Skip to main content
x
ዓለምን ያደናገጠው የኮሪያ ልሳነ ምድር ቀውስ

ዓለምን ያደናገጠው የኮሪያ ልሳነ ምድር ቀውስ

  • ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው ሚሳይል የትኛውም ሥፍራ ይደርሳል ተብሏል

ሰሜን ኮሪያ ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ከ37 እስከ 40 ደቂቃ የተምዘገዘገውንና 930 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዞ በጃፓን ባህር ውስጥ የወደቀውን የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ ማድረጓ፣ የአካባቢውን አገሮች ብቻ ሳይሆን ኃያላኑንም አስደንብሯል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2017 ወዲህ ይኼኛውን ጨምሮ 11 የሚሳይል ሙከራ ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ፣ የተዋጣ አኅጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ ማድረጓንና በዓለም የትኛውም ሥፍራ ሊደርስ እንደሚችል ማስታወቋን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ሌሊት በሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆን ኡን ትዕዛዝ የተወነጨፈው ሚሳይል፣ 2,802 ኪሎ ሜትር ከፍታ እንደነበረውም የኮሪያ ማዕከላዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ አስታውቋል፡፡

አሜሪካ የኑክሌር ጦር ሥጋት መሆኗ የሚያከትምበትና ሰሜን ኮሪያም ምርጥ በተባሉ ባለስቲክ ሚሳይሎች የታገዘ ጠንካራ የኑክሌር ምድር የሚያደርጋት ነው ተብሎ በኮሪያ ቴሌቪዥን መተላለፉን ሲኤንኤን አክሏል፡፡

ህዋሶንግ 14 የተባለው ሚሳይል፣ከ2,500 ኪሎ ሜትር ከፍታ በላይ ሆኖ ከ37 እስከ 40 ደቂቃ በመምዘግዘግ 930 ኪሎ ሜትር ተጉዞ  የጃፓንን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አልፎ በባህር ውስጥ ቢወድቅም፣ ሙከራው በሰሜን ኮሪያ ጎረቤት አገሮች ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም፡፡ ሙከራውም ከዚህ ቀደም ሰሜን ኮሪያ ካስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች ውጤታማ ነው ተብሏል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን ኮሪያን የባለስቲክና የኑክሌር ሚሳይል ፕሮግራም በማሽመድመዱ ረገድ ለውጥ አለማምጣታቸው፣ ሰሜን ኮሪያ በተያዘው ዓመት ብቻ 11 የሚሳይል ሙከራ እንድታደርግ አስችሏልም ተብሏል፡፡ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው ሚሳይል በጃፓን ባህር መውደቁን አስመልክተው ‹‹የማይታመን›› ብለዋል፡፡ ቻይና ሰሜን ኮሪያን ለማስቆም ጠንካራ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባት ተናግረው፣ የሰሜን ኮሪያውን ኪም ጆን ኡን፣ ‹‹ይህ ሰው በሕይወቱ የሚሠራው መልካም ነገር የለምን?›› ሲሉም በትዊተራቸው አስፍረዋል፡፡

አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ፕሮግራም ለማስቆም የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ከማድረግ ጀምሮ፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር ወታደራዊ ሠፈር መሥርታለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ ላይ በጃፓን ብቻ 39 ሺሕ ወታደሮችም ነበሯት፡፡

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ሽንፈቷ በኋላ በጦርነት እንዳትሳተፍ ማዕቀብ የተጣለባትን ጃፓን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል የአሜሪካ ጦር በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ ቢሰፍርም፣ ሰሜን ኮሪያ ይህንን በበጎ አታየውም፡፡ የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆን ኡንም፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሠፈረው የአሜሪካ ጦር የእሳቸውን መንግሥት ለመገልበጥ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ለዚህም ምላሹ በሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ፕሮግራም ወታደራዊ ክፍሉን ማጠናከር ሲሆን፣ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረትን አንግሷል፡፡ ሰሜን ኮሪያም በተለያዩ ጊዜያት ያስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች የሚጓዙበት ኪሎ ሜትር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሚሳይሎቿ ጎረቤቶቿ ዘንድ ብቻ ሳይሆን አሜሪካም መድረስ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኪም ጆን ኡንም በየትኛውም የዓለም ክፍል ሊደርስ የሚችል ሚሳይል እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡  

በጄምስ ማርቲን የጥናት ማዕከል ከፍተኛ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሜሊሳ ሃንሃም የሰሜን ኮሪያ የአኅጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ፣ አሜሪካ ፈታኝ ወደሆነ ድርድር እንድትመጣ ያደርጋታል ብለዋል፡፡

‹‹ለድርድር መንገድ ያለ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ድርድሩ እኛ (አሜሪካ) እንደምንፈልገው አይሆንም፡፡ አሜሪካ መደራደር የምትችለው ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ሥጋት እንዳትሆን ማድረጉ ላይ ሳይሆን በመጠኑ ላይ ገደብ ለማስቀመጥ ብቻ ነው፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ጃፓን የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ለ40 ደቂቃ ያህል በግዛቷ ውስጥ መምዘግዘጉን ስትገልጽ፣ የአሜሪካ ፓስፊክ ኮማንድ ደግሞ 37 ደቂቃ ነው ብሎታል፡፡ ሚሳይሉ ሰሜን አሜሪካ መድረስ እንደማይችልና ለአሜሪካም ሥጋት እንደማይሆን የሰሜን አሜሪካ የኤሮስፔስ መከላከያ ኮማንድ ቢገልጽም፣ በግሎባል ሴኩዩሪቲ ፕሮግራም የታቀፉ ሳይንቲስቶች ደግሞ፣ በአሜሪካ ሁሉንም የአላስካ ክፍል ሊደርስ ይችላል ብለዋል፡፡

ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ለዓለም ሥጋት መሆኗን አስመልክቶ፣ የኑክሌር ፕሮግራሟን ማሽመድመድ በሚቻልበት ከቻይናና ከጃፓን መሪዎች ጋር ቢመክሩም ሰሜን ኮሪያን ማለዘብ አልቻሉም፡፡ ባለፈው ሳምንት፣ ‹‹አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያሳየችው ትዕግሥት አብቅቷል፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህንን ተናግረው ሳምንት ሳይሞላው ሰሜን ኮሪያ ጎረቤቶቿንም ሆነ ዓለምን ያስደነገጠውን የሚሳይል ሙከራ አድርጋለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ በሚሳይል ሙከራዎቹ እመርታ እያሳየች ቢሆንም፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ሰሜን ኮሪያ ዒላማ የመምታት አቅም የላትም እንደሚሉ ቢቢሲ አስፍሯል፡፡ ሆኖም ሰሜን ኮሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚሳይል ሙከራዋ መሻሻሎችን እያሳየች፣ የተሳካ ሙከራ እያደረገችና ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የሚደርስ ሚሳይል ማምዘግዘግ እችላለሁ እያለች ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ ጃፓንን ስትፈታተን ይህ የመጀመርያዋ ባይሆንም፣ የአሁኑ ግን በምንም መሥፈርት ተቀባይነት እንደሌለው የአገሪቱ ዋና የካቢኔ ጸሐፊ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ጃፓንም ከአሜሪካና ከደቡብ ኮሪያ ጋር አብራ እንደምትሠራ ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ማበልፀግና የሚሳይል ፕሮግራም በሰማላዊ መንገድ ለማርገብ ቻይናና ሩሲያ ገንቢ ሚና እንዳላቸው በመጥቀስም፣ ጃፓን ከቻይናና ከሩሲያ መሪዎች ጋር ውይይት እንደሚኖራት አሳውቃለች፡፡

አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ሚሳይል ለመከላከል በማለት ሰሞኑን በደቡብ ኮሪያ የጀመረችው የመከላከያ ኃይል መስፋፋት አወዛጋቢነቱ ሳይረግብና ቻይናም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በቀጣናው ያለውን የደኅንነት ሥርዓት ያንቋሸሸ ነው ባለችበት ማግሥት፣ ሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራውን በተሳካ ሁኔታ ማድረጓ ነገሩ እንዴት ነው? አስብሏል፡፡

የቻይናና የጃፓን መሪዎች ከትራምፕ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ሰሜን ኮሪያን ከኑክሌር ነፃ ለማድረግ እንደሚሠሩ የገለጹ ቢሆንም፣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት ያላት ቻይና አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ሚሳይል ለመከላከል በማለት በደቡብ ኮሪያ በቅርቡ የጀመረችውን የመከላከያ ሥርዓት ግንባታ አትቀበልም፡፡ ሩሲያም ብትሆን አቋሟ እንደ ቻይና ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ በመከላከያ ዘርፍ እስከ ኑክሌር ማበልፀግ እየገሰገሰች ያለች አገር ናት፡፡ በተያዘው ዓመት ብቻ 11 የሚሳይል ሙከራ ከማድረጓ ባለፈም፣ እስከ 11,500 ኪሎ ሜትር መምዘግዘ የሚችል ሚሳይል እየሠራች ነው፡፡

የጀምስ ማርቲን ሴንተር ፎር ነንፕሎሪፍሬሽን ስተዲስ እንዳሰፈረው፣ ሰሜን ኮሪያ ተፈትነው አቅማቸውን ያሳዩ አራት ዓይነት ሚሳይሎች አሏት፡፡ እነሱም ህዋሶንግና ፑክጉክሶንግ 1,000 ኪሎ ሜትር፣ የዶንግ 1,300 ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም ሙሱዳን 3,500 ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ የሚችሉ ሲሆኑ፣ እነዚህም ተሞክረው የተረጋገጡ ናቸው፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ኬኤን-14 የተባለውንና አሥር ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘገውን፣ እንዲሁም 11,500 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፈውን ኬኤን-08 እየሠራች ነው፡፡

የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራም ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሥጋት ከሆነ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ በተለያዩ ጊዜያት የኑክሌር ፕሮግራሙን ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም፡፡ ፒዮንግያንግም እስካሁን አምስት የኑክሌር ሙከራ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡ የኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲህ ዓይነቱ ውጥረት ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት ጦሱ ለተቀረው ዓለም እንዳይተርፍ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡