Skip to main content
x
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ የሕዝብ ፍላጎትም አይረሳ!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ የሕዝብ ፍላጎትም አይረሳ!

ለአሥር ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ሲነሳ፣ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ ምክንያት የነበረው የሰላምና መረጋጋት መደፍረስን መቀልበስ በመቻሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አገር በምንም መመዘኛ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወድቃ መብት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ወዘተ. እያሉ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው አገርን ለአደጋ የሚዳርግ ችግር ሲፈጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሆነው ይኼ ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስተው የነበሩ ሁከቶችን በመደበኛው ሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ለስድስት ወራት ተደንግጓል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ለአራት ወራት ተራዝሟል፡፡  በፓርላማ ፀንቷል፡፡ አሁን ደግሞ ፓርላማው በአስቸኳይ በተጠራው ስብሰባ በቀረበለት ሪፖርት መሠረት አንስቶታል፡፡ መንግሥት ካለፈው መጠነ ሰፊ ችግር በመማር ካሁን በኋላ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይገባበት ማዕቀፍ መፍጠር አለበት፡፡ የእዚህ ማዕቀፍ ዋነኛ ማጠንጠኛ ደግሞ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ጥርጊያውን ማመቻቸት ነው፡፡ መፍትሔውም እሱ ነው፡፡ ሕዝብም እየጠበቀ የነበረው ይህንኑ ነው፡፡

      ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያንዳንዱን የመንግሥት ዕርምጃ እያየ ነው፡፡ እያንዳንዱ ድርጊትም ከሕዝብ አያመልጥም፡፡ የሁሉም ነገር ዳኛ ሕዝብ ነውና፡፡ ከዚህ ቀደም አገሪቷን ለከፍተኛ ሥጋት የዳረገው ሁከት የተቀሰቀሰው ሕዝቡ ውስጥ የተጠራቀመው ብሶት በመገንፈሉ ነው፡፡ ሕዝብን በየደረጃው የሚያዳምጠው በመጥፋቱ የአገር ህልውናን አደጋ ውስጥ የሚከት ክስተት አጋጠመ፡፡ ደም አፋሳሽ ስለነበረም የበርካታ ዜጎች ክቡር ሕይወት አለፈ፡፡ የአገር አንጡራ ሀብትም ወደመ፡፡ ከዚህ ሁሉ ውርጅብኝ በኋላ ሕግን በተለምዶ አሠራር ማስከበር ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፡፡ ካሁን በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ውስጥ መዘፈቅ በፍፁም መታሰብ የለበትም፡፡ በዚህ ሥልጡን ዘመን ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት ያስንቃል፡፡ ይልቁንም በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት እንዲፈጠር መደላድሉን ማመቻቸት ያስከብራል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ከማንም በላይ ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ መንገድ መራመድ ሲቻል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ምቹ የሆኑ መፍትሔዎች ይገኛሉ፡፡

      በአሁኑ ጊዜ የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ከሚገመተው በላይ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ እየታገዘ በተለያዩ የሙያ መስኮች ራሱን እያበቃ ነው፡፡ ስለአገሩ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ያለው ዕውቀት ተመንድጓል፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ ዘመን 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ እርከኖች በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ በየዓመቱ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ወጣቶች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይመረቃሉ፡፡ ይህ ማለት ከጊዜ ወደ ጊዜ የጠያቂና የሞጋች ትውልድ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የመንግሥት ውሳኔ ሰጪ አካላት ከሚያስቡት በላይ ርቆ በመጓዝ ላይ ያለው ይህ ዕውቀት የጨበጠ ትውልድ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በሕግ፣ በምሕንድስና፣ በሥራ ፈጠራ፣ ወዘተ. ብቻ ሳይሆን በአጠቃይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብርቱ ሐሳብ አፍላቂም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለዚህ አገር ትልቅ ፀጋና እሴት ነው፡፡ የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ መጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ደግሞ ያኮራል፡፡ ፖሊሲዎች ሲረቀቁም ሆነ ስትራቴጂዎች ሲወጡ የባለ ራዕይ ወጣቶችን ሐሳብ ማካተት ለአገር ይጠቅማል፡፡ ወጣቶች እየተገፉ የአገር ባለቤትነት መንፈሳቸው ሲጎዳ ጠብ ይፈጠራል፡፡ ጠቡ ደግሞ ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ከዚህ ቀደም የተከሰተው ይህ ነው፡፡ ሕዝብ በሥርዓቱ ላይ እምነት ሲያጣ ግንባር ቀደሞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ባለፈው ትውልድ ዘመን በሚገባ ታይቷል፡፡

የመንግሥት የእያንዳንዱ ቀን ውሎ በሕዝብ ይገመገማል፡፡ ሕዝብ መንግሥትን የሚያየው በማይክሮስኮፕ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል አሠራሩ ግልጽነት ባይኖረው እንኳ ከሕዝብ የተደበቀ ምንም ነገር የለም፡፡ ሕዝብ ተሳትፎው እያደገና በአገር ጉዳይ ባለቤትነቱ ሲጨምር ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ የመንግሥት ተሿሚዎች አሠራራቸው ግልጽ ይሆናል፡፡ ብልሹ አሠራሮችና ዘረፋዎች ይቆማሉ፡፡ ሕዝብን በሥርዓት ማገልገል ያለበት ተሿሚ በሥልጣኑ መባለግ አይችልም፡፡ መሸፋፈን ሲበዛ ግን የአገር ሀብት የሌቦች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ፍትሕ ይደረመሳል፡፡ ሕዝብን የሚያዳምጠው ይጠፋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደር ይቀርና ሕገወጥነት የበላይነቱን ይይዛል፡፡ አመፅ ይቀሰቀሳል፡፡ የሰው ክቡር ሕይወት ይቀሰፋል፡፡ አገር የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ትገባለች፡፡ ሁሌም ሕዝብ መከበር አለበት፣ መደመጥ ይኖርበታል፣ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ መሆን አለበት እንጂ ጌታው አይደለም፣ የሕግ የበላይነት ይከበር፣ ወዘተ. የምንለው በሁከትና በውድመት አገር ስለምትጠፋ ነው፡፡ ሕዝብ ለባሰ ችግር ስለሚጋለጥ ነው፡፡ ከሕዝብ በላይ ምንም የለምና፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ወዘተ. ያሉባት ኅብረ ብሔራዊ አገር ናት፡፡ በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ የጋራ እሴት ያለው ኩሩ ሕዝብ የሚኖርባት ታሪካዊት አገርም ናት፡፡ በአንድነቱ ኮርቶ፣ ልዩነቶቹን ጌጥ አድርጎ ተጋብቶና ተዋልዶ የሚኖር ይህ የተከበረ ሕዝብ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በሕግ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ሊከበሩለት ይገባል፡፡ ማንኛውም ዜጋ የፈለገውን አቋም የማራመድ፣ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በፈለገው ቦታ የመኖርና የመሥራት፣ ወዘተ. ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው፡፡ በዚህች ታሪካዊት አገር ‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ› የሚባለው ጊዜ ያለፈበት አባባል ተሽሮ፣ ዜጎች ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን የፖለቲካ ዓውድ የመፍጠር መልካም አጋጣሚ አሁን ነው፡፡ ለአንድ ዓመት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ሁከት ዳግም እንዳይመለስና በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ ድንጋጌዎች በተግባር ሥራ ላይ እንዲውሉ ሕዝብ ይጠብቃል፡፡ ኢትዮጵያ ድህነትን የምትዋጋው ግማሽ  ጎፈሬ ግማሽ ልጩ ሆና መሆን የለበትም፡፡ በአንድ በኩል የልማቱ ግስጋሴ ላይ ተሰቅሎ ሲወራለት፣ የዴሞክራሲ ጉዳይ እታች እንዘጭ ብሎ ሲታይ ሊያሳፍር ይገባል፡፡

ሕዝብን ማክበር ሥልጡንነት ነው፡፡ ለሕዝብ ፈቃድ ተገዥ መሆን ዴሞክራትነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የታላቅነት ማሳያ ነው፡፡ ሕገወጥነት የሥርዓተ አልበኝነት መገለጫ ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት አገርን ያመሰቃቅል እንጂ ለማንም አይበጅም፡፡ አገርን በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉ ሌቦች የሚቀፈቀፉት ሕገወጥነትን ተገን አድርገው ነው፡፡ ሕዝብን የሚያስለቅሱት በብልሹ አሠራር ነው፡፡ እጅ በእጅ ከሚደረገው የጉቦ ቅብብል ጀምሮ እስከ ውስብስቡ የአገር ሀብት ዘረፋ ውስጥ የሚገባው የሕግ የበላይነት እየተናደ ነው፡፡ ሕዝብ ይህንን እየየ አይታገስም፡፡ የፈለገውን ያህል ‹ጥልቅ ተሃድሶ› ቢባል ማንንም አያምንም፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነት ለመኖሩ የሚረጋገጠው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መልክ ሲይዝ ነው፡፡ ይህ በሌለበት ከኩርፊያ በዘለለ አመፅ ይከተላል፡፡ በዴሞክራሲያዊ አግባብ መፈታት ያለባቸው ችግሮች ወደ ኃይል ያዘነብላሉ፡፡ ለሰላም፣ ለመረጋጋትና ለዕድገት ፀር የሆነ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን ለሕዝብ ፈቃድ የሚገዛ ሥርዓት ለመፍጠር መፍጨርጨር ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ የሕዝብ ፍላጎቶች አይረሱ የሚባለውም ለዚህ ነው!