Skip to main content
x
የሆሄ ጥበባዊ መድረክ ድባብ

የሆሄ ጥበባዊ መድረክ ድባብ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተካሂዶ ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከነበሩት ጥበባዊ መሰናዶዎች መካከል የሀሁ ዳንስ ቡድን መጽሐፍ ተኮር ዳንስና የፌደራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ሕብረ ዝማሬ ይገኙባቸዋል፡፡ ፎቶዎቹ ክንውኑንና ታዳሚውን ያሳያሉ፡፡

ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን

 የቅኔው መጽሐፍ

የቅኔው መጽሐፍ ሳይቀር ይያዝና

እንግዲህ ከዛፍ ሥር ጋደም ይባልና፣

የግጥም መጽሐፍ ሳይቀር ይያዝና፣

ፍትፍቱ ባገልግል፣ ጠላው በቅምጫና፣

ጠጁ በብርሌ ቡናው በጀበና፣

እጣኑ ከገሉ ቦለለል ይልና፣ እግር ባልዞረበት ሥውር አለ ስፍራ

ካጀብ ተለይቶ ከግርግር ርቆ ሆኖ ካንች ጋራ

. . . .

ኸዚያ ወዲያማ፣

ኸዚያ ወዲያማ፣

ዝፈኝልኝ ነዋ እንጉርጉሮ በይ፣

‹‹አራዳም እንደሰው ይናፍቃል ወይ፣

አራዳ አራዳዬ አራዳ አራዳዬ፣

ሆይ-ሆይ! ገነት ማለት፣ ይች ናት ሆድዬ!››

ተስፋዬ ገሠሠ ‹‹መልክአ ዑመር ›› (1987 ዓ.ም.)
********

‹‹መላ ጂስሜን ጦርፎ ይዞኝ››

አንድ የወሎ ባላገር ወደ ሐኪም ቤት ሂዶ ‹‹ሕመምህ ምንድን ነው? ሲባል ‹‹አንድ አንከለፍ ነገር መላ ጂስሜን ጦርፎ ይዞ መጧሪያዬ ላይ ያስጨንቀኛል›› አለ፡፡  ዶክተሩ ተጨንቆ ‹‹ይህን የሚተረጉም ልጅ የለዎትም ወይ?›› ሲል ‹‹አንተ ራስህ አማርኛ አታውቅም ወይ?›› ተባለ፡፡ አንባቢዎችስ ምን ማለት ይመስላችኋል? ጅስም ሰውነት፣ መጦረፍ ቀሥፎ መያዝ፣ መጧሪያ ፊንጢጣ (ዓይነ ምድር መውጫ) ማለት ነው፡፡ ባላገሩ መናገር የፈለገው ‹‹ፊንጥጣዬ ላይ ብጉንጅ የሚመስል እባጭ ተፈጥሮ ሰውነቴን ቀሥፎ ይዞ ያሰቃየኛል›› የሚል ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ  እናቶችም የራስ ሕመም  መከራና ሥቃይ ሲፈጥርባቸው ‹‹መጥረቢያውን ይዞ ግንባር ግንባሬን ይፈልጠኛል፤ መዶሻውን ይዞ ራስ ራሴን  ይመታኛል›› የሚሏቸው ቃላት ለትርጉም  ያስቸግራሉ፡፡ አዎ የአማርኛ ቋንቋ በየክፍለ ሀገሩ እንደዚህ የተለያዩ የንግግር ፈሊጦች አሉት፡፡ ለምሳሌ በመሐል አገር የአዲስ አበባ ሕዝብ አባባል (ዘይቤ) ለመኪና ተጓዥ የሚነገረው ቃል ‹‹ተሳፈር›› የሚል ነው፡፡ በጎንደር ግን ተሳፈር ለማለት ‹‹በመኪና ላይ ተሰቀል›› ይላል፡፡ መክብብ አጥናው ‹‹የአእምሮ ማዝናኛ››  (2005)

*****

እንዲመስል አድርጐ የማስረዳት ጥበብ

ሰውዬው ጀብደኛነቱን ሲገልጥ ‘‘ጥንቸልዋ ስትሮጥ የኋላና የፊት እግርዋን ጆሮዋን ጭምር በአንድ ጥይት አቦነንኩት፤’’ አለ፡፡ ጓደኛው ግን ‘‘ኧረ እንደሚመስል አድርገህ አውራ! የኋላና የፊት እግርን ከጆሮ ጋር ምን አገናኝቷቸው ነው ይህን ሁሉ የአካል ክፍል በአንዲት ጥይት መምታት የምትችል?’’ አለው፡፡ ተኳሹም ሲመልስ ‘‘በኋላ እግሮችዋ ጆሮዋን ስታክ ነው፤’’ ብሎ ነበር፡፡ ግን ‹‹አንዱ የኋላ እግርስ እሺ ተመታ እንበል፣ የፊት እግሮቿስ ከጆሮ ግንድ ጋር አብረው እንዴት ተመቱ? ስለዚህ ‘‘ነብር ሳይገድሉ ቆዳውን ለመሸጥ ያስማማሉ፤ እንደሚባለው ነው፡፡ ፈጽሞ አንተ አልተኮስህም፣ ጥንቸሏም አልሞተችም’’ አለው፡፡