Skip to main content
x
የተሳሳቱ መረጃዎች የሕዝቡን ትስስር አያናጉ!

የተሳሳቱ መረጃዎች የሕዝቡን ትስስር አያናጉ!

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘመኑ መነጋገሪ ከሆኑ ዓበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ሐሰተኛ ወሬ (Fake News) ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ በየቀኑ በሚፈበረኩ ሐሰተኛ ወሬዎች ምክንያት ሰዎች የተለያየ ድምዳሜ ላይ በመድረስ ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተጋነኑና አማላይ በሆኑ ሐሰተኛ ወሬዎች አቅጣጫ የሚያስቀይሩ ኃይሎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የእነዚህ ዋነኛ ዓላማ የፖለቲካ ወይም የፋይናንስ ጥቅም ለማግኘት ሲሆን፣ በየቀኑ ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ሐሰተኛ ወሬዎች ያሠራጫሉ፡፡ ታዋቂ የሆኑ ዓለም አቀፍ መደበኛ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በእጅጉ እየተቸገሩበት ያለው ይህ አሳሳቢ ጉዳይ፣ በማኅበረሰቦች ውስጥም አስከፊነቱ እየገነነ መጥቷል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ኃላፊነት በጎደላቸው ወገኖች የሚሠራጩ ፕሮፓጋንዳዎች በሐሰተኛ ወሬ ሲታጀቡ፣ አደገኛ ከመሆናቸው የተነሳ ግጭትም ይቀሰቅሳሉ፡፡ የተረጋጋ ማኅበራዊ ትስስርን ያናጋሉ፡፡ ይህ ችግር በአገራችን አድማሱ እየሰፋ ነው፡፡ ዝም ከተባለ አደገኛ ነው፡፡

በመሠረቱ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተፈጥሯዊ በመሆኑ፣ ይህ መብት መቼም ቢሆን ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ፅኑ አቋማችን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን መብት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እየተተረጎመ የሕዝብን የጋራ እሴት ሊጋፋ አይገባም፡፡ መብቱ በራሱ ግዴታን ጭምር የሚያካትት በመሆኑ ሥልጡን ለሆነ የመረጃ ቅብብል ማዋል ካልተቻለ ከዴሞክራሲ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ያጣላል፡፡ ሰዎች በነፃነት መብታቸውን ማጣጣም የሚችሉት ሌሎችም በዚያው መንገድ እንዲጠቀሙበት ዕድሉ ሲመቻች ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን እየታየ ያለው በተለይ ፌስቡክን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ ዜናዎችን በማሠራጨት አደገኛ አዝማሚያዎችን መፍጠር ነው፡፡ ሐሳብን ሌላ በሐሳብ መሞገት የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ሲሆን፣ የተለያዩ ሐሳቦች በመስተናገዳቸው ተጠቃሚው ሕዝብ ነው፡፡ የተሳሳቱ መረጃዎች በብዛት ሲሠራጩ ግን ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ ይከታሉ፡፡ በዕለታዊ እንቅስቃሴው ላይ ለመወሰን ይቸገራል፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎች እንደ እውነት እየተወሰዱም መተማመን እንዲጠፋ እያደረጉ ነው፡፡

ሐሰተኛ ወሬዎች የራሳቸውን ዓላማ ባነገቡ ወገኖች አማካይነት በስፋት ሲሠራጩ ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ ቋንቋንና የመሳሰሉ ትስስሮችን ስለሚነኩ በቀላሉ ለደም አፋሳሽ ግጭት ይዳርጋሉ፡፡ ለጊዜው አሥጊነታቸውን ጎልቶ ባይታይ እንኳን ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ ቦምቦች ይሆናሉ፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ በግዴለሽነትና በጥራዝ ነጠቅነት የሚሠራጩ ሐሰተኛ ወሬዎች አድማሳቸው እየሰፋ ሲሄድ ለማመን የሚከብዱ አደጋዎችን ያስከትላሉ፡፡ ነገ በታሪክ ተጠያቂ የሚያስደርጉ አደገኛ ድርጊቶችን በእንጭጩ አለመቅጨት የሚያስከፍለው ዋጋ ሊተመን የማይችል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች ሐሳቦችን ሲለዋወጡ የሚታወቁበት ጨዋነት እየጠፋ ዘርን፣ እምነትን፣ ባህልን፣ የፖለቲካ አቋምንና መሰል ልዩነቶች ላይ ያነጣጠሩ አስከፊ አስተያየቶችን መስማት እየተለመደ ነው፡፡ የአደባባይ ሰው ሆነው ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለማካፈል የሚፈልጉ ሰዎችን በስድብ በማስበርገግ የሐሳብ ነፃነትን የሚጋፉ ወገኖች፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጥረው ዘረኝነትን ሲሰብኩ መስማት ያሳዝናል፣ ያሳፍራል፡፡ ለዚህ ዘመን በማይመጥኑ ሐሰተኛ ወሬዎች ሕዝብን በማተራመስ አገር ይበድላሉ፡፡ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ዘመናት በብዙ መከራዎች ውስጥ አልፏል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ እርስ በርሱ እየተሳሰበ፣ እየተረዳዳ፣ እየተፋቀረ፣ እየተጋባና እየተዋለደ በአርዓያነት የኖረን ይህንን ኩሩ ሕዝብ የማይመጥኑ ድርጊቶች በዚህ ዘመን ሲፈጸሙ ዝም መባል የለበትም፡፡ ይህ ጀግና ሕዝብ በዓለም ታሪክ ውስጥ አንፀባራቂ የሆነ ገድል የፈጸመና ለእናት አገሩ ትልቅ ፍቅር ያለው መሆኑ እየተዘነጋ በዘርና በመሰል ልዩነቶች እያዘናጉ ሐሰተኛ ወሬ መልቀቅ ተገቢ አይደለም፡፡ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ የሆነች አገርን በደምና በአጥንቱ የገነባ ሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን የሚገዘግዙና ለጥርጣሬ በር የሚከፍቱ ሐሰተኛ ወሬዎች በውስጡ በመርጨት ለማዳከም መሞከር የጠላት ሴራ ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ሴራ ደግሞ ዋነኛ ማጠንጠኛው ሐሰተኛ ወሬ ነው፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ በሒደት የሚያውቀው ነገር ስለሚኖር ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል፡፡ በእርግጥም ሲደርስበት ደግሞ ዓይንህ ላፈር እንደሚል የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና ወደፊት በታሪክ የሚያስጠይቁ ድርጊቶች ግን ከወዲሁ መገታት አለባቸው፡፡ ለሕዝብም ለአገርም አይበጁምና፡፡

የአሁኑ ወጣት ትውልድም ሆነ መጪው ትውልድ ጤናማ የሆነ ምኅዳር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጠላትነት የተመረዘው የአገሪቱ ፖለቲካ ውጤት የሆነው በፕሮፓጋንዳ የታጀበ ሐሰተኛ ወሬ አይጠቅማቸውም፡፡ ለውይይትና ለድርድር ራሱን ማስገዛት ያቃተው የዚያ ትውልድ እልህ የተሞላበት ቅራኔ፣ አገሪቱን ምን ያህል እንደጎዳት በግልጽ ይታወቃል፡፡ መነሻና መድረሻው ሥልጣን ብቻ ሆኖ ለሐሳብ ነፃነት ልዕልና ያልሰጠው የገነተረ ፖለቲካ፣ አሁን አራሙቻ ውስጥ ወድቆ የሐሰተኛ ወሬ መፈብረኪያ ሆኗል፡፡ መቼም ቢሆን ለማደግ ጥረት የማያደርገው የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ሽኩቻ ትውልዱን መጥለፍ የለበትም፡፡ ትውልዱም የሐሰተኛ ወሬዎች ማሟሻ እንዳይሆን ከቤተሰብ ጀምሮ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች መረባረብ አለባቸው፡፡ ትውልድን መታደግ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት አይመለከትንም ብለው አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ የሚሰማሩ ደግሞ ኃላፊነት የጎደላቸው ብቻ ሳይሆኑ ትውልድ ገዳይ ናቸው፡፡ ትውልድ የሚቀረፀው ኃላፊነት በሚሰማቸው ወገኖች ብቻ ስለሆነ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሙሉ ይህንን ጉዳይ በአንክሮ ሊያስቡበት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ሁሌም እንደምንለው ግልጽነት ሲጠፋ አገርን ችግር ውስጥ የሚከቱ አደጋዎች ይደቀናሉ፡፡ መንግሥት አሠራሩ ሁሌም ግልጽነት ከሌለው በውስጥም በውጭም ለሚፈበረኩ ሐሰተኛ ወሬዎች መንገዱን ያመቻቻል፡፡ ነገር ግን አንድ ብሔራዊ ችግር አጋጥሞ እሱን ለማስተካከል የእሳት አደጋ መከላከል ዓይነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ለሐሰተኛ ወሬዎች በር ይከፈታል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ሲኖር ግን ሕዝብ በቀላሉ መረጃ ስለሚደርሰው ከተሳሳቱ ወሬዎች ራሱን ይከላከላል፡፡ በመረጃ ላይ የሚመሠረት ሕዝብ በማንም አይታለልም፡፡ በዚህም ሳቢያ ሐሳቦች በነፃነት ሲንሸራሸሩ በሕዝብ ህሊና ይዳኛሉ፡፡ መረጃ የተነፈገ ሕዝብና የአቅጣጫ ማመልከቻው የጠፋበት መርከብ አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሐሰተኛ ወሬዎች የሚቀዘፍ አገር እንኳን ከድህነት ሊላቀቅ፣ ዴሞክራሲን ሊገነባ፣ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ቀርቶ ህልውናውን ለማፅናት ይቸገራል፡፡ ሕዝብም ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ይህንን ዓለም አቀፋዊ የሆነ ችግር በኢትዮጵያ ምድር ቦታ ለማሳጣት የሚመለከታቸው ሁሉ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ሕዝብ በእያንዳንዱ ዕርምጃው ያለ ምንም ተፅዕኖ መወሰን የሚችለው መረጃ በአግባቡ ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ በተሳሳቱ መረጃዎች ሳቢያ የሕዝቡ ትስስር መናጋት የለበትምና!