Skip to main content
x
የህልውና ሥጋት የሆኑት ወንዞች

የህልውና ሥጋት የሆኑት ወንዞች

 

ከጦር ኃይሎች ወደ ሜክሲኮ ሲያቀኑ አብነት መታጠፊያ ላይ የሚገኘው ወንዝ ነጭ አረፋውን አፍቆ ይታያል፡፡ መጠኑ ያነሰ ቢሆንም የሚወርደው ውኃ የጠቆረና ለአፍንጫም የሚሰነፍጥ ነው፡፡ ዳርና ዳሩ በፕላስቲክ ጠርሙሶችና በቆሻሻ የተበከለ ከመሆኑም ባለፈ በዙሪያው ቤቶች አሉ፡፡ ካረጁና ካዘመሙት ቤቶች የተወሰኑት በመፍረስ ላይ ቢሆኑም፣ ኑሮ በአካባቢው እንደቀጠለ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በአዲስ አበባ በሚገኙ ወንዞች ዳርና ዳር የተለመደ ነው፡፡ ዘነበ ወርቅን፣ ቀበናን፣ ወሎ ሠፈርና ሳር ቤትንና ሌሎች አካባቢዎችን አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞችም ቢሆኑ ከዚህ የተሻሉ አይደሉም፡፡

በክረምቱ አፈሩንና ቆሻሻውን፣ በበጋው ደግሞ የተበከለ ውኃ የሚፈጥረውን ክምር አረፋ ይዘው ሲጓዙ ማየቱ ተለምዷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በየወንዙ ዳር የተንጠለጠሉ ቤቶችን ማየቱ አዲስ አይደለም፡፡ የአደጋ ተጋላጭነታቸው በተደጋጋሚ የሚነገር ቢሆንም ከወንዝ ዳርቻ አሥር ሜትር እንኳን ያልራቁ ቤቶች መታየታቸው ከአደጋ የሚታደግ አካል የለም ወይ? ያስብላል፡፡ ወንዞቹ በከተማ መሀል አቋርጠው የሚሄዱ በመሆናቸው በየወንዙ ዳርቻ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚገኙም የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ይገልጻሉ፡፡

ራስ መኰንን ድልድይን ይዞ ወደ ፒያሳ የሚያቀናው ወንዝ ዳርቻ በመኖሪያና በንግድ ሱቆች የታጀበ ሲሆን፣ የካ ወረዳ 6ን የሚያቋርጠው ቀበና ወንዝም በነዋሪዎች የታጀበ ነው፡፡ ቴዎድሮስ አደባባይ ኤክስትሪም ሆቴል አካባቢ የሚገኘው ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ለአደጋ በጣም ተጋላጭ ተብለው የተመደቡ ናቸው፡፡ አቶ ንጋቱ እንደሚሉት፣ በዚህ ወንዝ አንድ ቤት ተደርምሶ የ7፣ 29 እና 35 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ቤተሰቦች ሕይወት ማሳጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድን የሚያቋርጠው ወንዝም ውስጥ ከዚህ ቀደም ስድስት ቤቶች ተደርምሰው የገቡ ሲሆን፣ በወቅቱ የሞት አደጋ አልተመዘገበም፡፡

በመልሶ ማልማት የሚፈናቀሉ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ በወንዞች ዳርቻ መስፈራቸው በሕጋዊ መንገድ የተገነቡ መኖራቸውም፣ የወንዝ ዳርቻ የአደጋ ተጋላጭነትን ከጨመሩት ይጠቀሳሉ፡፡

ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ በሚገኙ ስምንት ቅርንጫፍ ጣቢያዎቹ በአዲስ አበባ ያለውን የአደጋ ተጋላጭነት አስመልክቶ ያደረገውን ጥናት ጠቅሰው አቶ ንጋቱ እንዳሉት፣ በወንዝ ዳርቻ ለሚኖሩ ሰዎች ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ከሥፍራው ማንሳትና ሌላ ሥፍራ ማስፈር ብቻ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ በአካባቢው ለሚኖሩት ግንዛቤ ከመስጠቱ ባለፈ ለሚመለከታቸው አካላት የችግሩን አሳሳቢነት የጠቆመ ሲሆን፣ አንዳንድ ወረዳዎች በሕገወጥ ሰፋሪዎቹ ላይ ዕርምጃ መውሰድ መጀመራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ አንዳንዶቹ ወረዳዎች ደግሞ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ለከተማው አስተዳደር አሳውቀዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሕጋዊ ነዋሪዎች መኖራቸውም ነው፡፡

ከባለሥልጣኑ ባለፈ በወንዝ ዳር ስለሚኖሩ ሰዎች ተጋላጭነት እንዲሁም የሚበቅሉ አትክልቶች የጤና ጎጂነት በተለያዩ መድረኮች ቢወሳም ችግሩ ዛሬም አለ፡፡ በጎንደር በተካሄደው የከተሞች ሳምንት ከቀረቡ ጥናቶች አንዱም ይህንኑ ያመለከተ ነበር፡፡

 

አዲስ አበባ አጠቃላይ ከምትሸፍነው 54 ሺሕ ሔክታር ውስጥ 4,000 ሔክታሩን የሚይዘው የወንዞች ዳርቻ ነው፡፡ እነዚህ የወንዝ ዳርቻዎች የወንዞችን ንጽህና ለመጠበቅና አረንጓዴነታቸውን ሳያጡ እንዲቆዩ ለማስቻል ከንክኪ ነፃ መሆን ቢያስፈልጋቸውም በእውን ያለው ከዚህ ተፃፃሪ ነው፡፡ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በወንዞች ዳርቻ ከ15 እስከ 50 ሜትር (እንደየአካባቢው የአደጋ ተጋላጭነት መጠን) ርቀት ላይ ቤት መሠራት ቢኖርበትም፣ በርካታ ቤቶች በወንዝ ዳርቻ ተገንብተዋል፡፡ በሕገወጥ መንድ የተሠሩት ቤቶች ነዋሪዎች ከአንድ ቀን አንድ ቀን ይደረመሳል በሚል ሥጋት ቢያዙም፣ ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ አካባቢ አልተዘዋወሩም፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞች ብክለት ምክንያት የወንዝ ዳርቻ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የመላው ከተማዋ ነዋሪዎችና የተለያዩ ተቋሞች የሚለቁት ፍሳሽ ቆሻሻ ጭምርም ቢሆንም፣ የወንዝ ዳርቻዎች ያላግባብ መኖሪያ ሥፍራ ከመሆናቸውም ባሻገር ለወንዞቹ ብክለት ነዋሪዎቹ የሚለቁት ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡  እኚህ የተበከሉ ወንዞች በአዲስ አበቤዎች ብቻ ሳይሆን ወንዞቹ በሚደርሱባቸው የከተማዋ አጎራባቾችም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡

የወንዞች ጉዳይ ሲነሳ በወንዞቹ ውኃ የሚበቅሉ አትክልቶች ንጽህና ጉዳይም ተያይዞ ይነሳል፡፡ የአዲስ አበባዎቹ ቀበና፣ ባንተ ይቀጡ፣ ቁርጡሜ፣ መከተያ፣ ግንፍሌ፣ ቡልቡላና ሌሎችም ወንዞች ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሸበቧቸውና በአገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ሚሊዮኖችን እያሰጉ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች ለምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳይውሉ የሚከለክል ማሳሰቢያ ከወጣ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ዛሬም በብዙዎቻችን ገበታ የሚቀርቡት አትክልቶች በተበከለው ወንዝ አማካይነት በወንዞች ዳርቻ የተመረቱ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞችን ብክለት ለመታደግ፣ በወንዞቹ ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎችን የኑሮ ደኅንነት ለማረጋገጥና የወንዞቹን መዳረሻ አረንጓዴያማ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ወንዞቹ ዛሬም የህልውናችን ሥጋት እንደሆኑ ዘልቀዋል፡፡

ከሚያዝያ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀናት በጎንደር ከተማ በተካሄደው የከተሞች ፎርም ላይ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አሳሳቢው የወንዞች ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ የወንዝ ዳርቻዎች ከታሰበላቸው ጥቅም በተቃራኒው ለኅብረተሰቡ የአደጋ መንስዔ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ በፎረሙ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት፣ የወንዝ ዳርቻዎች ከከተማዋ 24 በመቶ የተፈጥሮ ቦታዎች አብላጫውን ድርሻ ቢወስዱም በንጽህና አለመያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

ወንዞች ከሚፈሱበት ቦታ በተጨማሪ በዳርቻቸው ግራና ቀኝ ወንዞቹን ለመጠበቅ ቦታ መተው ቢኖርበትም ሰዎች ሠፍረውባቸው ይገኛሉ፡፡ የወንዝ ዳርቻዎች ቢያንስ በ15 ሜትር ርቀት መከለል ሲገባቸው አብዛኞቹ ቤቶች የተሠሩት ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ በወንዞቹ አፋፍ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ ለጎርፍና ለመሬት ናዳም ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው፡፡ አካባቢዎቹ በንጽህና ባለመያዛቸውም ለጤና እክል ከመሆን ውጪ ይህ ነው የሚባል ጥቅም እንደማይሰጡም ይናገራሉ፡፡

የወንዝ ዳርቻዎች ነዋሪዎችን ለአደጋ ከማጋለጥ ባሻገር ባልተገባ ሁኔታ የከተማዋ ቆሻሻ ማስወገጃም ናቸው፡፡ የከተማዋ ፍሳሽ ማስወገጃ ከአሥር በመቶ በታች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ወደ ሰባት በመቶ የሚሆነው ቆሻሻ በመኪና ይወገዳል፡፡ የተቀረውና አብዛኛው የከተማው ቆሻሻ የሚወገደው በወንዞች ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች አዋሽን ተቀላቅለው ጉዳታቸው ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ድሬዳዋና ሌሎችም ክልሎችን ያዳርሳል፡፡ ለአዲስ አበባ ወንዞች መበከል ተጠያቂ የሆኑት ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የሕዝቡን ጤና ለማስጠበቅ ቆመዋል የሚባሉ የጤና ተቋሞች ጭምርም ናቸው፡፡

‹‹በከተማዋ 400 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውኃ በአንድ ቀን እንጠቀማለን፡፡ ከዚህ 80 በመቶው ተመልሶ ይወጣል፡፡ ከዚህ አብዛኛው ባልተገባ መንድ በወንዞች አማካይነት እየወጣ ነው፤›› በማለት አቶ ዋለልኝ ያስረዳሉ፡፡ ወንዞች እንዲሁም ዳርቻቸው ከተማዋን አረንጓዴያማ የማድረግ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም ይናገራሉ፡፡ በአሁን ወቅት የከተማዋ ተደራሽ አረንጓዴ ቦታ አንድ ሜትር ስኩዌር በአንድ ሰው ሲሆን፣ ሰባት ሜትር ስኩዌር በአንድ ሰው የማድረግ ዕቅድ እንዳለም ይገልጻሉ፡፡ ከተማዋ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንደ ደብረ ጽጌ ያሉ ትልልቅ ፓርኮች መገንባት ስለማይቻል የወንዞችን ዳርቻ እንደ አማራጭ መጠቀሙ የግድ ይላል፡፡ የወንዝ ዳርቻዎችን ተከትሎ ከላይ ወደ ታች የሚዘረጉ ፓርኮች የመሥራት ዕቅድ ይዞ ጽሕፈት ቤታቸው ከተቋቋመ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ የወንዞች ዳርቻን የማፅዳት ሥውን ጀምረዋል፡፡

በአዲስ አበባ በሦስት ወንዞች ዳርቻ ብቻ ወደ 166 ሺሕ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ መዳረሻዎቹ ለማጽዳትና ወደ ፓርክ ለመለወጥ ነዋሪዎቹ ተነስተው ሌላ አካባቢ መስፈር አለባቸው፡፡ ሰዎቹ ከአካባቢው መነሳታቸውና የወንዞች ዳርቻ መጽዳቱ ብቻውን ግን መፍትሔ አይሆንም፡፡ ወደ ወንዞቹ የሚለቀቅ ቆሻሻ በሌላ መንገድ መወገድ ካልቻለ የወንዞቹን ውኃ የተመረኮዙ ምርቶች አስጊ ናቸው፡፡

አቶ ዋለልኝ እንደሚሉት ወንዞቹ ንፁህ እንዲሆኑ ከተፈለገ አማራጭ የቆሻሻ ማስወገጃ መንገድ መዘጋጀት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ያቀረበውን አማራጭ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ባለሥልጣኑ በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ እያስገነባ ያለው የቆሻሻ ማስወገጃና የፍሳሽ ቆሻሻ ማፅጃ ይጠቀሳል፡፡ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚወጣውን ቆሻሻ ፈሳሽና ደረቁን በመለየት መልሶ ለአገልግሎት የማዋል ጅማሮም ይጠቀሳል፡፡ አዲስ አበባም ከዚህ በተጨማሪ የቆሻሻ መኪኖች የሚያነሱትን ቆሻሻ መጠን በመጨመርና በሌሎችም አማራጮች ቆሻሻ ማስወገድ ካልቻለች ችግሩ ለዘለቄታው አይፈታም፡፡

የአዲስ አበባ የወንዞች ልማት ፕሮጀክት በአሁን ወቅት በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ጉለሌና የካ ክፍለ ከተሞች 5,000 አባላት ያሉት 60 ማኅበራትን አቋቁሟል፡፡ ወጣቶቹም የጀሞና የቀበና ወንዞችን ማጽዳት ጀምረዋል፡፡

የተያዘው ፕሮጀክት በልደታ፣ አራዳና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የሚቀጥል ሲሆን፣ በቀጣይ ሃያ ዓመታት በአማካይ አሥር ቢሊዮን ብር ወጥቶበት ሁሉም ወንዞች ይዳረሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መዳረሻዎቹን አረንጓዴያማ ማድረግ ብቻውን ለውጥ ስለማያመጣም ነዋሪዎች ቆሻሻ በወንዙ እንዳያስወግዱ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ጀርመን ኤምባሲ አካባቢ 105 ቤቶች ተለይተው ነዋሪዎቹ ቆሻሻ በወንዝ እንዳያስወግዱ የድርድር ሥራ መሠራቱን ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ለዓመታት የዘለቀው ቆሻሻ የማስወገጃ መንገድ በአንዴ ይለወጣል ብሎ መጠበቅ ይከብዳል፡፡

በብክለቱ የሕክምና ተቋሞችና ፋብሪካዎች ተጠያቂ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ባለፉት አሠርታት ተረፈ ምርታቸውን ወደ ወንዝ በመልቀቅ የኅብረተሰቡን ጤና አደጋ ውስጥ ጥለዋል፡፡ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ግንዛቤና ብክለት ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ አቶ ለሜሳ ጉደታ እንደሚናገሩት፣ የተቋሞቹ ፍሳሽ ቆሻሻ ሳይታከም ወንዝ ይገባል፡፡ በርካታ ፋብሪካዎች ፈሳሽ ቆሻሻ የሚያክሙበት (ትሪትመንት ፕላንት) ሳይኖራቸው ለዓመታት ዘልቀዋል፡፡ ‹‹ወንዞች በከፍተኛ ደረጃ ተበክለዋል፡፡ የሰውና የወንዝ ግንኙነት ያለውም መጥፎ ደረጃ ላይ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የወንዞች ብክለት በሰዎች እንዲሁም በእንስሳት ጤናም ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች ብክለት ከከተማዋ ነዋሪዎች አልፎ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ አርሶ አደሮችንም እየጎዳ ይገኛል፡፡ ለብክለቱ 63 በመቶ ድርሻ የሚወስዱት ነዋሪዎቹ ሲሆኑ፣ ኢንዱስትሪዎች 37 በመቶ ይበክላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች የፋብሪካ ዝቃጭ ቆሻሻ መጠን ከ4.8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህን የተበከሉ ወንዞች ተጠቅመው የተበከለ የጓሮ አትልክት የሚያመርቱ ግለሰቦች ወደ 50 ሺሕ ገደማ ይገመታሉ፡፡

አቶ ለሜሳ እንደሚገናሩት፣ ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ እንደ ሊድ፣ አርስኒክና ክሮሚየም ያሉ ኬሚካሎች ያጠቋቸው አትክልቶች በከፍተኛ ሙቀት ቢበስሉም እንኳን ኬሚካሎቹ ስለማይጠፉ አደገኛ ናቸው፡፡ የወንዞች መበከል የተዛባ አካል ያላቸው ሰዎችና እንስሳት እንዲወለዱ እንዲሁም ለአዕምሮ ዕድገት ውስንነትና ካንሰርም ያደርጋል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ፀጉር የሌላት ጥጃ መወለዷ፣ እንደተወለደችም ጡት መጥባት ተስኗት ሕይወቷ ማለፉን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ፋብሪካዎች ፈሳሽ ቆሻሻውን አክመው የሚያስወግዱበት መንገድ መፍጠር እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ፋብሪካዎቹ አንድ ላይ ሆነውም ወጪ ቀናሽ በሆነ መንገድ በጋራ ፈሳሽ ቆሻሻ ማከም እንደሚችሉ ያክላሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋሞች እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፣ በወንዝ ዳርቻ ለመኪና እጥበትና የጓሮ አትክልቶችን ለማምረት ቦታ የሚሰጠውም በመንግሥት አካላት ነው፡፡ ወንዞችን ለማፅዳት እንዲሁም መዳረሻቸውን ለማልማት ያለው ተነሳሽነትና ለብክለታቸው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተቋሞች ላይ የሚሰወደው ዕርምጃ መላላት በተቃርኖ ይታያሉ፡፡

ቀድሞ እንደ ቁርጡሜ ባሉ ወንዞች ዓሳ ይኖር ነበር፡፡ ዛሬ በተቃራኒው የዓሳ ዝርያዎች ጠፍተው ለሰውና እንስሳት ህልውናም አስጊ ሆኗል፡፡ ወንዞች በአጭር ጊዜም ይሁን በረዥም ጊዜ ልዩነት የሚታይ ተፅዕኖ ማሳደር ከጀመሩ የመሰነባበታቸው ጉዳይ የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ የወንዝ ዳርቻ ነዋሪዎች ለሕይወትና ለንብረት እጦት ተጋላጭ መሆናቸው ነው፡፡ አቶ ዋለልኝ እንደሚናገሩት፣ በቅርብ በተሠራ ጥናት መሠረት ከተማዋ ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት አላት፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በወንዝ መዳረሻ መኖሪያቸውን የገነቡ የበለጠ የሥጋት ተጋላጭ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ዋለልኝ ጽሕፈት ቤታቸው የወንዝ ዳርቻዎች ሥነ ምህዳራዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የአጥቢያ ፓርኮች ግንባታ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ኅብረተሰቡና ወንዞች መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች ክለቦች ማቋቋምንም እንደ መፍትሔ ያነሱታል፡፡ በተጨማሪም ሰዎች በተፈጥሮ ሀብት ላይ ብክለት ሲደርስ ሲያዩ ፎቶ አንስተው ወይም ቪዲዮ ቀርፀው የሚልኩበት አፕልኬሽን በተግባር ማዋላቸውንም ይገልጻሉ፡፡

አቶ ለሜሳ በበኩላቸው ወንዞችን በተመለከተ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ድንገተኛ ሆነው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሳይሆን፣ የማኅበረሰቡን ደኅንነት ባማከለ ሁኔታ በሒደት የሚከወኑ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡