Skip to main content
x

የኑክሌር መዘዝ


በዮሐንስ አልታሞ

72 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የጃፓን ሁለቱ ከተሞች ሒሮሽማና ናጋሳኪ በአሜሪካኖቹ ቢ-29 የኑክሌር ቦምብ ጣይ የቦይንግ ሥሪት ጄቶች 16 ኪሎ ቶንና ሃያ ኪሎ ቶን የፍንዳታ አቅም ያላቸው የኑክሌር ቦምቦችን በሁለቱ ከተሞች በሦስት ቀናት ልዩነት አፈራርቆ በማፈንዳት 450,000 ሺሕ የሚገመት ሕዝብን ከፈጁ ወዲህ ያለፉ  ዓመታት፡፡ በቅርቡ የጃፓን መንግሥትና ሕዝብ በእነኛ ሰቅጣጭ ቀናት የተፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በሰው ልጆች ታሪክ ዳግም እንዳይከሰቱ መልዕክት በማስተላለፍ  72ኛ ዓመት መታሰቢያ ቀን አክብረዋል፡፡

በሒሮሽማ ከተማ የተጣለው ‹‹ትንሹ ልጅ›› እና የናጋሳኪው ‹‹ወፍራሙ ሰውዬ›› የተባለ ስያሜ የተሰጣቸው ሁለቱ የአቶሚክ ቦምቦች ጃፓን ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች እጇን እንድትሰጥ ያስገደዷት ሲሆን፣ የኑክሌር ቦምብ ጥቃትን በአገሯ ያስተናገደች የመጀመርያዋ አገር አድርጓታል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታም የመጨረሻዋ ሆናለች፡፡ ከዚያ ወዲህ አገሪቱ ከኑክሌር የፀዳ ዓለም እንዲፈጠር ቀዳሚውን ሚና በመጫወት ትታወቃለች፡፡ ከዚሁ ጋር የተገናኙ  ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ስምምነቶችን በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ፈርማለች፡፡ በመሆኑም እስካሁን የኑክሌር የጦር መሣሪያ አታመርትም፡፡ ሆኖም ለኃይል ምንጭነት የኑክሌር ኃይልን ታመርታለች፡፡

ለጃፓናውያን የኑክሌር የጦር መሣሪያ ማምረት የሒባኩሻዎችን መብት እንደመርገጥ ይቆጠራል፡፡ ሒባኩሻ ጃፓንኛ ቃል ነው፡፡ የቃሉ ቀጥተኛ ትርጎሜ በሁለቱ የጃፓን ከተሞች በተጣሉ የኑክሌር ቦምቦች ፍንዳታ ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸው፣ ነገር ግን በሕይወት የተረፉ ጃፓናውያንን ለመግለጽ ከጥቃቱ ወዲህ በጃፓናውያን የተፈጠረ ቃል ነው፡፡ ሒባኩሻዎች ለኑክሌር ጨረር በመጋለጣቸው ምክንያት ከደረሰባቸው ጉዳት ጋር በተገናኘ በሌላው ኅብረተሰብ መገለላቸው የሚያስጨንቃቸው ከመሆኑም ባሻገር፣ መንግሥት ነፃና ዘላቂ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ለበርካታ ዓመታት እንደ አንድ የተለየ የኅብረተሰብ ክፍል በመሆን ከፍተኛ ትግል አድርገዋል፡፡ በዚህም ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በተለየ የጤና አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ መብቶች ተከብረውላቸው በነፃ እያገኙ ይኖራሉ፡፡ ሒባኩሻዎች የኑክሌር ምርት በጃፓንም ሆነ በየትኛውም የዓለም ክፍል እንዳይመረት ከፍተኛ ቅስቀሳ ለማድረግ ራሳቸውን የሰጡ አክቲቪስቶችም ናቸው፡፡ ለዚህም ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰባት አሥርት ዓመታት በኃላም ቢሆን በተለያዩ የጤና እክሎች ላይ ቢቆዩም፣ በየዓመቱ ከሁሉም ሥፍራ በመሰባሰብ ለዓለም ማኅበረሰብ ከኑክሌር የፀዳች ዓለም እንድትፈጠር መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ በቅርቡ በጃፓን ምድር የተከበረው የመታሰቢያ በዓል ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው፡፡

በዓለማችን አወዛጋቢና አደገኛ ከሚባሉ የፖለቲካ ክስተቶች አንዱ የኑክሌር የጦር መሣሪያ ምርት ጉዳይ ነው፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ላይ የተወሰኑ አገሮች የመሣሪያው ባለቤት ነበሩ፡፡ እንደ አሜሪካና የሶቪየት ኅብረት፡፡ እነዚህ ሁለቱ ያላቸውን ኃይል በፍጥነት ከማጠናከር ይልቅ ቅነሳ እያሳዩ መጥተዋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ‹‹ቨርቲካል ፕሮሊፍሬሽን›› በሚሉት እየቀነሰ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ ከምርት ጋር በተገናኘ ትልቁ አሳሳቢው ጉዳይ ከዚህ ቀደም ኑክሌር ያልነበራቸው አገሮች ለመታጠቅ የሚያደርጉት ጥድፊያና ተነሳሽነት ዋነኛው ችግር መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ‹‹የሆሪዞንታል ፕሮሊፍሬሽን›› ብለውታል  እየጨመረ መሆኑን በመግለጽ፡፡

ህንድና ፓኪስታን መሣሪያውን ታጥቀዋል፡፡ እስራኤልም ትታማለች፡፡ ከዚያም ባለፈ የኑክሌር ምርት ለመግታት የተዘጋጀውን ስምምነት ‹‹ኑክሌር ነን ፕሮሊፍሬሽን›› ስምምነት አልፈረመችም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰሜን ኮሪያና ኢራንም እንዳላቸው እየተደመጠ ነው፡፡ ጥቂቶች ደግሞ የነበራቸውን ወደ ማውደም ደረጃም የተሸጋገሩ አሉ፡፡ ለአብነት ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ1991 በራሷ ፍቃድ ስድስት ያለቀላቸው የኑክሌር ቦምቦችን አውድማለች፡፡ ዩክሬንና ቤላሩስ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ የሶቬየት ኅብረት መፈረካከስ ተከትሎ ቀደም ሲል ወርሰው የነበሩትን ለሩሲያ መልሰዋል፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ከማድረግ ጥረት ጋር ተያይዞ የወሰዱት ዕርምጃ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የኑክሌር መሣሪያ ሥርጭት ጉዳይን አስመልክተው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እ.ኤ.አ. በ1963 እንደተናገሩት ቁጥጥር ካልተደረገ፣ ከሃያ የማያንሱ አገሮች የኑክሌር መሣሪያ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ታጠቁት አገሮች ጎራ (ካምፕ) መቀላቀላቸው እንደማይቀር ትንበያቸውን አሳውቀው ነበር፡፡ የተናገሩት አልቀረም፡፡ በአጭር ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኑክሌር ማብላያ ወደ መትከል የተሸጋገሩ አገሮች ቁጥር ጨመረ፡፡ በዚህም ኑክሌር ያልታጠቁ አገሮች እንዳይታጠቁ ክልከላ የሚያደርገው ስምምነት ትርጉም እየሆነ መጣ፡፡ የስምምነቱ ዋና መነሻ ሐሳብ የነበረው ሥርጭቱ ገደብ ካተበጀለት ብዙ አገሮች የኑክሌር ባለቤት ከሆኑ፣ መሣሪያው ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት ዕድል የዚያኑ ያህል ይጨምራል የሚል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1968 የተፈረመው ይኼው የዕገዳ ስምምነት መርሆዎቹ ይኼንኑ ዋነኛ ግብ ማሳካትን ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ፡፡

የዕገዳ  ስምምነት መርሆች ከሆኑት መካከል የኑክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤት የሆኑ አገሮች ወደ ሌሎች ኑክሌር አልባ አገሮች የኑክሌር ቴክኖሎጂ እንዳያሸጋግሩ፣ ኑክሌር የሌላቸው አገሮች የኑክሌር የጦር መሣሪያ እንዳያለሙ፣ ሁሉም የኑክሌር መሣሪያ የሌላቸው ነገር ግን ኑክሌር ለኃይል ምንጭነት ለመጠቀም የሚያስቡና የሚያለሙ ከሆነ ከዓለም አቀፍ አቶሚክ የኃይል ኤጀንሲ ጋር በየወቅቱ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ስምምነት እዲያደርጉ፣ እንዲሁም ቀደም ሲል የኑክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቁ አገሮች ተጨማሪ ምርት ላለማምረትና ያላቸውንም ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ድርድር ውስጥ እንዲገቡ የሚሉ ናቸው፡፡ 

በዚሁ መሠረት በዓለማችን በኑክሌር አጀንዳ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ምክክሮች፣ ድርድሮችና ስምምነቶች ከላይ የተመለከቱ አራት መሠረታዊ መርሆችን መነሻና መድረሻ ያደረጉ ናቸው፡፡ በእርግጥ የኑክሌር ሥርጭት ዕገዳ ስምምነት ድርድር በተካሄደበት ወቅት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ቻይና የኑክሌር የጦር መሣሪያ ቀደም ሲል የታጠቁ መሆናቸው ዕውቅና ያለው ነው፡፡ መሣሪያውን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት የወሰዱት ተጨባጭ ዕርምጃ አለመኖሩ፣ በሌላ በኩል ሌሎች እንዳይታጠቁ ዕገዳ ለማድረግ መደራደሩ የስምምነቱን አተገባበር ፈታኝ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ 

ከዚሁ የኑክሌር መሣሪያ ጋር በተገናኘ በዋናነት ከላይ የተመለከቱ መርሆዎችን መነሻ በማድረግ የተመሠረቱና የተዘጋጁ ስምምነቶች፣ ፕሮግራሞች፣ ነፃ ቀጣናዎች፣ ኤጀንሲዎችና ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ ለአብነት የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ፣ የኑክሌር አቅራቢ ቡድኖች፣ የኑክሌር ሥርጭት ደኅንነት፣ በርካታ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ ቀጣናዎች ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ አገሮች ያሉዋቸውን ጠቅላላ ኑክሌር ነክ ቁሳቁሶችን ለአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ እንዲገልጹ ይጠበቃል፡፡ ይህም ኤጀንሲው ኑክሌር የሌላቸው አገሮች የኑክሌር ሥርጭት ዕገዳ ስምምነቱን መተግበር አለመተግበራቸውን ለማጣራት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ አገሮቹ ፈቅደው ያላቸውን  ፋሲሊቲ የማያሳዩ ከሆነ ከላይ የተገለጹ መርሆዎች ተጥሰው የመገኘት ዕድል ይከሰታል፡፡ በዘጠናዎቹ መጀመርያ አካባቢ በኢራቅ የኪላደሲቲን የኑክሌር የጦር መሣሪያ ፕሮግራም መታየት፣ በአገሮች ያልተገለጹ የኑክሌር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አመላካች መሆኑን አቶሚክ ኤጀንሲው ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ከላይ የተገለጹ መርሆችን ለማስከበር ከተመሠረቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው የኑክሌር አቅራቢ ቡድን የኑክሌር የጦር መሣሪያ ልማትን ከመግታት አንፃር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ቡድኑ በቁጥር 30 አገሮችን ያቀፈ ነው፡፡ የኑክሌር ግብዓት ቁሳቁሶችን፣ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ነው፡፡ ቡድኑ በኤክስፖርት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችለው መሪ መመርያ በማዘጋጀት የጋራ ምክሮችንም ያደርጋል፡፡ የኑክሌር አቅራቢ ቡድኑ ዋነኛ ዓላማ አባላቱ ለገበያ የማያቀርቧቸው ኑክሌር ነክ ዕቃዎች፣ በተለይም ኑክሌር ለማበልፀግ የሚረዱ ጥሬ ዕቃዎችና ቴክኖሎጂዎች የኑክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት ፍላጎቱ ወዳላቸው አገሮች  እጅ እንዳይገቡ ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡ የዚህ ቡድን ተግዳሮት ደግሞ አባል አገሮቹ የሚዘጋጀውን መሪ መመርያ የአገራዊ ሕጎቻቸው አካል አድርገው እንዲተገብሩት ከማድረግ ባለፈ፣ መመርያውን  የሚያስተገብር ሥልጣን ያለው የበላይ አካል የለውም፡፡  በመሆኑም አተገባበሩ በአገሮቹ ሙሉ ይሁንታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

የኑክሌር መሣሪያ ሥርጭት ደኅንነት ኢንሼቲቭ በበኩሉ ኢመደበኛ ኢንሼቲቭ ሲሆን፣ የኑክሌር መሣሪያ ቁሳቁሶች ወደ አሸባሪዎች እንዲሁም መሣርያውን ለማልማት ፍላጎትና ፕሮግራም ወዳላቸው አገሮች እጅ እንዳይገባ መከላከል ነው፡፡ ይህ ኢንሼቲቭ እ.ኤ.አ. በ2003 በፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ይፉ ከሆነ ወዲህ 97 አገሮች ድጋፋቸውን የገለጹ ሲሆን፣ 21 ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ አርጀንቲናና ጃፓን የመሳሰሉት የኦፕሬሽናል ኤክስፐርት ቡድን አባላት በመሆን ኢንሼቲቩን ያስተግብሩታል፡፡ ተሳታፊ አገሮች በባህር፣ በአየር እንዲሁም በምድር በሚጓጓዙ የመጓጓዣ ዓይነቶች ላይ ክትትል  በማድረግ፣ አውዳሚ የጦር መሣሪያ እንዲሁም መሣሪያውን ለማምረት የሚረዱ የምርት ግብዓቶች ወዳልተፈለገ ሥፍራ እንዳይጓጓዙ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡

ይኸኛውም ኢንሼቲቭ የዓለም አቀፍ ሕግጋት ጉዳዮችን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት በአገሮች መካከል ቅራኔን የሚያጭሩ ጉዳዮችንም ሲፈጥር የቆየ ነው፡፡ የኢንሼቲቩ ተሳታፊ አገሮች ማናቸውንም ተጠርጣሪ መርከቦች፣ አውሮፕላኖችና የብስ ላይ የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች አውዳሚ የጦር መሣሪያ መያዛቸውን ከጠረጠሩ በየትኛውም የውኃ ክልልና በማናቸውም ሥፍራ በማስቆም፣ አውሮፕላንም ከሆነ እንዲያርፍ በማስገደድ ማጣራት፣ ከተገኘም ዕርምጃ መውሰድ የኢንሼቲቩ ዓላማ በመሆኑ እንደተገለጸው ከሉዓላዊ አገሮች ድንበር መጣስ ጋር የተያያዙ ውዝግቦችን ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ 

የኑክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ ቀጣና ሌላኛው የሥርጭት ቁጥጥር መንገድ ነው፡፡ በእነዚህ ቀጣናዎች መሣርያውን ማልማት፣ ማምረት፣ ማከማቸት፣ በግዥም ሆነ በተለያየ መንገድ ባለቤት መሆን ሕገወጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተለያዩ ቀጣናዎች በተለያዩ አኅጉራት ይገኛሉ፡፡ ለአብነት የአንታርቲክ ስምምነት፣ ሳውዝ ፖስፊክ- የራሮቶንጋ ስምምነት፣ የላቲን አሜሪካና ካሪቢያን-የትላቴሎኮ ስምምነት፣ የደቡባዊ ምሥራቅ ኤዥያ-ባንኮክ ስምምነት፣ አፍሪካ-ፔሊንዳባ ስምምነት የነፃ ቀጣናዎቹ ምሥረታ ስምምነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ነፃ ቀጣና ከመመሥረት ጎን የኑክሌር መስፋፋትና የኑክሌር መሣሪያ ባለቤቶች ያላቸውን ክምችት እንዲቀንሱ የሚጠይቁም ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም መንገዶች አውዳሚ የጦር መሣሪያውን መስፋፋት ለመግታት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፍ ሥልጣን ተሰጥቶት በበላይነት የሚያስፈጽም አካል እስከሌለ ድረስ፣ አገሮች ወይም መንግሥታት ችላ ካሉት የሚፈለጉ ውጤቶችን ማስመዝገብ አይቻልም፡፡ አብዛኞቹ የሚተገበሩት በአገሮች በጎ ፈቃድ ላይ በመመሥረት በመሆኑ፡፡ ለዚህም ነው ህንድ፣ ፓኪስታን፣ እስራኤልና  ሰሜን ኮሪያ ወደ ባለቤትነት እንደተሸጋገሩ የሚነገረው፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ሥርጭት ዕገዳ ስምምነት ፈራሚ አገር ብትሆንም፣ ግዴታዋን ምን ያህል ወደ ጎን እንዳለች ሰሞነኛውን የዓለም የፖለቲካ ትኩሳት መመልከት በቂ ነው፡፡ በአሜሪካ አንዲት ግዛት ላይ ጥቃት ለመሰንዘርም ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ይፋ አድርጋለች፡፡ አሜሪካም በበኩሏ አንዲት ጥቃት ከተፈጸመብኝ አፀፋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ሁሉን ሸክፊያለሁ ብላለች፡፡ ከደቡብ ኮሪያ ጋርም የወታደራዊ ልምምድ ጀምራለች፡፡ ሰሜን ኮሪያ ተደደጋሚ ሚሳይል የማስወንጨም ሙከራ ስታካሂድ በመቆየቷ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደጋሚ ማስጠንቀቂያ እየሰጠና ማዕቀብ እየጣለ ቢቆይም፣ አገሪቱ ከድርጊቷ ልትታቀብ አለመቻሏ አሁን ዓለም አቀፍ የኑክሌር ውጥረት ተከስቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኑክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ካለፉት የቀዝቃዛው ጦርነት ልምዶች የተለዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ አንደኛው አመለካከት የኑክሌር ባለቤት የሆኑ አገሮች መበራከት ለዓለም ሰላም አዎንታዊ ሚና አለው የሚለው ነው፡፡ መሣሪያውን የታጠቁ አገሮች መበራከት መሣሪያው ጥቅም ላይ እንዳይውል ያደርጋል የሚል መነሻ አለው፡፡ ለዚህም መከራከሪያው መሣሪያው በአንደኛው ወገን ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ የሚከሰት ከሆነ፣ ሌላኛው የታጠቀ በመሆኑ የመጠቀሙ ዕድል ይሰፋል፡፡ በዚህም አሸናፊና ተሸናፊ በሌለበት የጋራ ጥፋትና ውድመት ይመጣል፡፡ በመሆኑም  በአገሮች መካከል የኃይል ሚዛንን ብቻ በመጠበቅ ከመፈራራት የመነጨ መከባበር ስለሚፈጠር መሣሪያውን የሚታጠቁ አገሮች መብዛት፣ በዓለም ሰላም ያሰፍናል የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱ ናቸው፡፡  ሌላኛው አስተሳሰብ ደግሞ የኑክሌር መሣሪያ ታጣቂ አገሮች ቁጥር መጨመር ከተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ለዕልቂት በር የሚከፍት እንደሆነ የሚያምን ነው፡፡

የኑክሌር ባለቤት አገሮች ቁጥር መጨመር ለዕልቂት በር የሚከፍቱ ስለመሆናቸው የሚነሱ ነባራዊ ምክንያቶችን እንመልከት፡-

የኑክሌር ባለቤት ለመሆን የሚያልሙና እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የተወሰኑ አገሮች መሪዎች  የግል ባህሪ ጨካኝ መሆን፣ እነኝህ መሪዎች መሣሪያውን ካለሙት በኋላ በማንኛውም ባሻቸው ጊዜ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ፣ ከዚህ አንፃር የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ከዓለም መሪዎች ተገልለው መኖራቸው፣ የአገሩ ሕዝብ በድህነት ሲማቅቅ አገሪቱ ካላት የኢኮኖሚ አቅም በላይ በጦር ኃይል በማጠናከር ከዓለም ቁንጮ አድርገዋታል፡፡ የሚያስተዳድሩት ሕዝብ በረሃብ እየተገረፈ አገሪቱን የመሣሪያ መከማቻ አድርገዋታል፡፡ ከዚህ የበለጠ ጭካኔ የለም፡፡ በመሆኑም ሰውዬው በሌሎች ጠላቶቼ በሚሉዋቸው አገሮች ላይ የኑክሌር ቦምብ ለመጣል ወደ ኋላ የማይሉ ናቸው፡፡ በወግ አጥባቂው በሺያ ሙላህ የምትመራዋ ኢራን እ.ኤ.አ. በ2005 ፕሬዚዳንት መሐመድ አህመድ ነጃድን የአገሪቱ መሪ አድርጋ በመረጠቻቸው ወቅት በአንደበታቸው ስለእስራኤል ሲናገሩ፣ ‹‹ከዓለም ካርታ መጥፋት ያለባት አገር›› ብለዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት የጥላቻ አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎች ለጥፋት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በመሆኑም ሰዎቹ በዚህ ባህሪያቸውና ፍላጐታቸው ኑክሌት እጃቸው ላይ ካስገቡ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፡፡
በርከት ያሉ አገሮች የኑክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤት ከሆኑ የሰውም ሆነ ቴክኒካዊ ስህተቶች አደጋዎችን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ፣
በአሁን ወቅት የኑክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን የሚፈልጉ አገሮች እንዲሁም ባለቤቶቹ በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት ባለመግባባት የጦርነት አየር የሚነፍስባቸው ቀጣናዎች መሆናቸው፣ ለአብነት ፓኪስታንና ህንድ በካሽሚር  ጉዳይ፣ ኢራንና እስራኤል በጠላትነት የሚታዩ መሆናቸው፣ የኮሪያ ልሳነ ምድር በዓለም አደገኛ ከሚባሉ ሥፍራዎች አንዱ መሆኑ፡፡
የአውዳሚ መሣሪያውን የሚታጠቁ አዳዲስ አገሮች መፈጠር ሌሎችም እንዲታጠቁ ማነሳሻ መሆኑ ይኼም አደጋውን ከፍ እንደሚያደርግ፣ በእስያ አኅጉር የሰሜን ኮሪያ ኑክሌር የመታጠቅ ምልክት፣ ጃፓን ማበልፀጓን እንድትቀጥል በር መክፈቱ (ለጊዜው ለኃይል ጥቅም ቢሆንም)፣ በሺያ አስተዳደር ሥር ያለችው ኢራን ከታጠቀች የሱኒ ዓረብ አገሮችን እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉትን እንደሚያነሳሳ በአብነት ይነሳል፡፡
አዳዲሶቹ የኑክሌር ታጣቂ አገሮች የመሣሪያው አያያዝ ልምድ ስለማይኖራቸው ከዚሁ ጋር የተገናኙ  ችግሮች ቢከሰቱ በበቂ ሁኔታ የመከላከል አቅም ማደራጀት ስለማይችሉ፣ የጠላት ጥቃት ከተከሰተባቸው ውድመቱ የከፋ መዘዙም ከባድ ይሆናል፡፡
የኑክሌር የጦር መሣሪያ መበራከት በአሸባሪዎች እጅ መሣሪያው እንዲገባ ከፍተኛ ዕድል ይፈጥራል፡፡
እነዚህ  ከላይ የተዘረዘሩ ጉዳዮች የኑክሌር መሣሪያ መስፋፋትን ከሰላሙ ይልቅ ጥፋቱ ይበዛል የሚሉ ጠበብቶች የሚያስቀምጧቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ የኑክሌር አውዳሚነትና ዘመን ተሸጋሪ መዘዝ ጃፓናውያን በተግባር ዓይተውታል፣ የተቀረው ዓለምም ሰምቶታል፡፡ ሆኖም ዛሬም ድረስ የኑክሌር ጉዳይ አገሮችን ወደ ፖለቲካና ወታደራዊ ውጥረት ከቷል፡፡ አገሮች ኑክሌር ለሰላማዊና ለኃይል ምንጭነት እንዲጠቀሙ በሩ ክፍት መሆኑ፣ ይኼን ለማስፈተሽና ለማሳየት ፈቃደኛ ለመሆን የሚያሳዩት ዳተኛነት ሌላው የዓለማችን ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ የኃይል ሚዛን ጥበቃ የሚባል አስተሳሰብ አገሮችን አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ ከማድረግ ባሻገር የባላንጣነትን መንፈስ እያፋፋ፣ በአንፃሩ ወደ ፍጥጫ እንዲገቡ የሚጋብዝ ሆኗል፡፡ የኑክሌር ታጣቂ አገሮች የዓለም ዘብና ተቆጣጣሪ መንግሥት ለመሆን የሚያሳዩት አዝማሚያ በሌሎች ላይ የሚፈጥረው የደኅንነት ሥጋት፣ በኑክሌር መሣሪያ ፍተሻ ሰበብ የሚፈጸሙ የሉዓላዊነት ጥሰቶችና በደሎች፣ እነዚህ ሁሉ የኑክሌር ጥያቄዎች በአንድ ትውልድ ብቻ የማይመለሱ ቢሆንም በየደረጃው የሚያስፈልገው ምላሽ ካልተሰጠ ኑክሌር ለዓለም ሕዝብ ሥጋት እንጂ ሰላምና ዕድገት ሊያመጣ አይችልም፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ኑክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ፍላጎት ካላቸው አገሮች አንዷ ነች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2037 የኤሌክትሪክ ኃይል መጠኗ ወደ 37,000 ሜጋ ዋት ለማድረስ ፍለጎት ያላት ሲሆን፣ ከዚሁ መጠን 1,200 ሜጋ ዋት ከኑክሌር ኃይል የሚመነጭ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለዕርዳታ ሰጪዎች፣ ለፋይናንሰሮችና ለምሁራን በተዘጋጀ መድረክ ላይ ከወራት በፊት አሳውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ እ.ኤ.አ. ጁን 2017 የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሩሲያ አንድ ተቋም ጋር የኑክሌር መሠረተ ልማት ማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የኑክሌር ቴክኖሎጂን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ፕሮግራሞችን ለመተግበር፣ እንዲሁም በግብርናና በሕክምና ዘርፎች የኑክሌር ውጤቶችን መጠቀም የሚቻልባቸውን ዕድሎች መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ይህ ስምምነት ኑክሌርን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል አገራችን ከሌላ አገር ጋር የፈረመችው የመጀመርያው ስምምነት ነው፡፡ በመሆኑም አገራችንም በሒደት ለሰላማዊ ጥቅም የሚውል ኑክሌር ባለቤት የምትሆን ከሆነ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ውስጥ መግባቷ የማይቀር ይሆናል፡፡ አንደኛው በአቶሚክ ኤጄንሲ በየጊዜው ለመፈተሽ በሩዋን ክፍት ማድረግ ይሆናል፡፡ ሰላም!

፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡