Skip to main content
x
የአዋሽ ወንዝ ሙላት በኦሮሚያና በአፋር ሥጋት ፈጥሯል

የአዋሽ ወንዝ ሙላት በኦሮሚያና በአፋር ሥጋት ፈጥሯል

  • ብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አደጋ ከተፈጠረ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ አለ

የቆቃ ኤሌክትክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመሙላቱና ለግድቡ ደኅንነት ሲባልም ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ እየተለቀቀ በመሆኑ፣ የሚለቀቀው ውኃም ከአዋሽ ወንዝ ገባሮች ጋር ተዳምሮ  በኦሮሚያና በአፋር ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

የክረምት ወራት እየተገባደደ ቢሆንም፣ በተለይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየጣለ ነው፡፡ የዝናቡ መጠንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የተሰበሰበው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የጎርፍ ግብረ ኃይል አመልክቷል፡፡

በዚህ መሠረት በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን የሚገኙት በአዳማና በፈንታሌ ወረዳዎች፣ በአርሲ ዞን በመርቲና በጀጁ ወረዳዎች፣ በአፋር ክልል ዞን ሦስት የሚገኙት በአሚባራ፣ በዱለቻ፣ በቡሬ በሙዳይቱና በገዋኔ ወረዳዎች የውኃ ሙላቱ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል፡፡

‹‹አዋሽ ወንዝ አጠገብ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም የመስኖ ሥራ የሚያካሂዱ ተቋማትና ግለሰቦች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤›› ሲል የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስጠንቅቋል፡፡

የአዋሽ ወንዝ ሙላት ከፍተኛ ኃይል ያለው በመሆኑ፣ ዳር ላይ የሚገኙ ትልልቅ ዛፎችን በመጣል አቅጣጫ ሊቀይር ስለሚችል ከፍተኛ የመጥለቅለቅ አደጋ ሊከሰት ይችላል ተብሏል፡፡

ኮሚሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የመስኖ እርሻ ተቋማት አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል፡፡ አደጋ ሊከሰት የሚችለው ከቆቃ ግድብ በታች ብቻ ሳይሆን፣ ከቆቃ ግድብ በላይ ባሉ አካባቢዎችም ጭምር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ እንዳለው፣ ከግድቡ በላይ ያሉ ደቡብ ምዕራብ አካባቢ የሚገኙት ኢሉ፣ ልዩ ዞን፣ ሰበታ፣ ሐዋዝ ወረዳ፣ ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦራ፣ ሊበን፣ ጭቋላና ሎሜ ወረዳዎች ከባድ ዝናብ በተከታታይ በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል በአካባቢው የሚገኙ የኅብረተሰበ ክፍሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል፣ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል፡፡

የቆቃ ግድብ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችም የግድቡ ውኃ ወደ ኋላ እየሠፋ የሚመጣ በመሆኑ፣ ከግድቡ እንዲርቁ ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ አደጋው ከተከሰተ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

‹‹ከዘጠኝ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች፣ በተወጣጡ ባለሙያዎች የጎርፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ ምግብም ሆነ ምግብ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ለማቅረብ ዝግጅቱን ተጠናቋል፤›› ሲሉ አቶ ደበበ ገልጸው፣ ‹‹አደጋ ከመከሰቱ በፊት ግን ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፤›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡