Skip to main content
x
የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላም ለማዋል

የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላም ለማዋል

ኩሱም ጎፔል (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት ቴክኒካል ኤክስፐርት ናቸው፡፡ ምሥራቅና ምዕራብ አፍሪካን ጨምሮ በህንድ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በቬትናምና በሰሜን አውሮፓ ይሠራሉ፡፡ በቅርቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ሔሪቴጅ) በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሰላም ግንባታ ስላላቸው አስተዋፅኦ ከካሽሚር ኦብዘርቨር ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ስላላቸው ሚናና ባህልን መሠረት ካደረገ ማኅበረሰባዊ መቻቻል ምን መማር እንደሚቻል የገለጹትን ዶ/ር ኩሱም፣ በእንግሊዝ ለንደን ቃለ መጠይቅ ያደረጉላቸው ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተውጣጡት ዘይዲን ሲካንጋ፣ አሚና ፍራክስ ከይዲድ፣ በቀለ ሀብቶም፣ ጋይም አፈወርቂ፣ አቢስሚል ካሊፍ ገዲ እና ቻንዲ ግላድነስ ዋርሳማ ናቸው፡፡

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- በአህጉራችን ድህነትን በመቀነስና ሰላምን በማስፈን ረገድ ቱባ ባህላዊ ክንዋኔዎች ያላቸው የላቀ አስተዋፅኦ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሚካተቱት የማይዳሰሱ ቅርሶች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ኩሱም፡- ለዘመናት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ልዩና ማራኪ የማይዳሰሱ ቅርሶቻቸውን ስላምን ለመገንባት ተጠቅመውበታል፡፡ አንዳቸው ሌላቸውን የመገንዘብና የመቻቻል ባህል በዓለም ላይ በርካታ ሕዝቦችን እየተፈታተነ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ልናውለው እንችላለን፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ. 2003 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ ያወጣው መመርያ እነዚህን ቅርሶች ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ግጭቶችን ለመፍታት የሚረዱ እርምጃዎች ባህላዊ ቅርሶቹን መነሻ በማድረግ እንደሚፈጠሩ አምናለሁ፡፡ በማይዳሰሱ ቅርሶች ስምምነት መሠረት በአንድ ማኅበረሰብ እውቅና የተሰጣቸው ክንውኖች፣ ዕውቀቶች፣ ክህሎቶችና ሌሎችም ባህልን የሚገልጹ ሁነቶች በዘርፉ ይካተታሉ፡፡ ቅርሱ በግዙፍ በሚገለጽ ነገር ባይታይም በመዝገብ ይሰፍራል፡፡ ለማኅበረሰቡ የማንነት ጥያቄ መልስ የሚሰጥና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ቅርስ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በአካባቢው ካለው ተፈጥሮና ከታሪኩ ጋር ያለው ቁርኝትም ይታይበታል፡፡ ለሰው ልጆች የፈጠራ ክህሎትና የባህላዊ እሴቶች ብዝኃነትም አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ በዘርፉ ቋንቋ፣ ክውን ጥበባት፣ አፈ ታሪክ፣ ማኅበረሰባዊ ክንውን፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ ፌስቲቫልና ዕደጥበብ ይካተታሉ፡፡ ዘላቂነት ላለው እድገት እነዚህን ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ አገር በቀል ዕውቀት በአንድ ማኅበረሰብ ያለውን ሚና ከግምት በማስገባት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ማኅበራዊና ባህላዊ ሥርዓት ገዳ በዩኔስኮ መዝገብ ሠፍሯል፡፡

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ባህላዊ ቅርሶች መሀከል ሌላ ምሳሌ ሊጠቅሱልን ይችላሉ?

ዶ/ር ኩሱም፡-  የአፋሩን ፊነአ ሥርዓት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በባህላዊ መንገድ ግጭት የሚፈታበት፣ ማኅበረሰቡ የሚተዳደርበትና ሌሎችም የዕለት ከዕለት ክንውኖች የሚመሩበት ነው፡፡ የባህላዊ መሪዎች መምሪያ የሚተላለፍበትና በተግባር መዋሉ የሚረጋገጥበት መንገድ ነው፡፡ የአፋር መዳ የተባለው ባህላዊ መተዳደሪያ ማኅበረሰቡ እርስ በራሱና ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋርም ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው ያስችላል፡፡ በሆራ አርሰዴ ሐይቅ ዳርቻ የሚከናወነው ኢሬቻ ጥንታዊ ባህላዊ ክንውን ነው፡፡ ከተፈጥሮ ጋር  የሚያያዘው ሥርዓቱ፣ የሕይወት ምንጭ የሆነውን ዋቃ በማመስገንና በሌሎችም ሥርዓቶች ይከናወናል፡፡ የጥንት አባቶችና እናቶች ዕውቀት የሚሸጋገረው በአፈ ቃል ነው፡፡ ግብርናና አሳ ማስገርን ጨምሮ የልዩ ልዩ ሙያዎች ትምህርት ይተላለፋል፡፡ በባህሉ መሠረት በግለሰብና ማኅበረሰብ ደረጃም አገር በቀል ዕውቀት ይተገበራል፡፡ የሶማሊያው ዋዳዳ የሰዎችን ዝውውር የተመረኰዘ ባህላዊ የከዋክብት ቆጠራ ሥርዓት ነው፡፡ ትንግርቶች እውን የሚሆኑበትን ወቅት በመተንበይና በባህላዊ ሕክምና ዘዴም ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ግዴታዎችን ለመወጣት እድርና ከገንዘብ አስተዳደር ጋር የተያያዘው እቁብም ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- በአህጉሪቱ ቀንድ ያሉት ቅርሶች ስለሚጫወቱት ሚና በዝርዝር ቢያስረዱን?

ዶ/ር ኩሱም፡-  በአካባቢው ያለውን ባህል የቀረፁ እውነታዎች ከግምት መግባት አለባቸው፡፡ ታሪክ፣ የእምነት ሥርዓት፣ ቋንቋ፣ ስለ ወቅት ያለው ግንዛቤ፣ የቀን አቆጣጠር፣ ባህላዊ መድኃኒት፣ ሙዚቃ፣ ዳንስና ሥነ ጽሑፍ ይጠቀሳሉ፡፡ በየአካባቢ ላለው ልዩነት እውቅና በመስጠት መቻቻሉን መገንዘብ እንችላለን፡፡ ዶ/ር አየለ በክሪ ‹‹እሺ ይበልጣል ከሺ›› የሚለውን አባባል በማጣቀስ በአካባቢው ማኅበረሰብ መተሳሰብና ስምምነት አማካይነት የዘለቁ የተለያዩ ሥርዓቶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ክርስትና፣ አይሁድና እስልምና ለዘመናት የዘለቀው ባህላዊ የእምነት ሥርዓት ተፅዕኖ አድሮባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ወደ ዝቋላ የሚካሄደው ሃይማኖታዊ ጉዞ በሚከናወንበት ወቅት፣ ሌሎች ባህልን የተመረኰዙ ሥርዓቶችም በዛው አካባቢ ይካሄዳሉ፡፡ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሥርዓቶች እየተዳደሩ ልጅ ለማስጠመቅ፣ ታቦት ለማጀብና የሃይማኖት አባቶች ቡራኬ ለመቀበል የሚገኙ አሉ፡፡ ሁለት ሃይማኖቶች በተመሳሳይ አካባቢ ተቻችለው የሚኖሩት ፀብና ፉክክር ሳያስነሱ ነው፡፡ ነቢዩ መሐመድ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ615 ዓመት ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ሄደው መጠለያ እንዲጠይቁ አድርገዋል፡፡ ከተከታዮቻቸው መካከል ልጃቸው ሩቅያ፣ ኦትማንና ባለቤቱ፣ ኡም ስልማና ባለቤቱ እንዲሁም ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በወቅቱ የአክሱም ሥርወ መንግሥት ክፉ የማይሠራበት እንደሆነ ይታመን ነበር፡፡ የተከታዮችን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ተከትሎ የእስልምና ሃይማኖት በአገሪቱ ተስፋፋ፡፡ የተከበረው ነጃሽ አመዲን መስጅድ ሁለተኛው መካ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ንጉሱ የመሐመድን ተከታዮች ተቀብሎ በማስተናገዱ ነቢዩ መሐመድ አገሪቱ ከጂሀድ ነፃ እንድትሆን አውጀዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የነበሩ ነዋሪዎች የተቀደሰው ስፍራ ሆልቃ ሶፍ ኡመር እንዲዘጋጅም ረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ አይሁዳውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሃይማኖታቸውን የሚያከናውነበት ቦታ እንዲገነቡ አግዘዋል፡፡ ተቀራራቢ ቋንቋና ባህልም ይጋራሉ፡፡

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- እነዚህ ትስስሮች በዚህ አካባቢ ላሉ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሆኑ እሙን ነው፡፡ ትስስሩን እንዴት ይመለከቱታል?

ዶ/ር ኩሱም፡- በኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ ሀብቶች እደነቃለሁ፡፡ የቀን መቁጠሪያው ቀማሪዎች የዘመን አቆጣጠሩ ፈር ይዞ እንዲሄድ ማድረግ ችለዋል፡፡ እንደ ህንድ ባሉ ጥንታዊ ባህል ያላቸው አገሮች በጨረቃ ዑደት ይመራሉ፡፡ የቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት ክንውኖች ማለትም የጸሎት፣ የጾምና የፌስቲቫል ወቅት የሚታወቀውም በዑደቱ መሠረት ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ የኦሮሞ ሕዝብ የጨረቃን እንቅስቃሴ ከሰባት የተለያዩ ከዋክብት እይታ አንፃር በመመልከት በቀን መቁጠሪያ ይገለገላሉ፡፡ ይህም የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል ሲሆን፣ ወደ ደቡብና ሰሜን ባሉ አካባቢዎች የእስልምና ቀን አቆጣጠር ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ያለውን መንፈሳዊ ሕይወት የማነጽ ሥራ ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን መንፈሳዊነት ያጠናከረና ረዥም ዕድሜውን ያረጋገጠም ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጊዜ አረዳድ የተቀመረው ዓመተ ምሕረት፣ ዘመነ ፍጥረትን መነሻው አድርጎ ሃይማኖታዊና አገራዊ ቀን መቁጠሪያ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የልደት በዓል ታኅሣሥ 29 ይከበራል፡፡ የሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በበለጠ ትክክል መሆኑን ያምናሉ፡፡ በሰላምና በኅብረት ከመኖር አንፃርም የዘመን አቆጣጠሩ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የኢትዮጵያውያን ምሁራን የሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) ምልከታ በጊዜ አቆጣጠር ያላቸውን ኃይል ያሳያል፡፡ ጊዜን የሚቆጣጠሩ ያለፈውን ታሪክ ይቆጣጠራሉ፡፡ ያለፈው ጊዜያቸውን የሚቆጣጠሩ ደግሞ ዛሬያቸውንም ተቆጣጥረው ለወደፊቱ ማለም ይችላሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በዚህ የሚሰማው ክብርና በጥንት ሥልጣኔው ያለው ኩራትም በግልጽ ይስተዋላል፡፡

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡-  በእርግጥ በአካባቢው ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ የዘለቀ ተቻችሎ የመኖር ሒደት አለ፡፡ በሌላ በኩል ቅኝ ግዛት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም የፈጠረው ልዩነት አይካድም፡፡ አንድ ቋንቋ በቂ አይደለም የሚል አባባል አለና ልዩነቱ ያለውን ሚና ቢያስረዱን?

ዶ/ር ኩሱም፡- በጎሳና በዘር ያለውን ክፍፍል አልደግፍም፡፡ ያለ ጥርጥር መሰል ክፍፍሎች ከአውሮፓውያን ፈላስፋዎች የመነጩ ጽንሰ ሐሳቦችን የተመረኰዙ ናቸው፡፡ በዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ህንድን ጨምሮ በሌሎችም ቅኝ ግዛት በነበረባቸው ስፍራዎች ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጠባብ ምልከታ አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ላሉ ግጭቶች መነሻ የሚሆነው በቅኝ ግዛት ወቅት ለመፍጠር የተሞከረው ማንነት ነው፡፡ ለምሳሌ ጋይም ክብረ አብ በጥናታቸው እንደሚገልጹት፣ እንግሊዛውያኑ በኤርትራ ብሔርና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ያማከለ ልዩነት የመፍጠር ዓላማ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እንዳሉት ሕዝቦች የተለያየ ባህል ያላቸው ማኅበረሰቦች በመኖራቸው ክፍፍሉ አልተሳካም፡፡ እንደ ሐባብ፣ መንጋ፣ መርያና ቤኒ አመር ያሉ ትግርኛና ዓረብኛ የሚናገሩ ማኅበረሰቦች በአንድ አካባቢ በመቻቻል ስለሚኖሩ ለመከፋፈል አልተቻለም፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ሌሎችም በሃይማኖት፣ በቋንቋና አኗኗር ወጥነት የማይመሳሰሉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ጂቡቲን እንውሰድ፡፡ የአፋር ማኅበረሰብ ወደ አፋርና ኢሳ፣ ማለትም ወደ ዛሬዋ ኤርትራ (የቀድሞው መረብ ምላሽ) እና ኢትዮጵያ ተጉዘዋል፡፡ የኢሳ ሶማሌዎች ደግሞ ወደ ዛሬዋ ሶማሊያ መጥተዋል፡፡ 

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥታት የፈጠሯቸው የብሔር ክፍሎች አንገብጋቢ ጉዳይ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ክፍፍሎች በሕገ መንግሥትም የፀደቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አስተያየትዎ ምንድነው?

ዶ/ር ኩሱም፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጎሳና የብሔር ክፍፍልን በመቃወም አንድ ኢትዮጵያ እንዲኖር ይጣጣሩ ነበር፡፡ አካባቢው እንዲዋሃድ በመፈለግ ከጂቡቲና ኤርትራ ጋር ድርድር አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ አንድነት ተምሳሌትም ሆነዋል፡፡ ቅኝ ግዛትን በመቃወም የአፍሪካን አህጉር ለለውጥ አነሳስተዋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ የነበራቸው ሚናም አይዘነጋም፡፡ ወደ ደርግ ሥርዓት ስንመጣ በኢትዮጵያ ዙሪያ እንዳሉ አገሮች የአውሮፓውያንን ክፍፍል ለመቀበል ተገዷል፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በአንቀጽ 35 (1987) ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚል የተቀመጠው ይጠቀሳል፡፡ ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ያላቸው ሕዝቦች በአንድ ጎራ ይሆናሉ፡፡ ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች፣ 68 ዞኖችና 550 ወረዳዎች ይዘው በሰማንያ ኢትኖ ሊንግዊስቲከ ቡድን ይከፈላሉ፡፡ በተመሳሳይ በጂቡቲ የቤዛቤትና የአምበርትን ጉዳይ በመመልከት የፈረንሣይ አገዛዝ የፈጠረውን ልዩነት ማየት ይቻላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1883 ባህላዊ ሥርዓቶችና በሱልጣን የመመራት ሒደቱ በፈረንሣዮች ሳቢያ ተቋርጧል፡፡ ጂቡቲ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ አፋር፣ ዓረብና ኢሳ ሶማሌ በሚል የብሔር ክፍፍል ነበረ፡፡ የትኛው በቁጥር እንደሚበልጥና የቱ ሥልጣን መያዝ እንዳለበትም ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡ ፈረንሣዮች ከብሔሮቹ ለአንዱ ቅድሚያ በመስጠትና ሌላውን በመንፈግ ሒደት የፈጠሩት የከረረ ልዩነት በቀጣይ ዓመታት የምርጫ ሒደቶችም ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ጂቡቲ ነፃ ከወጣች በኋላ የኢሳ ሶማሌ ጎሳ አባል የሆኑ ሦስት ሺሕ ኢትዮጵያውያን ወደ አገሪቱ ሸሽተው ገብተዋል፡፡ የኦጋዴን ግጭት ሲነሳ ስደተኞቹ 42ሺሕ ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ችግሮቹ የሰዎች የስቃይ መንስኤ ሆነውም ዘልቀዋል፡፡       

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- ሶማሊያ በችግር የተሸበበች አገር ስለመሆኗ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወቃል፡፡ አገሪቱ ካሏት ቅርሶች አኳያ ምን መፍትሔ ይሆናል ይላሉ?

ዶ/ር ኩሱም፡-  በአውሮፓ አገሮች የደረሱበትን ደረጃ ያገኙት ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ በወሰደ ሒደት ነው፡፡ ወደ አፍሪካ ስንመጣ አውሮፓውያን የሕዝቡን ባህል ሳይገነዘቡና ማኅበረሰቡን ሳያማክሩም በጥቂት ሳምንታት ይኼንን ለመፍጠር ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረው የድንበር ክፍፍልም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር አስዋጁ እንደሚሉት፣ በ131 ማኅበረሰቦች ውስጥ 103 ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ድንበሮች ያልፋሉ፡፡ ይህ በአካባቢው ለተንሰራፋው ድህነት፣ ግጭትና የአስተዳዳር ችግር መንስኤ ነው፡ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለውን የሡልጣን አገዛዝ ስንመለከት፣ በግብርናና አርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ ሰዎች በበርበራና በኤደን ባህረ ሰላጤ ጥሩ የንግድ እንቅስቃሴ ነበራቸው፡፡ የተለያዩ ማኅበረሰቦች እርስ በእርስ የሚደጋገፉበት አስተዳደር ነፃነት ሰጥቷቸውም ነበር፡፡ ችግር በሚከሰትበት ወቅት አሪቡ በተባለ ሥርዓት የቀንድ ከብት የመለዋወጥ ባህል በአካባቢው አለ፡፡ አቅመ ደካሞችን መደገፍ የባህላዊው ሕግ መሠረት በመሆኑ ደንቡን የተላለፈ ይቀጣል፡፡ በአካባቢው የእስልምና ሃይማኖት ሥርዓቶችም የራሳቸው ቦታ አላቸው፡፡ ከሱፊዝም የተወሰዱ ሥርዓቶችም በስፋት ስለሚተገበሩ በማኅበረሰቡ መካከል ትስስር ይስተዋላል፡፡ ጣሊያን አሰብን፣ ፈረንሣይ ጂቡቲን፣ እንግሊዝ የኤደን ባህረ ሰላጤን ሲቆጣጠሩ ማኅበራዊ ትስስሩ ላልቷል፡፡ ሀጂ ሀፊዝ ሰይድ መሐመድ አብደላና አልሀሰን ኦፍ ዘ ሳሊህያ ብራዘር ሁድ፣ በእንግሊዝ ላይ የሽምቅ ውጊያ በማወጅ አንዲት ሶማሊያን ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡ የእንግሊዝ ኃይል የሶማሊያን ሃይማኖትና ባህል ማጥፋቱን ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ ሶማሊያ እ.ኤ.ኤ. 1960 ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የእንግሊዝና የጣሊያን አስተዳደር ተፅዕኖዎች ከግምት ሳይገቡ የተዋሃደች ሶማሊያ ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ በቀደመው የፈራረሰ ፖለቲካዊ ሥርዓት የተቃኘ አገር መፍጠር ስህተት ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ነገሮችን ለማሻሻል ሙከራ አድርገዋል፡፡ ቁርዓንን መሠረት ያደረገ ሥርዓት ለመፍጠር ቢሞከርም የቅኝ ግዛት ርዝራዥን ለማስወገድ ጥረት ስላልተደረገ ችግሮቹን ለመፍታት አልተቻለም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት የሶማሊያን ፀጥታና መረጋጋት ለመመለስ የተደረገው ጥረት ያስፈለገውም በተፈጠረው ችግር ሳቢያ ነው፡፡ አሁንም በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈጠሩ ችግሮች በማኅበረሰቡና በአገሪቱ አስተዳደር ያሳደሩት ተፅዕኖ መፈተሽ አለበት፡፡ አገር በቀል የሆኑ ቅድመ ቅኝ ግዛት የነበሩ ባህለዊ ሥርዓቶች ለመልካም አስተዳዳር የነበራቸው አስተዋጽኦም በአንፃሩ ሊታይ ይገባል፡፡

ካሽሚር ኦብዘርቨር፡- ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሌሎችም አጎራባች አገሮች የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተያያዘስ የሚያቀርቡት የመፍትሔ ሐሳብ አለ?

ዶ/ር ኩሱም፡-  ጣሊያን በዓድዋ ድል ከተነሳች በኋላ ሊፈጥሩ የሞከሩትን የኤርትራ ገጽታ ማየት አለብን፡፡ ኤርትራውያን ለዘመናት የነበራቸውን ማንነት እንዲሁም ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር የነበራቸውን ትስስር አላልቷል፡፡ ከጣሊያን አገዛዝ በኋላ፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠልና ከኢትዮጵያ ጋር እስከወዲያኛው ለመዝለቅ በፈለጉ ቡድኖች ለሁለት ተከፍላለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1961 እስከ 1991 በነበረው የሠላሳ ዓመታት ጦርነት ብዙ ኤርትራውያን ከቤተሰቦቻቸው የወረሱት ኢትዮጵያዊ ማንነት ጥያቄ ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡ ኤርትራ ከአህጉሪቱ ትልቁን ወታደራዊ ኃይል መያዟን ክብረአብ ይገልጻሉ፡፡ በርካታ ስደተኞች የሚወጡትም ከኤርትራ ነው፡፡ የሁሉንም ሕዝብ ተሳትፎ በማረጋገጥ አገራቸው እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች በብዛት ሲታሰሩ፣ በግድ ወታደራዊ ኃይል እንዲቀላቀሉ ሲደረጉ ችግሩ ይባባሳል፡፡ በመንግሥት የተቀመጡ የለውጥ ግቦችን ለማሳካት ሕዝቡ እንደሚሠራም ክብረአብ ያስረዳል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2002 ወዲህ ዋርሳይ ይካአሎ ዴቨሎፕመንት ካምፔን በተሰኘ ንቅናቄ ሳቢያ የስደተኞች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በሃይማኖት ረገድም ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች አክሱምን መንፈሳዊ ቤታቸው አድርገው ሲመለከቱ፣ ሙስሊሞች ነጃሺን ይመለከታሉ፡፡ የአገሪቱ አካሄድ ከአገሪቱ የእምነት ሥርዓትና የአኗኗር ዘዬ ጋርም ይጣረሳል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ድህነት የአካባቢው ማኅበረሰብ የስቃይ ኑሮ መንስኤ ሆነዋል፡፡ በድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት መፍትሔ ያሻዋል፡፡ ችግሮቹ የኤርትራን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም በሚጠቅም ንግግር መፈታት አለባቸው፡፡ በሁለቱ አገሮች ያለው ማኅበረሰብ የዘመናት ታሪክና ቅርስ መጋራቱ ይታወቃልና፡፡