Skip to main content
x
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሁለት ኩባንያዎች ከኦዚ አማካሪ ጋር ለመሥራት ተስማሙ

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሁለት ኩባንያዎች ከኦዚ አማካሪ ጋር ለመሥራት ተስማሙ

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዘርፉ የሚገባትን ያህል አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በመንግሥት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር፣ በተለያዩ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኩል አጋዥ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የቱሪዝም ክንፍ ሆኖ ብቅ ያለውና ‹‹ማይስ›› በሚል ምህጻረ ቃል የሚተዋወቀው ግብይትን፣ ማበረታቻዎችንና ዓውደ ርዕዮችን በአንድ አጣምሮ የሚሰናዳው ዝግጅት ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ በተለያዩ አገሮች ዘንድ የቱሪዝም ማስፋፊያና የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ማስተዋወቂያ መንገድ እየሆነ በመምጣት፣ የቱሪዝም ዕድገትን ለማምጣት አንዱ አማራጭ ሆኖ እየተሠራበት የሚገኘው ‹‹ማርኬቲንግ፣ ኢንሴንቲቭስ ኤንድ ኤግዚቢሽንስ –ማይስ›› በኢትዮጵያም ውጤታማ ሆኖ እንዲተገበር ኦዚ ሆስፒታሊቲ ቱሪዝም ማኔጅመንት ኮንሰልታንሲ የተባለው ድርጅት ከአንድ ዓመት እንቅስቃሴ ማድግ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ‹‹ማይስ ኢስት አፍሪካ ፎረም ኤንድ ኤክስፖ›› በሚል ስያሜ ያሰናዳውን የመጀመሪያ ዝግጅት አከናውኖ ነበር፡፡

በየዓመቱ በቋሚነት እንዲዘጋጅ ታቅዶ የተጀመረው ይህ ዓውደ ርዕይ፣ ሁለተኛውን ዙር ከጥቂት ወራት በኋላ ለማካሄድ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ይገኛል፡፡ በቱሪዝም መስክ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አማካይነት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት፣ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ብሎም ለሌሎች የንግድ መስኮች ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር ያስችላል የተባለው ይኸው ዝግጅት፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር አገርን በማስተዋወቁ ረገድም የድርሻውን እንደሚወጣ ይታመናል፡፡

ይህንን ጅምር ለማጎልበትና የአገሪቱን በዚያውም የምሥራቅ አፍሪካን ቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚተዳሩ ሁለት ኩባንያዎች ከኦዚ አማካሪ ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት፣ ረቡዕ ሚያዝያ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡ ለኢትዮጵያና ለምሥራቅ አፍሪካ ቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዘርፍና ለጉዞ ኢንዱስትሪው ውስጥ በመሳተፍ በጋራ ለመሥራት ከኦዚ ጋር የተስማሙት ሁለቱ የሚድሮክ ኩባንያዎች ሬንቦ ኤክስክሉሲቭ የመኪና አከራይና አስጎብኝ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንዲሁም ትራንስ ኔሽን ኤርዌስ (ቲኤንኤ) ናቸው፡፡ በመግባቢያ ስምምነታቸው ውስጥ ባስቀመጡት ስትራቴጂ መሠረት በዘርፉ ለውጥ ተኮር ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚንቀሳቀሱ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡  

ከማይስ ፅንሰ ሐሳብ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ሌሎችም ለቱሪዝም ዘርፉ ይበጃሉ የተባሉ ሥራዎችን የሚድሮክ ኩባንያዎች ከኦዚ ጋር አብረው ይሠራሉ ተብሏል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የቱሪዝም ገበያ ውስጥ ጎልታ እንድትወጣ ለማድረግ ኦዚና ሁለቱ የሜድሮክ ኩባንያዎች በጥናት ላይ የሚመሠረቱ፣ ሌሎች ወገኖችንም የሚያሳትፉ ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎችን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል፡፡

የኦዚ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል እንደገለጹት፣ የገበያ መሳብያ ስለቶችን በመቀየስ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት የኩባንያዎቹ የስምምነት መጠንሰሻ ነው፡፡

በጋራ መሥራቱ በጥናት ላይ እንዲመረኮዝ ከማድረግ ባሻገር የአገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ካለበት ደረጃ ወደፊት በሚያራምድ መንገድ ይተገበራል ተብሏል፡፡ በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን ዕምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ቁጥር የማሳደግ ሥራዎችን መሥራትን ያጠቃልላል፡፡ በተለያዩ የማስተዋወቂያ ዘዴዎች ተጠቅመው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄዱ ማድረግም የስምምነቱ አካል ነው፡፡

 በሬምቦው ኩባንያ ዋና ጽሕፈት ቤት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት የሬምቦ የመኪና አስጎብኚ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ታፈሰ ስለሺ፣ የቲኤንቲ ሥራ አስኪያጅ ካፒቴን ተፈሪ ኃይሌና የኦዚ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ተፈራርመዋል፡፡

በዚህ ስምምነት ላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳውና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ታደሰ ታድመዋል፡፡

ሬይንቦ ኩባንያ በመኪና ኪራይ መስክ የአስጎብኝነት አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 እንደ አዲስ ተዋቅሮ ሬይንቦ ኤክስኪዩቲቭ ካር ኤንድ ቱር ሰርቪስ በሚል መጠሪያ ተቋቁሞ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ተካቷል፡፡

ከኦዚ ጋር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመው ሌላው የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል ቲኤንኤ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እ.ኤ.አ. በ2004 የተመሠረተ ሲሆን፣ በዋናነት በአቭዬሽን አገልግሎት መስክ የተሰማራ ነው፡፡ ኦዚ በበኩሉ በቱሪዝም ዘርፍ የማማከር አገልግሎት በመሥጠት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ‹‹ሆቴል ሾው›› እንዲሁም ‹‹ማይስ ኢስት አፍሪካ ኤግዚቢሽን›› በመባል የሚታወቁትን ዓውደ ርዕዮች በማማጋጀትና በባለቤትነት የሚያስተዳድር ኩባንያ ነው፡፡