲሆን፣ የሙያና የሲቪክ ማኅበራቱ መሪዎችም እጅግም በአባሎቻቸው በሙሉ ዕምነት ተወክለዋል፣ በአገሪቱ ጉዳይ ላይም በኃላፊነት ስሜት ሊመክሩ የሚችሉ ናቸው ለማለት አዳጋች ነው፡፡ ይልቁንም ቢያንስ የ2010 ዓ.ም. የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ ደርሷል ለማለት ያህል የ2007 ዓ.ም. ምርጫ አፈጻጸም ግምገማ ብሎ መድረክ መፍጠር፣ የአገሪቱን የመድበለ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ ውኃ እንደበላለው አመላካች ነው፡፡

በመሠረቱ መድበለ ፓርቲ የሚባለው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉበትና ሁሉም በአገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩበት፣ ሁሉም የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ እኩል ዕድል የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡ ያሉት ፓርቲዎች ራሳቸውን ችለው ወይም ግንባር ፈጥረው መንግሥት ለመመሥረት የሚችሉበት ሥርዓትንም ይመለከታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ግንባር ፈጥሮ ማሸነፍና ሥልጣንን መጠቅለል፣ ለዚህ የሚያበቃ ድምፅ ለማግኘት ካልተቻለ ደግሞ ጥምር መንግሥት መመሥረት የሚቻልበት አሠራር ያለበት ነው፡፡ ይኼንን እውነት መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ራሱ ምርጫ ቦርድ በግልጽ ቢያውቁትም፣ በየራሳቸው ችግር ሆን ብለው እየጣሉትና እያዳከሙት ይገኛሉ፡፡ ይኼ በመሆኑም በመንደርተኝነትና በስግብግብ ሥልጣን ፈላጊነት የተወለካካፈ ወፈ ሰማይ ፖለቲከኛ እንጂ፣ ለመድበለ ፓርቲው አስተዋፅኦ የሚያደርግ የተደራጀ ኃይል ከቶም ማየት አልተቻለም፡፡ የተሞከሩ ተግባራት ቢኖሩም ወንዝ ለመሻገር አልቻሉም፡፡

በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቶች ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዋንኛ (ከፍተኛ) እና አነስተኛ አቅም ያላቸው ፓርቲዎች ሥልጣን የመያዝ ዕድል ስላላቸው፣ ለዚህም በብርቱ ስለሚፎካከሩ ብዙውን ጊዜ የፓርላማ አብዛኛውን መቀመጫ ማግኘት አይችሉም፡፡  ስለሆነም  የግዴታ ጥምረት ይፈጥራሉ፡፡ በዚህም ሕዝባዊ ተቀባይነትን በመገንባት ወደ ሥልጣን የመምጣት ዕድላቸውን  ያሳፋሉ፡፡ እንግዲህ የዚህ ዓይነቱ ጅምር ጭላንጭል እንከን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እየታየ ነው ወይ ስንል ነው እውነተኛው ጭንቀት የሚይዘን፡፡ በዚህ ዳተኛ ተግባር ኢሕአዴግና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ተገዳዳሪ ፓርቲዎችስ፣ ለዚህ ዓይነቱ የሠለጠነ አስተሳሳብ ዝግጁ ናቸው ብሎ መመርመርም ተገቢ ይሆናል፡፡

ልክፍቱ አሁንም ያለቀቀን ለመሆኑም ሕዝብ እየጮኸና እየጠየቀ፣ አልፎ ተርፎ በአመፅ ምድሩን እያናወጠ አሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥው ፓርቲን ጨምሮ) በድርድር ስም የጀመሩት ዕቃ ዕቃ ጨዋታ የሚመስል ጊዜ ማጥፊያ እውነታውን  የሚያጋልጥ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድም ሰሞኑን ሲያስረዳ፣ ‹‹እኔ ገለልተኛ ስለሆንኩ  ሜዳውን ከማማቻቸት አልፌ እነ እገሌ ተጣመሩ፣ ተዋህዱ ለማለት አልችልም…›› ብሏል፡፡ ታዲያ ሕዝቡ አሁንስ ስለምርጫ ምን ዓይነት ተስፋ ይዞ ይጓዝ ይሆን ብሉ መጠየቅ አርቆ አሳቢነት ይመስለኛል፡፡

በመሠረቱ በአንድ ዓለም አቀፍ እውነት መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚባለው ይበልጥ አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ መድረክ የሚበዛው ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ይልቅ በፓርላሜንታዊ ሥርዓቶች ውስጥ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓታቸው ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በውጤታማነት የተጠቀሙ በርካታ አገሮችም  አሉ፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ፣ ታይዋን፣ ፊሊፒንስ፣ ስፔን፣ ብራዚል፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ አየርላንድ፣ እስራኤል፣ ጣሊያን፣ ሜክሲኮ፣ ኖርዌይ፣ ፓኪስታን፣ ዴንማርክ፣ … ብዙ ናቸው፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች መካከል አንዱ ብቻ ተነጥሎ የፓርላማ አብላጫ ድምፅ የሚያገኝበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ያሉት የፖለቲካ መድበለ ፓርቲዎች አቅም ለማበጀት ጥምረት ይፈጥራሉ፡፡  በእኛ  አገርስ  ያለመታደል ጉዳይ ሆኖ የጥምረት መንግሥት መመሥረት ባንችል እንኳን የተለያዩ አመለካካቶች የሚደመጡበት ፓርላማ እንዴት እንጣ? እስከ መቼስ መውተርተር ይቻላል?

በአንዳንድ አገሮች መድበለ ፓርቲ ሥርዓቶች ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ፓርቲዎች ጥምረት ፈጥረውም ሆነ ሳይፈጥሩ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ሰፊ ዕድል የሚያገኙበት ዕድል አለ፡፡ ሁለት ፓርቲዎች ብቻ የሚያሸንፉበት ከሆነ ባለ ሁለት ፓርቲ ሥርዓት ይሆናል፡፡ ይኼም ምርጫውን የሚያሸንፉት ወይም ‹‹ያሸንፋሉ›› ተብለው የሚጠበቁት ሁለት ፓርቲዎች ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ከ2010 ዓ.ም. በፊት በእንግሊዝ የነበረውን ዓይነት ማለት ነው፡፡ ካናዳም ተመሳሳይ ነው፡፡ በእንግሊዝ በምርጫ የማሸነፍ ዕድል ያላቸው ኮንሰርቫቲቭና ሌበር ናቸው፡፡ ሌላኛው ትልቅ የሚባለው ፓርቲ የሊበራል ዴሞክራቶች ቢሆንም፣ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል በቂ መቀመጫ አግኝቶ አያውቅም፡፡

ያም ሆኖ ግን ከባለ አንድ ወይም ከባለ ሁለት ፓርቲ ሥርዓቶች ይልቅ የተሻለው የብዙኃን መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ነው፡፡ በአንድ ወይም በሁለት ፓርቲ ሳይወሰን በርካታ የተደራጀ አመለካከትና አቋም ያላቸውን ፓርቲዎች የሚያቅፍ በመሆኑ የተሻለ ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲ የመራጩን ሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ይፎካከራል፡፡ አንድ ነጠላ ፓርቲ የፓርላማውን ሥልጣን ያለተቀናቃኝ እንዳይዝ ለማድረግ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጥሩ ነው ሚባለውም ከዚሁ በመነሳት ነው፡፡

የእኛ ሁኔታ ግን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ አንደኛ አብዛኛው የአገሪቱ  ፓርቲዎች ብሔር ተኮር በመሆናቸው አገር አቀፍ ውክልና ያለው ፖሊሲና ይነስም ይብዛም ድጋፍ የላቸውም፡፡ ስለሆነም ለገዥው ፓርቲ በአጫፋሪነት ከማገዝ ያለፈ ሚና አይኖራቸውም፡፡ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲን ጨምሮ እዚህ ግባ የሚባል ኅብረ ብሔራዊ አጀንዳ ለመቅረፅ የቻለ የፖለቲካ ኃይል ጎልቶ ባለመውጣቱ፣ የሁሉም የመጨረሻ ግብ አንድ አገር መምራት ሳይሆን የተለያዩ መንግሥታትን መመሥረት እየመሰለ ይገኛል፡፡ አሳዛኝ የፖለቲካ ክስረት፡፡

በየትም አገር ቢሆን በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለመጠቀም የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በዋንኛነት የሕዝብ ድምፅ ለማግኘትና ለመመረጥ መሥራት አለባቸው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል ነፃነት ይሰጣል፡፡ ይደራጃሉ፣ ይናገራሉ፣ ይጽፋሉ፣ አቋማቸውን ለሕዝብ ያሳውቃሉ፣ ከሌላው ፓርቲ የሚሻሉበትን አማራጭ አቅርበው በሚዲያ ይከራከራሉ፡፡ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ግንባር ይፈጥራሉ፡፡ መድረክም ሆነ ኅብረት መጠሪያው ምንም ይሁን ምን ይሰባሰባሉ፡፡ ድምፅ አግኝተው ከተመረጡና መንግሥት ከመሠረቱ ገዥ ፓርቲ ወይም መሪ ፓርቲ ይሆናሉ፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ካሸነፉ አውራ ፓርቲ ይሆናሉ፡፡ ይኼ ሁሉንም እኩል የሚጠብቅ ዕድል ነው፡፡ ለዚህ ግን ገና 25 ዓመታችን ነው፡፡ 100 ዓመታት ይቀራል ብለን ልንተኛ አንችልም ፡፡

በመሠረቱ የአውራ ፓርቲ መኖር ዴሞክራሲን ወይም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን አያስቀርም፡፡ የአውራ ፓርቲ መኖር ሌሎች ፓርቲዎች መብታቸውን በአግባቡ እስከተጠቀሙ ድረስ የሚፈጥረው የጎላ ሥጋት አይኖርም፡፡ በእርግጥ ብዙ ጊዜ የአውራ ፓርቲ ተቃዋሚዎች ሥጋት የሚሏቸው ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመርያው ተደጋግሞ ሥልጣን ላይ ለብዙ ዓለመታት የቆየ ፓርቲ አምባገነን ይሆናል የሚል ነው፡፡ በእርግጥም ይኼ አያጋጥምም ለማለት አይቻልም፡፡ ፓርቲው ራሱ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲውን ካለጠናከራና የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህሉ ከተዳከመ ፈተናው በተግባር የሚታይ ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተገዳዳሪ ያጣ አውራ ፓርቲ የሌሎችን ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳብ አይቀበልም፣ እንደ ተጠቃሚ ተዋናይም አይመለከትም፡፡ ሚናቸውን አሳንሶ ያያል፡፡ አውራ ፓርቲ የመንግሥትና የፓርቲን ሥራ ይደበላልቃል፡፡ በመንግሥት ሀብት የፓርቲውን ሥራ ይሠራል፡፡ ቁልፍ በሆኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የራሱን ካድሬዎች ያለችሎታና ብቃታቸው ይሾማል፡፡ አውራ ፓርቲ የዴሞክራሲን ትርጉም ከሚፈልገው የተወሰነ አቅጣጫ አንፃር ብቻ ይወስዳል፡፡ ለሕዝባዊ ፖለቲካ ፀር ነው… ወዘተ  የሚል ትችትም ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ይኼንንም በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መነጽርም በማየት በተግባር መፈተሸ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

ምንም ተባለ ምን  ግን ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ግልጽና የተዋሀደ ፖለሲና አማራጭ ያላቸው ፖለቲከኞችና የተደራጁ ብርቱ ፓርቲዎች የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ ሕዝብን አማልሎ መመረጥ ያልቻለ አስተሳሳብ ምንም ዓይነት መድረክ እንደማያገኝም ግልጽ ነው፡፡ በፓርላማ ውስጥ ጫጫታ ለመፍጠርና ተመልካቹን ለማዝናናት ሲባል ተግዳሮት የሚፈጥሩ ተቃዋሚዎች፣ በፓርላማ አባልነት መግባት አለባቸው በማለት መሪው ፓርቲ መቀመጫዎችን በሙሉ ጠቅልሎ መያዝ የለበትም የሚሉ የዋህ ተቃዋሚዎች ተሳስተዋል መባሉም ለዚሁ ነው፡፡ ሕዝቡ ያልሰጣቸውን ድምጽ መሪው ወይም አውራው ፓርቲ ወይም ቦርዱ ከየት አምጥቶ ሊሰጣቸውና ፓርላማ ሊያስገባቸው ይችላል? የማይሆን ነገር ነው! በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ ፓርቲ እስከሆነ ድረስ ሕዝቡ ለራሱ የሰጠውን ድምፅ ራሱ ብቻ ሊጠቀምበት ሲገባ እየቆራረሰ ድምፅ ላጡ ተቃዋሚዎች ሊያድላቸው አይችልም፡፡ ይኼንንም ከግምት በማስገባት ገዥው ፓርቲም የመረጠውን ሕዝብ ድምፅ ማክበርና ማስከበር እንዳለበት ማሰብም ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

በአጠቃላይ በዚች አገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉም ኃይሎች፣ መንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት ያለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ሊያጤኑ የሚገባቸው ጊዜ ላይ እንደሚገኙ መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓትና የመድበለ ፓርቲ የሠለጠነ ፈለግን በተለይ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ሕገ መንግሥት ላይ ስለተጻፈ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ ወይም የማስመሰል ዴሞክራሲያዊነትና በውሸት ላይ የተመሠረተ አካሄድን በማሳደግ ስንዝር መራመድ አይቻልም፡፡ እጅና እግርን አጣጥፎ መፀለይም ያፀድቅ እንደሆን እንጂ ዴሞክራሲን ሊያሰፍን አይችልም፡፡ ስለሆነም መዳበሉን በመተው ለአገር የሚበጀውን፣ በመቻቻልና በመከባባር ላይ የተመሠረተውን እውነተኛ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጎዳና መጥረግ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ትውልዱ አሁን ውኃ እየበላው ያለውን አካሄድ አምርሮ እየሸሸ፣ አመፅና ሁከት ብሎም የተስፋ ቆራጭነትን መንገድ እንዲከተል በሩ መበርገዱ አይቀርም፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን ቀሪውን ጎዳና ማመቻቸት የግድ ይላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡