Skip to main content
x
የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት በ39 የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመሠረተባቸው

የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት በ39 የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመሠረተባቸው

  • የመከላከያ ሚኒስቴርን ሚስጥር አሳልፈው ሰጥተዋል ተብሏል
  • በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ገንዘብ ማስቀመጣቸው ተጠቁሟል

አራጣ በማበደር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ፣ ተጠርጥረው ከታሰሩበት አራጣ ማበደር ወንጀል በተጨማሪ 38 ክሶች ተመሠረቱባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ አቶ ዓብይ ሦስት አራጣ ማበደር፣ ሁለት የባንክን ሥራ ተክቶ መሥራት፣ አራት በሕገወጥ የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስስሎ ማቅረብ፣ አራት ከፍተኛ የማታለል፣ ስድስት በሕገወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ መላክ፣ አምስት ግብር አለመክፈል፣ ሰባት የተሳሳቱና ሐሰተኛ ሰነዶችን ማቅረብ፣ አራት ተጨማሪ እሴት ታክስ አለመክፈልና ሦስት ከባድ የማታለል ወንጀሎችን መፈጸማቸውን አብራርቷል፡፡

ተከሳሹ አቶ ዳዊት ከበደ በተባሉ ግለሰብ የተመዘገበ አዳል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር የተመዘገበና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10 ውስጥ የሚገኝ ሚስማር ፋብሪካን በመያዣነት በመያዝና ስምንት በመቶ ወለድ የሚከፈልበት ውል በማዘጋጀት፣ 800,000 ብር ማበደራቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተበዳሪው በየወሩ በስምንት በመቶ ሒሳብ 64,000 ብር ለስድስት ወራት 384,000 ብር እንዲከፍሉ ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

ተበዳሪው የወሰዱትን ገንዘብ መክፈል ሲያቅታቸው ተከሳሽ በመያዣነት የወሰዱትን ለንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተበዳሪው የተጻፈ ደረቅ ቼክ እንደሚያስመቱባቸው በመንገርና በማስፈራራት፣ ‹‹ፋብሪካውን ሸጬልሃለሁ ብለህ ፈርምልኝ›› በማለት ድርሻቸውን ሙሉ በሙሉ መውሰዳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ አቶ ዓብይ ፋብሪካውን ከወሰዱ በኋላ፣ አቶ ለማ ለሚባሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ዜጋ በ380,000 ዶላር በመሸጥ፣ ክፍያውን በአቶ ዓብይ ስም ጀርመን ፍራንክፈርት እንዲተላለፍላቸው ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡ ሌሎች ንብረቶችን ለአራጣ ማካካሻ በመውሰድ ለተበዳሪው አቶ ዳዊት ከበደ 23,000 ብር ብቻ በመስጠት ፋብሪካውን ከነማሽነሪውና ሁለት ተሽከርካሪዎች መውሰዳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 715(ሐ)ን መተላለፋቸውን ጠቁሟል፡፡ ተመሳሳይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ በመጣስ፣ አቶ ዳንኤል ወንድወሰን ኢኤል ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚባለውን ድርጅታቸውን ቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የእሽሙር ማኅበር በመመሥረት ደልቢ ኮል ማይኒንግ የሚባል ማኅበር መሥርተው የሥራ ውል ከተፈራረሙ በኋላ፣ ለሥራ ማስኬጃ ለአቶ ዳንኤል 2,997,000 ብር በሁለት ወር አበድረው 12 በመቶ ወለድ ጨምረው እንዲመልሱ መስማማታቸውንና ከወለዱ ጋር ያላግባብ 3,017,000 ብር እንዲከፍሉ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ተከሳሹ ሌላው አራጣ በማበደር ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆኑትና የእንግሊዝ ዜግነት ባላቸው አቶ ደረጀ ተክለ ሚካኤል ላይ ነው፡፡ አቶ ዓብይ በ1998 ዓ.ም. እንግሊዝ አገር በሄዱበት ወቅት ከአቶ ደረጀ ጋር ተገናኝተው ስለቢዝነስ ሲነጋገሩ፣ የመኪና ኪራይ አዋጭ መሆኑን አቶ ዓብይ ሲነግሯቸው ሊሞዚን ገዝተው እንዲልኩ መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ደረጀ መኪናውን በ52,000 ዶላር ገዝተው የላኩ ሲሆን፣ መኪናውን ጂቡቲ ወደብ ሲደርስ ግን አቶ ዓብይ ጂቡቲ ከሚገኝ ነጋዴ እንደተሸጠላቸው በማስመሰል በራሳቸው ስም ኤልሲ ከፍተው ወደ ኢትዮጵያ ማስገባታቸውን ጠቁሟል፡፡ አቶ ደረጀ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሲጠይቋቸው ለቀረጥ ከፍያለሁ ባሉት 900,000 ብር ላይ በየወሩ ስምንት በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ እንደጠየቋቸውም ክሱ ይገልጻል፡፡ አቶ ደረጀ ተስፋ ባለመቁረጥ በሽምግልና ሲጠይቋቸው አቶ ዓብይ 250,000 ብር በመስጠት አጠገባቸው እንዳይደርሱ እንዳስጠነቀቋቸውም ክሱ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም አቶ ደረጃ ወደ አገር ተመልሰው ለመሥራት የሰነቁትን ተስፋ እንዳጨለሙባቸው ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ዓብይ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005ን በመተላለፍ፣ ኢትዮጵያውያንን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር በመላክ ለግለሰቦች በከፍተኛ ወለድ አራጣ በማበደር በርካታ ገንዘብ ማግኘታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ እንዲሁም የመንግሥትን ይዞታ በሕገወጥ መንገድ በመያዝ ፈቃድ ሳይኖራቸው የባንክ ሥራ በመሥራት፣ ግለሰቦችን በማታለል ገንዘብና ንብረት በመውሰድ፣ የመንግሥትን ግብር በማጭበርበር ያገኙትን ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በራሳቸው፣ በቤተሰባቸውና አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላነፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ለመኖሪያ፣ ለሆቴል ግንባታ የተለያዩ ስፋት ያላቸው የከተማ ቦታዎችና የአክሲዮን ድርሻዎች በመግዛትና በባንክ በማስቀመጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ተከሳሹ በወንጀል ተግባር የተገኘን ገንዘብ ወደ ውጭ አገር በማሸሽ ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው ኮሜርስ ባንክ ፍሉካን ቅርንጫፍ፣ አሜሪካ በሚገኙ ፒኤንሲ ባንክ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ፣ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ማስቀመጣቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

አቶ ዓብይ በባለቤትነት የሚመሩት አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ያስመዘገቧቸውን የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ሲያከራዩ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት በማካሄዳቸውም ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሹ ምንም ዓይነት የውጭ አገር ንግድ ወኪልነት ሳይኖራቸው ወይም የኮሚሽን ሠራተኝነት የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በፖላንድ ዋርሶ ከተማ የተመዘገበውንና ቢፖሮማስ ቢፕሮን ትሬዲንግ የሚባለው የውጭ ድርጅት ውክልና እንደሰጣቸው የገለጹ ቢሆንም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አለመረጋገጡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም አቶ ዓብይ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች ለመግዛት አውጥቶ የነበረውን ውስን ዓለም አቀፍ ጨረታዎች፣ በድርጅታቸው አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ስም ለመጫረት የጨረታ ማስከበሪያ ሲፒኦ በማጻፍ በጨረታው በመሳተፍና ወክሎኛል ያሉት ድርጅት ሲያሸንፍ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመቅረብ የማስረከብ ሥራ መሥራታቸው፣ በተፈቀደ የንግድ ፈቃድ የሚሠራን ሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው መሥራታቸውን አብራርቷል፡፡ የፖላንዱን ኩባንያ ተወዳድሮ ካሸነፈው ጠቅላላ ዋጋ ላይ አምስት በመቶ ኮሚሽን 2,922,163 ብር በውጭ አገር ከሚገኘው ሚስተር ጃርስለው ጋር በመመሳጠር ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ ማሸሻቸውንም አክሏል፡፡ የቀረቡትን መሣሪያዎችንም ፎቶ በማንሳት በግል ሞባይላቸውና አይፓድ ላይ በመጫን ለሕዝብ በግልጽ ያልታወቀ ሚስጥርነት ያለው ጉዳይ፣ ላልተፈቀደላቸው ለተለያዩ ሰዎች ያሳዩና መረጃ የሰጡ መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡

አቶ ዓብይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 691(1)ን በመተላለፍ የግል ተበዳይ የሆኑትን አቶ ሚኪያስ ጌቱና ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ የሺ ግዛው (ሞተዋል) የግል ይዞታ የሆነውንና ስፋቱ 118 ሜትር ካሬ ቦታ የአዲስ ቪው ሆቴል አዋሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ለልማት ቦታውን እንደፈለገው እንደነገሯቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሚከፍላቸው ካሳ ትንሽ ስለሆነ እሳቸው የተሻለ ገንዘብ እንደሚሰጧቸው በማሳመን ቦታውን እንደወሰዱባቸው ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ገልጿል፡፡ ሟች ቦታውን ያቆዩት ለልጃቸው እንደሆነ ለአቶ ዓብይ ሲነግሯቸው፣ ‹‹እሱን ወደ ውጪ እልከዋለሁ›› ያሏቸው ቢሆንም፣ ልጁን ግን የላኩት ደቡብ ሱዳን መሆኑን አስረድቷል፡፡ ቪዛ አውጥተው ወደ ውጭ እንዲሄድ እንደሚልኩለት አሳምነው ወደ ደቡብ ሱዳን የላኩት ቢሆንም፣ ሳይልኩለት በመቅረታቸው ወደ አገሩ መመለሱን ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡ አቶ ዓብይ ለወ/ሮ የሺ ልጃቸውን ወደ ውጭ እንደላኩላቸው በማሳመንና እሳቸውንም እንደሚረዷቸው በመግለጽ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል በማዘጋጀት፣ ባልተከፈላቸው 30,000 ብር የግዢ ውል በማስፈረምና እሳቸውን የራሳቸው እናት ቤት ወስደው እንዳስቀመጧቸው ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ወ/ሮ የሺ በነበሩበት ቤት ውስጥ ሞተው መገኘታቸውንም ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ ከባድ የማታለል ወንጀል መፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተው በአቶ ዓብይ፣ አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሚስተር ጃሮስላው ፋልኮልስኪ (በሌሉበት)፣ ቢፕሮማስ ቢፕሮን ትሬዲንግ ኤስኤ (በሌሉበት) እና በድለላ ሥራ እንደሚተዳደሩ የገለጹት አቶ ዮናታን ቦጋለ በላቸው ላይ ነው፡፡

አቶ ዮናታን ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ቢውሉም በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠበቃቸው አቶ ሞላ ዘገየ አመልክተዋል፡፡ ተከሳሹ በድለላ ለአቶ ዓብይ አንድ ተሽከርካሪ በ60,000 ብር ያሸጡ ቢሆንም፣ ሊብሬውን ከሻጭ ወደ አቶ ዓብይ አለመተላለፉን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መኪናው የአቶ ዓብይ አይደለም ማለታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ መኪናው አቶ አሚር አህመድ የሚባሉ ግለሰብ መሆኑን በመግለጽ የወንጀል ፍሬ የሆነን መኪና አታለው መውሰዳቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ፣ በከባድ የማታለል ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ጠበቃቸው በደንበኛቸው ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደማይከለክል በመጠቆም፣ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዓብይም ባለሀብት፣ የቤተሰብ ኃላፊና የአደባባይ ሰው መሆናቸውን የተናገሩት ጠበቃ ሞላ ዘገየ፣ እሳቸውም የተጠቀሱባቸው አንቀጾች ዋስትና እንደማይከለክሉ በመግለጽ እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ በሰጠው ትዕዛዝ በአቶ ዓብይ ላይ የቀረቡ ክሶች ዋስትና እንደማይከለክሉ አረጋግጦ፣ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ፣ ተደራራቢ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች ዋስትና እንደሚነፈጉ መግለጹን አሳውቋል፡፡ በመሆኑም የጠየቁትን ዋስትና ውድቅ አድርጎታል፡፡ አቶ ዮናታን ግን በ15,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ለጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡