Skip to main content
x
የሥነጥበብ ዕርምጃ በጎንደር

የሥነጥበብ ዕርምጃ በጎንደር

ጎንደር ከተማ ሄዶ የፋሲል ግንብን ሳይጎበኝ የሚመለስ ሰው አለ ማለት ዘበት ነው፡፡ በጎንደር ቆይታችን ወቅት ከተለመደው በተለየ ወደ ፋሲል ግንብ የሚሄዱ በርካታ ሰዎች ስንመለት አዲስ ነገር ይኖር ይሆን ብለን ጠየቅን፡፡ ወደ ግቢ ከሚሄዱት ሰዎች አብዛኞቹ የባህል አልባሳት የለበሱ ሲሆን፣ በባጃጅና በቤት መኪናም የሚጓዙ ነበሩ፡፡ ወደ ግንቡ የበለጠ ስንቀርብ ከአቅጣጫው የሠርግ ዘፈን ይሰማ ጀመር፡፡ ወደ ግንቡ ያመሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች ሠርገኞች መሆናቸውንም ተገልጽጾልን በተለይም በሠርግ ወቅቶች የፋሲል አቅራቢያ በሙሽሮች ሚዜዎቻቸውና አጃቢዎቻቸው እንደሚጨናነቅም የከተማዋ ነዋሪዎች አስረዱን፡፡

ሠርጋቸውን በታሪካዊው ግንብ ውስጥ በማካሄድ የዕድሜ ልክ ትዝታ ለማትረፍ በቦታው ከተገኙ ሰዎች በቅርብ ርቀት ሌላ ትኩረታችንን የሳበ አካባቢ አስተዋልን፡፡ ወደ ፋሲል ግንብ ከሚያስገባው ዋና በር አቅራቢያ የአላፊ አግዳሚን እይታ የሚስብ ቤት አለ፡፡ ቤቱ በሰማያዊ ዳስ የተሸፈነ ሲሆን፣ መግቢያው ላይ በኖራና በሲሚንቶ የተሠሩ ቅርፆች ይገኛሉ፡፡ ከቅርፆቹ መካከል አንዳንዶቹ ተጠናቀዋል፡፡ የተቀሩት በከፊል ያለቁና በጅማሮ ያሉም ናቸው፡፡ ወደ ቤቱ ስንጠጋ አንድ ወጣት እጁ ላይ ያለውን ኖራ እየጠራረገ እንድንገባ በፈገግታ ጋበዘን፡፡ አቤኔዘር መንግሥቱ ይባላል፡፡ ቀራፂና ሠዓሊ ነው፡፡ ቤቱ መኖሪያው፣ ስቱዲየው፣ ሥራዎቹን የሚያሳይበትና የሚሽጥበት ጋለሪውም ጭምር ነው፡፡ ያገኘነው የአፄ ቴዎድሮስን ምስል በኖራ በትልቁ እየቀረፀ ነበር፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ እግር ሥር እየቀረፃቸው የነበረ አንበሶችን ራቅ ቀረብ እያለ ይመለከታል፡፡ መስተካከል አለበት ብሎ ያመነውን ቦታ በድጋሚ ይቀርፃል፡፡ ለሥራው የሚጠቀምባቸው ኬሚካሎች ጠረን ጠንካራ በመሆኑ ወደቤት እንድንገባ ጋበዘንና ተከተልነው፡፡

በቤቱ የተለያዩ ክፍሎች ሥዕሎች ተሰቅለዋል፡፡ ቤቱ ወደ ስቱዲዮነት ከመለወጡ በፊት በከተማው የታወቀ ባህላዊ ሬስቶራንት ነበር፡፡ ሬስቶራንቱ ይተዳደር የነበረው በአቤነዘር እናት ሲሆን፣ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ አቤኔዘር ቤቱን ወደ ጋለሪና ሬስቶራንት ለወጠው፡፡ ቤቱን በባህላዊ ምግቦቹ የሚያውቁ ደንበኞችና የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎች ያዘወትሩትም ጀመር፡፡ አቤኔዘር እንደሚለው፣ ጋለሪውና ሬስቶራንቱ ተጣምሮ መሄዱን ቢወደውም ከጥቂት ዓመታት በላይ ሊገፋበት ስላልቻለ ቤቱን ስቱዲዮ ብቻ አደረገው፡፡ ሥነጥበብን ለማሳየት ምቹ ቦታ በሌለበት ጎንደር የተወለደው አርቲስቱ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከአቢሲኒያ የሥነ ጥበብና ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ ወደ ጎንደር ተመልሶ መሥራት ጀመረ፡፡ ሆኖም በሥዕልና ቅርፃ ቅርፆ የሚታይባቸው ጎለሪዎች አለመኖራቸው ያሳስበው ነበር፡፡ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን በስቱዲዮዋቸው ከማሳየትና በሆቴሎች ወይም የስጦታ ቁሳቁስ መሸጫዎች ከማቅረብ የዘለለ አማራጭም የላቸውም፡፡

አቤኔዘር እንደሚለው፣ በዘርፉ ያለውን ክፍተት ከግምት በማስገባት የሠዓልያን፣ ቀራፅያንና ዕደጥበብ ባለሙያዎች ማኅበር ተቋቋመ፡፡ የሚፈልጉትን ዓይነት ቦታ ለማግኘት መቸገራቸውን የሚገልጸው ባለሙያው፣ ‹‹እንደ ጎንደር ባለ የቱሪስት መዳረሻ የሆነ ከተማ የሥነጥበብ ማዕከል አስፈላጊ ነው፤› ይላል፡፡ እሱ እንደ አማራጭ የወሰደው ሥራዎቹን ለመመልከትም ይሁን ለመግዛት የሚፈልጉ ሰዎችን ወደ ስቱዲየው መጋበዝ ቢሆንም፣ አብዛኛው አርቲስት የሚገኝበት አማካይ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው ይገልጻል፡፡

‹‹አርቲስቶች ቤታቸው እየሠሩ ቤታቸውን ይሸጣሉ፡፡ አንዳንዶች ወደ ሆቴሎች ሄደው ይሸጣል፡፡ ከዚህ በተለየ መደበኛ የሥነጥበብ ቦታ ያስፈልገናል፤›› ይላል፡፡ ጎንደርን የሚጎበኙ ሰዎች፣ ከፋሲል ግንብ፣ ከደብረ ብርሃን ሥላሴና ሌሎችም ጥንታዊ ቅርሶች ባሻገር ያለንበትን ዘመን የሚገልጽ ቦታ እንዲጎበኙ ከተፈለገ የሥነ ጥበብ ጋለሪ መገንባት እንዳለበትም ያክላል፡፡ ‹‹ጎብኚዎች የቀደመውን ትውልድ ታሪክ ከተመለከተ በኋላ አሁን ያለው ትውልድ ምን እየሠራ ነው? የሚለውን ጥያቄያቸው ምላሽ የሚያገኙበት ቦታ ያስፈልጋል፤›› ሲልም ያስረዳል፡፡

ወጣቱ አርቲስት በሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ የራሱን አመለካከት ከማንፀባረቅ ጎን ለጎን ጎንደርን የሚያሳዩ ሥራዎች ላይም ያተኩራል፡፡ ሥነጠቢባን በዚህ ረገድ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ያምናል፡፡ ባለሙያዎች ሥራቸውን አልፎ አልፎ እንዲያሳዩ ዕድል ከመስጠት ባሻገር የሥራቸው ጥበባዊ ዋጋ ተከብሮ በቋሚነት የሚያቀርበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡ ጥበቡ ዋጋ ተሰጥቶት ሲከበር ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን አዘውትረው ለሕዝቡ ለማድረስ እንደሚበረታቱም ይናገራል፡፡

‹‹ሥዕል፣ ፎቶግራፍ ወይም ቅርፅ ለማየት በሚያስችል ብርሃንና አቀማመጥ የተዘጋጀ ቦታ ያስፈልጋል ጥበቡም መከበር አለበት፤›› የሚለው አቤኔዘር፣ ወጣት የጎንደር አርቲስቶች ሁኔታዎች እንዲለወጡ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመንግሥትና በማኅበረሰቡም መደገፍ እንዳለበት ያስረግጣል፡፡

ባለሙያው ወደ ስቱዲዮው ሄደው ሥራዎቹን ከሚገዙ ሰዎች በተጨማሪ፣ ሥዕሎቹን ለሆቴሎችም በሽያጭ ያቀርባል፡፡ ጎንደር ውስጥ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲዘጋጁም ሥዕሎች ወይም ቅርፃ ቅርፆችም ይሠራል፡፡ አራት ሜትር በስድስት ሜትር ርዝመት ያለውና አፄ ቴዎድሮስን ከአራት አንበሶች ጋር የሚያሳየውን ቅርፅ እየሠራ ያገኘነው ጎንደር ከወራት በፊት ላስተናገደችው የከተሞች ፎረም ነበር፡፡

ጥበባዊ ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ቀርበው ምላሽ ካልተሰጠባቸው አርቲስቱ ጋር መቅረታቸው ብዙ ርቀት እንደማያራምድ የሚናገረው ወጣቱ፣ የሥነጥበብ ተደራሽነት ሲኖር የሕዝቡ አመለካከትም አብሮ እንደሚለወጥ ያምናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በከተማው ያሉ አርቲስቶች በነፃነት ሥራቸውን ሲሠሩ፣ ለሥነጥበብም ማኅበረሰቡ የሚሰጠው ዋጋ ብዙም አለመሆኑን ያክላል፡፡ ‹‹እኔ የምሠራው ሥራ ለወደፊት ስሜን የምተክልበት ነው፡፡ አሁን ከማንኛው ጥቅም በበለጠ የወደፊት አስባለሁ፤›› ይላል፡፡ በሥራዎቹ ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት ከቀረበ በኋላ ከኅብረተሰቡ የሚጠብቀውን ምላሸ አለማግኘት ተነሳሽነቱን እንደሚቀንስም ያስረዳል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ አንድ ቅርፅ ለመሥራት የሚወሰደውን ጊዜና የሚያስፈልገውን ጥበብ ስለማይገነዘብ ለሥራዎቹ ቦታ አይሰጥም፤›› የሚለው አርቲስቱ ጎንደር በኢትዮጵያ የሥነጥበብ ታሪክ ከነበራት ቦታ አንፃር አሁን ያለው ትውልድ ሥራዎች በጉልህ እንደማይታዩ ያስረዳል፡፡ በተለይም በጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ያለው አስገራሚ ሥነጥበብ ታይቶ የአሁኑ ትውልድ የት ደረሰ? ለሚለው ምላሽ የሚሰጥ አለመኖሩን ያክላል፡፡ በእርግጥም ወጣቶቹ የድርሻቸውን ለመወጣት ቢጣጣሩም ድጋፍ ካለገኙ ብዙ ርቀት መሄድ እንደማይቻልም በአጽንኦት ይገልጻል፡፡