Skip to main content
x
የአፈር ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ (1948 - 2009)

የአፈር ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ (1948 - 2009)

የኢትዮጵያ አርሶ አደር ምርታማነት ማሳደግ  የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችና የተሻሻሉ የመሬትና የአፈር ለምነት ማበልፀጊያ ዘዴዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ ይጠቀሳሉ፣ የአፈር ሳይንቲስቱ ተካልኝ ማሞ (ፕሮፌሰር)፡፡

ፕሮፌሰር ተካልኝ በየአካባቢው በስፋት የሚገኘውን የኮትቻ አፈር ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ የእርሻ መሣሪያ በማጠንፈፍ ምርታማነቱ እንዲጨምርና ቴክኖሎጂው በአርሶ አደሮች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው፣ ከሁለት አሠርታት ለሚበልጥ ጊዜ ድጋፍ በማድረጋቸውና ኅብረተሰብን ያሳተፈ የተፋሰስ ልማትን መርህ የተከተሉ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እንዲተገበሩ በማስቻላቸው ለዓለም አቀፍ ዕውቅና አብቅቷቸዋል፡፡

በ1996 ዓ.ም. የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንም ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም. የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የግብርና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባገለገሉባቸው ጊዜያት፣ በአሁኑ ወቅት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የማኅበረሰብ አቀፍ ተፋሰስ ልማት ስትራቴጂ በመንደፍና በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ረቂቅ ፖሊሲውን ማዘጋጀታቸው ይወሳል፡፡

ፕሮፌሰር ተካልኝ በአፈር ኬሚስትሪና ለምነት፣ በሰብል ጥናት፣ የአፈር መረጃና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማሳተማቸውም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጆርናል መሥራችና ዋና አዘጋጅ ሆነው መሥራታቸውን ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡

ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ፕሮፌሰር ተካልኝ በተለይ የአፈር መረጃ እንዲደራጅ ከማድረጋቸውም ባለፈ፣ አርሶ አደሩ ለምርት የሚጠቀመው ማዳበሪያ የየአካባቢውን አፈር መሠረት ያደረገ እንዲሆን የላቀ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ በቅርቡም የአፈር ጤናና ለምነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተው ለመንግሥት አቅርበዋል።

ከስኮትላንዱ አበርዲን ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ1985 በአፈር ኬሚስትሪና ለምነት በማስትሬት ዲግሪ፣ ቀጥሎም ዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁት ፕሮፌሰር ተካልኝ፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለሪፖርተር በላከው መረጃ መሠረት በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት፣ በተመራማሪነት፣ በደብረ ዘይት እርሻ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርነት፣ በአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ፣ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በማማከር ሠርተዋል፡፡ በአፈርና የአፈር ለምነት መረጃ አያያዝ ላይ ባበረከቱት የምርምር ውጤትም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በ2003 ዓ.ም. የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

ፕሮፌሰር ተካልኝ በ2006 ዓ.ም. ለያራ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ሽልማት፣ በ2007 ዓ.ም. በዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ዓለም አቀፍ ልዩ የአፈር አምባሳደርነት ሲመረጡ፣ የዓለም አቀፉ ማዳበሪያ ኢንዱስትሪ ማኅበርም የመሬት መሸርሸርን በመከላከሉ ረገድ፣ የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስና የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በነበራቸው ሚና በ2008 ዓ.ም. የኖርማን ቦርላግ ሽልማት ሰጥቷቸዋል፡፡

በሞሮኮ በሚገኘው የአፍሪካ አፈር ጥናት ማዕከል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት ፕሮፌሰር ተካልኝ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምናቸውን በሚከታተሉበት እንግሊዝ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን አስከሬናቸውም ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብቶ ሥርዓተ ቀብራቸው ቅዳሜ ጳጉሜን 4 ቀን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

ፕሮፌሰር ተካልኝ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡