Skip to main content
x
የመቃብር ዋጋ

የመቃብር ዋጋ

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተገኙት ምዕመናን በማስቀደስ ላይ ነበሩ፡፡ ጎላ ብሎ የሚሰማውን ፀሎት ተከትለው ምዕመኑ አብረው ይፀልያሉ፣ እየሰገዱ ለፈጣሪ ምሥጋና ያስገባሉ፡፡ የፍልሰታ ፆም ወቅት ስለነበር ያስቀድሱ የነበሩት ሰዎች ቁጥር ከወትሮው ላቅ ያለ ነበር፡፡

 ከሞት በኋላ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የሁሉም ምዕመን ትልቁ ፀሎትና ምኞት ነው፡፡ ፀሎታቸው መስመር ያለመስመሩን ግን ምድራዊ ሕይወታቸው ከመጠናቀቁ በፊት ምንም የሚያውቁበት መንገድ የለምና ቀን ከሌት መፆም መፀለይ ፈጣሪን ማወደስ ሥራቸው ያደረጉ በርካታ ናቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ በሌላው ጥግ የሚገኙት ደግሞ ለዘለዓለሙ ያሸለቡ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ዝነኛና ታዋቂ የነበሩ ሰዎች ሳይቀሩ ለመቃብር በተዘጋጀው ቦታ በድናቸው አርፏል፡፡ ለብዙዎች ሚስጥር የሆነውን ከምድር በኋላ ስለሚኖረው ሌላ ሕይወት የሚያውቁ እነሱ ናቸው፡፡ በአንዳንድ የውጭ ፊልሞች እንደሚታየው እነኚህ ሁለቱን ዓለሞች የሚያገናኝ መስመር (ዋርም ሆል) መፍጠርና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ጋር ተገናኝቶ ስላሉበት ዓለም ጥቂት ቢነግሩን የሚል ምኞት ያሳድራል፡፡

በመስመር የተደረደሩት ሐውልቶች የሟቾችን አጭር የሕይወት ታሪክና ዓለማዊው ሕይወት ከንቱ መሆኑን የሚናገሩ ጥቅሶች ተጽፈውባቸዋል፡፡ በአደጋ ሕይወታቸውን ያጡ የበረራ አስተናጋጆችና ሌሎች በአንድ ትልቅ ሐውልት ስማቸውና የተወለዱበት ቀን ተጽፎ ይታያል፡፡ አብዛኛዎቹ ሐውልቶች በውድ ዕምነ በረድ የተሠሩ ናቸው፡፡ ምናልባትም በከተማው ውስጥ ከሚታዩ አብዛኛዎቹ ሕንፃዎች የተሻለ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይባቸው ናቸው፡፡

ነገር ግን ከአንዳንዶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ የተዘነጉ ይመስላሉ፡፡ በዳዋና ከዛፎች ላይ በሚወርደው የቅጠል ርጋፊና ብስባሽ ተውጠዋል፡፡ በዕድሜ ብዛት የተሰባበሩም አሉ፡፡ ከመጠን በላይ ተጠጋግተው የተሠሩ በመሆናቸው ለመተላለፍ ያስቸግራል፡፡ ሁኔታው የሚደብት ስሜት ይፈጥራል፡፡ ሞትን ይበልጥ እንዲፈሩት፣ ከሞት በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት እንዲጨነቁ የሚያደርግ ስሜት ያሳድራል፡፡

በዓለም ላይ የቱንም ያህል የሚያስጨንቁና ለማጣት የሚያሳሱ ነገሮች ቢኖሩ ነፍስ የመጀመርያው ነው፡፡ ሰው ምንም ያህል ጀግና ቢሆን፣ ነገሮችን ለመጋፈጥ ደፋር ቢሆን፣ በነፍሱ የሚመጣበትን ነገር ግን አጥብቆ ይፈራዋል፣ ይሸሸዋልም፡፡ አንዳች ለነፍስ አስጊ ነገር ሲፈጠር ሰዎች በድንጋጤ አስገራሚ በሆነ ፍጥነት አጥር ዘለው ሊያመልጡ፣ ከአቅማቸው በላይ የሆነን ሰው ሊገድሉ አሊያም ሌሎች የማይታመኑ ነገሮችን በደመ ነፍስ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ገና ድክድክ ማለት የጀመረ ሕፃንና እርጅና የተጫናቸው አዛውንት ሞትን የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ የሚወስዱት ዕርምጃ ለየቅል ቢሆንም፣ ጥሪያቸው ግን አንድ ነው፡፡ ሞት አፋፍ ላይ የደረሰች ነፍሳቸውን በደመ ነፍስም ቢሆን ማትረፍ፡፡

የሰውን ልጅ ከሞት ለማንሳት የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ብዙ ተሞክሯል፡፡ በዚህ ረገድ ምናባዊ ገጸ ባህሪ የሆነውን ዶክተር ፍራንክ አንስታይንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ እስትንፋስ አንዴ ከተቋረጠ በኋላ በምንም ተዓምር ሕይወትን መልሶ ማስቀጠል እንደማይቻል ያረጋገጡ ናቸው፡፡ ስለዚህም ሞት የማይጋፉት፣ ነገር ግን የማያመልጡት ተፈጥሯዊ የሕይወት ዑደት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እስትንፋስ በሚቋረጥበት ቅፅበት የሚተካው የዓለም መጨረሻ የሆነው ዘላለማዊ እንቅልፍ ብቻ ነው፡፡

ይህ ዘላለማዊ እንቅልፍ ከዚህ ዓለም የተሻለ ነገር ይኑረው? አይኑረው? ያልተፈታ ሚስጥር ነው፡፡ ይሁንና ማንም ቢሆን የተሻለ ነገር ሊኖር ይችላል የሚለውን ሐሳብ ከግምት በማስገባት በራሱ ላይ ዕርምጃ የሚወስድ የለም፡፡ በሕይወታቸው ተስፋ የቆረጡ ‹‹በምድር ከመኖር ዘለዓለማዊ እረፍት ይሻለኛል፤›› በሚል በሕይወታቸው ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ቢወስኑም እስትንፋሳቸውን ለመቁረጥ ድፍረቱን በማጣት ውሳኔያቸውን የሚሰርዙ እንዳሉም ዕሙን ነው፡፡

አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ነውና በምንም ዓይነት መንገድ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ወደ ዘለዓለሙ ቤታቸው፣ ወደ መጡበት አፈር ይመለሳሉ፡፡ ሞት በሰው ልጆች ከሚደርስ አሳዛኝ ክስተት የመጀመርያው ነው፡፡ የሟች ቤተሰቦችና ሌሎች በቅርበት የሚያውቁት በሐዘን ስብር የሚሉበት፣ አምርረው የሚያለቅሱበት፣ ፈጣሪን የሚያማርሩበት ከባድ ሐዘን ውስጥ የሚገቡበት የሕይወት አጋጣሚ ነው፡፡

የሟች በጎ ነገሮች ሁሉ የሚወሱበትና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መኖሩን የሚመኙለት ነው፡፡ ለወትሮው አስቸጋሪ ባህሪ ያለውና ቤተሰቦቹን ሲያሳዝን የኖረ ሰው ሳይቀር ደግና ሩኅሩኅ ተብሎ የሚነገርለትም በሞቱ ጊዜ ነው፡፡ ጠላቴ ብሎ የሚያስቡት ሞተ ሲባል እንኳ የማይደነግጥ የለም፡፡

የሟችን የመጨረሻ ፍላጎት ማሟላት ጥያቄ የሌለው ተግባር ይሆናል፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሟችን ኑዛዜ ማስፈጸም፣ በመረጠው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲቀበር ማድረግ፣ የሟች የመጨረሻ ፍላጎቶች እንዲሟሉም በፍትሐ ብሔር ሕጉ ለሟች የተሰጠው መብት ነው፡፡

ብዙዎች አሟሟቴን አሳምርልኝ ሲሉ የቀብራቸውን ሁኔታም በማሰብ ነው፡፡ አሁን ካሉበት ሕይወት በበለጠ ስለቀብራቸው ሁኔታ የሚጨነቁ ብዙ አሉ፡፡ የማኅበራዊ ትስስር ዋና መገለጫ ለሆነው ዕድር መሠረትም ሞት ሲከሰት መረዳዳት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የቀብር ሥነ ሥርዓት አስፈጻሚዎችን መጠቀም በአሁኑ ወቅት እየተለመደ መጥቷል፡፡

ሟች የትና በምን ዓይነት ሁኔታ መቀበር እንዳለበት ሲታሰብ፣ ሳጥን ወይስ በሰሌን ይቀበር? የሚለው ጉዳይም አሳሳቢ ነው፡፡ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሰሌን መቀበር ይመረጣል፡፡ በሌላው እምነት ተከታዮችም በሰሌን መቀበር ያለ ቢሆንም  በብዛት በሳጥን ሲቀበሩ ይስተዋላሉ፡፡

‹‹እኔ በሰሌን መቀበር ነው የምፈልገው፡፡ ሳጥን ምንም አያደርግልኝም፤›› አሉ በስሜት ወደ ተደረደሩት የአስከሬን ሳጥኖች እጃቸውን እያወናጨፉ፡፡ ነገር ግን ህልውናቸው የተመሠረተው የአስከሬን ሳጥን በመሸጥ ነውና የተለያዩ ዓይነት ሳጥኖችን ደርድረው የገበያ ያለህ እያሉ ነበር፡፡ በላቀች አስፋው የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት የሚሠሩት እኚህ ሰው፣ በከተማው ውስጥ ስላሉ የአስከሬን ሳጥን መሸጫ ሱቆች ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡

‹‹ምኒልክ አካባቢ 10፣ መርካቶ 25፣ ጴጥሮስ 10፣ ጎተራ ስምንት፣ ሰዓሊተ ምሕረት አሥር፣ ቸርችል አካባቢ ደግሞ ሰባት የአስከሬን ሳጥን መሸጫ ሱቆች አሉ፣›› አሉ ተፎካካሪ በዝቶብናል በሚል ድምፀት፡፡ በክፍሉ ውስጥ 20 የሚሆኑ የተለያየ ደረጃና ዋጋ ያላቸው የአስከሬን ሳጥኖች ተደርድረዋል፡፡ በየቅርጫቱ ተሞልተው የተደረደሩ አበቦችም አሉ፡፡

ሳጥኖቹ ከ1,500 እስከ 5,000 ብር ድረስ ይሸጣሉ፡፡ በ5,000 ብር የሚሸጠው ሳጥን ሙሉ በሙሉ በእንጨት የተሠራና ቫርኒሽ የተቀባ ነው፡፡ ሌሎቹ በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡት ደግሞ በተለያዩ ጨርቆች የተጌጡ ናቸው፡፡ በብዛት ገበያ ያላቸውም ከ1,500 እስከ 2,000 ብር ድረስ ባለው የሚሸጡት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ቀብር የማስፈጸም ሥራ ሲሠሩ በአንዴ እስከ ስድስት ሰው እንደሚያሰማሩና በሰው ከ1,500 እስከ 2,000 ብር እንደሚያስከፍሉ ይናገራሉ፡፡ በመቃብሩ ላይ የአበባ ጉንጉን የሚደረግበት ከሆነም እንደ ጉንጉኑ ዓይነት ከ120 እስከ 300 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ሥራው ፉክክር የበዛበትና በደላሎች እጅ እየገባ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በተለያዩ ወጪዎች የታጀበው የቀብር ጉዳይ የማይናቅ ገበያ ፈጥሯል፡፡ ከመቃብር ቆፋሪዎች ጀምሮ የተለያየ ሚና ያላቸው ይሳተፉበታል፡፡ የተሻለ የሚንቀሳቀሱትም ገበያቸው የደራ ነው፡፡ ‹‹ሰው በደነገጠበት ሰዓት ክፈል የተባለውን ነው የሚከፍለው፡፡ በ5,000 ብር የሚሸጠውን ሳጥን 40,000 ብር ግዙ ሲባሉ ሳይከራከሩ ነው የሚገዙት፤›› ይላሉ በገበያው ያለውን የማጭበርበር ሁኔታ ሲገልጹ፡፡

ከሳጥኑ ሌላ የሚቀበሩበትን ቦታ መምረጡም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዶች የት መቀበር እንደሚፈልጉ በኑዛዜያቸው ይገልጻሉ፡፡ ቀደም ብለው አስፈላጊውን ወጪ የሚሸፍኑም ያጋጥማሉ፡፡ ስሞት ብለው ፉካ ወይም ቤት አሠርተው የሚጠብቁም አሉ፡፡ የቤተሰብ አባላት በአንድ ላይ የሚገቡበት የመቃብር ቤት አሠርተው ከቤተሰቡ አባል ሲሞት በቤቱ የሚያስገቡም እንዲሁ፡፡

የወይዘሮ አስቴር እንዳለ ወላጅ አባት በ83 ዓመታቸው ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡ የሥርዓተ ቀብራቸውንና የሚቀበሩበትን ሁኔታ ያደላደሉት ግን  በጉብዝናቸው ወቅት ነበር፡፡ የሞቱት ከ11 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ቤተ ክርስትያን በፉካ ለመቀበር ቅድመ ክፍያ የፈጸሙት ከመሞታቸው 12 ዓመታት በፊት እንደነበር ወይዘሮ አስቴር ይናገራሉ፡፡

በፉካ የመቀበር ፍላጎት ያላቸው ብዙዎች ምንም እንኳን ዋጋው ከፍተኛ ቢሆንም በየእምነት ተቋማቱ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ‹‹ሰው ሞቱን ሳይሆን መውደቂያውን ነው እያሰበ ያለው፡፡ ቀብር መሬት ላይ ብቻ ቢሆን ቦታ አይበቃም፤›› ይላሉ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በፉካ ክፍል ከሚሠሩ መካከል የሆኑት ቄስ፡፡

በቤተ ክርስትያኗ ከ1,200 በላይ አስከሬን የሚይዙ ሁለት የፉካ ሕንፃዎች ይገኛሉ፡፡ በጌጠኛ እምነ በረድ በተከደኑት ፉካዎች ላይ ሟች የተወለደበትና የሞተበት ዓመት ከፎቶግራፋቸው ጎን በጉልህ ተጽፎ ይታያል፡፡ ክፍሉ መቃብር ሳይሆን ግድግዳው ተጌጦ የተሠራ ወና ቤት ነው የሚመስለው፡፡ ቅዝቃዜው፣ ፀጥታውና የተላበሰው የጨለማ ድባብ የሚደብት ስሜት ይፈጥራል፡፡ በየፉካው ላይ የተለጠፈው የሟች በፈገግታ የታጀበ ፎቶ ማየትም የተለየ ስሜት ያሳድራል፡፡ አጠቃላይ ያለው ድባብ ግን ሞትን ይበልጥ አግዝፎ የሚያሳይ ዓይነት ነው፡፡

በፉካ ውስጥ ለመቀበር ትልቅ አቅም ይጠይቃል፡፡ እንደ ቄሱ ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ያስከፍሉ የነበረው 15 ሺሕ ብር ነበር፡፡ አሁን ግን 40 ሺሕ ብር ገብቷል፡፡ ክፍያው የመጨረሻ ሳይሆን በየተወሰነ ዓመት የሚታደስ ነው፡፡ በድናቸው በፉካ ውስጥ እንዲቀመጥ የሚገቡት ውል በየ15 ዓመቱ መታደስ አለበት፡፡ ተጨማሪ 15 ዓመታት በፉካ ውስጥ እንዲቆይ ተጨማሪ 40 ሺሕ ብር መክፈል ግድ ይላል፡፡ አለዚያ ግን አስከሬኑ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡

‹‹ምንም የሌላቸው ሰዎች አይደፍሩትም፡፡ ውላቸውን ማደስ ያልቻሉም አፅሙን ወስደው ሌላ ቦታ ያስቀብራሉ፡፡ ካልሆነም እዚሁ ቤተ ክርስቲያኗ ባዘጋጀችው ቦታ እንዲያርፍ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ ለአገልግሎቱ የሚያስከፍሉት ዋጋ ውድ የሚባል ቢሆንም ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ክፍት ቦታ የላቸውም፡፡ ባዶውን የተቀመጠ ፉካም አይታይም፡፡

በሰባት ዓመታት ውስጥ የሰው ልጅ ሥጋ ጠፍቶ አፅም ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜም አፅሙን አውጥቶ ሌላ ቦታ ማስቀበርና ፉካውን ለሌላ በድን ማረፊያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ‹‹አጥንት ብቻ ስለሚሆን ከጎን ሌላ አዲስ አስከሬን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ እህቴ ስትሞት የአባታችን አፅም በላስቲክ ተደርጎ በአንድ ጥግ እንዲቀመጥና የእህቴ አስከሬን እንዲቀበርበት አደረግን፡፡ እንዲህ ማድረግ የሚቻለው የቤተ ዘመድ ብቻ ሲሆን ነው፡፡ እኔና ሌሎች ወንድምና እህቶቼም በዚህ መንገድ የወላጆቻችንን ፉካ ለመጋራት ተመዝግበናል፤›› በማለት ቤተሰብ ከሆኑ ፉካውን መጋራት እንደሚቻል ይናገራሉ ወይዘሮ አስቴር፡፡

ለፉካ የሚከፈለው ክፍያ ከአንዱ ቦታ አንዱ የተለያየ ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋጋው እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ከዚህም ውጪ መሬት ውስጥ የሚቀበሩ አንዳንዶች ለሚያሠሩት ሐውልት ከ100 ሺሕ ብር በላይ እንደሚያወጡ ቄሱ ይናገራሉ፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተለያየ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ይዘወተራሉ፡፡ በድኑን የማቃጠል ልማድ የተለመደ ሲሆን፣ መሬት ውስጥ መቅበርም በበርካታ አገሮች የሚዘወተር ተግባር ነው፡፡ አስከሬን አቃጥሎ አመዱን ለመያዝ አነስተኛ ጠርሙስ በቂ ነው፡፡ ለመቅበር ግን በድኑን መያዝ የሚችል ቦታ ማግኘት ግድ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፊያ ልማት ኤጀንሲ የዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አጃኢብ ኩምሳ በከተማው 80 የሚሆኑ በእምነት ተቋማት ሥር የሚገኙ፣ 15 ደግሞ በመንግሥት የሚተዳደሩ ዘላቂ ማረፊያዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በመንግሥት ከሚተዳደሩት ማረፊያዎች በኮልፌ ክፍለ ከተማ የሙስሊም፣ ጀሞ፣ ፊሊጶስ የተባሉ ሦስት ማረፊያዎች አሉ፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ የሚገኙ ዘላቂ ማረፊያዎችም ይገኛሉ፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ቦሌ አካባቢ አዲስ በመገንባት ላይ ያሉ  ዘላቂ ማረፊያዎችም እንዲሁ፡፡ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ደግሞ ዮሴፍና መካኒሳ፣ እንዲሁም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሸጎሌ፣ ቀጨኔ፣ ካቶሊክ የሚባሉ በመንግሥት የሚተዳደሩ ዘላቂ ማረፊያዎች ናቸው፡፡

‹‹የቀብር ቦታ ድንበር የለውም፡፡ ማንም በፈለገው ቦታ መቀበር ይችላል፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ አንድ የቀብር ቦታ ከ20 ሺሕ ካሬ ሜትር ስኩዌር በላይ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ በመንግሥት የሚተዳደሩ ዘላቂ ማረፊያዎች ለተለያየ እምነት ተከታዮችና ቀባሪ ለሌላቸው ዜጎች አገልግሎት የተዘጋጁ ናቸው፡፡

ማንኛውም ዜጋ የቀብር ቦታ በነፃ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይሁንና በቀብር ሒደት የሚወጡ ወጪዎችና ሌሎችም ወጪዎችን መሸፈን ግድ ነው፡፡ ‹‹የሟች ቤተሰቦች አንዳንድ መረጃ ፈልገው ወደ ኤጀንሲው ሲመጡ፣ አፅሙን አንስተው ሌላ ቦታ ለመቅበር ሲፈልጉ 20 ብር እንዲከፍሉ ይደረጋል፤›› በማለት ማንም ሰው የቀብር ቦታዎች በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው ይናገራሉ፡፡

ይሁንና በከተማው ውስጥ የሚገኙ የቀብር ቦታዎች ውስን በመሆናቸው በየሰባት ዓመቱ አፅማቸው ተነስቶ፣ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ቦታ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ አቀማመጣቸውም  ማንነታቸውን ከሚገልጽ ጽሑፍ ጋር አፅማቸው በላስቲክ እየተደረገ ነው፡፡

በሥራው ላይ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ አንዳንድ የእምነት ተቋማት በመቃብር ስም የሚወስዷቸውን ቦታዎች ለሌላ ተግባር ሲያውሉ ይታያል፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ሕገወጦች የተለያዩ ጌጣጌጦችን ለመውሰድ ሲሉ ከመቃብር ውስጥ አስከሬን የሚያወጡባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አስከሬኑ የተቀበረበት ሳጥን ከባህር ማዶ የመጣ ከሆነም አስከሬኑን ከመቃብር ውስጥ አውጥቶ ሳጥኑን የመውሰድ ነገር እንዳለ አቶ አጃኢብ ይናገራሉ፡፡

በፍጥነት እያደገ ለሚሄደው የዓለም የሕዝብ ቁጥር በቂ አገልገሎትና ምርት ማቅረብ የብዙዎቹ አገሮች ችግር ነው፡፡ ኢኮሎጂ ግሎባል ኔትወርክ የተባለ ተቋም እ.ኤ.አ. በ2011 ባወጣው መረጃ መሠረት 131.4 ሚሊዮን ልጆች በየዓመቱ ይወለዳሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ 55.5 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ፣ 6,316 ሰዎች በየሰዓታቱ ይሞታሉ፡፡ በዓለም ትልቁ የመቃብር ሥፍራ በቨርጂኒያ የሚገኘው ኦሪንተን ሲሆን፣ የአሜሪካና የተለያዩ 11 አገሮች ዜግነት ያላቸው የ400 ሺሕ ዜጎችን አስከሬን ይዟል፡፡ በየዓመቱ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ይጎበኙታል፡፡