Skip to main content
x
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከስድስት ዓመታት በኋላ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከስድስት ዓመታት በኋላ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሒደት በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ እንደደረሰ መንግሥት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ለስድስት ዓመታት ያህል በግንባታ ላይ ያለው ይህ ግድብ እስከ አሁን ድረስ ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ምንም እንኳ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአምስት ዓመት ውስጥ በከፊልም ቢሆን የግንባታ ሒደቱ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ግንባታው በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሒደት ላይ እንደሚገኝና በቅርቡ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የህዳሴ ግድቡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ሰሞኑን ለመንግሥት ሚዲያዎች ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የህዳሴ ግድቡ ምክር ቤት ዘጠነኛ ጉባዔውን  በካፒታል ሆቴል ባካሄደበት ወቅት የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) እንደተናገሩት፣ ግድቡ በአሁኑ ወቅት በጥሩ የግንባታ ሒደት ላይ ይገኛል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ እስካሁን ድረስ በግንባታ ሒደቱ የገንዘብ እጥረት እንዳልገጠመ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ምንም ያህል የፖለቲካና የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩንም ግድባችን  ብሔራዊ መግባባት የፈጠረና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ መስመርና ዓላማ ያሠለፈ ፕሮጀክት  ነው፤›› ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ በተጣለ ማግሥት በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫዎች በርካታ የድጋፍ ሠልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁሩ ድረስ ያለው በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በዕውቀቱ ለመርዳት  ቁርጠኝነቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ተስተውሏል፡፡ ይህ ትብብር ግድቡን ከግማሽ በላይ እንዲደርስ ያስቻሉ ድጋፎችን ለማስተባበር ትልቅ ሚና መጫወቱም ይነገራል፡፡

የግብፅ መንግሥትና ፖለቲከኞች የግድቡን መሠረት መጣል ሲኮንኑና ሲቃወሙ መስማት አደስ አገር አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ ይታተሙ የነበሩ የግብፅ ጋዜጦች ይዘውት ይወጡ የነበረው ርዕስ አንቀጽና የርዕስ አንቀጹን ዋነኛ መልዕከት የያዘው የካርቱን ሥዕል ይህንኑ ያንፀባርቁ ነበር፡፡ ግብፃዊያን የግድቡን ዕውን መሆን እንዲቃወሙ ከመሥራትም አልፎ፣ በጉልበታቸው እንዲያፈርሱ የሚጠይቁ መልዕክቶችን ሳይቀር እነዚህ የሚዲያ ውጤቶች ይዘው ይወጡ ነበር፡፡

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከዘመናት ህልምና ቁጭት በኋላ ያገኘው እንደሆነ የሚገለጸው ይኼ ፕሮጀክት ልዩነት ሳይታይ መላ ሕዝቡ በጉልበት፣ በገንዘብና በዕውቀት ከጎኑ ሆኖ እንዲደግፍና እንዲጠብቀው መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲጠይቅም ተደምጧል፡፡

ግብፅ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከእስያ እስከ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ እጇን በማስገባት ኢትዮጵያ ለምትገነባው ግድብ ዕርዳታ እንዳታገኝ ማድረጓ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቢሰማም፣ አገሪቱ በራሷ አቅም ከአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ግድብ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ፈጥሯል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የገጠማትን ሕዝባዊ ተቃውሞና ጥያቄ ተቋቁማ የግድቡን ግንባታ ማስቀጠል መቻሏና ከግማሽ በላይ ማድረሷ፣ እንደ ጠንካራ ጎን የሚወሰድ መሆኑን የውጭ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ይገልጻሉ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ በተከሰተው ተቃውሞ በርካታ የሰው ሕይወት የጠፋ ቢሆንም፣ የግድቡ ግንባታ አንድም ቀን ሳይቋረጥ 24 ሰዓት ሙሉ እየተከናወነ መሆኑን መንግሥት አመልክቷል፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ እስከ 6,450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል፡፡ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ችግር እንደሚፈታ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ በአርባ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋን ሱዳን ሳይቀር ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ኢንጂነር ስመኘው ተናግረዋል፡፡

በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የግንባታ ሒደቱ መጠናቀቅ በጉጉት የሚጠበቀው ይህ ግድብ፣ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት የግድቡን የግንባታ ሒደት በተመለከተ በ2009 ዓ.ም. የተካሄደውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለምክር ቤቱ አባላት ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ይህ በ28 ገጽ ተቀንብቦ የቀረበው ሪፖርት በዋናነት ያተኮረው በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ነው፡፡ ሪፖርቱ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ዙሪያ የመላውን ኅብረተሰብ ተሳትፎ ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች፣ የዲያፖራ ተሳትፎን ለማጠናከር የተከናወኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሥራዎች፣ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን አካቷል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ፣ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት፣ የችቦ መቀባበል ሥነ ሥርዓት፣ የዓባይ ቀን የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ የእግር ኳስ ውድድር፣ የዓባይ ቀን የጎዳና ላይ ትርዒት፣ የብስክሌት ውድደር፣ የሕፃናት የሥዕል ውድድር፣ የሥዕልና የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ፣ ሊቀ ናይል የጥያቄና መልስ ውድድር፣ የስድስተኛ ዓመት አከባበር በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራባቸው መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ተገኝቶ የነበረው 8.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ ነገር ግን በ2009 ዓ.ም. የአገሪቱን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የመንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ባለሀብቶች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ዳያስፖራው፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ በቦንድ ግዥ፣ በልገሳና በገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማድረግ 10.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ አርሶና አርብቶ አደሮች በ2009 ዓ.ም. ያደረጉት አስተዋፅኦ በጉልበት ሲተመን 23.85 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ማበርከት መቻሉም ተጠቅሷል፡፡ ከ19.8 ሚሊዮን በላይ የሰው ኃይል የተሳተፈበት ሥራ መከናወኑም ተብራርቷል፡፡

በዚህ ዓመት የህዳሴ ግድቡን ዕውን ለማድረግ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ  ክፍተቶችና ችግሮች እንደነበሩም ተጠቁሟል፡፡ በተለይ በየደረጃው ያለው አመራር እንደ ሌሎች ሥራዎች እኩል በመያዝ ማንቀሳቀስ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ ተለይቷል፡፡ የዳያስፖራ ቦንድ መረጃ አያያዝና አመላለስ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት መካከል የቅንጅት ማነስ እንዳለ ተገልጿል፡፡

 በዚህ ሪፖርት የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ በወቅቱም የህዳሴ ግድቡ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴና አቶ ደመቀ መኮንን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) የህዳሴ ዋንጫው ከክልል ክልል ብቻ ለምን ይንቀሳቀሳል? ወደ ግል ተቋማትስ ለምን እንዲሄድ አይደረግም? የሚል ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ ወ/ሮ ሮማን በምላሻቸው፣ ‹‹ይህ ዋንጫ ሐሳቡ ሲጠነሰስ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተሰጠ ነው፡፡ ዓድዋ ይፋ ሲሆንም ከህዳሴ ግድቡ ጋር የሚያመሳስለው ነገር ስላለና የአሸናፊነት ምልክት ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለብሔር ብሔረሰቦች የተሰጠ በመሆኑ ወደ ግል ተቋማት ሊሄድ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዋንጫው በአንድ ክልል ለአንድ ዓመት ነው የሚቆየው፡፡ ችቦው ግን ለአንድ ወር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ችቦ ወደ ተቋም እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዋንጫው ግን የብሔር ብሔረሰቦች ምልክት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር አረጋ፣ ‹‹በማዕድን ኢንዱስትሪ መሬት ውስጥ ያለውን ወርቅ መሸጥ ይቻላል፡፡ የህዳሴ ግድቡ ወደ ፊት የሚያመነጨውን ኤሌክትሪክ ኃይል ካሁኑ ለምን መሸጥ አልተቻለም?›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ከመድረኩ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው የባለሀብቱን ተሳትፎ ከማሳደግ አኳያ በተለይ በፌዴራሉና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ተቀናጅቶ ከመሥራት አኳያ ክፍተት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪውና ዝቅተኛ ባለሀብቱ ብቻ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሻል ሻል ያለው ባለሀብት ደግሞ በፌዴራል የመሳተፍ አዝማሚያ ስላለው፣ በጋራ መሥራት ካልተቻለ ክፍተቶችን መፍታት አንችልም፤›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ወ/ሮ ሮማን በምላሻቸው፣ ‹‹ከአዲስ አበባ ጋር ተቀናጅቶ ከመሥራት አኳያ የተነሳው ጥያቄ ትክክል ነው፣ እንቀበላለን፡፡ ወደ ፊትም መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ትክክለኛ አቅጣጫ አስቀምጠን በዚያ መንገድ መሄድ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት የቦንድ ግዥን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡ አንድ አባል፣ ‹‹የቦንድ ግዥ ገደቡ እስከምን ድረስ ነው?›› በማለት ሲጠይቁ፣ ሌላ አባል ደግሞ፣ ‹‹በቦንድ ግዥ ላይ ሰፊ ልዩነቶች አሉና ይኼንን እንዴት ነው ማጣጣም የሚቻለው?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ወ/ሮ ሮማን መንግሥት አዲስ አቅጣጫ ማስቀመጡን ይፋ አድርገዋል፡፡ ኅብረተሰቡን ከሦስት ጊዜ በላይ እንዲገዛ ማድረግ ሊጎዳው ስለሚችል መንግሥት እንደማይገፋፋ ተናግረዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ለስድስት ዓመታት ያህል የቦንድ ግዥ ያላቋረጡ ተቋማትና ግለሰቦች እንዳሉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የመከላከያ ሠራዊት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ የፌዴራል ፖሊስና በስልጤ ዞን ውስጥ የምትገኘውና የም ተብላ በምትጠራው ወረዳ ውስጥ የሚኖሩ የመንግሥት ሠራተኞችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ሌሎች ጥያቄዎች መካከል ግድቡ የሚፈጥረውን ሰው ሠራሽ ሐይቅ መጠበቅን በተመለከተ ምን እየታሰበ ነው? የሚል ይገኝበታል፡፡ የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው የሰው ሠራሽ ሐይቁ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዓሳ ዕርባታ፣ የቴክኖሎጂ ፓርኮችና የጥናት ማዕከሎች በሐይቁ ዙሪያ እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡ ከሐይቁ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ሌላ ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት እንደማይኖርም አክለዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ተረጋግጦ ወደ ግንባታ እንደተገባ አስታውሰው፣ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም ባልተናነሰ ለታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች የሚሰጠው ጥቅም እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሙሴ ያዕቆብ (ዶ/ር) የግድቡን ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አነስተኛ በመሆኑ፣ ብዙ ወንዞችና የተፈጥሮ ሀብቶች አደጋ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ደመቀ በበኩላቸው የትኩረት ማነስና የተፋሰስ ልማት ጉዳዮችን አቀናጅቶ ከመምራት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ አውስተዋል፡፡ በዓባይ ተፋሰስ ያሉ 22 ወረዳዎችን እስከ ደቡብና ሰሜን ጎንደር፣ እንዲሁም ከእንጦጦ እስከ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ያለውን ተፋሰስ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ባህር ዳር ያለው የጣና ተፋሰስ ማዕከልም ተፋሰሶችን ከህዳሴ ግድቡ ዘላቂነት ጋር ቃኝቶ ሥራውን የመምራትና ተቋማዊ ተልዕኮውን የመውጣት ግዴታ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ግድቡ እስከ 375 ዓመታት ድረስ ያገለግላል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ለአካባቢ ጥበቃ ካለው አናሳ ግንዘቤ የተነሳ ግድቡ የታሰበውን ያህል ጊዜ  ሊያገለግል እንደማይችል የምክር ቤቱ አባላት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም መወረር፣ የጉናና የጮቄ ተራሮች አደጋ ላይ መውደቅ የግድቡን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹በጣና ዙሪያ ያሉ ተፋሰሶችን መታደግ ግድቡን በዘላቂነት እንድንጠቀምበት ያስቻላል፤›› ብለዋል፡፡

ከህዳሴ ግድቡ ጎን ለጎንም ሌሎች የመንገድ፣ የመልሶ ማቋቋም፣ የግንባታና  የደን ምንጣሮ እየተከናወነ መሆኑን ኢንጂነር ስመኘው ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤቱ ዘጠነኛ መደበኛ ጉባዔውን በካፒታል ሆቴል ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በ2009 ዓ.ም. በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የተከናወነው ሥራ አነስተኛ ነው፡፡

አንድ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹በራሳችን ውኃ ስንዋረድ ኖረናል፡፡ እኛ ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ውኃችንን ስንሰጣቸው ብንኖርም እነሱ ግን ዋጋ ሳይሰጡን ኖረዋል፡፡ የተዋረድን ሰዎች ነበርን፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ዋጋ እንዳለን እናሳያቸዋለን፤›› በማለት በቁጭት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ቀይ ባህር በጀርባችን እየመጣ ስለሆነ (ሰው ሠራሽ ሐይቁን ሲገልጹ) በዙሪያው ምን የታቀደ ነገር አለ?››  በማለት ጠይቀዋል፡፡

ወደ ፊት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚጎርፍ ተስፋቸውን የገለጹት ሌላ የምክር ቤት አባል፣ የቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ እ.ኤ.አ. በ2020 ከበካይ ጋዝ ነፃ የሆነ ተሽከርካሪዎች ለመጠቀም ማቀዷን ገልጸው ኢትዮጵያ ወደ ፊት በተለይ የቤት መኪና፣ ታክሲና የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ጉልህ ሚና ስለሚኖረው በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲነዱ ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በ2009 ዓ.ም. የተሠራው ሥራ ምን እንደሚመስል በቀረበው ሪፖርት የምክር ቤቱ አባላት ከተወያየ በኋላ፣ በ2010 ዓ.ም. ዕቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የነበሩ ውስንነቶችን በማረምና የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ የግድቡን ግንባታ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የተገኘውን 10.5 ቢሊዮን ብር ወደ 11.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት፣ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ በማሳሰብ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡