Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

አንዲት ወገናችን አንዱ የአሜሪካ ከተማ ምግብ ቤት ትከፍታለች፡፡ በፊት አልፎ አልፎ የዘመድና የጓደኞች ዝግጅት ላይ ምግብ በመሥራት ታግዝ ስለነበረ፣ በዚያውም አንቺ እኮ ምግብ ቤት ብትከፍቺ ያዋጣሻል ስለተባለች ነበር የከፈተችው።

እናም ምግብ ቤት መክፈቷን ለወዳጆቿ ታበስራለች። ከተከፈተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም እነዚያው “ማኅበርተኞቿ” ሊደግፏትና ምግብ ቤቷን ሊመርቁላት ተሰባስበው ይሄዳሉ። ሰባት ያህል ቢሆኑ ነው። ከዚያ ወዲያ ያለውን ከራሳቸው እንከታተል።

“ገባን፣ አነስ ያለችና እስከ 25 ሰው የምትይዝ ምግብ ቤት ነች፣ ስንገባ ብቻዋን ነበረች፣ በመምጣታችን ደስ አላት፣ አስተናጋጅ እንዳላገኘችና ብቻዋን እንደምትሠራ ነገረችን፣ እኛም ብዙ እንዳናስቸግራት፣ ተመሳሳይ ጥብስ ነገር በዛ አድርጋ እንድትሠራለን ነገርናት።

‹‹አስተናጋጅም፣ ምግብ አዘጋጅም ራሷ ነበረች፡፡ ለእኛ ምግብ ልትሠራ ገብታ በመቅረቷ፣ ከእኛ በኋላ የመጡ ሦስት ያህል ፈረንጆች የሚታዘዛቸው አልነበረም፡፡ አሥር ደቂቃ ያህል ዝም ብለው ሲቀመጡ ከመካከላችን አንዷ ተነስታ፣ ይቅርታ ጠይቃ ታዘዘቻቸው፣ . . .ጥብስና በያይነቱ ነበር ያዘዙት፡፡ . . . ጓደኛችን ልትነግራት ውስጥ ገባች፣ ገና የእኛን ሥጋ እየከተፈች ነው። . . . በኋላ ተነጋገርንና ከመካከላችን ሁለት ሰዎች ሊያግዙዋት ገቡ፡፡ ብርጭቆና ውኃ የት እንዳለ ጠይቀን፣ እኛው ሌሎቹን ውኃ በማቅረብ አስተናገድን።

‹‹ዝርዝሩ ይቆይና፣ የእኛ ምግብ ተሠርቶ እስኪወጣ አንድ ሰዓት ያህል ወስዷል፡፡ የሰዎቹማ፣ ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ነው የመጣላቸው። እሷም ልታቀርብ ስትመጣ ወጥ ወጥ መሽተቷ አልቀረም። ልንስተናገድ መጥተን፣ አስተናጋጅና ምግብ አቅራቢ ሆነን ቀረን።

‹‹ቢሆንም ግን አሳዘነችን። በኋላማ በቃ እኛም እየሄድን ከምንሳቀቅና እሷንም ከምናሳቅቃት ባንሄድ ይሻላል ብለን ይኸው ከሄድን ቆየን። እኛም ደውለን፣ እሷም ደውላ አታውቅም፣ እንዴት እንደሆነችም እንጃ . . .››

ይህን ታሪክ ስሰማ የብዙ ወገኖቻችን አጋጣሚ መሆኑ ተሰማኝ፣ ከብዙ ቦታ ብዙ ታሪክ አውቃለሁና። ሰዎች ተደላድለው ይሠሩ የነበረው ሥራ ትተው “የራሳቸው ንግድ” ለመክፈት መሞከራቸው በሐሳብ ደረጃ ጥሩ ቢሆንም፣ ከጥሩ የንግድ አማካሪ ማጣትና  ከዝግጅት ጉድለት፣ እንዲሁም በትክክል ምን ለማድረግ እንደታሰበ ካለማወቅ ሰዎች ያላቸውን ተቀማጭ ሁሉ በትነው፣ በመጨረሻም ንግድ ቤቱን ዘግተው ሲቀመጡ ማየት አሳዛኝ ነው።

ምግብ ቤት ሰዎች ከፈቱ ስላሉን ብቻ አይከፈትም። ጓደኛ ተማምኖም አይከፈትም፣ ገንዘብ እጅ ላይ ስላለ ብቻም አይከፈትም። ምግብ መሥራት ጎበዝ ስለሆንን ብቻም አይከፈትም። ድንገት የተለቀቀ ቤት አለ ስለተባለ ብቻም አይከፈትም። ቢዝነስ አለው/አላት ለመባል ብቻም አይከፈትም።

ንግድ የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው። ሙያ አንዱ ነው፣ መስተንግዶ ሌላው ነው፣ ሒሳብ አያያዝም ወሳኝ ነው፣ ማስተዳደር (ማኔጅመንት) ማወቅ ግዴታ ነው፣ ንግድን ማስተዋወቅ (ማርኬቲንግ) አንገብጋቢ ነው፣ መነሻ ገንዘብ (ካፒታል) ወሳኝ ነው። ከእነዚህ አንዱ ከጎደለ ጣሪያ የሌለው ቤት ማለት ነው። ሁሉንም ደግሞ አንድ ሰው ላያውቀው ይችላል፡፡ በሁሉም ቦታ በቂ ዕውቀት ቀድሞ መገብየት፣ ሙያ ያለውንም ሰው ቀጥሮ ማሠራት ግድ ይላል። አለበለዚያ በስሜትና በግፊት ንግድ ተጀምሮ፣ እንኳን አዲስ ገንዘብ ሊያመጣ፣ ያለውንም ወስዶ ባዶ እንዳያስቀር፣ ለጤና ጉድለትም እንዳይዳርግ ያሠጋል።

የምንተማመንባቸው ጓደኞቻችን፣ ቤተሰቦቻችንና ማኅበርተኞቻችንም “ስንጨናነቅ ላለማየት” ቀስ በቀስ መቅረታቸው አይቀርም። በማይሆን ሁኔታ ሰዎች የለፉበትን ገንዘብ ሲያጡ ያሳዝናል።

(ቴዎድሮስ ዳኜ፣ በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው)