Skip to main content
x
የተቋጨው የኮፓ ኮካ ኮላ ብሔራዊ ሻምፒዮና

የተቋጨው የኮፓ ኮካ ኮላ ብሔራዊ ሻምፒዮና

ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች መካከል በሚካሄደው የኮፓ ኮካ ኮላ ሻምፒዮና የዘንድሮው አዘጋጅ ኢትዮ ሶማሌ አሸናፊ ሆኗል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ ከነሐሴ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት በተካሄደው ዓመታዊ የኮካ ኮላ እግር ኳስ ዋንጫ ኢትዮ ሶማሌ በወንዶች አማራን 4ለ1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል፡፡

ኢትዮ ሶማሌ ከዋንጫና ወርቅ ሜዳሊያ በተጨማሪ 50 ሺሕ ብር ሲሸለም፣ አማራ የብር ሜዳሊያና 30 ሺሕ ብር፣ ሦስተኛ የወጣው አፋር የነሐስ ሜዳልያና 20 ሺሕ ብር ተሸልመዋል፡፡ በስፖርታዊ ጨዋነት ሐረርና ጋምቤላ ክብሩን ሲያገኙ፣ በኮከብ ተጫዋችነትና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የኢትዮ ሶማሌው አብዱላሂ አሚን ሁለት ዋንጫና 10 ሺሕ ብር፣ በኮከብ በረኛነት የኢትዮ ሶማሌው ኤልያስ ሙክታር ዋንጫና 5 ሺሕ ብር ተሸልመዋል፡፡

በሴቶች ምድብ በተካሄደው ተመሳሳይ የፍፃሜ ጨዋታ ደቡብን ከአማራ ጋር ያገናኘ ሲሆን በውጤቱም ደቡብ 5ለ1 መረታት ክብሩን ተቀዳጅቷል፡፡

ደቡብ ከዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ በተጨማሪ 50 ሺሕ ብር፣ አማራ የብር ሜዳልያና 30 ሺሕ ብር፣ ሦስተኛ የወጣው ኦሮሚያ የነሐስ ሜዳልያና 20 ሺሕ ብር፣ አግኝተዋል፡፡ በስፖርታዊ ጨዋነት ድሬዳዋና አዲስ አበባ፣ በኮከብ ተጫዋችነት፣ ኮከብ በረኛነትና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የደቡቦቹ ኢየሩሳሌም ሳሙኤል፣ አምሳል ፍሥሐና ደንቡሽ አባ ሲመረጡ፣ እያንዳንዳቸው ዋንጫና 5 ሺሕ፣ 5 ሺሕ ብር ተሸልመዋል፡፡

ኮፓ ኮካ ኮላ ከመጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ሲካሄድ መክረሙና በ2,000 ትምህርት ቤቶች በተካሄደው ውድድርም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ከ36 ሺሕ በላይ ተማሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

በሻምፒዮናው መክፈቻ የኮካ ኮላ ብራንድ ማናጀር ወይዘሪት ትዕግሥት ጌቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የኮፓ ኮላ ውድድሮች ስኬቶችን በመጥቀስ፣ ውድድሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደፊት ተስፋ እንደሚሆን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡