Skip to main content
x
የአልማዝ አያና የድል ድባብ በለንደን

የአልማዝ አያና የድል ድባብ በለንደን

በእንግሊዝ መዲና ለንደን እየተካሄደ ባለው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. 10 ሺሕ ሜትር ውድድር አልማዝ አያና ያሸነፈችው፣ ዓምና በሪዮ ኦሊምፒክ እንዳደረገችውና እንደለመደችው ከግማሽ በላይ የሆነውን ርቀት ብቻዋን በመሮጥ ነበር፡፡ አልማዝ በ30:16.33 ደቂቃ በርካቶችን በደረበችበት ፈጣን አሯሯጧ፣ እሷን ተከትላ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ጥሩነሽ ዲባባ ናት፡፡ ወርቅና ብር ያጠለቁት ሁለቱ አትሌቶች ከድላቸው በኋላ በአጭር ርቀት ሩጫ የዓለም ቁንጮ ከሆነውና በ100 ሜትር ሦስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀው ጃማይካዊው ዩዜን ቦልት ጋር ፎቶ ተነስተዋል፡፡ የምስሉ ቅርፅ ‹‹ሐ›› መስሏል፡፡ ሐምሌ 30 ቀን በተካሄደው የወንዶች ማራቶን ውድድርም ታምራት ቶላ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳልያ አግኝቷል።

***

እንደ አትሌት የሚሠለጥኑ የ85 ዓመት አዛውንት

በቻይና ዢያን ነዋሪ ናቸው፡፡ 85 ዓመት ቢሞላቸውም፣ እየተገለባበጡ እየሮጡና በተለያዩ የሰውነት ማፍታቻ ማሽኖች ላይ እየወጡ የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ኤስኤን እንደሚለው፣ አዛውንቷ የአካል ብቃት እንቅስቃሴውን ሲያቀላጥፉት ጎረምሳ ይመስላሉ፡፡ በየቀኑ አትሌቶች የሚያደርጓቸውን ዓይነት ልምምዶችም ያደርጋሉ፡፡