Skip to main content
x

የሙስና አረሞች በአግባቡ ይታረሙ

በዳዊት ወልደ ኢየሱስ

አገር የሕዝብ ናት፡፡ ሕዝብም የአገር ነው፡፡ አገር ከሌለ ሕዝብ አይኖርም፡፡ ሕዝብም ከሌለ አገር አይኖርም፡፡ ሁለቱም ድርና ማግ ናቸው፡፡ ሁለቱም በአንድ ላይ ይደሰታሉ፣ በአንድ ላይ ይከፋሉ፡፡ ሁለቱም በሥራ ያድጋሉ፣ በዘረፋ ይቀጭጫሉ፡፡ በአጠቃላይ የአንዱ መኖር የሌላውን ህልውና ይወስናል፡፡ የአገርንና የሕዝብን ህልውና ከሚፈታተኑ አረሞች መካከል ደግሞ ሙስና ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡

ሙስና ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ ሥልጣንና ኃላፊነትን በመጠቀም  የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትና ንብረትን መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር እንዲሁም በጉቦ፣ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በሃይማኖት ትስስር ላይ በመመርኮዝ አድሏዊ በሆነ አሠራር ፍትሕን እያዛቡ የግል ጥቅምን ማካበትና ሌላውን ወገን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥቀም፣ መጉዳት የሚለው ጠቅለል ያለ ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡

ይህ ክፉ አረም ለማደግ እየተውተረተረች ያለችውን አገራችን ክፉኛ እየጎዳት ይገኛል፡፡ በጥቂት ሆዳሞችም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጉስቁልና ከቧቸዋል፡፡ እንዳይጮሁም አረሙ አንቆ ይዟቸዋል፡፡ ስለሆነም አጎንብሰው እየሄዱ ይገኛሉ፡፡ ምናልባት አሁን መንግሥት የያዘው አረምን የማስወገድ ዘመቻ መፍትሔ ይኖረው ይሆን?

ሦስተኛው የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ከሆነ፣ ‹‹መንግሥት ከአሁን በኋላ በአገሪቱ አለመረጋጋትን የሚያስከትሉ የሙስና ወንጀል ተግባራትን እንደማይታገስ አስጠንቅቀው የባለሥልጣን ከለላ ያላቸው አይነኩም የሚለው አመለካከት ቦታ እንደሌለው›› በይፋ ገልጸዋል፡፡ ይህ በተግባር ከተከናወነ ውጤቱ ሩቅ ጊዜ አይወስድም፡፡ 

በእርግጥ የዘንድሮው ሙሰኞችን የማደንና ለፍርድ ማቅረብ ዘመቻ ታሪካዊ ነው ሊባል ይችላል፡፡ መጎብኘት ያለበት ተቋም፣ የሥራ ዘርፍ፣ ባለሥልጣን፣ ነጋዴ፣ ባለሀብት፣ ወዘተ እየታደኑ በመረብ ውስጥ የገቡት እየተያዙ ነው፡፡ ነገር ግን ለመረቡ አስቸጋሪ የሆኑትስ እንዴት ይያዙ ይሆን? ይህ ለመልስም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሌላው አረሙን ሲነቅሉ ደህነኛው አብሮ ተጀምሎ እንዳይነቀልም ሥጋት አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜም አረሙ እንደ መልካም ዘር ሊታይ ይችላል፡፡ ይህም ሌላ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› እንደሚባለው መያዝ ያለበት ሌባ ሊያዝ ይገባዋል፡፡ ትንሽ ሳይል ትልቅ ሕግ ሙሰኛውን ሊጠይቀው ይገባል፡፡ ያኔ መልካም ዘር ብቻ ይሆንና ያም ዘር ፍሬ አፍርቶ ለአገር፣ ለወገን የሚበጅ ይሆናል፡፡ ንፁህ ኅሊና ያላቸው ሰዎች ህልምም ዕውን ይሆናል፡፡

አረሙን ለማስወገድም ሁሉም በተሰማራበት መስክ ሊረባረብ ይገባል፡፡ ‹‹የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በራሳቸው የሚወስዱት የአስተዳደር ወይም የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከባድ የሥነ ምግባር መጣስና የሙስና ወንጀል የተፈጸመ ለመሆኑ ጥርጣሬ ሲኖራቸው ሥልጣን ላለው የምርመራ አካል ሪፖርት የማድረግ ግዴታ አለባቸው፤›› ይላል የተሻሻለው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 26፡፡

ስለሆነም ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ከባድ የሥነ ምግባር ጥሰቶች መከሰታቸውንና የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ ጥርጣሬ ካለው የዲሲፕሊን ዕርምጃ ለመውሰድ ከመንቀሳቀሱ በተጨማሪ የሙስና ወንጀልን የመመርመር ሥልጣን ለተሰጠው አካል/ኮሚሽን የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም አረሙ በአግባቡ እንዲታረም ይረዳል፡፡ አሁን እየታየ ያለው የማጣራት ዘመቻ እንዳለ ሆኖ፡፡  

ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ መረጃዎች እንዲደርሱት ሁኔታዎች ተመቻቹ ማለት ደግሞ የሙስና ወንጀል ፈጻሚዎች ከቅጣት እንዳያመልጡ ለማድረግ አንድ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ይህ ግዴታ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን፣ በልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ  ሠራተኞችም ጭምር ነው፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 2 የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሥልጣን በመሥሪያ ቤት የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ ወይም በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ በሚጠረጥርበት ጊዜ፣ አግባብ ላለው የምርመራ አካል የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበትም ተደንግጓል፡፡ ይህም ታማኝነት የሚለውን የሥነ ምግባር መርሆን ከማስፈጸም ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በሌላ በኩል የሙስና ወንጀል መፈጸሙን እያወቁ ወንጀሉን የማጋለጥ ግዴታን በግዴለሽነት አለመወጣት ተጠያቂነትንም ያስከትላል፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 8 እንደተገለጸው ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በሚሠራበት መሥሪያ ቤት የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ እያወቀ በቸልተኝነት ሳያሳውቅ ቢቀር፣ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራትና እስከ አሥር ሺሕ ብር መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

ምናልባትም ብዙዎቻችን ግንዛቤ የሌለን ከላይ በተጠቀሱት የአዋጁ አንቀጾች ላይ ነው የሚመስለኝ፡፡ ለዚህም ነው ሌቦች ሲሰርቁ በቸልተኝነት ዝም እያልን ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በመበራከት ለይቶ ለማረም አስቸጋሪ እየሆነ ያለው፡፡ በየጊዜው እየወጣ ያለው የሙሰኞችና የተዘረፈው የአገርና የሕዝብ ሀብት ቁጥር መረጃ አስደንጋጭ የሆነው፡፡ ኅሊና የጎደለው ካልሆነ ይኼን ያህል ገንዘብ እንዴት አንድ ግለሰብ ይዘርፋል ብለን እጃችንን ከአፋችን እስከምንጭን ድረስ እያስገረመን ያለው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የማያሳብ ጨካኝ በማለት ምሬታችንን እየገለጽን ያለነው፡፡ ሌላም ሌላም…፡፡ ስለሆነም ከአሁን በኋላ ለሌባ ቸል ማለት ይብቃ!

ይህን ስናደርግ የሌባው ቅስም ይሰበራል፡፡ ለወደፊቱ ሊዘርፍ የተዘጋጀም ይደነግጣል፡፡ በዚህም የቅድመ መከላከል ሥራውን አከናወንን ማለት ነው፡፡ አባቶቻችን የውጭ ጠላቶችን በጀግንነትና በትግል አሸንፈው አገራቸውን በነፃነት አኑረዋል፡፡ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ተምሳሌት እንድንሆን አድርገውናል፡፡ ቀና ብለን እንድንራመድም አድርገውናል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በአገራችን ውስጥ ለውስጥ በመሄድ ሙሰኞች እያጎበጡን ነው፡፡ በዕድገታችን ላይ ጥላሸት እየቀቡ እያወየቡን ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንዳንሠለፍም ወደኋላ እየጎተቱን ነው፡፡ እስከ መቼ? በእውነት አያስቆጭም? አሁንም ሌቦችን በማጋለጥ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡

 

አሁን መንግሥት እየሄደበት ያለውን ሙሰኞችን አሳድዶ የመያዝ ዘመቻ አጠናክሮ በመቀጠል በአግባቡ እንዲታረሙ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ቢታመንም፣ ሕዝቡ ደግሞ የተዘረፈውን የአገር ሀብት በዓይነትና በመጠን ተገልጾለት ወደ መንግሥት ካዝና መግባቱን ማወቅ  ይፈልጋል፡፡ ለነገሩ የተዘረፈው ገንዘብ በጅምር ላይ ላሉ ፕሮጀክቶች ውሎ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ለውጥ ያመጣ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡  

ስለሆነም ሙሰኞችን ለማረም በጋራ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ማሳው ሰፊ ነውና! ይህ ሲሆን ነው ከሙሰኞች የፀዳች አገር የምትኖረን፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሌባውና እውነተኛው አገር ወዳድ የሚለየው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሁሉም ዜጋ በፍትሐዊነት ከዕድገቱ ፍሬ የሚበላው፡፡ ይህ ሲሆን ነው የምናልመውን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ መንገዳችን የሚጠረገው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡