Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

እሺ ታሪካችን ይጥፋ፡፡ ወንዞቹም ይድረቁ፡፡ አፍሮ ተራሮችን ተረክበን ራሰ በራ ስናደርጋቸው የማንም ጣት ወደማንም አጠቆመም፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ አበሳ ተጋርጦብን ዝምታ ላይ ነን፡፡ አሁን አቢጃታ ምን ላይ ነው፡፡ የእነኛ ባህር ማዶ አቋርጠው የሚመጡ ወፎች ማረፊያ የብስ እየሆነ ነው፡፡

ጣናንም አረም ወረረው የሚለው መርዶ ቀለል ያለ ዜና ሆኖ ቢሞት ይዞን በሚሞተው ተፈጥሮ ላይ ዳተኝነት እያሳየን ነው፡፡ እኔ ግን ጣናን ባሰብሁ ጊዜ የዝምታው አለመሰበር ምንድን ነው? እላለሁ፡፡ እንዴት ሐይቅ ተረክቦ ሜዳ ለማስረከብ የተዘጋጀ ትውልድ እንሆናለን፡፡ አረም የወረረውን ጣናን እውን የእኔ ሀገር ገበሬ ሊያውም የጣና ዳር ጎበዝ ያዝ እንግዲህ የሚለው ካገኘ ሊያቅተው ነው፡፡

ጥናቶች በዙ፡፡ ምርምሮች በዙ፡፡ ውጤታቸውን ካልተገበርናቸው ፋይዳቸው ምንድን ነው? የዶክተሮቹ ጣናን ተከትሎ ደም መትፋት ውሎ አድሮ፣ ነው እንዴ እየተባለ የሚታለፍ ችግር ከሆነ እነሱስ ስለምን ደከሙ? ለመሆኑ ጣናን ያክል ሐይቅ በዚህ አረም ፈተና ውስጥ ሲገባ እያንዳንዳችን ተናግረን ነበር ብለን የምናልፈው ዋዛ ፈዛዛ ጉዳይስ ነው?
እንዴት ዓባይን ተማምና ቢሊዮን ብር ግድብ ላይ የምታውል ሀገር የዓባይ ምንጭ የሆነው የበረከት ሐይቅ አደጋ ሲጋረጥበት ችላ አለች? ዜጎቿስ?

እሺ እኛ ሐይቅ ሜዳ ማድረግ ልማዳችን ነው፤ ዓለም እንዴት ዝም ይለናል? ልጆች ብርጭቆ እንዳይሰብሩ በወላጆቻቸው የሚጠበቁት እኮ ወላጆች ክፉ ስለሆኑ ሳይሆን ብርጭቆው የልጆቻቸው ሀብትም ስለሆነ ነው፡፡

 እናስ መዘገብኩት ያለው ዩኔስኮ የብዝኃ ሕይወት ሀብቱን የሚገዳደር ፈተና ሲመጣ እንደኛው ሊመለከት ከሆነ ይሄ ከእድር መዝገብ በምን ተለየ? የእድርስ መዝገብ ሟችን በቋሚ እየቀየረ ይኖር የለ፡፡ አሁንም ለስብሰባ፣ ምን እናድርግ ብሎ ለመምከር፣ መፍትሔ ፍለጋ ለመባዘን ጊዜ የለንም፡፡ የደንቢያን ዳርቻ የጣና ክፍል እንቦጭ ወሮት ረግረግ መስሏል፡፡ ያለ ቦታው የገባው አረም የሚያጠፋውን ብዝኃ ሕይወት መጀመሪያም በወግ አለየንውምና ከወጪ ቀሪ ብለን ተፈጥሮን ባንመዝን እንኳን ያለን ሀበት ነበረን ለማለት አፋፍ ላይ ስንቆም መፍጠን ይኖርብናል፡፡

ጣና አፋፍ ላይ ነው፡፡ ገደሉ ቢርቅም ጣና ለብቻውን የሚገባበት አይደለም፡፡ አብረን እንገባለን፡፡ አብረን እንሰበራለን፡፡ እንዴት ነው የዝምታው መጠን ልኬት፡፡ ማን መጦ አቤት ሊል? ማን ቀዝፎ ጣናን ሊታደገው ነው የምንጠብቀው? ድርቅ አይተናል፡፡ ሲርበን እህል ተረድተናል፡፡ ተራሮቻችንን መንጥረን ዝናብ ሲፈልግ የሚመጣባት ሳይፈልግ የሚቀርባት ሀገር ተረክበናል፡፡ ሐይቅ ግን የሚረዳን የለም፡፡ በስንዴው ማዳበሪያ ተጭኖ የሚመጣ ተፈጥሮ አይደለም፡፡ ዓሣውን እንረዳዋለን፡፡ ዓሣ ማስገሩን ቢያስተምሩን ግን ሐይቁ ከሌለ ምኞት ነው፡፡ ያለንን እያጣን ነው፡፡ ድሮም ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነውና፡፡

ሔኖክ ሥዩም በፌስቡክ ገጹ እንደጻፈው