Skip to main content
x
ውጤት አልባው የውጭ ተጨዋቾች ዝውውር

ውጤት አልባው የውጭ ተጨዋቾች ዝውውር

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅን ቀልብ መግዛት ከቻሉ ስፖርቶች ውስጥ እግር ኳስ ተጠቃሽ ነው፡፡ እግር ኳስ በተለይም አሁን አሁን ማኅበረሰብን፣ ፖለቲካን እንዲሁም የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት የመለወጥ ትልቅ አቅም እንዳለው ይታመናል፡፡  ስፖርቱ በሜዳ ውስጥ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ወይም ከተጨዋቾች ግዥ ጀምሮ የተሻለ የፋይናንስ ጥቅም ለማግኘት ሙሉ ክለቡን እስከመሸጥ ደረጃ ይደረሳል፡፡

ክለቦችም ውጤት ለማምጣት በሚል በረብጣ ብሮች ተጫዋቾችን ያስፈርማሉ፡፡ ከተመሠረተ ሩብ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የተጨዋቾች ግዥ ሒደት ከውጤቱ ጋር ላይጣጣም የኃያላን የእግር ኳስ መንገድ እየተከተለ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ የተጨዋቾች ክፍያ የላብ ተብሎ ከሚከፈልበት ዘመን ጀምሮ በዓመት 10,000 ሺሕ ብር ክፍያ ሲሰማ ጉድ የተባለበት ጊዜ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ለተጨዋቾች ክፍያ ለመፈጸም በሚሊዮኖች እያፈሰሱ ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች፣ ለአገር ውስጥ ተጨዋቾች ከሚያወጡት ረብጣ ገንዘብ በተጨማሪ በተለያዩ የውጭ አገር ክለቦች የወጣትነት ጊዜያቸውን አጠናቀው ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያዞሩ ተጨዋቾችን ማስፈረሙን ተያይዘውታል፡፡ ምንም እንኳን በእግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል የተባሉት አገሮች ተመሳሳይ ሒደት የሚከተሉ ቢሆንም በክለባቸው ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ተጨዋችን ለማስፈረም ከአንድ እስከ አሥር ዓመት ሊፈጅባቸው እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

በ2009 ዓ.ም. ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ከ30 በላይ እንደሚደርሱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህንኑ የውጭ ተጨዋቾች ዝውውር ተከትሎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ማግኘት ከባህር ውስጥ ሳንቲም የመፈለግ ያህል ሆኗል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ከውጭ ያስፈረሟቸው ግብ ጠባቂዎች ከስድስት በላይ መሆናቸውና ቁጥራቸውም እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ እየሆነ ስለመምጣቱ ጭምር ባለሙያዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ግብዓት የሆኑት ክለቦች ተተኪ ተጨዋቾች ከማፍራት ይልቅ፣ የውጭ ተጨዋቾች የማስፈረም አባዜ ላይ መውደቃቸው እያነጋገረ መጥቷል፡፡ ከነዚህ ክለቦች አንዳንዶቹ ለዚህ በዋናነት ምክንያት የሚሉት፣ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ውድድር ላይ መሳተፋቸውን ካረጋገጡ በኋላ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የውጭ ተጨዋቾችን ማስፈረም ብቸኛ አማራጭ ተደርጎ ስለሚወሰድ እንደሆነም የሚያምኑ አሉ፡፡ ጉዳዩ ሌላ አማራጭ እንደሌለው አድርገው መውሰዳቸው አሉታዊ ጎን እንደሆነ እነዚሁ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የውጭ ተጨዋቾችን ወደ ክለባቸው በማምጣት የሚታወቁ ክለቦች ለ2010 የውድድር ዓመትም በተመሳሳይ ተጨዋቾችን እያስፈረሙ መገኘታቸው ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

‹‹የውጭ ተጨዋቾች በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የእግር ኳስ ጊዜያቸው መጠናቀቂያ ኢትዮጵያን ነው የሚያደርጉት፤›› የሚሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ናቸው፡፡ ባለሙያው በ2009 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አድጎ በዚያው ዓመት ወደ ከፍተኛው ሊግ የወረደው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ፣ በውድድሩ አጋማሽ ላይ ያስፈረማቸው ሁለት የጋናና አንድ የኮንጎ ተጨዋቾች ዕድሜና ለክለቡ ያበረከቱት ፋይዳ የወረደ መሆኑን ማሳያ በማድረግ ያለውን እውነታ ይናገራሉ፡፡

‹‹ከታክቲክ ባሻገር በተፈጥሮ ከተሰጣቸው አካላዊ ብቃት ከእኛ አገር ተጨዋቾች የተሻሉ የሚያደርጋቸው ነገር የለም፤›› የሚሉት አሠልጣኙ ከውጭ የሚፈርሙ ተጨዋቾችን ክለቦች የሚመለመሉበት መንገድና የባለሙያዎች የስብዕና ጉዳይ የችግሩ መንስዔ መሆኑ ይናገራሉ፡፡  ለዚህም ተጨዋቾቹ በኢትዮጵያ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ የሚያሳዩት ዝቅተኛ ችሎታ ማሳያ እንደሆነ ጭምር ያክላሉ፡፡

አሠልጣኞች ለውጭ አገር ተጨዋቾች ትኩረት የሚያደርጉበት ምክንያት ልምድ ማካፈል እንዲችሉ እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች ላይ ቢጠቅሱም፣ በአንፃሩ ግን በዝውውሩ ሒደት አሠልጣኞች ከሚያገኙት የገንዘብ ጥቅም ትስስር ምክንያት ይህ አስተያየት እንደሚሰጥ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡  

በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጨዋቾች የዝውውር መመርያ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ክለብ ከአምስት በላይ የውጭ አገር ተጨዋቾች ማስፈረም እንደማይችልና በአንድ ጨዋታ ላይ ከሦስት በላይ ተጨዋች ማሠለፍ እንደማይችል ቢቀመጥም፣ ሕጉ በአግባቡ እንዳይተገበር የዝውውር ደንቡ በራሱ አከራካሪ ጉዳይ እንዳለው ይነገራል፡፡

ክለቦች በውድድር ላይ መቆየትና ተሳታፊ መሆን ብቻ የዓመት ዕቅዳቸው እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች የሚነሳ ጥያቄ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች የአጭር ጊዜ ዕቅድ መከተላቸው ችግሩን እንዳሰፋውም ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም ክለቦች ከውጭ የሚያስፈርሙዋቸውን ተጨዋቾች ክህሎትን የማረጋገጥ ሒደት በዕቅዳቸው እንደሌላቸውና የውጭ አገር ዜጋ መሆናቸውን ብቻ በመመልከት እንደሚያስፈርሙ የአገሪቱን የዝውውር ደንብ ተሞክሮ በመመልከት መረዳት እንደሚቻል የሚናገሩ አሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፊርማቸውን የሚያኖሩት የውጭ አገር  ተጨዋቾች የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ደካማ መሆንና ክለቦች ታዳጊዎች የመተካት ልምድ አለመኖሩ ዋነኛ ክፍተት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ ተተኪ የሚሆኑ ተጨዋቾች ሁሉም ክለቦች እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ከነዚህም መካከል ተጨዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን እንዲመጡ ዕድል የሚሰጡ ጥቂት ክለቦች ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ  የውጭ ተጨዋቾች የማስፈረም አባዜ የተጠናወታቸው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከታችኛው ሊግ ለሚመጡት ክለቦች ጭምር መጥፎ አርዓያ እየሆኑ እንደሚገኙም ይነገራል፡፡ ከብሔራዊ ሊግ ጀምሮ በፍተኛ ሊግና ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆናቸውን ካረጋገጡ ክለቦች መካከል መቐለ ከተማ ከወዲሁ ሦስት የውጭ አገር ተጨዋቾች ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል፡፡ እስከዛሬ ከታየው ተሞክሮ ከውጭ ሊጎች ወደ አገር ውስጥ ከመጡ ተጨዋቾች ጥሩ ልምድ ማካፈል ችለዋል ከሚባሉት ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊሱ በረኛ ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦንዶንካራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ተጨዋች ውጭ ውጤታማ ሆኖ የተሻለ ልምድ ማካፈል የቻሉ ተጨዋች ስም መጥቀስ ግን አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የተለያዩ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡

የክልል ክለቦች በብዙ ልፋትና ድካም እንዲሁም ከእያንዳንዱ የከተማው ኅብረተሰብ ኪስ በሚወጣ ገንዘብ በውድ ዋጋ ተጨዋችን አስፈርሞ እግር ኳሱ ላይ ለውጥ የማይታይ ከሆነ፣ ክለቦች ራሳቸውን መመልከት እንደሚገባቸው እነዚሁ ባለሙያዎች መልዕክታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ባለው ሁኔታ የብሔራዊ ቡድኑ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ጥያቄ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከዓመት ዓመት የተጨዋቾች የዝውውር ክፍያን ብቻ ተመልክተው ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱትን የዕድሜ ጠገብ ተጨዋቾች መፍትሔ መሻት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ይመለከተናል የሚሉ መንግሥታዊ አካሉና የክለብ አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ጭምር እነዚሁ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡