Skip to main content
x
የተጠያቂነት ዳር ድንበሩ በግልጽ ይታወቅ!

የተጠያቂነት ዳር ድንበሩ በግልጽ ይታወቅ!

ሕግ የሚከበረው ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት አለ የሚባለው ሁሉም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በሕግ ፊት እኩልነት መሆን የሚረጋገጠው ተጠያቂነትም ሲታከልበት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መኖሩ የሚጠቅመው ደግሞ በሥርዓት ለመተዳደር ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት እንዳለበት በግልጽ ደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በግልጽ ሠፍሯል፡፡ መንግሥት ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ እንደሆነ ዋናው ምስክር ሕዝብ መሆን ሲገባው፣ በሰበብ በአስባቡ የሕዝብን ምስክርነት ማግኘት እየተሳነው ነው፡፡ በተደጋጋሚ የአገር ሀብት በማባከን ሪፖርት የሚቀርብባቸው ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂነት ስለሌለባቸው ዝም ይባላሉ፡፡ ድንገት እንደ ሰሞኑ ግርግር ሲጀመር ከየአቅጣጫው ለሚነሳ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የተጠያቂነት ዳር ድንበሩ ግልጽ አይደለም፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግሥትን ሥራ የሚያከናውኑ ተቋማትና ተሿሚዎች በሕግ የተሰጣቸው ሥልጣን አለ፡፡ ከሥልጣኑ ቀጥሎ ተጠያቂነታቸውም  ተዘርዝሯል፡፡ በተለይ አንድን ተቋም የሚመራ ባለሥልጣን በየደረጃው ለተወከሉ ተሿሚዎች ጭምር ኃላፊነት ሲኖርበት፣ በሚመራው ተቋም ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን የመከታተልና የመቆጣጠር ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነት አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን የሙያ ሥነ ምግባሮችንም ይመለከታል፡፡ በተቋሙ ውስጥ ከሪፖርቶች አቀራረብ ጀምሮ እስከ ሥራ አፈጻጸሞች ያሉ የተጣሩ መረጃዎች ግልጽነትን ለማስፈን የሚረዱ ሲሆን፣ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ተጠያቂነትን ያጎለብታሉ፡፡ አንድ ተቋም በመንግሥት የፋይናንስ ሕግ መሠረት ሥራውን ማከናወን አቅቶት ተገቢ ያልሆኑ ክፍያዎችን ሲፈጽምና ለሙስና የሚያጋልጡ ሕገወጥ አሠራሮችን ሲከተል ተጠያቂነትን እየናደ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ተሿሚዎችም ይህንን እያወቁ ሕገወጥ አሠራር ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ከበላይ ሆኖ የሚመራው ሹም ደግሞ ሥራን በአግባቡ ባለመምራት በአገር ሀብት ላይ ውድመት ያደርሳል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥፋቱ ይመለከተዋል ማለት ነው፡፡ ብልሹ አሠራሮች የሚስፋፉት በእንዲህ ዓይነቱ ሕገወጥ ጎዳና ነው፡፡ ጠያቂም ተጠያቂም በሌለበት ጎዳና ማለት ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የፌዴራል ዋና ዓቃቤ ሕጉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚባሉት በሚኒስትርና በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ ያሉት የፖለቲካ አቅጣጫ ከመስጠት ባለፈ ብዙ ሚና እንደሌላቸው፣ ይልቁንም በዳይሬክተር ደረጃ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በገንዘብና በቢሮክራሲያዊ ጉዳዮች የመወሰን ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡ ሚኒስትሮቹ ሚና የላቸውም ባይባልም በአብዛኛው ኃላፊነቱ የሚወድቀው ከታች በሚገኙት ላይ እንደሆነም አክለዋል፡፡ የተጠያቂነት ጉዳይ ሲነሳ ግን ማንም ተሿሚ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሥራውን ማከናወን ካቃተው ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ተሿሚ ሆኖ አቅጣጫ ከመስጠት ባልተናነሰ የአገር ሀብትን የመጠበቅና በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ግዴታው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡ ኃላፊነትን አለመወጣት ደግሞ በሕግ ያስጠይቃል፡፡ በፌዴራል ዋና ኦዲተር በሚቀርቡ ሪፖርቶች መሠረት ተጠያቂነት ያለባቸው ተቋማት ድርጊታቸው እየተዘረዘረ ሲቀርብ፣ የሚመለከታቸውን ተሿሚዎች ለሕግ ማቅረብ አለመቻል ምን ያህል ጥያቄዎች እንዳስነሳ ይታወቃል፡፡ በፓርላማ አባላት ሳይቀር ይህ ሁኔታ እንዲህ የሚቀጥለው እስከ መቼ ድረስ ነው ተብሏል፡፡ ያውም በተደጋጋሚ፡፡ ሕዝብ ደግሞ ግራ ሲገባው የሚያገኘው ምላሽ ኢምንት ነው፡፡

በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ከሕዝብ የተደበቁ አይደሉም፡፡ መንግሥት ራሱ በተደጋጋሚ ሙስና የሥርዓቱ አደጋ ነው ሲል ተሰምቷል፡፡ አሠራሩ ግልጽ ባለመሆኑ ግን የባለሥልጣናቱ የተጠያቂነት ዳር ድንበር አልታወቀም፡፡ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ስም ዝርዝር ሲወጣ፣ የሚጠየቁት እነዚህ ብቻ ናቸው ወይ ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ አሳማኝ መልስ መቅረብ አለበት፡፡ የሙስና ወንጀልን ማጣራት ውስብስብና ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣ ተጠያቂነቱም በተቻለ መጠን ፍትሐዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ፈጽሞታል የተባለውን የሙስና ወንጀል ሌላው የማይጠየቅበት ከሆነ በሕግ ፊት እኩልነት አለ ብሎ መናገር ቀልድ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በሥልጣን ያላግባብ መበልፀግ ወይም ሥራን በአግባቡ ባለመምራት ተጠያቂ የተደረጉ እንዳለ ሁሉ፣ አሁንም ሥልጣኑን ያላግባብ የተገለገለበትም ሆነ ያላግባብ የበለፀገ ተጠርጣሪ መጠየቅ አለበት፡፡ የአሁኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ዕርምጃ የተወሰደው መንግሥት የሙስና ተሳታፊዎችን ሕግ ፊት ለማቅረብ በገባው ቃል መሠረት ነው ከተባለ፣ ተጠያቂነት ያለባቸው ተሿሚዎችም እንዲሁ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው ማለት ነው፡፡

በተለይ የመንግሥት ሥራን ለመምራት ኃላፊነት ያለባቸው ተሿሚዎች ለሕዝብ  ተጠያቂነት እንዳለባቸው በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› እየተባለ የአገርና የሕዝብ ሀብት ቅርጥፍ ተደርጎ እየተበላ፣ ተጠያቂነትን በእኩል ደረጃ ለማሳየት አለመቻል ያስጠይቃል፡፡ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ አገር በሥርዓት መመራት የምትችለው በሙሰኛ ሹማምንት ላይ የሚጨክን ቁርጠኛ አመራር ሲኖር ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ሕዝብ የሚከናወነውን የሚመለከተው እንደ ድራማ ነው፡፡ ሙስና የሚፈነጭበት አገር የፈለገውን ያህል ለልማት ቢጣጣር ውጤቱ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› ነው የሚሆነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነቱም በተግባር ሲረጋገጥ ሕዝብ እርካታ ይሰማዋል፡፡ ነገን በተስፋ እያለመ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ተሳትፎው ይጨምራል፡፡ የባለቤትነት መንፈሱ ከፍ ይላል፡፡ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ ሲባል አሠራሩ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ስለማግኝቱ እርግጠኛ ይሁን ማለት ነው፡፡ በጉያው ውስጥ አቅፎ የያዛቸውን ሙሰኞች ለሕግ እያቀረበ ጤናማ ሥርዓት መገንባት ካልቻለ ለአገር ፈተና ነው፡፡ ትውልድ በትውልድ እንደሚተካው ሁሉ መንግሥት በሌላ መንግሥት ይተካል፡፡ አገር ግን በምንም አትተካም፡፡

ተጠያቂነት የሚጠቅመው ከደመነፍሳዊ አሠራር በመውጣት ዘመናዊት፣ ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች አገር ለመገንባት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቷ አገር ስትኖር ዜጎች በሰላምና በፍቅር ተከባብረው ይኖራሉ፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት በፍትሐዊ መንገድ ይከፋፈላል፡፡ ዜጎች እንደ ችሎታቸውና ጥረታቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በብሔር፣ በእምነትና በጥቅም ግንኙነት ልዩ ተጠቃሚ መሆን አይቻልም፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩልና ተጠያቂነታቸውም ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይከበራሉ፡፡ በአገራቸው ውስጥ በፈለጉት ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ ዋስትና ይኖራቸዋል፡፡ ከመብቶቻቸውና ከጥቅሞቸው በተጨማሪ አገራቸውን በተሠለፉባቸው ሙያዎች የማገልገልና ተሳትፎ የማድረግ ግዴታዎቻቸውን ይወጣሉ፡፡ ተሳትፎአቸው በዕውቀት ላይ ስለሚመሠረት ለአዲሶቹ ትውልዶች አርዓያ ይሆናሉ፡፡ ሙስና በሞራልና በሥነ ምግባር የዘቀጡ ኃይሎች መገለጫ በመሆኑ በአንድነት ይታገሉታል፡፡ ለሕግ የበላይነት ልዕልና በትልቁ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ በዚህ ዓይነት እሳቤ ላይ በመመሥረት የተጠያቂነት ዳር ድንበሩ ግልጽ መሆን አለበት!