Skip to main content
x
የቀድሞ ተፋላሚዎች በኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

የቀድሞ ተፋላሚዎች በኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙዋይ ኪባኪ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ለኬንያ ፕሬዚዳንትነት ሲፋለሙ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡ ሁለቱም እ.ኤ.አ. በ2013 ምርጫ የተሳተፉ ሲሆን፣ በኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊነት ምርጫው ተጠናቋል፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2007 ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ሚስተር ኦዲንጋ በሙዋይ ኪባኪ የመሸነፋቸውን ውጤት ባለመቀበላቸው በተነሳ ብጥብጥ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ600 ሺሕ በላይ ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ኡሁሩ ኬንያታና የፖለቲካ አጋራቸው ዊልያም ሩቶ ብጥብጡን አቀነባብረዋል ተብለው ውጤት ባይገኝበትም፣ በዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) ቀርበውም ነበር፡፡

የቀደመ ሰላም የሌላቸው ሁለቱ ተፋላሚዎች በዘንድሮው ምርጫም ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ተገናኝተዋል፡፡ በኬንያ 19 ሚሊዮን ያህል መራጮች የመረጡ ሲሆን፣ ውጤቱም በኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ይገለጻል፡፡ ሆኖም ምርጫው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሥጋት ያጠላበት ነው፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው የምርጫ ውጤቱ የሕዝብ አመፅ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንት ኬንያታም በምርጫው ዋዜማ ባደረጉት ንግግር፣ ሕዝቡ ውጤቱን በሰከነ መንፈስ እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡ 19 ሚሊዮን መራጮችንም፣ ‹‹ምርጫውን በሰላም እንጨርሰው፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ኬንያ ነፃነቷን ከእንግሊዝ ከተቀዳጀች በኋላ የመጀመርያው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆሞ ኬንያታ ልጅ የ55 ዓመቱ ኡሁሩ ኬንያታ በዘንድሮ ምርጫ የሚወዳደሩት ለሁለተኛ የፕሬዚዳንትነት ዘመን ነው፡፡ ተቀናቃኛቸውና የኬንያ የመጀመርያው ምክትል ፕሬዚዳንት ጃራምጊ ኦጊንጋ አዲንጋ ልጅ የሆኑት የ72 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ አሸናፊነቱ ተሳክቶላቸው ባያውቅም፣ ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ተሳትፈዋል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለረዥም ጊዜ ተፋላሚ ሆነው የከረሙት ዕጩዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎችን በሰላማዊ መንገድ አጠናቀው አያውቁም፡፡  በተለይም ሚስተር ኦዲንጋ በነበሩ ምርጫዎች ሁሉ ምርጫ መጭበርበሩን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡ በምርጫ ዋዜማና ማግሥትም በኬንያ ብጥብጥና ሞት ሳይሰማ አልታለፈም፡፡ እ.ኤ.አ. የ2013 ምርጫ በኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊነት መጠናቀቁን የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ሲገልጽም፣ እንደ እ.ኤ.አ. 2007 ሞትና መፈናቀል ጎልቶ ባይከሰትም፣ ከችግር የፀዳ አልነበረም፡፡

የአሁኑ ምርጫ ከመከናወኑ ሳምንት አስቀድሞም ከፍተኛ የምርጫ አስፈጻሚ ባለሥልጣን ተገድለዋል፡፡ ይህም ሆነ ተብሎ ምርጫውን ለማጭበርበር የተቀነባበረ ነው ተብሏል፡፡ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ሕዝባቸውን የጠየቁት በምርጫ ሰበብ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም ነው፡፡ ‹‹መርጣችሁ ወደ ጎረቤታችሁ ቤት ሂዱ፡፡ ጎረቤታችሁ ከየትም ይምጣ ከየት፣ ብሔሩ ከየትኛውም ቢሆን፣ ቀለሙ ወይም ሃይማኖቱ ከእናንተ የተለየ ቢሆንም ልዩነት አትፍጠሩ፣ ተጨባበጡ፣ ያላችሁን ተካፍላችሁ ብሉ፣ ውጤቱንም በትዕግሥት እንጠብቅ፡፡ ኬንያ ከምርጫው በኋላም ለዘለዓለም ትኖራለች፤›› ሲሉ ስለሰላምና አንድነት ሰብከዋል፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ናሽናል ሱፐር አሊያንስ መሪና የፕሬዚዳንት ኬንያታ ተቀናቃኝ ራይላ ኦዲንጋ በበኩላቸው፣ ምርጫው ይጭበረበራል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በናይሮቢ ኪቤራ መንደር ምርጫ ካካሄዱ በኋላ ባደረጉት ንግግርም፣ ‹‹በብዛት ወጥተን እንምረጥ፡፡ ምርጫ ካለቀ በኋላ ማታ በናይሮቢ ኡሁሩ ፓርክ እንገናኝና ውጤቱን እንጠባበቅ፤›› ብለዋል፡፡

በሰሜን ናይሮቢ ምርጫ ያከናወኑት ኡሁሩ ኬንያታ ደግሞ፣ ‹‹ተወዳዳሪዎቼ ድምፅ ብናጣም የሕዝቡን ድምፅ እናክብር፡፡ በራሴ በኩል ሕዝቡ የሚሰጠውን ድምፅ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በጋራ ማነፅ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

በምርጫ ውዝግብ ሳቢያ የብሔር ግጭት በማያጣት ኬንያ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2007 ምርጫ ከተከሰተው በብሔር ተከፋፍሎ ድምፅ የመስጠትና የመገዳደል ልምድ እ.ኤ.አ. በ2013 መሻሻል ቢኖርም፣ ተፅዕኖው በዘንድሮው ላይ ታይቷል፡፡ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም፣ ኬንያውያን ምርጫውን በእርጋታ እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የምታደርጉት ምርጫ ኬንያን ወደ ኋላ ይመልሳታል ወይም አንድ ያደርጋታል፡፡ የወደፊቷን ኬንያ በፍርኃትና በመከፋፈል አታደብዝዟት፣ በተስፋና በአንድነት ኑሩ፤›› ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ የኬንያታም ሆነ የኦዲንጋ ቤተሰቦች እንዲሁ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ነበሩ፡፡ በኬንያ ነፃነት ታሪክ ውስጥም የሥልጣን ሽግግሩ በምርጫ ቢሆንም፣ በቤተሰብ መካከል ያጠነጠነ ነው፡፡ ይህ አካሄድ የፈጠረው የብሔር መከፋፈልም ዛሬ ድረስ ይታያል፡፡ የፀብ መነሻም ነው፡፡  በአሁኑ ምርጫ አመፅ ሊነሳ ይችላል በማለት 180 ሺሕ የፀጥታ ኃይሎች በመላ አገሪቱ ተሰማርተዋል፡፡

በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ስምንት ዕጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ቀልብ የሳቡት ደግሞ የቀድሞ ተቀናቃኞቹ ኬንያታና ኦዲንጋ ናቸው፡፡ ለማሸነፍም 50 ሲደመር አንድ ይጠበቃል፡፡ ከ47 ካውንቲዎች 24 ካውንቲዎችን ማሸነፍም እንዲሁ፡፡ በምርጫው ስድስት የተለያዩ የምርጫ ካርዶች ቀርበዋል፡፡ ለፕሬዚዳንትነት፣ ለብሔራዊ ምክር ቤት፣ ለሴኔት ተወካዮች፣ ለአስተዳዳሪዎች ሴኔትና ለአገሪቱ ፓርላማዎች ናቸው፡፡

በፓርላማ ከሚኖረው 47 መቀመጫ 16 የሴኔት መቀመጫ ለሴቶች የተያዘ ነው፡፡ በስድስቱ የምርጫ ዘርፎች 14 ሺሕ ዕጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ 45 በመቶ የሚሆነው መራጭም ከ35 ዕድሜ በታች ነው፡፡

ኬንያታ እ.ኤ.አ. በ2013 የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ከያዙ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አምስት በመቶ ቢያድግም፣ ኬንያውያን ዕድገቱ አይታየንም ይላሉ፡፡ አስተዳደሩንም ብዙ ገንዘብ ተበድሯል በማለት ይወቅሳሉ፡፡ ፖለቲካል ሳይንስና ኢኮኖሚክስ ያጠኑትና በፋይናንስ ሴክተር ከተሰማሩ ቤተሰቦች የተገኙት ኬንያታ ግን፣ ለመሠረተ ልማት የሚወሰድ ብድርን ከዕድገት ጋር ያያይዙታል፡፡ የ72 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ እ.ኤ.አ. በ1982 በወቅቱ ፕሬዚዳንት ዳኔል አራፍሞይ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገው ከታሰሩ በኋላ፣ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ዕውቅና ያተረፉ ናቸው፡፡ ሆኖም ከአንዱ ፓርቲ ወደሌላው የሚቀየሩ በመሆናቸው የሥልጣን ጥመኛ አስብሏቸዋል፡፡ አምባገነንነትን የሚዋጉ ዴሞክራት ናቸው ቢባሉም፣ ሥልጣን ለማግኘት ያገኙትን ድንጋይ የሚፈነቅሉም ይባላሉ፡፡ በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ያጠኑ ሲሆን፣ በኬንያ ለረዥም ጊዜ በእስር ከቆዩ ሰዎችም ከቀዳሚዎቹ ይመደባሉ፡፡

ፎርብስ እ.ኤ.አ. በ2015 እንዳሠፈረው ኬንያታ በአፍሪካ ከሚገኙ የመጀመርያዎቹ 30 ቱጃሮች አንዱ ናቸው፡፡ በሪል ስቴትና በፋይናንስ ሴክተር የተሰማሩ ሲሆን፣ ኦዲንጋ ደግሞ በኬንያ ከሀብታም ደረጃ ይመደባሉ፡፡ የፈሳሽ ሲሊንደር ጋዝ አምራች ድርጅትንም ይመራሉ፡፡ ፔትሮሊየም በማስመጣትና በማከፋፈልም ይሠራሉ፡፡

ኬንያታ የኩኩዩ ብሔረሰብ ተወላጅ ሲሆኑ፣ ኦዲንጋ ደግሞ ሉዎ ናቸው፡፡ በኬንያ አልረግብ ያለውና በብሔር ላይ የተመሠረተው ምርጫ ሁሌም በሕዝቡ መካከል አለመተማመንና አመፅ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉትም ሆነ በንግድ ከዚህ የፀዱ አይደሉም፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሌሎች ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ ቢሆንም፣ ፅንፍ የረገጠ ብሔርተኝነቱ ሕዝቡን ባለመተማመን ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡ ይህም ምርጫ በመጣ ቁጥር ሥጋት ነው፡፡ የዘንድሮ ምርጫ ግን ከዚህ የፀዳ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል፡፡ በኬንያ በአዲሱ የምርጫ ሥርዓት ትንሽ መደናበር ከመፈጠሩ በቀር፣ ለኅትመት እስከገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ ከወትሮው የተለየ ድርጊት አልታየም፡፡