Skip to main content
x
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ተሸላሚዎቹ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና ተሸላሚዎቹ

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በግዙፍነት ታላቅ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለመገደብ የመሠረት ድንጋይ ከጣለች ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም የግድቡን መጠናቀቅ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በግድቡ መጠናቀቅ ብዙ ነገሮች እንደሚቀየሩም ተስፋ አድርገዋል፡፡

ምቹ የሆነ የአየር ንብረት፣ ለማዕድንና ለተለያዩ መሠረተ ልማቶች የሚውል መሬት፣ ለኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚውሉ ወንዞችና ተፋሰሶች ያሏት አገር እስከ ዛሬ ድረስ ከድህነት መውጣት አለመቻሏ የብዙዎች ቁጭት ነበር፡፡ ይህ ግድብ እስከ 6,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ይጠበቃል፡፡ ግድቡ በአሁኑ ወቅት ከግማሽ በላይ ሥራው ተጠናቋል፡፡ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ከመፍታቱ ባሻገር፣ አገሪቱ ለማደግ በምታደርገው ሁለንታዊ እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት ሆኖ እደሚያገለግልም ይጠበቃል፡፡ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ኃይል የማመንጨት ዕምቅ አቅም ቢኖራትም ሳትጠቀምበት ቆይታለች፡፡

ሚያዚያ 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ የቀድሞው  ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹የግድቡ መሐንዲሶች እኛ፣ የገንዘብ ምንጮቹ እኛው . . . ነን፤›› በማለት ንግግር  ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ይህን የተናገሩት ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ገድባ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት መንቀሳቀስ ስትጀምር የግብፅ መንግሥት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ ያደርግ በነበረው ውትወታና ጥያቄ መሠረት፣ አበረታች ምልክት ባለመስጠታቸው የተነሳ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ መጣሉን የተረዳው የአገሬው ሕዝብም ከጫፍ እስከ ጫፍ ደስታውን የገለጸበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡

የግብፅ የዓባይን ወንዝ ለብቻዬ ልጠቀም አባዜ ተሽሮ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ተጠቅማ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች እንዲጠቀሙ እየተሄደበት ያለው መንገድም በብዙዎች ዘንድ ደስታ የፈጠረ ነበር፡፡

የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ወዲህ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እንደቀጠለ መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የግንባታ ሒደት 58.4 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ይፈጃል ተብሎ የተገመተው ገንዘብ 80 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ከኅብረተሰቡ አሥር ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የሕዝቡ ተሳትፎ በገንዘብ ሲተመን ከ10 እስከ 15 በመቶ ይጠበቅ እንደነበር የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ በአሁኑ ወቅት ስምንት በመቶ መድረሱንና ይህም ተሳትፎ በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህን የኅብረተሰብ ተሳትፎ ቀጣይነት ለማረገገጥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሐፈት ቤት በ2008 እና በ2009 ዓ.ም.  ባዘጋጃቸው ሁነቶችና ፕሮጀክቶች ላይ ሁለንተናዊ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የምሥጋና ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው በዚህ የምሥጋና ፕሮግራም ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የህዳሴ ግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን፣ የመገናኛና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተጋብዘው ነበር፡፡

በዕለቱ በተዘጋጀው የሽልማትና የምሥጋና ፕሮግራም ላይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ግደቡ ዕውን እንዲሆን የተሻለ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት ተሸልመዋል፡፡

በዚህ የሽልማት ፕሮግራም ላይ የተመሠገኑት አካላት በተሳትፎአቸው መሠረት አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሽልማት፣ ሁለተኛ ደረጃ የክሪስታል ዋንጫ ሽልማት፣ ሦስተኛ ደረጃ የላቀ የምስክር ወረቀትና አራተኛ ደረጃ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡

አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሽልማት የሚባለውን የሽልማት ዓይነት ያገኙት ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የክሪስታል ዋንጫ ሽልማት የተሰኘውን ሽልማት ያገኙት 46 ተቋማትና ግለሰቦች ናቸው፡፡ አራተኛ ደረጃ የምስክር ወረቀት የተሰኘውን የሽልማት ዓይነት ያገኙ ተቋማት ከ350 በላይ እንደሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለዚህ ሽልማት የበቁ ተቋማትና ግለሰቦች ቁጥር ከ460 በላይ እንደሆነ በዕለቱ ይፋ ሆኗል፡፡

በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ሮማን፣ ‹‹የዓባይ ወንዝን ለመገደብ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያግደን በጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ክንዳችን ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን ከግማሽ በላይ አድርሰነዋል፤›› ብለዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡ ጠቅላላ የሥራ ክንውን 58 በመቶ በላይ እንደደረሰ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአሁን በኋላ የሚቀረው ሥራ ቀላል እንደሆነና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የመሠረት ድንጋይ ከጣለች በኋላ በግብፅ በኩል የተለያየ አቋም ሲያዝ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በቅርቡ የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ እስከ ዛሬ ድረስ ሥልጣን ላይ ቢቆዩ ኑሮ ግድቡን ሊያፈርሱት እንደሚችሉ ስለመናገራራው ሪፖርቶች መውጣታቸው አይረሳም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በአሁኑ ወቅት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከተፋሰስ አገሮች ጋር ተቀራርበው  ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸው  ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ ግብፅ የዓባይ ወንዝን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተፋሰስ አገሮች ያረቀቁትን ስምምነት እስከ ዛሬ ድረስ ባትፈርምም፣ ወደ ስምምነት መድረኩ መጥታ መደራደር መጀመሯ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ግብፅ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በ1929 በኋላ ደግሞ በ1959 ከሱዳን ጋር በመሆን የዓባይ ወንዝን ለብቻቸው ለመጠቀም ስምምነት መድረሷ ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድቡ በተፋሰስ አገሮች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመረዳት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ዓለም አቀፍ አጥኝ ቡድኖችን ቀጥረው እያሠሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ሒደት ውስጥ የገባችው መተማመን ለመፍጠር እንጂ የግንባታው ዕጣ ፈንታ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ እንዳልሆነ ደጋግማ ትገልጻለች፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ግንባታውን ሌትና ቀን እያከናወነች ነው፡፡ የዚህን ግድብ ግንባታ ጫፍ ለማድረስም ብሔራዊ ምክር ቤቱ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶችን ከማዘጋጀት ባሻገር፣ ዜጎች የማያቋርጥ ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ እያደረገና ለዚህም በጎ ምላሽ እያገኘ መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአገራችንን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይበልጥ እያጎለበተ ከመምጣቱ በላይ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማዳበር በመተማመንና በመተባበር መኖር እንድንችል የመሠረት ድንጋይ ሆኗል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የዚህ ሽልማት መዘጋጀት ዓላማም ቀሪ ሥራውን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ጉልበት ለመፍጠር እንደሆነም አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሽልማት የተሰኘውን ሽልማትና ምሥጋና ያገኙት ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ክሪስታል ዋንጫ ተሸላሚዎች መካከል ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን፣ ሞኤንኮ፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ጊፍት ሪል ስቴት፣ አዲስ ፓርክ ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሸራተን  አዲስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አምቼ፣ ሪየስ ኢንጂነሪንግ፣ ኒያላ ሞተርስ ኮርፖሬሽን፣ ሰንሻይን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ፣ ማራቶን ሞተርስ፣ በጥረት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኢትዮ ኒፖንና ሆራ ትሬዲንግድ ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ ስፖርታዊ ሒደቱን በመደገፍና በማስተባበር የተሸለሙት ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ናቸው፡፡

በማስታወቂያ ሥራዎች ሁለተኛ ደረጃ የክሪስታል ተሸላሚ ከሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች መካከል ደግሞ ሳምሶን አድቨርታዚንግ፣ ደቦል መልቲ ሚድያ ፕሮዳክሽን፣ አንበሳ ማስታወቂያ፣ ሠራዊት መልቲ ሚድያ፣ ሸዋፈራሁ ማስታወቂያ፣ ርሆቦት ፕሮሞሽን ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ ተሸላሚ ከሆኑት የሚድያ ተቋማት መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ አዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ናቸው፡፡

በዚሁ ዘርፍ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የተሸለሙት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሸንና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ናቸው፡፡ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ በማዋጣት ድጋፍ አድርገው ከተሸለሙት መካከል ደግሞ ቫርኔሮ ሪል ስቴት፣ ዳሸን ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ዓባይ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ የብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽንና በላይነህ ክንዴ አስመጭና ላኪ ይገኙበታል፡፡

በዕለቱ በተዘጋጀው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ሦስተኛ ደረጃ  የላቀ የምስክር ወረቀት ተሸላሚ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት በአሥር የተለያዩ ዘርፎች ተለይተው ለሽልማት በቅተዋል፡፡ ከእነዚህ ግለሰቦችና ተቋማት መካከል ደግሞ ጥቂቶቹ ሐበሻ ዊክሊ፣ ቦስተን ፓርትነር፣ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ አልታ ኮምፒውተር፣ ስናፕ ኮምፕዩተርና ዮናስ ታደሰ ይገኙበታል፡፡

በዚሁ ዘርፍ ተሸላሚ ከሆኑ የሚዲያ ተቋማት መካከል ጥቂቶቹ ናሁ ቲቪ፣ ጄ ቲቪ፣ ቃና ቲቪ፣ ዛሚ ኤፍኤም፣ ብሥራት ኤፍኤም፣ ሸገር  ኤፍኤም፣ ኦሮሚያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት፣ ሪፖርተር ጋዜጣ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ ፕሬስ ድርጅት፣ ሰንደቅ ጋዜጣና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ይገኙበታል፡፡ በዚሁ የሽልማት ዘርፍ ሌሎች ያልተጠቀሱ ተቋማትና ግለሰቦች ለሽልማት በቅተዋል፡፡   

በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድቡ 24 ሰዓት የግንባታ ሒደቱ እየተከናወነ ሲሆን፣ የግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝቡ ተሳትፎ እንዳይቆምና ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሰብ የምሥጋናና የሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ በዚህ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን እንዳስቀመጠ እየተናገረ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ የተሻለ ተሳትፎ የነበራቸውን ግለሰቦችና ተቋማት በአቋራጭ ሸልሟል፡፡

ፖለቲካዊ አንድምታው ጉልህ የሆነው ይህ ግድብ በአሁኑ ወቅት በሦስቱ አገሮች ማለትም በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን ስምምነት መሠረት ግድቡ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ ለማስጠናት ዓለም አቀፍ የአጥኝዎች ቡድን ተቋቁሞ አያጠና መሆኑ ይታወቃል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሸምሰዲን አህመድ ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር፣ ‹‹ኢትዮጵያ ይህን ግድብ ገንብታ ድህነትን ከመቅረፏ ባሻገር ለታችኞቹ ተፋሰስ አገሮችም ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ አካል ካለ  ዓለም አቀፍ ፓናል ኦፍ ኤክስፐርትስ ተቋቁሞ ሊያየው ይችላል ማለት፣ ኢትዮጵያ ይህን ክፍት አድርጋ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ አጥኝዎችን በመሰየምና ከሦስቱ አገሮች ባለሙያዎችን በመመደብ እ.ኤ.አ. ከመስከረም 2014 ጀምሮ ጥናት እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህን ጥናት የሚያካሂዱት የፈረንሣይ ኩባንያዎች ሲሆኑ አንደኛና ዋነኛው ኩባንያ ቢአርኤልአይ ሲሆን ሁለተኛው ኩባንያ ደግሞ አርቲሊያ ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት ሦስቱ አገሮች ባስቀመጡት መመርያ መሠረት እንደሆነም አምባሳደር ሸምሰዲን ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ድረስ እነዚህ ሦስቱ አገሮች 13 ዙር ውይይቶች እንዳደረጉ አስረድተዋል፡፡

 እነዚህ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እያደረጉት ያለውን ጥናት በየጊዜው ለአገሮቹ እያቀረቡና እያስገመገሙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስካሁን ድረስ እያቀረቡት ባለው የጥናት ውጤትም በብዙ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረስ አመቻላቸው እየተገለጸ ሲሆን፣ አምባሳደር ሸምሰዲን ደግሞ፣ ‹‹ካይሮ ላይ ተካሂዶ በነበረው 13ኛው ሰብሰባ ላይ ስምምነት ያልደረስንባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በግንቦት ወር አዲስ አበባ ባካሄድነው 14ኛው ዙር ስብሰባ ልዩነታችንን በመፍታት አጥኝዎቹ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አጥኝ ቡድኑ ሥራን በተገቢው ሁኔታ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው፣ 15ኛው ዙር ስብሰባ በሱዳን ካርቱም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

ለእነዚህ ዓለም አቀፍ አጥኝ ኩባንያዎች የሚከፈለውን ክፍያ ሦስቱ አገሮች እኩል አዋጥተው እንደሚከፍሉ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡