Skip to main content
x
የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ አዲሱ መርሐ ግብር

የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ አዲሱ መርሐ ግብር

የአፍሪካ  እግር  ኳስ  ኮንፌዴሬሽን  (ካፍ) ከሳምንታት  በፊት  ለአፍሪካ እግር  ኳስ  ማደግ  አስተዋፅኦ  ያደርጋል  ያለውን  አዲስ  የውድድር  መርሐ  ግብርና  የተሳታፊውን  ቁጥር  ከ16  ወደ  24  ከፍ  ማድረጉ  ይታወሳል፡፡ 

በቀጣይ  የአፍሪካ  አገሮች  ዋንጫ ተግባራዊ  እንዲሆን  በካፍ  አመራር  የፀደቀው  የተሳታፊ  አገሮች  ቁጥር  ጭማሪና  መርሐ  ግብር  ለውጥ  እያነጋገረ  ይገኛል፡፡

ቀድሞ ከ56 አገሮች 16 አገሮች  ወደ  ውድድሩ  በማጣሪያ  እንዲገቡ  ይደረግ  ከነበረው፣ አሁን ቁጥሩ ወደ 24 ከፍ ማለቱ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ዕድልን የሚፈጥር ነው የሚሉ አሉ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዕድል ሰፋ ባለ ቁጥር  ተጫዋቾች በተለያዩ ክለቦች ለመመረጥና ለመጫወት በር ይከፍታል፡፡

 ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ በተሳተፈችበት የ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ክህሎታቸውን ማሳየት የቻሉ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በመድረኩ ሌላ አማራጫ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም አዲሱ መርሐ ግብር በገንዘብ አቋማቸው ደንደን ያሉ የአፍሪካ አገሮች ብቻ ውድድሩን የማዘጋጀት አቅም ስለሚኖራቸውና የኢኮኖሚ ደረጃቸው ዝቅ ያሉ አገሮችም በጣምራ የሚያዘጋጁበት ዕድል ማስፋቱን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ይኼም በሁለት አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር የአገሮቹን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በመጨመርና የማዘውተሪያ ቦታና የስታዲየም ግንባታዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡

የቡድኖች ቁጥር በመጨመር በእግር ኳሱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ላልደረሱ አገሮች ማጣሪያዎቹን በቀላሉ ለማለፍ ቢረዳቸውም ጨዋታዎቹ ተመጣጣኝነት ላይኖራቸው፣ የሻምፒዮናው ጥራት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል የሚሉም አልጠፉም፡፡

በሌላ በኩል የፉክክር መጠኑ ይቀንሳል የሚለው ሐሳብ ጎልቶ ቢታይም የቁጥሩ ከፍ ማለት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ተጫዋቾች ልምድ እንዲያገኙ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ይነገራል፡፡

‹‹ከልምድ ባሻገር በየምድቡ ጨዋታ ላይ የተጫዋቾችን ተነሳሽነት ከፍ ያደርጋል፡፡ በዚህም ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት የነበረው ተነነሳሽነት መመለስ ይቻላል፤›› በማለት የአራዳ ክፍለ ከተማ አሰልጣኝ ሚሊሻ ጉግሳ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ለሚደረጉ የምድብ ጨዋታዎች አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ከተሳትፎ ባሻገር ተጫዋቾች ኃያላን ክለቦች ዓይን ውስጥ እንዲገቡና ተፎካካሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

ከሳምንታት በፊት ጉባኤውን በሞሮኮ ራባት ላይ ያደረገው ካፍ፣ የአፍሪካ ዋንጫ የውድድር ቀን ለውጥ ሌላኛው ያስተላለፈው ውሳኔ ነበር፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ በሰኔና ሐምሌ ወር እንዲሆን በአዲሱ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

እስካሁን የአፍሪካ ዋንጫ በጥርና የካቲት ወር ላይ መሆኑ በተለያዩ ሊጎች ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾችና ክለቦችን ቅር የሚያሰኝ ወቅት እንደነበር ይወሳል፡፡

በፊፋ ሕግ መሠረት አንድ ክለብ ተጫዋቹ አገሩን ወክሎ እንዲጫወት ሲፈልግ ለተጫዋቹ ፈቃድ መስጠት እንዳለበት ቢደነግግም በምልዐት ባለመተግበሩ ባለፉት የካፍ አመራሮችና የአውሮፓ የክለብ ባለቤቶች መካከል ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡

ከፊፋ ፕሬዚዳንት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገረው አዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት መሐመድ መሐመድ፣ አዳዲስ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ሥራቸውን ተያይዘውታል፡፡ ውድድሩን ከጥር ወደ ሰኔና ሐምሌ መውሰዱ የአፍሪካን እግር ኳስ የገቢ መጠን ለመጨመር ያስችላል የሚል እምነት ያላቸው ፕሬዚዳንቱ፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቁት የአውሮፓ ውድድሮች የአፍሪካ ዋንጫ በሚከናወንበት ወቅት የተመልካች ቁጥር ስለሚጨምር የማስታወቂያ ገቢ ለመጨመር ያስችላል የሚል ምክንያት አስቀምጠዋል፡፡

ለየት ያለ አስተያየት ያላቸው የቀድሞው የካፍ ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን ከጥር ወደ ሰኔ መለወጥ አስፈላጊ አይደለም ይላሉ፡፡ ሰኔና ሐምሌ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የዝናብ ወቅት በመሆኑ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በኢትዮጵያ ክረምት በመሆኑ በተለይ የማጣሪያ ጨዋታዎችን በዋናዎቹ ስታዲየሞች ለማካሄድ ስለሚያዳግት፣ እንደ ድሬዳዋና አዳማ ባሉ ከተሞች ለማካሄድ ያስገድዳል የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ በሌላ በኩል የአዘጋጅነት ዕድሉ በተወሰኑ አገሮች ላይ ብቻ ይጠላጠላል ይላሉ፡፡ 24 አገሮችን ማስተናገድ የሚያስችል መሠረተ ልማትስ አገሮቹ ይኖራቸዋል ወይ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ካፍ በአህጉራዊው ሻምፒዮና ከሌሎቹ አህጉሮች የእስያና የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግም ዕቅድ እንዳለው ተሰምቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ካሜሩን በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ከ16ቱ ሌላ ስምንት አገሮች እንዲጨመሩ መወሰኑ ላዘጋጇ ራስ ምታት እንደሚሆንባት እየተነገረ ይገኛል፡፡