Skip to main content
x

የሕግ የበላይነት ማስከበርን ከዘመቻ የማላቀቅ ፈተና

በውብሸት ሙላት

መንግሥት ብዙ ነገሮችን በዘመቻ መልክ ማከናወን ይመርጣል፡፡ ልማት በዘመቻ፣ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በዘመቻ፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን በዘመቻ፣ አዳዲስ አሠራሮችን መተግበር በዘመቻ፣ ሙሰኞችን መክሰስ በዘመቻ አያሌ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ዘመቻ ማድረግ ይቀናዋል፡፡ ዘመቻው ሲጠናቀቅ በዘመቻ የተፈጸመው ጉዳይ የሚያስቀጥል ተቋም ቢዘረጋ በዘመቻ በተገኘው ድል ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ዘመቻዎችም ላይ አመኔታ ይኖረዋል፡፡ ዘመቻው ውጤታማ ሳይሆን ከቀረና  በየጊዜው የሚታወጁ ያዝ ለቀቅ የሚደረጉና የወረት ከሆኑ ግን ለበርካታ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡

መንግሥት ምንም እንኳን የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማቋቋምና በየጊዜው ሕጎችን ቢከልስም፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሳተፉባቸውን የሙስና ወንጀሎችን በማጣራት ክስ የሚመሠርተው ግን በዘመቻ መልክ ነው፡፡ የሁልጊዜ ተግባር ከማድረግ ይልቅ ወቅት እየጠበቁ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ባለሥልጣናት ለአንድ ወቅት ጭዳ በማድረግ ከእንደገና የተወሰኑ ዓመታትን ማረፍ ይመርጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የሕግ የበላይነትን የዘወትር ተግባር ካለማድረግ ይመነጫል፡፡ በዋናነት የሕግ የበላይነትን ማስከበር የሁልጊዜ ሥራቸው ማድረግ የሚጠበቅባቸው፣ በፌደራል ደረጃ፣ በአሁኑ አወቃቀር እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ እነሱም እንዲሁ ዘመቻ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡

የሕግ የበላይነትን ማስፈን ለመንግሥት (ለገዥው ፓርቲ) ትልቅ ፈተና መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ በልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ ከፍተኛ አመራሩ በሕግ በጣም የታሰረ ሳይሆን እንደሁኔታው መወሰን እንዲችል ስለሚፈለግ በየሰበብ አስባቡ ለፖሊስ ምርመራና ክስ እንዲጋለጥ አይፈለግም፡፡ የዚህ አሠራር መነሻው ደግሞ በልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ መሪው ፍጹም ለራሱ የግል ጥቅም የማይስገበገብ እንደሚሆን ስለሚጠበቅ ነው፡፡ በአገራችን እየሆነ ያለው ግን እንደመርሑ አይመስልም፡፡

ተጨማሪው የመንግሥት ፈተና የሚመነጨው ከገዥው ፓርቲ የቀደመ ሶሻሊስታዊ ባሕርይ ነው፡፡ በሶሻሊዝም የሕግ የበላይነት ከፍተኛ ቦታ የሚሠጠው፣ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ የበላይነት ይቀድማል፡፡ ሌላው ፈተና የሚመነጨው የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ መተግበር የተጀመረው የፓርቲው አመራሮች በቦናፓርቲስት (ንዑስ ከበርቴ) መሆን ከጀመሩ በኋላ መሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ ላይ ደግሞ ብሔርን መሠረት ያረገው የፓርቲው አወቃቀር ባለሥልጣናት ላይ በቀላሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሲባል ሙስና ውስጥ የተዘፈቁትን ከሕግ በታች ማድረግ አዳጋች ነው፡፡

የሰሞኑም የባለሥልጣናት፣ የባለሀብትና የደላሎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ያው ዘመቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከላይ የተገለጹት የመንግሥት ፈተናዎች ይመስላሉ ለዘመቻው መነሻ የሆኑት፡፡ ይህ ጽሑፍ የሙስና መንሰራፋት በሕግ የበላይነት ላይ የሚያስከትለውን አደጋ  በማሳየት  የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተቋማዊና የዘወትር ተግባር እንዲሆን በተለይም ዓቃቤ ሕግን መጠየቅ ነው፡፡ 

ሙስና ለሕግ የበላይነት ጠንቅነቱ

ከትርጉምም ይሁን ከጽንሰ ሐሳብ አንፃር ሙስና እጅግ በጣም ሰፊና ውስብስብ የሆኑ ለሥነ ምግባር ተቃራኒ ተግባራትንና የወንጀል ድርጊቶችን እንደሚያካትት ግልጽ ነው። በኢትዮጵያም በአገር ሀብትና ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ድርጊቶች በሕዝብ ወይም በመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ቢሆኑም፣ አገሮች እንደሚያወጧቸው የፀረ ሙስና ወንጀል ሕጎች ትርጉሞቹ ይለያያሉ።

ለሙስና መንሰራፋት በርካታ ምክንያቶች ማንሳት ይቻላል፡፡ በብዙ ጽሐፍት ዘንድ ፖለቲካዊ መንስዔዎች ተብለው የሚጠቀሱትን ብቻ እናንሳ፡፡ የየትኛውም አገር መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ከሆነ፣ የሕግ የበላይነት ማስፈን ከቻለ፣ ሥልጣን አንድ ቦታ ሳይከማች የተከፋፈለበት ሥርዓት ከተዘረጋ፣ በሕዝብ ዘንድ ከፍ ያለ ታማኝነት ካተረፈ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተሞላበትን አሠራር ካዳበረ በተወሳሰበ የሙስና ችግር የመዘፈቅ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ የእነዚህ ተቃራኒዎች በሰፈኑባት አገር ደግሞ ሙስናውም አብሮ መንሰራፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ፣ የሕግ የበላይነት ከራቀው፣ የሥልጣን ክፍፍልና ነፃ ፍርድ ቤት ከሌለ፣ ዜጐች በሕግ አግባብ በአገራቸው ሠርተው እንዲጠቀሙ ስለማያበረታታ፣ ሚዛናዊ ያልሆነ አስተዳደር ስለሚከተል ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥቅምና ፍላጐቶች ስለሚቆም ሙስና እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለሙስና ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩት ውስጥ የመጀመሪያው ደካማ የሆነ ፖርላሜንታዊ የቁጥጥርና የግምገማ ሥርዓት መኖር ነው፡፡ ጠንካራ ፓርላሜንታዊ ቁጥጥር መኖር አስፈጻሚው አካል ተጠያቂነቱ ስለሚጨምር ሙስና ሊቀንስ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ ቁጥጥር ሙስናን ለመቆጣጠር የሚያስችልብት አቅም ላይ ድርሷል ማለት አይቻልም፡፡ ወርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት የተባለ ተቋም ኢትዮጵያን በተመለከተ ባወጣውን መረጃ መሠረት ሕግ አውጭው በ2016 ዓ.ም. አስፈጻሚውን የሚቆጣጠርበት ሁኔታ ከመቶው ሲሰላ 42 ብቻ ነው፡፡

የሙስና ወንጀሎች ሲፈጸሙ አጥፊዎችን ተከታትሎ ለፍርድ እንዲቀርቡና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያበቃ የፖለቲካ ተነሳሽነት አለመኖር ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ምንም እንኳን ሙስናን ብቻ የሚከተታል ኮሚሽን ተቋቁሞ ለአሥራ አምስት ዓመታት ገደማ ቢሠራም፣ መጨረሻው ውጤታማ አልሆነም ተብሎና ሁሉንም ወንጀሎች ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲከታተላቸው ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ ብዙ ጊዜ በዘመቻ መልክ ሲሠራ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤቶችም በየክልሉ ሁሉ ሳይቀር በሙስና ለተከሰሱ ብቻ ዳኝነት የሚሰጡ ችሎቶችን አቋቁመው ነበር፡፡ ከሰሞኑ የሆነውም ከነመላኩ ፈንታ ጉዳይ በኋላ፣ ሌላው ዘመቻ ነው፡፡ በየወቅቱና ሁልጊዜም ወንጀል መፈጸም ወይም አለመፈጸሙን ከመከታተል ይልቅ ወቅት እየጠበቁ የሚሰጥ የፖለቲካ ውሳኔ መነሻነት የሚደረግ እንጂ የሁልጊዜ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መኖሩን አያመለክትም፡፡ በመንግሥት ሚዲያም ሲተላለፍ የሰነበተው ዜና የሚያረጋግጠው ይኼንኑ ነው፡፡ መንግሥት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ጥልቅ ተሃዲሶ ለማድረግ ቃል በገባው መሠረት አጥፊዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን እንጂ የሁልጊዜ ተግባሩ መሆኑን አያሳይም፡፡

ሌላው የሙስናን ጉዳይ ውስብስብ የሚያደርገው የፍትሕ ሥርዓቱ ግልጽነት የጎደለው አሠራር መከተሉ ነው፡፡ የሙስና ወንጀሎች ላይ ምርመራም ሆነ ክስ ለመጀመር የሚከተለው አሠራር ግልጽነት የጎደለው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ፖሊስም ይሁን ዓቃቤ ሕግ መረጃን መነሻ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ባለፈ የሚጠብቀው የፖለቲካ ውሳኔ የፍትሕ ሥርዓቱን ለሁለት አማልክት እንዲገዛ አድርጎታል፡፡ አንዱ ፖለቲካ፣ ሁለተኛው ለሕግ!

ከመጠን በላይ የተማከለ አስተዳደር ካለ፣ ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ያለውና ይህም ያለገደብ እንዲቀጥል የተደረገ ከሆነ ለሙስና መከሰት መንስዔ ይሆናሉ፡፡ አስቸጋሪው ነገር፣ ጥርጣሬው በከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ሲሆን፣ አስቀድሞ የፓርቲ ውሳኔ መጠበቁ የፀረ ሙስናው ትግል እንደሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በጣም በተማከለ ሁኔታ ስለሚወሰኑ እንዲሁም የፓርቲው አሠራር ለሕዝብም ይሁን ለሚዲያው ክፍት ባለመሆኑ በአገራችን ያለው ሁኔታም ከዚህ አንፃር ለሙስና መንሰራፋት ምቹ መሆኑን ያሳያል፡፡

እንግዲህ የሙስና መንስዔዎቹ ምንም ይሁኑ ምንም፣ ፈርጀ ብዙ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸው ግን ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው፡፡ በጥቅል የሚከተሉትን እንጥቀስ፡፡

የግዕዝ ሥርወ ቃሉ እንደሚያመለክተው ሙስና ‘ጥፋት’ ነው፡፡ በአገር ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጥፋትን የሚስከትል ነው፡፡

 ሙስና በኢኮኖሚው ላይ ቀውስ በመፍጠር የአገር ልማት እንዲቀጭጭና ኢኮኖሚ ዕድገቱም እንዲገታ፣ ኪሳራና ውድቀት እንዲፋጠንና ድህነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ በማድረግ ዜጎች ወደ ከፋ የኑሮ አዘቅት ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋል፡፡  ለኢኮኖሚ ዕድገት የተነደፉ የልማት ፕሮጀክቶች ለኅብረተሰቡ የጎላ ጥቅም እንዳያበረክቱ ያደርጋል፡፡ የመንግሥት በጀት ለተገቢውና ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ተግባር እንዳይውል ያደርጋል፡፡ የአገርን ሀብት ጥቂት ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች እንዲቀራመቱት ሁኔታዎችን በማመቻቸት አብዛኛውን ሕዝብ ለድህነት፣ ለችግርና ለከፋ የጉስቁልና ኑሮ ይዳርጋል፡፡ ለሕዝብ የሚቀርቡ የፍጆታ ዕቃዎች መጠንና ጥራትን በመቀነስ የግብይትን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በማናር ሕዝብን ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ ይሆናል፡፡

የሚከፋው ግን፣ ሙስና በሕዝቦች ዘንድ የሞራል ውድቀት፣ የሥነ ምግባር ቀውስና የሕግ የበላይነት እንዳይሰፍን በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል መቻሉ ነው፡፡ ሙስና በሕግ እኩል የመዳኘትንና የመንግሥት አገልግሎት ጥራትን ስለሚቀነስ የሕግ የበላይነት ስሜትን ከኅብረተሰቡ ዘንድ በማጥፋት ማኅበረሰቡን ላልተረጋጋ ሕይወት ይዳርጋል፡፡ በዚህም የሕዝቡ ሰላማዊ ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

ሙስና ሕዝብ በመንግሥትና በሕግ የበላይነት ላይ አመኔታ እንዲያጣና በዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው በማድረግ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የመንግሥት ሥራዎች ከተገቢው አሠራርና ከሕግ ውጪ እንዲከናወኑ በማድረግ፣ ዜጐች በአገራቸው ሀብት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መብታቸው እንዲጓደልና አድልኦ እንዲፈጸምባቸው ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ሕዝቦች በመንግሥት ላይ የሚኖራቸው እምነት እንዲሸረሸር ያደርጋል፡፡ በዚህም የተነሳ በመንግሥትና በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክፍተት በመፍጠር ሆድና ጀርባ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ ሲያድር በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋትን መፍጠሩ ግልጽ ነው፡፡ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በተራው ሥርዓት አልበኝነትንና የመብት ረገጣን በማስከተል የሕግ የበላይነትን ያቀጭጫል፤ ሲብስም ያጠፋል፡፡ በሴራሊዮን፣ በላይቤሪያ፣ በኮንጐ፣ በሶማሊያ የደረሰው መጠነ ሰፊ ቀውስ ከሙስና ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሙስና ጉዳይ አገራዊ ከመሆን አልፎም ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ከሆነ ከሁለት ደርዘን ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ አሁንም፣ አጀንዳነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውጥቷቸው የነበሩትን ‹‹የሚልኒየሙ የልማት ግቦች›› የሚባሉት የተካውና እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ መሳካት ያለባቸው፣ ‹‹ቀጣይነት ያለው የልማት ግቦች›› (Sustainable Development Goals)  የሚባለው አሥራ ሰባት ግቦች ያሉት ሲሆን አሥራ ስድስተኛው ግብ ሥር ሙስናን መዋጋት፣ግልጽነትን ማሳደግ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን መግታትና የመረጃ ተደራሽነትን ማሻሻል የሚል ንዑሳን ግቦችን አካትቷል፡፡

ግብ አሥራ ስድስትን በተመለከተና ራሱን ችሎ የአገሮች ጥረትና ስኬት እ.ኤ.አ. በ2019 ይገመገማል፡፡ እስከዚያ ድረስ ያሳዩትን ለውጥና እንቅስቃሴ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይቀርባል፡፡ ቀጣይነት ላለው የልማት ግቦች ስኬት በተለይ የሙስና ጉዳይ ኢኮኖሚያ ዕድገትን የሚያደናቅፍና ድህነትን የሚያባብስ ጋሬጣ ስለሆነ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ተወስዷል፡፡ በእርግጥ በማደግ ላይ ካሉት አገሮች ወደ ውጭ የሚወጣው ሕገወጥ ገንዘብ እያደገ መጥቶ ባለፈው ዓመት ብቻ 1.26 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱ ሲታይ ይህም በራሱ ትልቅ ጋሬጣ ነው፡፡

ይህን ግብ በተመለከተ ቀድሞ የየአገሮቹ ሁኔታ መታወቅ የተፈለገው በዚህ ግብ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሳያመጡ ሌሎቹን ግቦች ማሳካት የሚታሰብ ስላልሆነ ነው፡፡ ስለሆነም በቀረችው ሁለት ዓመታት ውስጥ ዕመርታዊ ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅባቸው አገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ሙስናን ከመቀነስ አኳያ አገሪቱ ብዙም የደረጃ መሻሻል አለማሳየቷ ነው፡፡

የፀረ ሙስና ትግሉን የሚያፋጥነውን የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ጋር በተያያዘ የአገሪቱ አፈጻጸም ሲታይ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ በተለይም ሙስናን ሊቀንሱ የሚችሉ አሠራሮች ጋር የሚያያዙት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆሉ እንጂ እየተሻሻሉ መሄዳቸውን የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡ እንደውም ተቃራኒውም የሚያረጋግጡ አሉ፡፡

ይህን የሙስና አደጋ ለመቅረፍ ዋናው መፍትሔ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ካልተከበረ ሙስናን መግታት አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡ በአገሪቱም እየታየ ያለው የሕግ የበላይነት አለመኖር ነው፡፡ ከሕግ የበላይነት ይልቅ የፖለቲካ መፍትሔ ቅድምናም የበላይነት ይዟል፡፡ መንግሥትም ሙስናን ለመዋጋት የመጀመሪያ ምርጫው ፖለቲካዊ መፍትሔ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ከሕግ የበላይነት ጋር የሚጋጭ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት የተለያዩ ፈርጆች

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥቱን ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለማፋጠን እንዲሁም በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ሲባል በተወካዮቻቸው ያፀደቁት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እንዲሁም ሕግ ተርጓሚው የመንግሥት አካላት በሕግ መሠረት ብቻ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውና ከሕግ በታች መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡

አስፈጻሚው አካል፣ በሕግ አውጪ አካል በሚወጡ ሕግጋት አማካይነት የተለያዩ መንግሥታዊ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚቋቋሙ የአስተዳደር አካላትም የተቋቋሙባቸውን ሕግጋት ሳይተላለፉ መሥራት  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም ቢያንስ ከመርሕ አንፃር፣ የሕግ የበላይነት ተቀብለው መሥራት ግድ ይላቸዋል፡፡

የሕግ የበላይነት፣ በመልካም አስተዳደር መርሕ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ሰዎች መብታቸውን የሚገኙትም ሆነ የሚያጡት በሕግ መሆንና ልዩነት ሳይደረግ ማንንም የሚገዛው ሕግ ሆኖ ሰዎች ከሕግ በታች በመሆን ለሕግ ተገዥ ሲሆኑ የሕግ የበላይነት አለ ማለት ነው፡፡ በሕገ መንግሥት ሥልጣኑ ገደብ ባልተበጀበት ንጉሣዊና አምባገነን መሪዎች ባሉባቸው አገሮች መሪዎቹ ራሳቸው ሕግ ይሆናሉ፡፡ሕጉም የበታቻቸው ይሆናል፡፡ መሪዎቹ የፈለጉትን ዓላማ ለማሳካት ግን ሕግን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ሕግ ያወጣሉ፣ እሱን ያስፈጽማሉ፡፡ እነሱ ግን ከሕጉ በላይ ስለሆኑ ሕጉ አይመለከታቸውም፡፡ ‹‹ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ›› እንዲሉ፡፡

የሕግ የበላይነት ባላበት አገር ግን ንጉሡ፣ የበላይ የሚሆነው ሕግ እንጂ ሰው አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው (ንጉሥም ቢሆን) ለሕግ ይገብራል፣ ይገዛል እንጂ ሕግ ለሰው አይገብርም፣ አይገዛም፡፡ የበላይ የሚሆነው ሕግ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ‹‹ንጉሥ›› ሲባል እንደዘመኑ፣ አስተዳደር ይትባሃሉ ሊቀያየር የሚችል ትዕምርታዊ ቃል መሆኑን ነው፡፡ ግለሰብም ብቻ ሳይሆን ቡድንንም ያመለክታል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲ ቁንጮ ላይ ያሉትን ወይም ሌሎች አይነኬ ሹማምንትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቁምነገሩ፣ በሕግ የማይነካ ሰው እንዳይኖር የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነው፡፡

ከላይ ስለሕግ የበላይነት የቀረቡት ሐሳቦች በዋናነት የሥነ ሥርዓት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በርካታ የሕግ ምሁራንም የሚጋሯቸው እነዚሁኑ ሥነ ሥርዓታዊ የሕግ የበላይነት አላባውያንን ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተወሰኑ ምሁራን ደግሞ የሕግ የበላይነት ሲባል ተራ የሥነ ሥርዓት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲንም ያካትታል ይላሉ፡፡ የዓለም ባንክም፣ በየአገሮቹ የሕግ የበላይነት እንዲከበር በሚያደርገው ጥረት የተቀበለው ብያኔ የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲን ያካተተውን ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተጠቀምነው ግን ሥነ ሥርዓታዊ የሆኑትን ብቻ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት ይዞታ በአሁኗ ኢትዮጵያ

‘ወርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት’ (World Justice Project) የተባለው ተቋም በአገሮቹ ያለው የሕግ የበላይነት ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ መረጃ በየዓመቱ ያወጣል፡፡ ለተቋሙ የሕግ የበላይነት ሲባል የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይሁን ማንኛውም ግለሰብ የሕግ ተጠያቂነት ያላቸው ስለመሆኑ፣ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች ግልጽነት፣ ለሕዝብ ይፋ መደረጋቸው፣ ቶሎ የማይቀያየሩ ወይም የተረጋጉ እንዲሁም በትክክል መፈጸማቸውና የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበሩ፣ ሕጎች የሚወጡበትና የሚፈጸሙበትን ሁኔታ፣ ፍትሕ የሚሰጥበት አኳኋን የሚያጠቃልል ነው፡፡

ተቋሙ ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2014 ከ99 አገሮች 88ኛ ነበረች፡፡ በ2015 ደግሞ ከ102 አገሮች 91ኛ ነበረች፡፡ ተቋሙ ደረጃውን ሲያወጣ 43 መለኪያዎች ጥቅም ላይ ያውላል፡፡ ለእያንዳንዱ መለኪያ በዜሮና በአንድ ነጥብ ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ በ2016 ያገኘችው ነጥብ 0.38 ነው፡፡ በመቶኛ ሲሆን ሰላሳ ስምንት ከመቶው መሆኑ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. የነበራት 0.42 ሲሆን ለውጧ እንደካሮት ዕድገት ወደታች ሆኗል ማለት ነው፡፡

ተቋሙ የሕግ የበላይነት መረጋገጡን ከሚለካባቸው መሥፈርቶች ውስጥ የተወሰኑትንና አገሪቱ ያገኘቻቸውን ነጥቦች እንመልከት፡፡ ከመንግሥት ሥልጣን ገደብ ለመኖሩ 0.35 አግኝታለች፡፡ የአስፈጻሚውን ሥልጣን ሕግ አውጭው የሚገድበው ስለመሆኑ ደግሞ 0.42 ነው፡፡ በኦዲት ሪፖርት መሠረት አስፈጻሚው አካል ኃላፊነቱን ለመወጣቱ 0.39 ተሰጥቷል፡፡ የዳኝነት ተቋሙ አስፈጻሚው አካልን መቆጣጠሩ በተመለከተ 0.35 አግኝታለች፡፡ ባለሥልጣናት በጥፋታቸው የመቀጣታቸው ሁኔታ 0.37፣ የሙስና አለመኖር 0.44፣ እኩል አገልግሎት ማግኘትና አድልኦ አለመኖር 0.34 አግኝታለች፡፡ እኩል አገልግሎት መስጠትን በተመለከተ በ2012 ከነበረው 0.5 ገደማ እየባሰበት መሄዱን ያሳያል፡፡ የመንግሥት ግልጽነት (Open government) በተመለከተ ደግሞ 0.27 ነው፡፡

የዓለም ባንክም ኢትዮጵያ ያላትን የሕግ የበላይነት አፈጻጸም እ.ኤ.አ. ከ1996 ጀምሮ እስከ 2015 ድረስ አስቀምጧል፡፡ ባንኩ አገሮች የሚያገኙትን ነጥብ ከ-2.5 (ነጌቲቭ) እስከ 2.5 ባሉት መካከል ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1996 ጀምሮ ከዜሮ በላይ አግኝታ አታውቅም፡፡ በአማካይ -0.72 ሲሆን የተሻለ አፋጻጸም የነበራት በ2014 -0.42 ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት አገሪቱ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ አሳሳቢ ሊባል በሚቻል ደረጃ ላይ መሆኗን ነው፡፡

የዓቃቤ ሕግ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት

የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም እንዲኖረው ማድረግ ለኅብረተሰቡ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ለአገር ዕድገት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ከፍትሕ አስተዳደሩ  ውስጥ ወንጀልን በመከላከልና በመመርመር ብሎም ክስ በማቅረብ የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ረገድ ዋናዎቹ ተዋናዮች ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡

የወንጀል ክስ ለማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው ዓቃቤ ሕግ ለሚያቀርበው ክስ መነሻ የሚሆኑ መረጃዎችና ማስረጃዎች ገና ከመነሻው በጥንቃቄና በተሟላ ሁኔታ ተሰባስበው ሊያዙና ሊቀመጡ ይገባል፡፡ በመሆኑም የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ዓቃቤ ሕግ ከምርመራው ተግባር መነሻ ጀምሮ በአንድ የወንጀል ጉዳይ ማስረጃ ሊሆኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ምንነት፣ ዓይነት፣ እንዴት ሊፈጠሩ እንዲሚችሉ ወይም አፈጣጠራቸው፣ ኑባሬያቸው ወይም ሕልውናቸው፣ የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ሳይጣስ እንዴት ሊሰባሰቡ እንደሚገባ፣ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸው፣ ከመርማሪ ፖሊሶች ጋር በቅርበት መሥራትና ክትትል ማድረግ አለበት፡፡

ይህ እንግዲህ ውስብስብ እንደሚሆኑ ለሚታሰበው የሙስና ወንጀሎችንም ይጨምራል፡፡ እንደውም ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፖሊስ የበለጠ መጠናከርን ይጠይቃል፡፡ የሰሞኑን የባለሥልጣናት፣ የባለሀብቶችና ደላሎች እሥራትን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ አንድን ሰው በወንጀል ጠርጥሮ ምርመራ መጀመር ፖለቲካዊ ዕርምጃ እንደመውሰድ ቀላል አይደለም ይበሉ እንጂ እውነታው ግን ተቃራኒው ይመስላል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ፣ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፖሊስ ቀድሞ ተበታትኖ ይካሔድ የነበረውን ምርመራና ክስ ወደ አንድ ተቋም በመጠቃለሉ የተሻለ አደረጃጀትና ብቃት በማዳበር የሁልጊዜ ተግባሩ ማድረግ ካልቻለ በአዋጅ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት እየተሳነው ይሔዳል፡፡ ሕዝቡም የሕግ የበላይነት ላይ ያለው አመኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየወረደ መሔዱን ይቀጥላል፡፡ በሕግ አምላክ ሲባል ሕግን ያከብር የነበረው ኅብረተሰብ የነበረውን እንጥፍጣፊም ብትሆን አሟጥጦ እንዳይጨርስና እንደገና እንዲያንሰራራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

ከላይ የተጠቀሱት በመነሳት መንግሥት ምንም እንኳን ለልማት ቅድሚያ በመስጠት በተለይም በከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚፈጸሙ ወንጀሎችንም ይሁን አጠቃላይ ትግሉን ፖለቲካዊ መፍትሔን ማስቀደም ልማቱን ማፋጠን ሳይችል ይቀርና የሕግ የበላይነትም ልማትም እንዳናጣ አካሔዱን ማጤን ይገባዋል፡፡ የሕግ የበላይነትም ጠፍቶ ልማትም ከጠፋ ነገሩ ድምፃዊው እንዳለው ሁለተኛ ጥፋት ነው፡፡

‹‹ገንዘብ አላት ብሎ መልከ ጥፋ ማግባት፤

ገንዘቧ ያልቅና ሁለተኛ ጥፋት››

መንግሥት፣ ድህነትን መቀነስ የህልውና ጉዳይና የሞት ሽረት እንደሆነ እየማለ በመገዘት ያለማሰለስ ይናገራል፡፡ የተለያዩ የዕድገት ዕቅዶችንም በተለያዩ ጊዜያት ይፋ በማድረግ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን፣ የሙስናው መጠን ከመቀነስ አኳያ ብዙም ለውጥ እያመጣም አይደለም፡፡ የፀረ ሙስናውን ትግል የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ይልቅ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚል የፖለቲካ መፍትሔ በመምረጥና ኪራይ ሰብሳቢነት ደግሞ ወንጀል ሊሆንም ላይሆንም የመቻሉ ጉዳይ የፀረ ሙስና ትግሉ የተድበሰበሰ ሆኗል፡፡ የሙስና መጠኑ ካልቀነሰ ደግሞ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ግቦች ቅርቃር ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ስለሆነም፣ የልማት ዕቅዶቹም እንደታሰበው ሊሳኩ አይችሉም ማለት ነው፡፡ ሙስናን መሠረት ያደረጉ ወንጀሎችን የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ መቀነስ ካልተቻለ የልማቱም ጉዳይ አደጋ ውስጥ መውደቁ አይቀርም፡፡ ይህንን ሁኔታ፣ የሚከተለው አገርኛ ግጥም የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ 

‹‹በነጠላ ጫማ በአንቺ አረማመድ፣

እንዴት ሊያልቅልሽ ነው የአንቻሮ መንገድ፡፡››

በዚህ የፀረ ሙስና ትግል፣ በዚህ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በጊዜው ያለመጠናቀቅና ሀብት ብክነት እንዴት የልማታዊ መንግሥት ግቦችን በማሳከት ወደ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ደረጃ መድረስ ችለን ከዚያ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት አጀንዳዎች ቅድሚያ መስጠት ላይ እንደሚደረስ መገመት ከባድ ነው፡፡ ስለሆንም፣ የሕግ የበላይነት ማስከበር የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ከፖለቲካዊ መፍትሔ የሕግ የበላይነትን ማስቀደም፣ ከፖለቲከኞቹ ውሳኔ ወደ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ውሳኔ መሸጋገር ግድ ይላል፡፡

ከአዘጋጁ- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡