Skip to main content
x

የልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጁና ውዝግቡ

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ስለሚያገኘው ልዩ ጥቅም የሚደነግገው አዋጅ የበርካታ ሰዎች የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከግለሰብ እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በግንባርም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተስተናገዱ አያሌ ጭቅጭቅና ንትርኮችን ያዘሉ ጽንፈኛና አክራሪ ክርክሮችን ሳይቀር አድምጠናል፡፡ አብዛኛው ክርክር ወደ መግባባት ሳይሆን ወደ አደገኛ ግጭት እንዲያመራም ሥጋት ያዘለ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ ዕውቀቱና ብቃቱ ያላቸው ብልህና አዋቂ ዜጎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መጋበዙ ተገቢ ይሆናል፡፡ ሐሳቡን የሚቃወሙና የሚደግፉ ሰዎች በሚያደርጉት ክርክር መካከል ያስተዋልኩትን ትዝብትና አስተያየት እንደሚከተሉ አቀርበለሁ፡፡

የተቃዋሚዎች መነሻ

በእነዚህ ወገኖች የሚቀርበው ሐሳብ በቅድሚያ አንድ ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መገንባት የሕገ መንግሥቱ ዋና ግብ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ የተገለጸውን የሚፃረር ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱን ቁልፍ ግብ የሚቃወም በመሆኑ ከሕግ አንፃር ሲታይ አቋማቸው ስህተት ነው፡፡ ከሕዝቦች ጥቅም አኳያ ሲፈተሽም ሕዝቦች በጨቋኝና በተጨቋኝ ግንኙነት ተጠምደው በኋላቀርነት ቀንበር ውስጥ ሆነው ቅድሚያ ለሕልውናቸው ሲጣጣሩ የኖሩትን፣ በአገራቸው ድህነት ላይ በማተኮር ያዳበሩትን የአብሮነትና የአንድነት መንፈስም ክፉኛ ይሸረሸራል፡፡ ዋጋም ያሳጣል፡፡ ይህ አመለካከት በተፈጥሮ ፀጋዋና በታሪኳ ቀንተው አገሪቱን በማተራመስ ሕዝቦቿን ለመከራ ለመዳረግ ሌት ተቀን ለሚተጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝብና አገርን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ተቃዋሚ እንጂ ድጋፍ የለውም ይላሉ፡፡ ስለዚህ ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ግብና በመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍትሐዊ የጋራ ጥቅም መስተካከል ተገቢና ትክክል ነው የሚል የተቃዋሚዎች ጥቅም የክርክር አስተያየት ነው፡፡

የረቂቅ አዋጁ ደጋፊዎች የመከራከሪያ ነጥብ

ረቂቅ አዋጁ ከ130 ዓመት በፊት በወራሪ ጦር ከኦሮሞ ሕዝብ የተነጠቀውን የባለቤትነት መብት የፌዴራል ሥርዓቱ ያስመለሰ በመሆኑ ትክክልና ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ባይመለስም በረቂቅ አዋጁ የተቀመጡ ልዩ ጥቅሞች በአስገዳጅ ሁኔታ በአዋጅ በተገለጸው መሠረት በአስቸኳይ መተግበር አለባቸው በማለት አቋማቸውን ይገልጻሉ፡፡

      ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የኦሮሞ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ የማይመለሱ ብርቱ ተቃውሞዎችን ያሰማሉ፡፡ በረቂቅ አዋጁ የተሰጠው ጥቅም ለኦሮሞ ሕዝብ ችግር ፍትሐዊ ለውጥ አያመጣም፣ ይልቁንስ ገዢው ፓርቲ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል የኦሮሞን ሕዝብ ከነፃነት ትግሉ ለማዘናጋት ያወጣው የማዘናጊያ ስልት ነው በማለት የልዩ ጥቅም አዋጁን ከመቀበል ይልቅ ለሙሉ ነፃነቱ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ይጠይቃሉ፡፡

       የልዩ ጥቅም አዋጁ ተቋሚዎችና ደጋፊዎች ክርክር በጋራ ጥቅም መሠረት ሲመዘን የረቂቅ አዋጁ ቀጥተኛ ባለቤቶች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና በከተማዋ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮች በመሆናቸው፣ የክልሉ መንግሥት ሚና አለው፡፡ የፌዴራል መንግሥትን የሚመራትን ኢትዮጵያን ወክላ የምትገኝ፣ የሙሉ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ መኖሪያ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአብሮነት ማሳያ ከተማ አዲስ አበባ በመሆኗ ይኼንን የጋራ መንፈስ ማስጠበቅ የፌዴራል መንግሥት ከባድ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡

      ታዲያ የጉዳዩ ፍሬ ነገር ይኼ ሆኖ ሳለ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጉዳዩን በመለወጥ ከአዋጁ ደጋፊዎች ያልተናነሰ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተገፋፋበት መሠረታዊ

የልዩ ጥቅም ማስከበሩ ሒደት ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግ በጋራ ጥቅም ላይ ካልተመሠረተ፣ የመጨረሻ ውጤቱ ለሁሉም ኪሳራ ነው፡፡ በግል ጥቅም ላይ የተመሠረተ ልዩ ጥቅም ፍለጋ ፍትሐዊ ስለማይሆን፣ ሰዎችን በአሸናፊነትና በተሸናፊነት ሥር በመውደቅ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለማጥፋት ተሠልፈው ወደፊት በቀላሉ ሊወጡት በማይቻላቸው የመከራ አራንቋ  ውስጥ ራሳቸውን ሊያገኙት ይችላሉ፡፡

      ስለዚህ ልዩ ጥቅም ለማስከበር ሲታሰብ፣ ለጋራ ጥቅም ሲባል፣ የሚገኙ መብቶችንም በፍትሐዊነት መጠቀምን ታሳቢ ማድረጉ ግምት ውስጥ የሚገባ ይመስለኛል፡፡  

      ለምሳሌ በረቂቅ አዋጁ በአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ምክንያት ከእርሻ ቦታቸው ለሚፈናቀሉ ሰዎች ተገቢ ካሳ መፈጸምና በዘላቂነት የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲኖራቸው ድጋፍ መስጠት ትክክልና ተገቢነት ያለው የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ማደግና በልማት መስፋፋት ምክንያት የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ለእርሻ መሬታቸው ተገቢውን ካሳ ሳያገኙና ሳያቋቋሙ ከቦታቸው አልተነሱም ማለት አይቻልም፡፡ ያገኟትን  ጥቂት ገንዘብ ለጊዜያዊ ፍጆታ በማዋል ለድህነት ሲዳረጉ እያየን ነው፡፡ በመንግሥት ከሚደረግባቸው መፈናቀል ሳያንስ፣ ለባለሀብቶች መሬታቸውን በርካሽ ሸጠው፣ የተሰጣቸው ጥቂት ገንዘብ አልቆባቸው መሬታቸውን ለሸጡለት ባለሀብት ዘበኛ ሲሆኑ ማየትም አሳዛኝ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና የከበሩ የክልሉ ተወላጆች አርሶ አደሩ መሬቱን እንዲሸጥ በደላላነት እያግባቡ ሲንቀሳቀሱ መታየታቸው ነው፡፡ አንዳንዶችም መሬቱን ሸጠህ ገንዘቡን ውሰድ መሬቱ እንደሆነ ነገም ያንተ ነው በማለት ቅንና ኩሩውን አርሶ አደር ያጭበረብራሉ፡፡

በዚሁ አካሄድ መሬት በመሸጥ ብዙ ገንዘብ አካብቶ በእንግሊዝ ይኖር የነበረ ዜጋ አውቃለሁ፡፡ በቅርቡ ወደ አገሩ ተመልሶ በአልሚነት ስም አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ቢወስድም ወዲያውኑ ሸጦታል፡፡ ከስደት ወደ አገሩ የሚመለስ ሰው መሬት በድርድር ያገኛል፡፡ መሬቱንም የተረከበው የኦሮሚያ መንግሥት የክልሉ ተወላጆች የመኖሪያ ቤት በመሥራት እንዲችሉ መሬት በነፃ እንዲሰጥ በሚፈቅደው መመርያ ተጠቅሞ ነው፡፡ ይኼ የግል ጥቅም አሳዳጅ ሰው የሚያደርገው ነገር ከቡድን ጥቅም ይልቅ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል የግለኝነት ባህሪይ መግለጫ ነው፡፡

ራስ ወዳድነትና ግለኛ ጥቅም ገዢ አመለካከት ሆኖ የጋራ ጥቅም ከተገፋ፣ በታሪክ እንደታየው ለማይቀለበስ ቀውስ ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ይኼንን አደገኛ ግላዊ የስስትና የራስ ወዳድነት አዝማሚያ ኅብረተሰቡን ለውድቀት ከመዳረጉ በፊት ሕዝቡና መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በጋራ ሆነው፣  ለትክክለኛ የትግል አቅጣጫ ትኩረት ቢሰጡና ቢሠሩ፣ አገርና ሕዝብን ከሚያስፈራው መከራ ሊጠብቁት ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡

ስለሆነም የልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጁ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመፅደቁ በፊት ለሕዝብ ውይይት መምራቱ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ በስፋትና በንቃት በረቂቅ አዋጁ ላይ የተመለከቱት የልዩ ጥቅም ይዘቶች ላይ ሊያወያይበት ይገባል እላለሁ፡፡ በውይይቱ የጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረቱ ሐሳቦች፣ በሰከነ አኳኋን፣ በዕውቀት በተረጋጋ ውሳኔ ድጋፉን ወይም ተቃውሞውን ማስቀመጥ ዴሞክራሲያዊነት ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችም የልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጁ ላይ ሕዝቡ በስፋትና በንቃት እንዲሳተፍ በመቀስቀስ፣ በማስተባበርና በመምራት ጉልህ ሚናቸውን ለመውጣት ቢንቀሳቀሱ፣ አገራቸውና ሕዝባቸውን ጠቅመው፣ አንድነትን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም ለሕዝቡ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ የመሆን ዕድል ሆነው የሚታዩበት አጋጣሚ እንደሚሆንላቸው እገምታለሁ፡፡ አገሪቱ በሙስናና በከባድ የአስተዳደር ችግሮች ውስጥ በመሆኗ፣ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ በሙሉ ቅድሚያ ለአገሬ ሕልውናና ደኅንነት በማለት መብቱና ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ሁሉም ይስማማል፡፡

ስለዚህ መንግሥትና በጥረት የተገኘውን ልማትና ዕድገት በማስቀጠል አንድ ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሕገ መንግሥቱ የጎደለውን ግብ በፅናትና በቆራጥነት ቁሞ ሕዝቡን በማታገል ስለ ልዩ ጥቅም የተሰናዳው አዋጅ ያላያቸውን ችግሮች ከዚህ መንፈስ በመነሳት ማስተካከልና ማረም እንዳለበት ይጠበቃል፡፡ ይኼን ሲያደርጉ ብቻ ነው ለሁሉም ዜጎች በእኩልነት የምትጠቅም፣ በህዳሴ የተረጋጋችና የበለፀገች ታላቅ አገር ለማነፅ የተገባው ራዕይ እውን የሚሆነው፡፡ 

(ደደ፣ ከአራት ኪሎ)

      ***

የመቃብር ዋጋ ቅር ያሰኛቸው ዕድርተኞች አቤት ይላሉ

 ቤተ ክርስቲያን እንደ ሥርዓቷና የአሠራር ሕጎቿ ኃላፊዎችን እንደየሥልጣናቸው ደረጃና ኃላፊነት ባመነችባቸው መስኮች የምትሾማቸውን ህሩያን ታሰማራለች፡፡ አንዱን ወደ ሌላ ታዘዋውራለች፡፡ ለምሳሌ ከቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወደ ኮተቤ ቅድስት ሐና ማርያም የተደረገው የአመራሮች ዝውውር እዚህ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲመት ምዕመኖቿን ከቃለ ወንጌል ባሻገር፣ ቤተ ክርስቲያኗ በምትሰጣቸው ቤተ ክርሲቲያናዊ አገልግሎትችም ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ዓላማዋ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ከእነዚህ አገልግሎቶች አንዱ ሥርዓተ ቀብር ነው፡፡ በየጊዜው እየተጣበበ ከመጣው የሥርዓተ ቀብር ማስፈጸሚያ ቦታ ጥበት አንፃር ችግር መኖሩ እሙን ነው፡፡ ይሁንና ለአንድ ፉካ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚጠየቀው የገንዘብ መጠን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ከሰው አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡

ሰሞኑን በቀበና አካባቢ ነዋሪ የነበሩ አንዲት እናት በገጠማቸው የጤና መታወክ ምክንያት በምንሊክ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ ቆይተው ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ተለይተዋል፡፡ ስለሆነም ቤተሰቦቻቸው ከሆስፒታል አስከሬን ተረክበው ወደ ኮተቤ ሳዓሊተ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በመውሰድ ሥርዓተ ቀብራቸውን ለማስፈጸም የገጠማቸው ችግር ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በአጥቢያችን ከሚገኙ ሌሎቹ ቤተ ክርስቲያናት ቀድሞውኑም ቦታ ስላልነበረን እንዲሁም የሚጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑና መክፈል ባለመቻላቸው፣ የቀብሩን ሥርዓት ለማስፈጸምና አስፈላጊውን ሒደት ለማሟላት የተወከሉት የቤተሰብ አባላት በቦታው ሲደርሱ የተሰጣቸው ምላሽ ትንሽ ከቤተ ክርስቲያኒቱ እሴቶች ወጣ ያለ ይመስላል፡፡ የሞተ ሰው ለመቅበር 4,000 (አራት ሺሕ ብር) መክፈል ግድ ነው ተብለዋል፡፡ ‹‹ገንዘቡ ካልተከፈለ አናስቀብርም፡፡ የቀብር አስፈጻሚነት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት በየአካባቢው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡  ለእነሱ ሲሆን እስከ ብር 20 ሺሕ ብር ትከፍሉ የለ ወይ ምነው እዚህ ሲሆን 4,000  ብር መክፈል እምቢ የምትሉት? እምቢ ብንል መብታችን ነው፡፡ ያለን ሰፊ ቦታ ስለሆነ ብንፈልግ ለጋራዥ አለያም ለሌላ ሥራ እናከራየዋለን፤›› በማለት የቤተ ክርሲያኒቱ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሬሳው ከሆስፒታል ከወጣ ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ እንደምንም ተብሎ ከእድርም ከየትም አሰባስበን ክፍያውን በመፈጸም አስቀበረናል፡፡

 የዕድር ኃላፊዎች ነገሩን ችላ ሳይሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ኃላፊዎች ስለጉዳዩ በድጋሚ ለማነጋገር ሲሞክሩም ‹‹ይኼ አዲስ አሠራር የቤተ ክርስቲያኒቱን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ የተደረገ ነው፡፡ አሠራሩ ካልተመቻችሁ በሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች ማስቀበር ትችላላችሁ፡፡ ኑሮ ተወዷል፤›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው ተመልሰዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱ እኮ የሁሉም ጓዳ እየነካካ ነው፡፡ በመሆኑም ድሆችና አቅመ ደካሞች ፉካ ውስጥ ለማስቀበር የሚችሉበት ምን ያህል አቅም አላቸው ነው ጥያቄው? የእድር አመራሮች ሰሞኑን ድንገተኛ ስብሰባ ጠርተው ለአባላቱ ነገሩን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የዕድር ክፍያ ጨምሩ፣ ሐዘን በደረሰ ጊዜ ለእናንተ መልሰን የምንሰጠው ገንዘብ መጨመር አለበት፡፡ አለበለዚያ ለማስቀበሪያ ቤተ ክርስቲያኒቷ እየጠየቀች ያለው ገንዘብ ጨምሯል፤›› በማለት ሲናገሩ፣ ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ እየመጣ ያለው የአገልግሎት ክፍያ ጨምሩ ጥያቄ ጭንቅላቱን ያዞረው አብዛኛው ዕድርተኛ፣ በነገሩ ሳይስማማ ቀረ፡፡  ወደፊት የቤተ ክርስቲያን አሠራር እንደተባለው ተለውጦ ከመቀበሪያ ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቷ ያላትን ቦታ ለነጋዴው ብቻ እስከምታከራየው አለያም ቀብር በፉካ ብቻ ይሁን ብላ እስከምታውጅ ድረስ እናስብበትና የወርሐዊ ክፍያችን እናሻሽላለን በማለት ነገሩን ሳይቀበሉት ተበትነዋል፡፡ እንደው ግን መቀበሪያ ቦታ ለማግኘት ይኼንን ያክል ክፍያ መጠየቅ ነበረበት ወይ? ያስብላል፡፡ የሌለው ምን ይሁን የሚለውም አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ መስጠት የሚገባት ይመስለኛል፡፡

ቤተ ክርስቲያቱ ከሰባት ዓመት ባላነሰ ጊዜ የተቀበረን ሰው አጽም አንሱ ቦታው ለልማት ይፈለጋል፡፡ ይህ ካልተቻለም ቤተ ክርስቲያኒቷ ባላት ፉካ ውስጥ አስገቡ ለዚህም አሥር ሺሕ ብር ክፈሉ ማለቷም የታወቀ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷን እርምጃ ትወስዳለች መባሉንም ሰምተናል፡፡ እርምጃው ምን ይሆን ብዬ እንድጓጓ አድርጎኛል፡፡ ሰው ሲሞት በገዛ ቤተ ዕምነቱ መቀበር ካልቻለ ወዴት ይሄዳል?

(ሰብለወንጌል፣ ከቀበና)