Skip to main content
x
የአፍሪካ ኅብረት 29ኛው የመሪዎች ጉባዔና የምሥራቅ አፍሪካን በሁለት ጎራ የመሠለፍ ቀውስ የመፍታት ፈተና

የአፍሪካ ኅብረት 29ኛው የመሪዎች ጉባዔና የምሥራቅ አፍሪካን በሁለት ጎራ የመሠለፍ ቀውስ የመፍታት ፈተና

29ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ከሰኔ 20 እስከ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡ ስብሰባው ማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የየአገሮቹ ቋሚ መልዕክተኞች ስብሰባ በማካሄድ ተጀምሯል፡፡ የዘንድሮው 29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ‹‹Harnessing the Demographic Divided through Investment in Youth›› በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ፣ የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የኅብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ጉባዔውን ማካሄድ የጀመረው የአፍሪካ ኅብረት፣ በዋናነት በየአገሮቹ ያሉ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አዳዲስ አሠራሮችንና ፖሊሲዎችን እንደሚቀርፅ ይጠበቃል፡፡

በተፈጥሮ ሀብቷ ባለፀጋ መሆኗ የሚነገርላት አፍሪካ በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል የሌላት በመሆኑ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ በመጠቀም በአኅጉሩ ያሉ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እየተከናወነ እንዳልሆነና ለዚህም ዜጎች ለስደት ሰለባ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አፍሪካ ካለባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረትና ድህነት ባሻገር የአሸባሪዎች መናኸሪያ እየሆነች ነው፡፡ መቀመጫውን ሶማሊያ አድርጎ ሽብር በማድረስ ከሚታወቀው አልሻባብ እስከ ናይጄሪያው ቦኮ ሐራም፣ በሊቢያ ከሚንቀሳቀሰው አይኤስ እስከ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች መናኸሪያቸውን አፍሪካ አድርገዋል፡፡  

29ኛ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሌላው ጉዳይ በአፍሪካ እየተስፋፋ ስለመጣው ስለዚሁ ሽብርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይም ሶማሊያ ከአልሻባብ ጥቃት ነፃ ስለምትወጣበት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ፣ ከአፍሪካ ኅብረት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣው የሽብር ጥቃት በአኅጉሪቱ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ እንደሆነ የኬንያ ‹‹ዴይሊ ኔሽን›› ባለፈው ሳምንት ዘግቧል፡፡ በዚህ የሽብር ጥቃት በቅርብ ጊዜያት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያ ሰለባዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

አፍሪካ ከተጋረጡባት የሽብር ጥቃቶች ባሻገር ሰሞኑን የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ከኳታር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ሌላው ሥጋት እየሆነባት መምጣቱን፣ የተለያዩ የመረጃ አውታሮች ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ የባህረ ሰላጤው አገሮች ኳታርን ከአባልነቷ እንድትወጣና ሌሎች አገሮችም ከእሷ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ስታግባባ ሰንብታለች፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ ምኞት  ዕውን ሆኖ ዛሬ ታላላቅ አቅም አላቸው ተብለው የሚጠቀሱት የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ግብፅን ጨምሮ፣ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል፡፡

የባህረ ሰላጤው አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ፣ በአፍሪካ በተለይም በቀይ ባህር ቀጣና ውስጥ ባሉ አገሮች ቀጥተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

የኳታር ከቀጣናው መውጣት ለአፍሪካ አገሮች መከፋፈል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ የባህረ ሰላጤው አገሮች ስብስብ በአፍሪካ ብሎም በዓለም  አገሮች ዘንድ ልዩነት እየፈጠረ መሆኑን፣ የቱርክ ‹‹አናዶሉ›› የመረጃ መረብ ገልጿል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ሰሞኑን እያወጣችው ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የዓለም አገሮች በተለይም የአፍሪካ አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በግልጽ እንዲያቆሙ አሳስባለች፡፡ ይህ የሳዑዲ ዓረቢያ የማስጠንቀቂያ ደወል አፍሪካን የሚያሳስብ ጉዳይ እንደሆነ እየተገለጸ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ከዚህ በፊት የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሞሃማት ሙሳ ፋቂ የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች  በኳታር ላይ የወሰዱት የማግለል ዕርምጃ በአገሮች መካከል መከፋፈል የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር፣ በአፍሪካ አገሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 2017 የገልፍ አገሮች ማለትም ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬንና ግብፅ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በይፋ አቋርጠዋል፡፡ የእነዚህ አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ በአፍሪካ በተለይም በኤርትራና በጂቡቲ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ማምጣቱም አልቀረም፡፡

 29ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑ እየተነገረ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ቀላል እንደማይሆን ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ የኳታር ከቀጣናው መገለል አሜሪካና ቱርክን ጨምሮ አገሮች የተለያየ አቋም እንዲይዙ እያደረገ ነው፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉብኝት ያደረጉት በሳዑዲ ዓረቢያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ተነሳ አሜሪካና ሌሎች አጋር አገሮች ከሳዑዲ ዓረቢያ ጎን መቆማቸው እየተነገረ ነው፡፡ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተወሰኑ የሙስሊም አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል ሕግ አውጥተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሕግ ለማውጣት ያስገደዳቸው አንዱ ምክንያት የተወሰኑ የሙስሊም አገሮች አሸባሪ ቡድኖችን እንደሚረዱና በአገራቸው ላይም የሽብር ጥቃት እንዳይከሰት በመፍራት እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያና አጋሮቿ ኳታር ‹‹ሐማስ›› እየተባለ የሚጠራውን ቡድን እንደምትረዳ በመፈረጅ ከቀጣናው እንድትወጣ አድርገዋል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ የባህረ ሰላጤው አገሮች ስብስብ ሰሞኑን በኳታር ላይ ይህን ዓይነት ዕርምጃ መውሰዱ ደግሞ አሜሪካን ጨምሮ የተወሰኑ የአውሮፓ አገሮችን ጮቤ እያስረገጠ መሆኑም ተነግሯል፡፡ በዚህም የተነሳ የተወሰኑ የሙስሊም አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጥላው የነበረውን ዕገዳ ልታነሳ እንደምትችል ሰሞኑን ‹‹ሲኤንኤን›› ዘግቧል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲብ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው ከኳታር ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል፡፡ የዓረብ ባህረ ሰላጤው አገሮች በኳታር ላይ 13 ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸው የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚነካ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የግብፅና የኳታር ግንኙነት በቀጣናው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ቢሆንም፣ አሁን ግን ጉዳዩ ውኃ የገባው ጨው እንደሆነ ባለሙያዎች ሲናገሩ እየተደመጠ ነው፡፡ ግብፅ በቀይ ባህር በኩል ያለውን ቀጣና በአራት ዓይኗ እየተከታተለች እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን፣ የኳታር ጦር ከዱሜራ ግዛት መውጣት ደግሞ ለግብፅ የብሥራት ዜና እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

 በቀይ ባህር አካባቢ በተለይም በጂቡቲ ላይ የዓለም አገሮች ትኩረትና ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ፈረንሣይ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቻይና፣ አሜሪካና ሌሎች አገሮችን ጨምሮ ይህን ቀጣና በዕይታቸው ሥር ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል፡፡

አፍሪካ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድርና እንድትመራ ብሎም ሀብቷን  እንድትቆጣጠር የተለያዩ ምክረ ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቢሰሙም፣ በዚህ ቀጣና ያለውን ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታ ከግብፅና ኢትዮጵያ በስተቀር ትኩረት የሚሰጠው እንደሌለ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል የቀረበ ጥናት ጠቁሟል፡፡ ግብፅ በቀይ ባህር በኩል የሚያልፍንና ማንኛውንም ጉዳይ በተለየ ዕይታና አመለካከት የምታይ አገር እንደሆነች ይሰማል፡፡ በኤርትራና በጂቡቲ ድንበር አካባቢ ለሰባት ዓመታት ያህል ሰፍሮ የነበረውን የኳታር ጦር መውጣት ተከትሎ የተወሰኑ አገሮች ጮቤ እየረገጡ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

የአሰብን ወደብ ለረጅም ዓመት እንደተከራየችው የሚነገርላት ሳዑዲ ዓረቢያ በቀጣናው ያላትን ኃይል ማጠናከር እንደምትፈልግ ሲነገር ይሰማል፡፡ በቀይ ባህር በኩል ደግሞ ግብፅ ከኤርትራ ጋር የጋራ ግብረ ኃይል እንዳቋቋመችም እየተገወራ ነው፡፡ ኤርትራ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከግብፅ በዓመት ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደምታገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አገሮች ወደዚህ ቀጣና መጥተው የራሳቸው ቦታ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ እንደሆነ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ አበበ ዓለሙ ይናገራሉ፡፡

በዚህ ቀጣና ያለው አሠላለፍ ከባድና ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመፍታት አዳጋች እንደሚሆን አቶ አበበ ይስማማሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በ29ኛው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ይህንን ጉዳይ አንስቶ የሚመክርበት እንደሆነ ቢጠቆምም፣ ዘላቂ መፍትሔ ከማምጣት አንፃር አስቸጋሪ እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና የአፍሪካ ኅብረት በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተፈጠረውን የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ሥፍራው እንደሚልክ የኅብረቱ ኮሚሽነር ቢገልጹም፣ ጉዳዩ ቀላል እንደማይሆን እየተነገረ ነው፡፡ ኤርትራ በተደጋጋሚ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የማዕቀብ ሰለባ መሆኗ ደግሞ ጉዳዩን የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ አገሮች አሠላለፋቸውን እንዲያሳምሩ ማሳሰቢያ መናገር፣ የግብፅ ወደ ዱሜራ ግዛት ለመሄድ ፍላጎት ማሳየትና የኢትዮጵያ አካባቢውን በንቃት መከታተል ጉዳዩን የከፋ ሊያርገው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ከእኔ ጋር ወይም ከኳታር ጋር አሠላለፋችሁን ለዩ ማለቷ ስህተት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አበበ፣ የኢትዮጵያ አሠላለፍ የኋላ ኋላ ወደ ጂቡቲ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ መጠቀምና የግብፅ ከኤርትራ ጋር የጋራ የጦር ቀጣና መመሥረት ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጠው እንደሚያደርግ፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የውጭ ፖሊሲ ተንታኝ ተናግረዋል፡፡

ለዘመናት ኢትዮጵያንና ግብፅን ሲያወዛግብ የነበረው የዓባይ ወንዝ አገሮች አሠላለፍ እንዲይዙ ምክንያት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ሰሞኑን ስለናይል በኡጋንዳ የመከረው የአባል አገሮች የመሪዎች ስብሰባ፣ ኢትዮጵያና ግብፅን በመጠኑም ቢሆን እንዳወዛገበ እየተነገረ ሲሆን ባለሙያው ይህ ጉዳይ ከሁለቱ አገሮች አልፎ ወደ ኤርትራና ጂቡቲ ሊሸጋገር የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ጦርነት ማስቆም ያልቻለው የአፍሪካ ኅብረት፣ አሁንም በኤርትራና በጂቡቲ እንዲሁም ከእነሱ ጎን በተሠለፉ አገሮች ላይ ያለውን ፖለቲካዊ አንድምታ ለመፍታት እንደሚቸገር ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

ሰሞኑን ናይልን በተመለከተ በተካሄደው የአባል አገሮች ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ተገኝተው ነበር፡፡ የሁለቱ አገር መሪዎች ቁርጥ ያለ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ የግብፅ ‹‹ኢንዲፔንደንት›› ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የዓባይ ወንዝ ቀይ መስመር የተሰመረበት ጉዳይ ነው ብሏል፡፡ ይህ ወንዝ ሁለቱን አገሮች ለዘመናት ሲያጨቃጭቅ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ግብፅ ታሪካዊ መብት እያለች የምትጠራውን እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት ውድቅ በማድረግ፣ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ነው፡፡ ግብፅ ግድቡን በአንክሮ እየተከታተለችው እንደሆነም ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቀሙት የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ እስከ ዛሬ ድረስ በሥልጣን ላይ ቢቆዩ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ልትገድብ እንደማትችል መናገራቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡት ሰንብተዋል፡፡

በዱሜራ ግዛት የተነሳ ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ የሚነገርላቸው ኤርትራና ጂቡቲ፣ ከኋላቸው ደግሞ ኢትዮጵያና ግብፅ ጉዳዩን በተለየ ትኩረት እየተከታተሉት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለቱ አገሮች ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት እንዳለባቸው እየገለጸ ቢሆንም፣ ግብፅ ደግሞ ሠራዊቴን በአካባቢው አሰማርቼ ለሁለቱ አገሮች ሰላም ላስፍን እንዳለች ቢነገርም፣ ጨዋታው ያለው ከበስተጀርባ እንደሆነ  አቶ አበበ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ከ1990 ዓ.ም. ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ዓይንና ናጫ ሆና ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል የዘለቀችው ኤርትራ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከግብፅ ጎን የመቆም ምክንያቷ የዓባይ ወንዝ ከኢትዮጵያና ከግብፅ ጋር ያለውን ትስስር በማጥናት ነው፤›› የሚሉት የውጭ ፖሊሲ ተንታኙ፣ ጉዳዩ ከዚህም አለፍ ያለ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ እስከ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ እንደሚቆይ የተነገረው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጉዳዩን በልዩ ትኩረት ዓይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ቢነገርም፣ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች የራሳቸው አሠላለፍ ስላላቸው አፋጣኝ መፍትሔ ከማምጣት አንፃር ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ባድመና ሽራሮ፣ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ዓባይ ወንዝ፣ በኤርትራና ጂቡቲ መካከል ደግሞ የዱሜራ ግዛት ውዝግቦች መኖር ቀጣናው ከባድ እንደሆነና በአንድ ወይም በሁለት ቀናት የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ሊፈታ እንደማይችል ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

‹‹የኳታርና የቱርክ ወዳጆች በአንድ ጎራ፣ የሳዑዲ ዓረቢያና የአሜሪካ፣ እንዲሁም የግብፅ ወዳጆች በሌላ ጎራ የመሠለፍ አዝማሚያ እየታየ በመሆኑ ጉዳዩ የከረረ ነው፤›› ሲሉ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኙ ያስረዳሉ፡፡

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ የባህረ ሰላጤው አገሮች ስብስብ በኳታር ላይ ዕርምጃ መውሰድ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ የባህረ ሰላጤው አገሮች በኳታር ላይ ዕርምጃ መውሰድ መፍትሔ ለማምጣት በሚኬድበት መንገድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አቶ አበበ ይናገራሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ይህንን ጉዳይ በዋናነት ይዞ ሲንቀሳቀስ በመጀመሪያ ሕግ በጣሱ አፍሪካ ውስጥ ባሉ አገሮች ግብፅን ጨምሮ ዕርምጃ በመውሰድ ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ አንድን አገር 13 ያህል መሥፈርቶች ደርድሮ ይህን ግዳጅ ካልተወጣሽ ማለት አሁንም በቀጣናው ሰላም ለማስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡

ኤርትራ በመሪ ደረጃ በጉባዔው ላይ አለመሳተፏ ደግሞ ሌላው ችግር ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ በቀጣናው በተለይም በሰሜን ምሥራቅ ያለውን የአፍሪካ ቀጣና የማተራመስ ዕቅድ እንዳለው የሚነገረው የኤርትራ መንግሥት፣ አሁንም የአፍሪካ ኅብረት የሚወስነውን ውሳኔ ለመቀበል ዝግጁ ሊሆን እንደማይችል መላምቶች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት በዱሜራ ግዛት በኤርትራና በጂቡቲ መካከል በነበረው እሰጥ አገባና ጦርነት ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የወሰነውን ውሳኔ ኤርትራ አልቀበልም ማለቷ ይታወሳል፡፡ ከዓረብ አገሮች በስተቀር ራሱን እንዳገለለ የሚነገርላት የኤርትራ መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ ለሚከሰቱ ሽብሮችና ግጭቶች ዋነኛውን ሚና እንደሚጫወት፣ በጥር ወር 2009 ዓ.ም. የታተመውና ‹‹ዲስኮርስ›› የተሰኘው መጽሔት ገልጿል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የተጋረጠውን ፈተና ከመፍታት አኳያ የአፍሪካ ኅብረት ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ በተለይም የ29ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ በዚህ ቀጣና ያለው አሠላለፍ መስመር ማስያዝ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለሁለት እየተከፈለ የመጣውን የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አሠላለፍ ኢትጵያ ገለልተኛ ሆና እየተከታተለችው እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ስትናገር ተደምጧል፡፡ ኳታርና ኢትዮጵያም ከብዙ ዓመታት በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በቅርቡ አድሰዋል፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነትም ጥሩ የሚባል እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ገልጿል፡፡ በዚህ በሁለት በተከፈለው የኳታርና የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥታት ጎራ የኢትዮጵያ አሠላለፍ ወዴት መሆን እንደለበት የኋላ ኋላ  እንደሚወሰን የሚታወቅ ቢሆንም፣ አቶ አበበ ግን ከሳዑዲ ጎን ልትሆን እንደማትችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የግብፅና የኤርትራ በአንድ ወገን መሠለፍ ኢትዮጵያ በግድ ወደ ኳታርና ጂቡቲ እንድትሄድ ያስገድዳታል፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለቱ ቡድኖች ችግራቸውን በመቀራረብና በመወያየት መፍታት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ወደ አንዱ ጎን ልትሄድ እንደማትችልና የማደራደር ተግባሯን እንደምትቀጥል ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነትና ኃያልነት ተጠቅማ በቀጣናው እያንዣበበ ያለውን የፖለቲካ መንፈስ ማረጋጋት እንዳለበት እየተነገረ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በ29ኛው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ከዚህ በፊቱ የተሻለ አሠራርና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት የቀጣናውን ሰላም ማስከበር እንዳለበት ተነግሯል፡፡

የአፍሪካ አገሮች በዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል መሠረት አድርገው ወደ አንዱ ወገን ሳያዳሉ፣ ሚዛናዊ በሆነና በሰከነ መንገድ ጉዳዩን ማጤንና መከታተል እንዳለባቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በቀይ ባህር ያለውን ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታ ኢትዮጵያንና ግብፅን በመያዝና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የግጭት ቀጣና እንዳይሆን መሥራት ተገቢ መሆኑን ብዙዎችን ያስማማል፡፡