Skip to main content
x
የአውሮፓ ኅብረትን ዝቅተኛ የአፍላቶክሲን ደረጃ ያሟሉ በርበሬ ላኪዎች ከገበያ ውጭ የመሆን ሥጋት ገብቷቸዋል

የአውሮፓ ኅብረትን ዝቅተኛ የአፍላቶክሲን ደረጃ ያሟሉ በርበሬ ላኪዎች ከገበያ ውጭ የመሆን ሥጋት ገብቷቸዋል

  • ለሥጋታቸው መነሻው የመንግሥት አሠራር ነው

በርበሬን ጨምሮ የተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የሚተዳደሩ ድርጅቶች ከመንግሥት ዕውቅና የሚሰጣቸው በማጣታቸው ከአውሮፓ ገበያ የመውጣት ሥጋት እንዳደረባቸው ገለጹ፡፡ ለሥጋታቸው መነሻው ወደ አውሮፓ በሚልኩት በርበሬ ውስጥ የሚገኘውን አፍላቶክሲን የተባለ አደገኛ ኬሚካል መጠን በተፈቀደው ልክ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጣቸው የመንግሥት አካል በማጣታቸው ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በርበሬ ላኪዎች እንደገለጹት ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት በቅርቡ ባሻሻለው ሕግ መሠረት፣ ወደ አባል አገሮች የሚገባው በርበሬ በውስጡ እንዲኖረው የሚፈቀደው የአፍላቶክሲን ይዘት በኪሎ ግራም ከአሥር ማይክሮ ግራም መብለጥ የለበትም፡፡ ይሁንና ይህንን በመመልከት የኤክስፖርት ማረጋገጫ መስጠት የሚጠበቅባቸው መንግሥታዊ ተቋማት ለላኪዎቹ ማረጋገጫ ለመስጠት እያቅማሙ በመሆናቸው፣ የበርበሬ የወጪ ንግድ ከአውሮፓ ገበያ ውጭ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አቶ ሚሊዮን አሰፋ፣ ሚሊዮን አሰፋ ፉድ ስቶር ኤክስፖርት የተባለ ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ፣ ከሌሎች ምርቶች ባሻገር በበርበሬ ላኪነትም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አብዛኞቹ የበርበሬ ደንበኞቻቸው በስዊድን እንደሚገኙ ገልጸው፣ ለደንበኞቻቸው ለመላክ የጥራት ደረጃውን በላቦራቶሪ ያስመረመሩትን ከ2,300 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን በርበሬ፣ ማረጋገጫ የሚሰጥላቸው አካል በማጣት ለሦስት ወራት ያህል ተከማችቶ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባደረገው ምርመራ የአውሮፓ ኅብረት ካስቀመጠው የአሥር ማይክሮ ግራም ዝቅተኛ መጠን በእጅጉ ያነሰ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በላቦራቶሪው ውጤት መሠረት የአቶ ሚሊዮን በርበሬ ውስጥ የተገኘው የአፍላቶክሲን መጠን በአንድ ኪሎ ግራም ውስጥ የተገኘው 2.78 ማይክሮ ግራም አፍላቶክሲን በመሆኑ፣ ይህንን አመሳክሮና ናሙና ወስዶ በማረጋገጥ ዕውቅና የሚሰጥላቸው የመንግሥት ተቋም እንዳጡ አቶ ሚሊዮን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ፣ ይህንን የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በበኩሉ እንደ በርበሬ ያሉ የግብርና ምርቶችን የጥራትና የጤና ደረጃ የሚያረጋግጠው ግብርና ሚኒስቴር መሆኑን ጠቅሶ እንደመለሳቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ አዲስ የተዋቀረው የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ግብይትና ልማት ባለሥልጣን ስለጉዳዩ ይመለከተው እንደሆነ ሪፖርተር ጠይቆ፣ የምርት ልማትና ገበያ የማፈላለግ ድርሻ እንጂ የምርት ጤንነትንና ጥራትን መቆጣጠር የሥልጣን ወሰኑ ባለመሆኑ፣ ጉዳዩ እንደማይመለከተው ከባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይልቁንም ግብርና ነክ የወጪ ምርቶችን የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ሚኒስቴሩ መሆኑን ኃላፊዎቹ አረጋግጠዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ከሪፖርተር ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው የባለሥልጣኑ ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ግን ይህንን ውድቅ አድርጓል፡፡

ከምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ስለ ላኪዎቹ ሥጋት ምላሽ እንዲሰጡ ኃላፊዎችን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ቢሞከርም ሊሳካ አልቻለም፡፡ ከተቋማቱ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት ያልቻሉት እነ አቶ ሚሊዮን፣ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በመውሰድ መፍትሔ ለማግኘት መሞከራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትም መልሶ ወደ እነዚሁ ተቋማት እንደመራቸው ጠቅሰው፣ በመንግሥት ተቋማት መካከል በሚታየው የተንዛዛ ቢሮክራሲ ሳቢያ ምርቶቻቸው ለብልሽት እየተዳረጉባቸው እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር እንዲህ ባለው አሰልቺ ቢሮክራሲ ሳቢያ የኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ምርቶች ከአውሮፓ ገበያ ውጭ ለመሆን መቃረባቸውንም በመግለጽ ሥጋታቸውን እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በበርበሬ ምርት ህንድና ሜክሲኮ የኢትዮጵያ ድርሻ እየተቀራመቱ መምጣታቸው ሥጋታቸውን እንዳባባሰው ይጠቅሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር (ለሁለት በመከፈል የቅመማ ቅመም ዘርፉ ለብቻ እየወጣ የሚገኝ ማኅበር ነው) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ወደልደ ሰማያትም የላኪዎቹን ሥጋት ይጋራሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ ምግብ ነክ የግብርና ምርቶችንም ሆነ የእንስሳት መኖ ጤናማነትን የሚያረጋግጡ የላቦራቶሪ ተቋማት በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር ከሚገኘው ጊዜያዊ የምርት ማቆያና መቆጣጠሪያ ተቋም ውስጥ መካተት እንደሚኖርበት ጠቅሰው፣ ይኸው ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሲቀርብ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡

የሥነ ምግባር ችግር ባለባቸው ላኪዎች ሳቢያ ለጤና አሥጊ የሆኑ ምርቶች እየተላኩ የሚደርሰው ኪሳራ ሳያንስ፣ ዕውቅና የተሰጣቸው የመንግሥት ላቦቶራቶሪዎች አለመኖራቸውም ጉዳቱን እንደሚያባብሰው አቶ አሰፋ ይናገራሉ፡፡ የአውሮፓ የቅመማ ቅመም ገበያ በተለይም የኢትዮጵያ በርበሬ በጣም ተፈላጊነት ያለው ቢሆንም፣ ምርቱ በከፍተኛ ደረጃ አዋጭ በመሆኑ የኢትዮጵያን ላኪዎች በመቀናቀን ገበያውን መቆጣጠር የሚፈልጉ የሌሎች አገሮች ላኪዎች ኢትዮጵያውያኑን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው መታሰብ እንዳለበትም ይመክራሉ፡፡   

ከበርበሬ ባሻገር የለውዝ ምርትን ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍላቶክሲን ሳቢያ ችግር ሲገጥማቸው እየታየ ነው፡፡ አፍላቶክሲን ‹‹ኤስፐርጊለስ ፍሌቨስ›› እና ‹‹ኤስፐርጊለስ ፓራሲተከስ›› በተባሉ የፈንገስ ዝርያዎች የሚከሰት አደገኛ ኬሚካል ነው፡፡ ቢ1፣ ቢ2፣ ጂ1፣ ጂ2 የሚባሉ ዝርያዎችም አሉት፡፡ እነዚህ በሰብሎች ላይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ኤም1፣ ኤም2 የተባሉ በእንስሳት ተዋጽኦዎች ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎችም አሉ፡፡ B1 የሚባለው የአፍላቶክሲን ዝርያ ከሌሎቹ በተለየ አደገኛ ነው፡፡ የጨጓራ ካንሰር የሚከሰተው በዚሁ ቢ1 በተባለው የአፍላቶክሲን ኬሚካል አማካይት  እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ኤም1 በእንስሳት ተዋጽኦ ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል ሲሆን፣ እንደ ቢ1 ሁሉ አደገኛ ነው፡፡