Skip to main content
x
የአካባቢ ቀን ሲከበር

የአካባቢ ቀን ሲከበር

ለአየር ንብረት መዛባት የኢንዱስትሪው መበልፀግና የአኗኗር ዘይቤ እንደ ምክንያት ይነሳሉ፡፡ የአየር ንብረት መዛባቱ ደግሞ፣ ለመዛባቱ ምክንያት የሆኑ ሰዎችን ብሎም እንስሳትንና ዕፅዋትን እየጎዳ ነው፡፡ ድርቅና ጎርፍ እየተፈራረቁ ዓለምን እየፈተኗት ሲሆን፣ ብዙዎችም አየር መዛባት ምክንያት በከተሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች እየሞቱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ደሃ አገሮች አየር ንብረት ለውጡ መዛባት ቀዳሚ ተጠቂ ናቸው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ኃያላን አገሮች በገንዘባቸውም ጭምር እየደገፉ ቢሆንም፣ የአየር ንብረት ለውጡን ለመከላከል በሚያስችሉ ዕርምጃዎች ላይ ሁሉም አይስማሙም፡፡ አሜሪካ የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደማትቀበል ማሳወቋም ለአካባቢ ጥበቃው ሥራ ራስ ምታት ነው፡፡

ለዓለማችን ዋና ተግዳሮት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመታደግና ግንዛቤ ለመፍጠር የዓለም አካባቢ ቀን ይከበራል፡፡ በኢትዮጵያም ከግንቦት 28 ቀን እስከ ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚቆየው የአካባቢ ቀን በመከበር ላይ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ አካባቢ ፕሮግራም (ዩኤንፒ) አጋፋሪነት ‹‹ዜጎችንና ተፈጥሮን ማስተሳሰር›› በሚል መርህ በመከበር ላይ ያለውን የአካባቢ ቀን  አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገብረማርያም ባሳለፍነው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ፀጋዬ እንደሚሉት፣ ግሎባል ፈንድ በሚለው መዋቅር አማካይነት ለአካባቢ ጥበቃ ትልቋ ለጋሽ አሜሪካ ብትሆንም፣ አንድ አገር ከስምምነቱ ወጣ ማለት የዓለም አጠቃላይ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት አይደሉም፡፡ ሆኖም ተፅዕኖውን ዝቅ ለማድረግ የአውሮፓ ኅብረትና ቻይና ኅብረት እየፈጠሩ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ይህንን ውሳኔያቸውን ደግመው ሊያዩት ይችላሉ፡፡

ከግሎባል ፈንድ ተቋዳሽ መሆንና የኃያላን መንግሥታት ገንዘብ ፈሰስ ማድረግ ወሳኙ ጉዳይ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎንም ችግኝ ተከላ ትኩረት ይሰጣዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ተመናምኖ የነበረው የደን ሽፋን እያገገመ ቢሆንም ከችግኝ ተከላና መፅደቅ ጋር ተያይዞ ችግሮች ይነሳሉ፡፡

ይህንን አስመልክቶ አቶ ጸጋዬ እንደሚሉት፣  አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ቀደም ሲል ሦስት በመቶ ብቻ የነበረው የደን ሽፋን በአሁኑ ጊዜ ወደ 15.5 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ በየክፍለ ከተሞች አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ችግኞችን ከመትከል ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ያሉት ወንዞች መበከላቸውም ይነሳል፡፡ በወንዞች ላይ ከሚታዩት ተግዳሮቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ መጠራቂሚያ መሆናቸው ሲሆን፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ፣ ወንዞችን ለማልማትና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እያንዳንዱን ወንዝ አቅም በፈቀደ መጠን ለማልማት የሚያስችሉ ጅምሮች መኖራቸውን አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡

በወንዝና ወንዝ ዳርቻዎች ላይ ለብክለት መንስኤ የሆኑ አንዳንድ ድርጅቶችን ባለሥልጣኑ እያዘጋና እንዲስተካከሉ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ከሚሠሩ ሕንፃዎችና ለግንባታ ከሚውሉ መስተዋቶች ጋር በተያያዘም፣ በከተማዋ በመስተዋት ካሸበረቁ ሕንፃዎች ውስጥ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን ሳያልፉ የተገነቡ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

መሥሪያ ቤታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቆጣጠር የጀመረ ሲሆን፣ አምና ለአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ከቀረቡ 380 የሕንፃ ግንባታዎች መካከል ስምንቱ ውድቅ መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ዜጎችንና ተፈጥሮን በማስተሳሰር ላይ ያለመው የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀንም፣ ዜጎች  በተፈጥሮ ላይ በሚያደርጉት ተፅዕኖ ሳቢያ መልሰው እየተጎዱ መሆኑን በማጉላት፣ ችግኝ በመትከልና ግንዛቤ በመስጠት በኢትዮጵያ እየተከበረ ይገኛል፡፡

የአካባቢ ቀን ሲከበር በአገሪቷ ከግንባታ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከአኗኗር ጋር ተያይዘው ለአየር ብክለት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችም ይታወሳሉ፡፡